Friday, February 24, 2012

ኪዳናት ስንት ናቸው?


                                         እግዚአብሔር ስንት ኪዳን ሰጠ?

      “..........አዎ! እግዚአብሔር ልጆቹ ይጠቀሙ ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ቅዱሳኑ ጋር ቃል ኪዳን  ገብቷል፡፡ ከእነዚህም ኪዳነ አዳም፣ ኪዳነ ኖኅ፣ ኪዳነ አብርሃም፣ ኪዳነ ዳዊት እንዲሁም በጌታችንና   በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በሙሉ የተሰጠ ሐዲስ ኪዳን ተጠቃሾች ናቸው ….....”             
                  
                                 ( የአንድ አድርገን ብሎግ አስተምህሮ)

 
                   «.....ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር»ዕብ ፰፣፯
    « ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው»ዕብ ፱፣፲፭
                                 (መጽሐፍ ቅዱስ)
  
አንድ አድርገን ብሎግ  የአዲስ ኪዳኑን የኢየሱስ ክርስቶስን ኪዳንና  ሌሎችንም ዘርዝሮ የኪዳነ ምሕረትን ጨምሮ ብዙ፣ ብዙ ለመዳን የሚሆኑ ኪዳኖች  እግዚአብሔር ለሰው ልጆች እንደሰጠ ያለምንም መሸማቀቅ በኩራት ዘግቦልን ይገኛል። ስህተቱን የከፋ የሚያደርገው እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠው «ኪዳን» ሁለት ብቻ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ የተነገረውን በመካድና በዚህ የክህደት አስተምህሮ ውስጥ ሌሎችንም ይዞ ወደጥፋት ለማምራት ማወጁ ነው።
 አንድ አድርገን ብሎግ ክህደቱን ለማስፋፋት «ኪዳነ አዳም፣ኪዳነ ኖኅ፣ኪዳነ አብርሃም፣ ኪዳነ ዳዊት እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ ሐዲስ ኪዳን» እግዚአብሔር ለእኛ ጥቅም የሰጠን ኪዳኖች ናቸው ሲል ያለምንም ሀፍረት ጽፏል።
መጽሐፍ ቅዱስ ግን እግዚአብሔር የሰጣቸው ኪዳኖች ሁለት ብቻ መሆናቸውን በግልጽ አስቀምጧል። «ነቀፋ የተገኘበት ፊተኛውና የዘለዓለም ርስት የሚሆን አዲስ ኪዳን » ናቸው በማለት።
 «.....ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር»ዕብ ፰፣፯
                     
          «  « ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው»ዕብ ፱፣፲፭                         
        

                    «ፊተኛው ወይም ብሉይ ኪዳን»

እግዚአብሔር ይህንን ኪዳን የሰጠው ለሰው ልጆች ሁሉ ሳይሆን እርሱ ለመረጣቸው ሕዝቦች ብቻ ነበር። ይኸውም ከጥፋት ውሃ በኋላ የአባታቸውን የኖኅን ገመና የሸፈነውና፣ የበረከት ልጅ ሆኖ የተመረቀ በምድር ቡሩክነት  የተመረጠው የሴም ዘር  ነበር። «እንዲህም አለ፦ የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፥ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን»፱፣፳፮  የተመረጡትና የበረከት ምርቃት የወረደላቸው ሴማውያን የእግዚአብሔር«ሕዝቦች» ሲባሉ ከነዓናውያን ግን «አሕዛብ» ተብለው መቅረታቸውንና የመጀመሪያውንም ቃልኪዳን እግዚአብሔር የሰጠው ለእነዚህ ሴማውያን እስራኤል ብቻ እንደሆነ ከቅዱሱ መጽሐፋችን ላይ እናነባለን። የሴም የትውልድ ሐረግ እስከአብርሃም ድረስ ያለውን ከዘፍጥረት ፲፩ ጀምሮ እናገኘዋለን። እንግዲህ እነዚህ ሕዝቦች ናቸው ከአሕዛብ የተለዩ ተብለው በእግዚአብሔር የተመረጡት።
«አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ»ዘጸ ፲፱፣፭
«ሙሴና ሌዋውያን ካህናት ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ። እስራኤል ሆይ፥ ዝም ብላችሁ አድምጡ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነሃል» ዘዳ ፳፯፣፱
 እነዚህን ሕዝቦች እግዚአብሔር መርጧቸዋል። ከእነዚህ ምርጦቹ ጋር ለእርሱ ቅድስና በሚሆን መልኩ የመሪና የተመሪ ሕግ የሆነውን ውል በሙሴ በኩል በኮሬብ ተራራ ላይ  ሰጥቷል። ይህ ህዝብ በዚህ ህግ እየተመራ ኖሯል። ህጉን ሲጥሱ እየቀጣቸው፣ ሕጉን ሲጠብቁ እየባረካቸው እንደኖሩ ሙሉ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ በሰፊው ይነግረናል። ይህ የመጀመሪያው ኪዳን መሆኑ ነው። ለሕዝብና ለአሕዛብ የሚሆን ሌላ ሕግ እስኪመጣ ድረስ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ጋር ቃል የተገባባበት የቀደመው ኪዳን  ስፍራውም ኮሬብ ነው። ኪዳኑንም በ፲ ቱ ሕግጋት ሥር የሚጸና ልዩ ልዩ አፈጻጸሞችን የያዘ መተዳደሪያ ውል ነበር።


«አብርሃምም በጎችንና ላሞችን አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው ሁለቱም ቃል ኪዳን አደረጉ» ዘፍ፳፩፣፳፯ ይህ ማለት እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠው የኪዳን ሕግ አካል ነው ማለት አይደለም። እግዚአብሔር ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያእቆብ ቃል ገብቶላቸው እንደነበር እናውቃለን። ያ የእግዚአብሔር ቃል ግን በረጅሙ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ኪዳን ውስጥ ያለና የሚጠቃለልና ወደ ማዳን አዲሱ ኪዳን የሚያደርስ የጥላው ቃል ኪዳን ነው እንጂ እግዚአብሔር በተለያየ ጊዜ የተለያየና ወጥነት የሌለው ኪዳን በመስጠት የሚኖር ስላይደለ እንደዚያ በማሰብ  ከትልቅ ስህተት ላይ እንዳንወድቅ ልንጠነቀቅ ይገባል።ኪዳኑ አንድ ኪዳን ነው።

«አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ» ዘዳ ፭፣፪ እንዳለው ሙሴ።
የተሰጠው የቀደመው ሕግ አንድ ብቻ ሲሆን እሱም የብሉይ ኪዳን ሕግ ተብሎ የሚጠራው እንጂ ሌላ የኪዳን ሕግ አልነበረም።
የዚህ ኪዳን ዓላማ እንደእግዚአብሔር እቅድ ከተፈጸመ በኋላ በሌላ ኪዳን ይተካ ዘንድ እግዚአብሔር እንደፈቀ እናያለን።
 ይህ ኪዳን እንዲያረጅና በሌላ አዲስ ኪዳን እንዲለወጥ የግድ ሲሆን እግዚአብሔር ውሉን ከመተካቱ በፊት የውሉን መቀየር አስፈላጊነትና ምክንያት በቅድሚያ አሳውቋል።

የቀደመው ኪዳን ድክመቶች፣

1/ ለአንድ ለተወሰነ ሕዝብ ብቻ የተሰጠ መሆኑ፣
2/ ሕጉን ቢጠብቁትም ፍጹም ማድረግ የማይችል በመሆኑ፣
3/ ሕጉን ዕለት ዕለት መፈጸም የግድ በመሆኑ፣
4/ ሕጉ ርስት ምድርን የማውረስ ተልዕኰን ብቻ የያዘ በመሆኑ፣
5/ ሕጉ የቀደመውን ሰው በደል ማስቀረት የማይችል በመሆኑ ምክንያት አዲስ ሕግ ለመስጠት እግዚአብሔር ፈልጓል።
ይህንን ፈቃዱንም እንዲህ ሲል ተናግሯል።

ኤር ፴፩፣፴፪-፴፫
«ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፦      
ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል»   


ይህ አዲሱ ሕግ የሚያሟላቸው የሕግ ብቃቶች፣

1/ ለተወሰነ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለሕዝብና ለአህዛብ ሁሉ የሚሆን ሕግ መሆኑ፣
2/ የቀደመው ሕግ ከመሻሩ በፊት ሕጉን ለመጠበቅና ለመፈጸም የሚችል ፍጹም ሰው በመገኘቱ፣
3/ ሕጉን አንዴ ፈጽሞ ለዘለዓለም ማጽናት የሚችል በመሆኑ፣
4/ ሕጉ በሰማያዊው ሊቀ ካህናት አገልግሎት መቅደስ ውስጥ የሚያስገባ በመሆኑ፣
5/ ሕጉ በአንዱ ሰው በደል የገባውን ኃጢአት፤በአንዱ ደም መስዋዕት ለሁሉም የሚሰራ መሆኑ፣ ናቸው።

