ካለፈው የቀጠለ
ክፍል 3
በባለፈው ጽሁፋችን ሞርሞኒዝም የብዙ አማልክት እምነት ቦታ ሆኖ የእምነቱ ተከታዮችም ወደዚህ ወደአማልክትነት ለመቀየር ብዙ መታገልና መጣር እንደሚገባው ተመልክተናል። የዚያኑ ቀጣይ ክፍል ደግሞ እነሆ አቅርበናል።
«እስራኤል ሆይ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው»ዘዳ6፣4
እግዚአብሔር አንድ አምላክ ሆኖ ሳለ ብዙ አማልክት አድርጎ ማቅረብን ጆሴፍ ስሚዝ ከየት አመጣው? ብለን ብንጠይቅ መልሳችን አጭር ነው። ከሔዋን ጀምሮ ሲያሳስት የኖረው ሰይጣን በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የብርሃንን መልአክ መስሎ ከሰጠው መገለጥ የተገኘ ትምህርት ነው። መሐመድ በ7ኛው ክ/ዘመን «ሂሩ»ዋሻ እየሄደ ከአላህ መልአክ ከጅብሪል አገኘሁት ባለው በሚያንዘፈዝፍና በሚያንቀጠቅጥ መገለጥ አላህ አይወርድም፣አይወለድም፣ ዒሳ(ኢየሱስ) ነብይ እንጂ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም፣አልተሰቀለም፣ አልሞተም የሚል የክህደት ትምህርትን ከሰይጣን ተቀብሎ ለዓለም አስተላለፈ። እነሆ እልፍ አእላፋት ይህንኑ አምነው ይገኛሉ።
እግዚአብሔር አንድ አካል፣አንድ ገጽ ነው በማለት በመሐመድ በኩል ሲያሳስት የኖረው ሰይጣን በጆሴፍ ስሚዝ በኩል ደግሞ የለም «አምላክ ቁጥር ስፍር የለውም» ሲል መገኘቱ ሰይጣን የሰውን ልጅ ለማሳሳት መቼም ቢሆን አርፎ እንደማያውቅ ነው። እሱ ስራው ሰው የሚጠፋበት መንገድ ማዘጋጀት፣ ከእውነት ጋር የስህተት ትምህርቶችን አቀላቅሎ መስጠትና ለጥፋት ማዘጋጀትን መደበኛ ስራው አድርጎ ይንቀሳቀሳል። የሚገርመው ግን እስላሞች ይሁኑ ሞርሞኖች ያለእነርሱ ሌላው እንደማይጸድቅ፣ ሲኦል እንደሚወርድና ፈጣሪ የወደድኩት ሃይማኖት የእናንተን ነው እንዳላቸው አድርገው ራሳቸውን አሳምነው መገኘታቸው ነው።
እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን ነገር ቢኖር የትኛውም ሃይማኖት እኔ ትክክል ነኝ ስላለና በስሩ ሚሊዮኖችን ስላሰለፈ ወይም ሃይማኖቱ ከተመሰረተ ብዙ ዓመታትን ስላስቆጠረ ብቻ በእድሜው ወይም በሰው ብዛቱ ትክክለኛ ሃይማኖት ሊሆን እንደማይችል ልንረዳ ይገባል። በእድሜማ ቢሆን ኖሮ የአይሁድን ሃይማኖት የሚቀድም አልነበረም። ዳሩ ግን ወደገዛ ወገኖቹ መጣ የተባለውን የኢየሱስን መድኃኒትን ባለመቀበላቸው ወደፍጹም ድነት ሳይደርሱ ቀሩ። « የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም»ዮሐ1፣11
እንደዚሁ ሁሉ መዳን በልዩ ልዩ መንገድ እንደሆነ የሚያስተምሩ ሁሉ ከላይኛው ሀኪም ያልታዘዘ መድኃኒት አብሮ በመውሰድ እውነተኛውን መድኃኒት እንዳይታመኑበት ወይም በቂ አድርገው እንዳይመለከቱ ወይም ለነፍሳቸው እረፍት እራሳቸው ልዩ ልዩ መንገድ በመፍጠር የሚድኑ እንዲመስላቸው የሚያደርገው ያው የተለመደ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን ያመነጨው ነው እንጂ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ልዩ ልዩ የመዳኛ መንገዶች ኖሮ አይደለም።
የሐዋ4፥12
«መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና»
ሰይጣን እውነት የምትመስልን ክህደት ለሰዎች በማስተማር ከንስሐ የተሻለና በአዳኙም ባለማመን መዳን እንደሚቻል ክፋትን ሲዘራ «ጥርኝ ውሃ ለተጠማ የሰጠና 78 ሰው የበላ ሰው፣ በሰማይ የኃጢአት መመዘኛ ሚዛን የተቀመጠ አስመስሎ በሰው ኅሊና በመሳል፣ ሚዛኑ ላይ በሽወዳ መልክ የሌላ ሰው ጥላ ሲያርፍበት ካለምንም ችግር ወደገነት የይለፍ ወረቀት እንዳገኘ» በማስተማር ሰዎች ንስሐ ባይገቡና እግዚአብሔርንም ባያምኑ መዳን የሚቻልበት መንገድ እንዳለ በመጠቆም እንደ መሐመድ ይሁን እንደጆሴፍ ስሚዝ ተከታዮች የእኛ ትምህርት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ፍጹም ነው እንዲሉ ያስደርጋል።
እንግዲህ ሞርሞኖች ትምህርታቸውን በመግፋት ኢየሱስን ከኤሎሂም በስጋ የተወለደ ነው በማለት ክህደታቸውን ያጠናክራሉ።
ከሁሉ የሚገርመው የሞርሞኖች ክህደት ኢየሱስና ሉሲፈር የእግዚአብሔር ልጆች ሲሆኑ በሰማይ ባለው የሲኖዶስ ምክር ቤት በተደረገው ጉባዔ ላይ ሉሲፈር ያቀረበው ሃሳብ በምድር ያሉትን ፍጥረቶች ሁሉ እያስገደድን ወደአማልክትነት እንቀይር ሲል ኢየሱስ ግን የለም መብታቸው ተጠብቆ የምድር ፍጥረቶች ሁሉ በራሳቸው ነጻነት መወሰን አለባቸው የሚል ሃሳብ በማቅረቡ ሂድና ዓለሙን አድን ተብሎ በጉባዔው እንደተላከ ያስተምራሉ። ኢየሱስ ወደምድር ለተሰጠው ተልእኮ ሲመጣ በውሳኔው የተበሳጨው ሉሲፈር 1/3ኛውን ሰራዊት አሰልፎ ኢየሱስን ሊወጋ ወደምድር መምጣቱንና በዚህም የተነሳ ዲያብሎስ እንደተባለ ይተርካሉ።
ሰይጣን ክፉ ጠላት መሆኑ የሚታወቀው ሁሉንም ነገር የክርስቶስን አዳኝነት በመሸፈን ሰዎችን መጋረድ ነው። ክርስቶስ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ህጻናትን ሳይቀር በማስጨፍጨፍ ከመድኃኒታችን ሊለየን ብዙ ደክሟል። ምንም ወንጀል ሳይኖረው መልካሙ ስራውን(ሰው መፈወሱን) እንደጥፋት በመቁጠር አስከስሶ በመስቀል ላይ አውሎታል። የኢየሱስ ሕይወት በዚያ የሚበቃ መስሎት መቃብር አስጠብቋል። ከአርዮስ ጀምሮ ኢየሱስ የዓለሙ መድኃኒት እንዳይደለ ክህደትን ሲዘራ ኖሯል። በመሐመድም ሆነ በሌሎች የክህደት ትምህርቶች ውስጥ ዋናው ነጥብ የክርስቶስን መድኃኒትነት ከሰዎች ፊት መጋረድ ነው። ክርስቲያኖች ነን የሚሉና ክርስቶስን በስም እየጠሩ በሚያመልኩ ሰዎች መካከል እንኳን የክርስቶስን መድኃኒትነት እያወቁ ጣልቃ ትምህርት እያስገባ ሌሎች የተስፋ መንገዶች በማሳየት ያስክዳል። ኢየሱስ ስለሚወዳችሁና ከጽኑ ፍቅሩ የተነሳ በዚህ፣ በዚህ ሁሉ መንገድ እንድትድኑ ፈቅዶላ ችኋል እያለ ሰው ከ7 ትውልድ፣ወደ 12 ትውልድ፣ከ12 ትውልድ ወደ30 ትውልድ የአድናችኋለሁ ቃልኪዳን ፍለጋ እንዲንከራተት ያደርጋል። ፍርፋሪዬን የበላ፣ ደጄን የረገጠውን አድንላችኋለሁ የሚል ተስፋ እንዲሹ ሌሊትና ቀን ያተጋል። ይህ ሁሉ ከመድኃኒቱ ፈቀቅ እንዲሉና መድኃኒቱን የሚተካ መድኃኒቶች እንደሰጠ በማስመሰል የሚያቀርበው ክህደት ነው።
በጸጋው አልዳንም ያስብላል። «በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ» ሮሜ 3፣24
ወይም መዳን በስራ ነው ብሎ ሹክ ይላል። «መጽሐፍስ ምን አለ? አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት»ሮሜ 4፣3
አብርሃም ምንም ልጅ ባልነበረው ወቅት ዘርህን እንደሰማይ ከዋክብት፣ እንደባህር አሸዋ አበዛልሃለሁ ሲባል ሳይጠራጠር በማመኑ ጻድቅ እንደተባለው ሁሉ ለእኛ በሞተልን በክርስቶስ የተነሳ የእግዚአብሔር ልጆች መባላችንን አምነን በመቀበልና ልጅነታችንን ጠብቀን መገኘት ሲገባን ልጅ መባላችንን ትተን ልጅ ለመባል የቃል ኪዳን ፍርፋሪና ደጅህን የረገጠ የ40 ቀን ህጻን አደርግልሃለሁ ቃል ፍለጋ እንድንንከራተት የሚያደርገው ያ ጆሴፍ ስሚዝን ተገልጦ ይህ ነው እውነተኛው መንገድ ብሎ ያሳሳተው ጠላት መሆኑን ልናውቅ ይገባል።
ይቀጥላል.....