Monday, February 27, 2012

በክብረ መንግሥት የማኅበረ ቅዱሳን ግጭት

በጉጂ ቦረና ሀገረ ስብከት በክብረ መንግሥት (አዶላ ወዩ) ከተማ ዓርብ የካቲት 16 ቀን 2004 ዓ.ም "ማኅበረ ቅዱሳን" በቀሰቀሰው ግጭት የእመቤታችን የቅድስት ኪዳነ ምሕረት በዓለ ንግሥ ሳይከበር መዋሉን ከሥፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ በክብረ መንግሥት (አዶላ ወዩ) ከተማ በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ዓመታዊ በዓለ ንግሷ የሚከበረው የእናታችን የኪዳነ ምሕረት መታሰቢያ በዓለ ንግሥ ሳይከበር የዋለው በአካባቢው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ የቅዳሴ ሥርዓቱም ሳይካሄድ ቤተመቅደሱ ተቆልፎበት መዋልና ማደሩን አረጋግጠናል፡፡ የግጭቱ መነሻ የሆነው "ማኅበረ ቅዱሳን" በመላው ዓለም ከጠረፍ እስከ ጠረፍ እንደሚያደርገው ሁሉ በክብረ መንግሥትም እኔ ያልፈቀድኩት ሥርዓት አይካሄድም፤ እኔ ያልፈቀድኩለት አገልጋይ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ አይደርስም በሚል ትዕቢት ተነሳስቶ የቀሰቀሰው ሁከት ነው፡፡ የሁከቱ ቀንደኛ መሪ ሲያምር ተክለ ማርያም የተባለ የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ የነበረ ሰው መሆኑ ታውቋል፡፡ ይኸው ግለሰብ በሀገረ ስብከቱ መኪና ኮትሮባንድና ሌላም ሌላም የንግድ ሥራ ሲሠራበትና "ማኅበረ ቅዱሳን"ን ሲያገለግልበት ቆይቶ፣ በዚሁ የሙስና ሥራውና የመልካም አስተዳደር ብልሹነቱ የተማረረው ሕዝብ እንዲነሳለት ለጠቅላይ ቤተክህነት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ካለፉት ስድስት ወራት በፊት ከቦታው ተነስቶ አዲስ አበባ ወደሚገኘው ትንሣኤ ዘጉባዔ ማተሚያ ቤት የተዛወረ ሰው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ግለሰቡ፣ የጠቅላይ ቤተክህነቱን ሕጋዊ አሠራር ተቀብሎና አክብሮ በማተሚያ ቤቱ መደበኛ ሥራው ላይ ተገኝቶ መሥራት ሲገባው የሀገረ ስብከቱን ተሽከርካሪ መኪና ይዞ በመሰወር የግል ጥቅሙን ሲያሳድድበት መክረሙን በዚሁ ብሎጋችን መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ የቦረና ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የጽ/ቤቱን መኪና ይዘው ተሰወሩ በሚል ርዕስ ያቀረብነውን ዘገባ እዚህ እዚህይመልከቱ ሰውዬው የሚደረግበትን የፖሊስና የኅብረተሰቡን ክትትል በመፍራት ባልተጠበቀ ሰዓት መኪናዋን ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አቁሟት የጠፋ ሲሆን፣ ከጊዜ በኋላ ደግሞ አረሳስቶ ብቅ ማለቱንና ጽ/ቤቱን እንደገና መውረሱን የአካባቢው ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ይህ ግለሰብ፣ የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤትና በእጁ የሚገኘውን ንብረት አላስረክብም ብሎ ሙጭጭ ከማለቱም በላይ የ"ማኅበረ ቅዱሳን"ን ጭፍሮች በዙሪያው በመኮልኮል፣ በምትኩ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡትን ሊቀ ትጉሃን ተሾመ ኃ/ማርያምን አላሰገባም በማለት ከስድስት ወራት በላይ ሲያንከራትቷቸው መቆየታቸው ታውቋል፡፡