ስለሆነም፣
 «አሁን ግን በሚሻል ተስፋ ቃል በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ እንደሚሆን በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት አግኝቶአል።ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፥ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቶአል፣ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ» ዕብ ምዕ ፯ እና ፰

መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነታና የኪዳናት ሕጎች እነዚህ ብቻ መሆናቸውን እየተናገረ ከኢየሱስ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳኑ ሕግ ጋር የሚቆጠሩ ብዙ ኪዳናት ለሰው ልጆች መሰጠታቸውን የሚጽፉ ክፍሎችን ምን እንላቸዋለን።
የምድራዊቷ ኢየሩሳሌም ሕግና የሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ሕግ ፣ብሉይና አዲስ ተብለው ከመሰጠታቸው ውጪ ከኢየሱስ ሕግ ጋር የሚቆጠሩ ሕጎች የማን ሕጎች ናቸው?
እነዚህ ክፍሎች የጻፉትን እዚህ ላይ ድጋሚ እናሳይ!

..........አዎ! እግዚአብሔር ልጆቹ ይጠቀሙ ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ቅዱሳኑ ጋር ቃል ኪዳን  ገብቷል፡፡ ከእነዚህም ኪዳነ አዳም፣ ኪዳነ ኖኅ፣ ኪዳነ አብርሃም፣ ኪዳነ ዳዊት እንዲሁም በጌታችንና   በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በሙሉ የተሰጠ ሐዲስ ኪዳን ተጠቃሾች ናቸው .....[አንድ አድርገን ብሎግ]
እኛ ግን እነዚህኞቹን መናፍቃን እንደዚህ እንላቸዋለን።
እንደዚህ የሚል የኪዳን ሕግ ከእግዚአብሔር የወጣ የለም። የሰው ልጆች ይጠቀሙበት ዘንድ የተሰጠው ኪዳን ሁለት ብቻ ሲሆን የፊተኛይቱ ሕግና በክርስቶስ ደም የተመሰረተችው የአዲስ ኪዳን ሕጎች ብቻ ናቸው።
ሕዝብና አህዛብ አንድ የሆኑባት፣ ፍጹም ድነት የምታስገኘው አዲሲቱ ኪዳን በህያው የእግዚአብሔር በግ፣በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሠረተችው ኪዳን ናት። ከዚህ ኪዳን ውጪ ሰውን ሊያድን የሚችል ኪዳን እግዚአብሔር ለሰው ልጅ አልሰጠም። ከዚህ ኪዳን ጋር በትይዩ የሚቆጠር ወይም የሚደመር ምንም ምድራዊ ቃል ኪዳን የለም።
የክርስቶስ የደሙ ኪዳን የሚያድን መሆኑ ከታወቀ ለምንድነው ሰዎች ሌላ ቃልኪዳንን ተስፋ አድርገው ሌላም መንገድ አለ የሚሉት? የክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ደሙ ዓለሙን ሁሉ ካዳነ ሰዎች ቁልቁል ወርደው በመጠኑ ለተገደበ 12 እና 30 ትውልድ የሚያድን ሰው የሚፈልጉት ለምንድነው? ምን ለመጨመር ወይም ምን ያላገኙት ኖሮ ለማሟላት ነው?
ባለመድኃኒቱ ኃጢአተኞችን ፍለጋ አይደለም እንዴ የመጣው? ወይስ ኃጢአተኞችን  ስለሚጸየፍ ሌላ የኃጢአተኞች የቃል ኪዳን የጓሮ በር ተሰርቷል? ይህ ሃሳብ የመንፈስ ቅዱስ ሳይሆን ብዙ የመዳን መንገድ እንዳለ የሚሰብክ የጠላት አሠራር ነው።
ከዚህ ኪዳን ውጪ ሰዎች የሚጠጉበት ወይም ተስፋ የሚያደርጉበትና ዓይናቸውን የሚሰቅሉበት ኪዳን እንደሌለ ጳውሎስ እንዲህ ብሎናል።
«መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና» የሐዋ ፬፣፲፪
ከሰማይ በታች ለመዳን የሚሆን ኪዳን አለ፣ የሚል እሱ ማነው?