ለልብ ሕመምተኛው የድረሱለት ጥሪ ማቅረብ ተሀድሶን መደገፍ ነው! አንድ አድርገን ብሎግ(እዚህ ላይ ይጫኑ)
በጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ የቤተክርስቲያን በዓላት ሲከበሩ ከካቶሊክ ፣ ከግሪክ እና ከሌሎች ተቋማት በእንግድነት እንደሚጠሩ ይታወቃል። ምነው ያኔ በሃይማኖት የማይመስሉን ተገኝተዋል የሚል ተቃውሞ ያልቀረበ?
ጉዳዩና ቂም በቀሉ ያለው ለህመምተኛው የእርዳታ ጥሪ ለማድረግ የተንቀሳቀሱት እነትዝታው ሳሙኤል፣ እነምርትነሽ ጥላሁን በመሆናቸው ብቻ ነው። ምርትነሽ በመዝሙሯ ያስተማረችውንና ያነጸችውን የክርስትና ምግባር ዋጋ ማሳጣት ለምን?
እነምርትነሽ ካልጠፉ የልብ ህሙምም የእርዳታ በሩ ድርግም ይበልበት ክርስትና ነው? ወይስ ጸረ ክርስትና?
ያገኘነውን መረጃ እናካፍላችሁ! መልካም ንባብ!
ለእንዳለ ገብሬ የተዘጋጀው የዕርዳታ ገቢ ማሰባሰቢያ ጉባዔ በቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ የግል ውሳኔ ታገደ ዕገዳው ቀሲስ ሳሙኤል በሰው ሕይወት ላይ ያስተላለፉት ውሳኔ በመሆኑ፣ በወንጀል ሊያስጠይቃቸው ይችላል ቤተክርስቲያን የበላይ ኃላፊ ሲያዝ፣ የበታች ኃላፊ የሚሽርበት ሥርዓት አልበኝነት የነገሠባት ተቋም ሆናለች በከፍተኛ የልብ ሕመም ለሚሰቃየው እንዳለ ገብሬ ማሳከሚያ የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ ጥር 20 ቀን 2004 ዓ.ም የተዘጋጀው ጉባዔ በቀሲስ ሳሙኤል የግል ውሳኔ መታገዱ ከጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመለከተ፡፡ ታማሚው አቶ እንዳለ ገብሬ ቤተክርስቲያን ድጋፍ እንድታደርግለት ባቀረበው ማመልከቻ ላይ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ በኩል አስፈላጊው የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባዔ እንዲዘጋጅለት መርተውለታል፡፡ የመምሪያው ኃላፊ መምህር አዕመረም በግል ከታማሚውና ከልዩ ልዩ ክፍሎች ጋር በመነጋገር ጉባዔውን የሚያዘጋጁት መምህራን የስብከት አገልግሎት ማስረጃዎችን ከመንፈሳዊ ኮሌጆችና ከአጥቢያ ቤተክርስቲያናት አቅርበው እንዲያካሂዱለት ከመወሰናቸውም በላይ አንድ የፕሮግራም መሪ እና የስብከት መምህር ከጠቅላይ ቤተክህነቱ በማከል ጉባዔው በተጠቀሰው ዕለትና ቦታ እንዲካሄድ ወስነው ወደ ባህርዳር አካባቢ መጓዛቸው ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ጉባዔው ካልታገደ ተኝተን አናድርም ያሉት የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሠራዊት አባላት መምህር አዕመረ አለመኖራቸውን አይተው የመምሪያውን ምክትል ኃላፊ ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱን በመወትወትና በማስፈራራት ጭምር አለቃው የወሰኑትን በመሻር የዕገዳ ማስታወቂያ እንዲያወጡ ያዟቸዋል፡፡ ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱም ያለአንዳች ማቅማማት የአለቆችን ትዕዛዝ በመሻር ጉባዔው መታገዱን ዓርብ አመሻሽ ላይ ማስታወቂያ የለጠፉ ሲሆን፣ የአዳራሽ ቁልፍ የያዘውን አቶ በሪሁንን ቁልፉን ይዞ ከአካባቢው እንዲሰወር በመንገር ጉባዔ አለብኝ በማለት ወደ ድሬዳዋ ተጉዘዋል፡፡ ቅዳሜና እሁድ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ሆን ብለው ይሁን በአጋጣሚ በሥፍራው ባለመኖራቸው ጉባዔው እንዲካሄድ ማስደረግ ባለመቻሉ አስተባባሪዎች ፕሮግራሙን ለመሠረዝ መገደዳቸው ታውቋል፡፡ የዕርዳታ ጥሪውን በመስማት ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ የተመመው ሕዝብ በርካታ ሲሆን፣ ለምን ይታገዳል በሚል ብሶት ውስጥ ስለነበር ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ለሌላ ቀን መተላለፉ በማስታወቂያ እንዲነገረው ተደርጓል፡፡ ታማሚው አቶ እንዳለ ታክሞ ለመዳን የቀረው ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ሲሆን እስከ መጨረሻው ሰዓት ከቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ ዘንድ በመሄድ "ስለ እግዚአብሔር ብለው አይጨክኑብኝ" ብሎ ቢማፀንም፣ ቀሲሱ ከ"ማኅበረ ቅዱሳን" ለሚሰጣቸው ድርጎ ልባቸው ተሸንፎ ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን ሊወጡ አልቻሉም፡፡ ቤተክርስቲያን የዕርዳታ እጆቿን ስትዘረጋ ዕርዳታው በአግባቡ እንዳይደርስና የታማሚው ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ማድረግ በኃላፊነት የሚያስጠይቅ ከመሆኑም በላይ አደጋ ላይ ያለን ሰው በቸልተኝነት (ምን አገባኝ በሚል ስሜት) ተገቢውን አለማድረግ ራሱን የቻለ ወንጀል መሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ተደንግጓል፡፡ ጉዳዩ በዚህ ብቻም የሚታለፍ ሳይሆን ቤተክርስቲያናችን ዘርና ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ጾታ ሳትለይ ለማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ዕርዳታ የምትሰጥ ከመሆኑ አንፃር የቤተክርስቲያናችንን መልካም ገጽታ የሚያጎድፍ እኩይ ተግባር ነው፡፡ የጉባዔው አስተባባሪዎችም አስፈላጊውን መረጃዎች አሟልተው በቤተክርስቲያን ልጆች አገልግሎቱ የሚሰጥ በመሆኑ፣ ጉባዔው የሚታገድበት አንዳች ምክንያት አልነበረም፤ የለምም፡፡ በቤተክርስቲያናችን፣ በተለይም "ማኅበረ ቅዱሳን" እንደልብ ጣልቃ እየገባ ማተረማመስ ከጀመረ ወዲህ ሥርዓት ታውኳል፡፡ ማንም ማንንም ከማይሰማበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ቅዱስ ሲኖዶስና የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጁ የሚያስተላልፉት መመሪያና ትዕዛዝ በተራ የበታች ሠራተኞች ይሻራል፤ ይቀለበሳል፡፡ የአቶ እንዳለን ጉዳይ እንደማሳያ ብንቆጥረው የመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤትና የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ የሰጡት ትዕዛዝ በአንድ ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ ተሽሯል፡፡ በሪሁን የተባለው የአዳራሽ ቁልፍ ያዥ ቁልፉን ይዞ ተሰውሯል፡፡ ይህ በቤተክርስቲያን የተካሄደ ውንብድና እንጂ አገልግሎት ሊባል አይችልም፡፡ ዓለም በግልፀኝነትና በተጠያቂነት ዘመን ስትራመድ ቤተክርስቲያን ግን ርስ በርስ መጠላለፍ በበዛበት እና የጨለማው ዓለም ተንኮል ተተብትባ ስትታይ ይህንን ትውልድ በእጅጉ ያሰቅቀዋል፡፡ ውሳኔዎች የሚመሩት በእምነትና በሥርዓት መሆኑ ቀርቶ፣ ገንዘብ የዳኝነቱን ቦታ ሲረከብ ማየት ያለንበትን አሳዛኝ ሕይወት ያመላክታል፡፡ የእግዚአብሔር ምሕረትና ጥበቃው ከእኛ አይለይ!!! አሜን!!! Posted by Dejeselaam at 1:48 AM
source' dejeselaam blog