 ይህ በእንዲህ እንዳለ በጥቅምት 2004ቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ሆነው የተመደቡት ብፁዕ አቡነ ኤውስጣቴዎስ ቢመደቡም፣ ከአሜሪካ ተነስተው ወደ ነጌሌ ቦረና መሄድ ስላልፈለጉ፣ ሲያምር ተክለ ማርያም ብቻውን የሊቀጳጳስነቱንና የሥራ አስኪያጅነቱን ቦታ ደራርቦ በመያዝና በ"ማኅበረ ቅዱሳን" ጭፍሮች እየታገዘ አጥቢያ ቤተክስቲያናትንና ካህናትን ሲያተረማምስ መቆየቱን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ ሲያምር ተክለማርያም የኮሎምቢያ አማፂ ይመስል ያለ "ሀይ!! ባይ" በገዛ ቤተክርስቲያኑ ላይ እየፋነነ ሥርዓት አልበኝነትን ሲያስፋፋ ከመክረሙም በላይ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ እስኪመደብ ድረስ ጠቅላይ ቤተክህነትና መንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት በጋራ በወሰኑት መሠረት ቆሞስ አባ ወልደ ጊዮርጊስን የበላይ ጠባቂ አድርጎ ወደ ሥፍራው ቢልክም ሲያምር ተክለ ማርያምና የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ጭፍሮች ሥራ አናስጀምርም በማለት በሁከቱ ገፉበት፡፡ በሕገወጡ ሲያምር ተክለ ማርያምና በ"ማኅበረ ቅዱሳን"ጭፍሮች የተማረረው ሕዝብ እና ሊቀ ትጉሃን ተሾመ ኃ/ማርያም አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ቤተክህነት በተከታታይ ቢያቀርቡም፣ የሚሰጣቸውን የውሳኔ ደብዳቤ የሚያስወስንላቸው ጠፍቶ ግራ በመጋባት መቆየታቸው ታውቋል፡፡ በመጨረሻም፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ንብረትና ማህተም የተከለከሉት የሀገረ ስብከቱ የበላይ ጠባቂ ቆሞስ አባ ወልደ ጊዮርጊስና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ትጉሃን ተሾመ ኃ/ማርያም በ"ሁከት ይወገድልኝ" አስወስነው መብታቸውን በፍርድ ቤት እስኪያስከብሩ ድረስ በክብረ መንግሥት (አዶላ ወዩ) ከተማ የሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በጊዜያዊነት ለመክፈት እንዲፈቀድላቸው ጥያቄአቸውን ለጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት - አዲስ አበባ አቀረቡ፡፡ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤትም ሁኔታውን ከመረመረ በኋላ የመፍትሔ ሃሳቡን ተቀብሎ ፈቀደላቸው፡፡ በዚህ መሠረት ሁለቱ አባቶች ከጊዜያዊ ጽ/ቤታቸው ሆነው እስከ በዓለ ንግሡ ዕለት ድረስ መደበኛ ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ እንደነበር ታውቋል፡፡ እንደሚታወቀው፣ "ማኅበረ ቅዱሳን" በቤተክርስቲያንና በአገልጋዮች ላይ ጥቃት ለመክፈት ሲያስብ ጥገኛ ኪራይ ሰብሳቢና ሥነምግባር የጎደላቸውን ሰዎች ታኮ ነው፡፡ በዚህ መሠረት፣ እነ አቶ ዘውዴ አበሩ፣ መሪጌታ ልሣነወርቅ ሁንዴ፣ ያሬድ ውብሸት ከነሚስቱ እንዲሁም ለጊዜው የአባቷን ስም ያላወቅነው ፋንቱ የምትባል የሴትነት ቅርጽና ባህርይ የሌላት ነውጠኛ የሆነች ግለሰብ እና፣ ሌሎችም ረብሻ የሚቀሰቅሱበትን አጋጣሚ ሲጠብቁ የየካቲት ኪዳነ ምሕረት በዓለ ንግሥ ምቹ ሆኖ አገኙት፡፡ በዕለቱ ሊፈጽሙት ያሰቡትንና የወጠኑትን ሤራ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት እንዲያመቻቸውም የሀገረ ስብከቱ የበላይ ጠባቂ እና ሥራ አስኪያጁ ወደ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ዝር እንዳይሉ ካስጠነቀቁ በኋላ፣ ይህንን ማሰጠንቀቂያ ሳያከብሩ ቢገኙ ለሚደርሰው ችግር ተጠያቂ እንደማይሆኑ በአካባቢው የፍትሕና ፀጥታ አስተዳደር በኩል ዛቻና ማስፈራሪያ ላኩ፡፡ የአካባቢው የመንግሥት አካላትም ለነዚሁ ወሮበሎች በምዕመናን የአምልኮ ሥፍራዎች እከሌ ይግባ እከሌ አይግባ የሚል ገደብ ሊጣል እንደማይቻል አስገንዝበው፣ ይልቁንም በሕገመንግሥት የተደነገገውን የሰዎች በነፃነት የማምለክ መብት እንዲያከብሩና ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፤ በራሳቸው በኩል ችግር አለብን የሚሉ ከሆነም በሕግ አግባብ መጠየቅ እንዳለባቸው፣ ከዚህ ውጪ ግን በጉልበታችን እንጠቀማለን ቢሉ ኃላፊነቱን ራሳቸው እንደሚወስዱ አስጠንቅቀው ልከዋቸዋል፡፡ የሆነው ሆኖ፣ አማፂው ቡድን የሆዱን በሆዱ ይዞ ዕለቷን በጉጉት ይጠብቅ ጀመር፡፡ በበዓለ ንግሡ ዕለት ማልዶ ወደ ቅጥር ግቢው የገባው እፍኝ የማይሞላው የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ምልምል ሠራዊት ቦታ ቦታውን ይዞ የሀገረ ስብከቱን ኃላፊዎችና ምዕመናንን መጠባበቅ ያዘ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ቆሞስ አባ ወልደ ጊዮርጊስና ሊቀ ትጉሃን ተሾመ ኃ/ማርያም በሥፍራው ሲደርሱ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ወጠምሾች በሩን እንቅ አድርገው ይዘው አናስገባም ብለው ሕዝቡ ደግሞ ከውጭ መግቢያ አጥቶ ሜዳ ላይ እንደፈሰሰ ይመለከታሉ፡፡ ሕዝቡ እንገባለን ሲል፣ ወሮበላው አትገባም ሲል የተካረረው ግፊት ሲጦዝ ከጫፍ ደረሰ፡፡ የወሮበሎቹ ቀንደኛ መሪ የሆነው ዘውዴ አበሩ የተባለው ግለሰብም ዐውደ ምሕረቱ ላይ ቆሞ በቤተክርስቲያኗ ድምፅ ማጉያ ይለፈልፍ ጀመር፡- «. . . ሁከት ለመፍጠር የመጣችሁ አካላት ወደ ግቢው እንዳትገቡ!! እንገባለን ብትሉ ግን፣ በዓለ ንግሡ የማይከበር መሆኑን እንድታውቁት . . .» ሌላም፣ ሌላም እያለ ሕገ ወጥ ንግግሮችን ማሰማቱን ቀጠለ፡፡ የሕዝብ ኃይል ከውጪ እንደማዕበል ሲነቃነቅ ስጋት የገባቸው ወሮበሎች ደወል በመደወልና በድምፅ ማጉያ በመደንፋት ሁከቱን አቀጣጠሉት፡፡ ኡኡታው ቀለጠ፡፡ ሁኔታውን በቅርብ ሲከታተል የነበረውና ማን ምን እንደሆነ በቂ ጥናት ያደረገው የመንግሥት ፀጥታ ጠባቂ ኃይል ወደ ቅጥር ግቢው በመዝለቅ በቤተክርስቲያንና በሕዝብ ሉዓላዊነት ላይ አደጋ የጋረጠውን ወንበዴ ጠራርጎ በቁጥጥር ሥር በማዋል ከርስ በርስ ዕልቂትና ከፍተኛ የደም መፋሰስ ታድጎታል፡፡ ይህንን ሀገር ያወቀውንና ፀሐይ የሞቀውን እውነት የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ብሎጎች የሆኑት "አንድ አድርገን" እና "የመላው ዓለም የተዋህዶ ቤተሰብ" ቅጥፈት በተሞላበት መልዕክታቸው ሕዝብን ከመንግሥት ጋር ለማጋጨት ሞክረዋል፡፡ እንደ ፈረስ ላዩ ላይ ተፈናጠው ወዳሻቸው የሚጋልቡትን ዘውዴ አበሩን ቅዱስና ንጹሕ ሰው በማስመሰል በ80 ዓመታቸው የታሰሩ ሽማግሌ አሉ በማለት እውነታውን ለማዛባት ሞክረዋል፡፡ ዘውዴ አበሩ ማነው? ለአንባብያን እንግለጽ፡፡ ዘውዴ አበሩ ማለት ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ እጁ በፖሊስ እስከ ተያዘበት 16/6/2004 ዓ.ም ድረስ ለ32 ዓመታት ሕዝብ ሳይመርጠው በሰበካ ጉባዔ አባልነት ስም ቤተክርስቲያኗን ተጣብቷት የኖረ ሰው ነው፡፡ በቃለ ዐዋዲው ግን የአንድ የሰበካ ጉባዔ አባል የሥራ ዘመን 3 ዓመት ብቻ ነው፡፡ በድጋሚ ከተመረጠ ለተጨማሪ 3 ዓመት አገልግሎ ዞር ነው፡፡ ዘውዴ አበሩ ግን ቤተክርስቲያኗን እንደግል ወፍጮ ቤቱ ነው የተቆጣጠራት፡፡ ዐውደ ምሕረቱ ላይ ወጥቶ ያለ ሥልጣኑ የፈነጨውም በዚሁ ባደረበት ትዕቢቱ ነው፡፡ ታሪክ ራሱን ይደግማል እንደሚባለውም፣ በየካቲት 15/1976 ዓ.ም ለኪዳነ ምሕረት በዓለ ንግሥ ዋዜማ ምሽት ላይ ከተለያዩ የገጠር አካባቢዎች ለአዳር የመጡትን ምዕመናን በዱላ እየነረተ ከቅጥር ግቢው ማስወጣቱን የዚያው ከተማ ነዋሪዎች ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡ እንደ ዘውዴ አበሩ ዓይነቱ የእንጨት ላይ ሽበቶች በየከተማው አሉ፡፡ " Friday, February 10, 2012 ብታምኑም ባታምኑም ይህ ሆኗል!! በሞራ ገለጣ የተጀመረች ነፍስ፣ በሞራ ገለጣ ተጠናቀቀች" በሚል ርዕስ ያቀረብነውን ዘገባ ይመለከቷል፡፡click here አብዬ ቢሻው ሀዋሳ ላይ እንደዚያው ነበሩ፡፡ እዚያው ከተማ ውስጥ አንድ ባላምባራስ የሚባሉም "ሊቀጳጳስ አስደንግጥ" ሰው እንዳሉም ተነግሮናል፡፡ አዲስ አበባም ሆነ ሌሎች አጥቢያዎች ውስጥ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች አይጠፉም፡፡ ዋናው ነገር "ማኅበረ ቅዱሳን" ልክ እንደ ሰይጣን በእንደነዚህ ዓይነት ደካማ ሰዎች ጉያ ውስጥ ተሸሽጎ የሚመጣ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ ከአንድ ቤት እስከ አራት ሰው፣ የሚያጠቡ እህቶችም መታሠራቸውን እነዚሁ ብሎጎች ዘግበዋል፡፡ የሚያጠቡ እህቶች ስለመታሰራቸው መረጃው ባይደርሰንም፣ በርግጥ ያሬድ ውብሸት የተባለ ሰው ከነሚስቱ ታስሯል፡፡ የሆነው ሆኖ ለወንጀል ክራይቴሪያ አለው ሊባል አይችልም? ወንጀል ከፈጸመ መጠየቅ አለበት፡፡ "የልጅ እናት ነኝ፤ ወንጀል አልፈጽምም" ማለት ያለባት መጀመሪያ ነው፡፡ ምርጫዋ ከሆነ ምን ይደረግ? መቼም ይሁን፣ በማንኛውም ቦታ፣ "ማኅበረ ቅዱሳን" ከውስጥ በአንዳንድ ሆዳም ካህናት ካልታገዘ በስተቀር ወደ ቤተመቅደስ ዘው ሊል አይችልም፡፡ ክብረ መንግሥት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን እየበጠበጠ ያለውም በእነ መሪጌታ ልሣነ ወርቅ ሁንዴና ቀሲስ ወርቁ ጀርባ ታዝሎ ነው፡፡ እነዚህ ካህናትና ሌሎችም ስማቸውን ያላነሳናቸው ካህናት "ማቅ" ጠዝጥዞ እንደ መጋኛ ፊታቸውን ካጣመመው በኋላ ስለሚሰጣቸው ድርጎ በማሰብ የአመፀኞችን መሪ የሚጠመዝዙት እነርሱው ናቸው የሚሆኑት፡፡ "ውሻ የጌታዋን ጌታ አታውቅም" እንዲሉ እነዚህ ካህናት ለጠቅላይ ቤተክህነትና ለሕጋዊዎቹ አባቶች መመሪያ በመገዛት ፈንታ አጥንት ለሚወረውርላቸው "ማኅበረ ቅዱሳን" በመታዘዝ ደመወዝ እየከፈለች የምታስተዳደራቸውን ቤተክርስቲያን ይወጋሉ፡፡ ይህ ችግር በክብረ መንግሥት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ሥጋዊ ድካም ያለባቸው ሊቃነጳጳሳት ውስጠ ሚስጥራቸው ታውቆ፣ "ይህንን ካልፈቀዱ እንዲህ ብለን እናጋልጥዎታለን" እየተባሉ (Black mail ተደርገው) ራሳቸው በቅዱስ ሲኖዶስ መንበራቸው ላይ ሆነው ያስተላለፉትን ውሳኔ ራሳቸው በማኅበሩ ላይ ተፈጻሚ እንዳይሆን እየተከላከሉ መሆናቸውን በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ ከዚህ አንፃር "ማኅበረ ቅዱሳን" በገንዘብና በሕገ ወጥ አሠራር ደርጅቶ፣ እንደማኅበር የአባላቱ ስም ዝርዝር በመንግሥትና በቤተክህነት ሳይታወቅ፣ በገንዘብ ዝውውሩ ላይ ጥናትና ኦዲት ሳይደረግ፣ ቤተክርስቲያንን ሁለንተናዊ ቀውስ ውስጥ እየዘፈቃት ከመሆኑም በላይ ፀረ መንግሥት ቅስቀሳዎችን ጭምር ውስጥ ለውስጥ በማካሄድ ለሕዝብና ለመንግሥት የርስ በርስ ብጥብጥ የሚተርፍ የማፊያ እንቅስቃሴውን በሰፊው ተያይዞታል፡፡ ለዚህም ነው ይህንን ያስተዋሉት የሕወአት አንጋፋ ታጋይ አቦይ ስብሐት ነጋ ለፍትሕ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ መጠይቅ "ማኅበረ ቅዱሳን የቤተክህነት ዕዳ ነው" ያሉት፡፡ በክብረ መንግሥት ከተማ የተከሰተውን ችግር ለማጥራት ሕዝብና መንግሥት በወንጀል ተዋናዮቹ ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አቅላቸውን ስተው፣ ከቤተክህነት ይልቅ ለማኅበሩ ያጎበደዱ ካህናት በአስቸኳይ ከቦታቸው ሊነሱ ይገባል፡፡ ሥልጣነ ክህነቱ ያላቸው የሀገረ ስብከቱ ኃላፊዎች በውጭ ቆመው ሥልጣነ ክህነቱ የሌለው አንድ ሥራ ያጣ ሽማግሌ ቤተክርስቲያንን ለ32 ዓመታት ቆንድዶ የሚይዝበት አንዳች ምክንያት የለውም፡፡ ቤተክርስቲያን ራሷን ከ"ማኅበረ ቅዱሳን" እጅ አዙር አገዛዝ ነፃ እንድታወጣ የሁሉም ቅን አማንያን ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ እንጹም፤ እንጸልይ፣ እንትጋ!!! source-dejeselaam-dejeselaam.blogspot