Sunday, March 18, 2012

ፖፕ ሺኖዳ ሣልሳዊ


 (የደጀብርሃን ልዩ ዘገባ) ፖፕ ሺኖዳ ሳልሳዊ አረፉ! ፎቷቸው ላይ ሀገሬ በሰማይ ነው የሚሉ ይመስላሉ!

የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ሆነው ከ1971(እ ኤ አ) ጀምሮ በማገልገል ላይ የነበሩት ፖፕ ሺኖዳ ሳልሳዊ በፕሮስቴት ካንሰር፣ በጉበትና ሳንባ በሽታ ለዓመታት ሲሰቃዩ ቆይተው በተወለዱ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ፖፕ ሲኖዳ በኮፕት ክርስቲያን ልጆቻቸው ዘንድ እጅግ በጣም ተወዳጅና ተፈቃሪ የነበሩ ሲሆን በበሽታ እየተሰቃዩ ከወንጌል አስተምህሮ ሳይለዩ፣ ቅዳሴ ሳያቋርጡ፣ በሐዋርያው ጉብኝቶቻቸው፣ አድባራትና ገዳማቶቻቸውን በማጽናናት ሌሊትና ቀን ደክመው አገልግሎታቸውን ለግብጽ ቤተክርስቲያን በትጋት ፈጽመው ያለፉ ታላቅ አባት ነበሩ። «ባባ ሹኑዳ» እያሉ የሚጠሯቸው ልጆቻቸው አስተምህሮአቸውን ለመስማት ሲሽቀዳደሙ፣እግሮቻቸውን፣ እጆቻቸውን ለመሳለም ሲሰለፉ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም። ይህ ሁሉ ለክርስቶስ ቤተክርስቲያን የተሰለፉበትን አባታዊ ተልእኰ በመፈጸም እድሜአቸውን ሙሉ ባበረከቱት ትጋት የተነሳ የተሰጣቸው ትልቅ ክብር እንጂ ለውዳሴ ከንቱ እንዳልሆነ ሁላችንም የምንመሰክረው ሐቅ ነው። በአንድ ወቅት በቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ትምህርተ ወንጌል አስተምረው የተናገሩትና እሳቸው አልቅሰው ምእመናኑን ሁሉ ያስለቀሱት መቼም አይረሳም።
እንዲህ አሉ! «ልጆቼ ካስተማርኳችሁ ሁሉ ያልነገርኳችሁ ብዙ ነገር በልቤ ውስጥ አለ፣ እሱን ለእናንተ አልነግርም ፣ የልቤን ለሚያውቅ ለኢየሱስ ለክርስቶስ ትቼዋለሁ» ሲሉ ቁጭ ባሉበት ስቅስቅ ብለው አለቀሱ።ቤተክርስቲያኑን የሞላው ሕዝብ ተከትሎ አለቀሰ። ቅዳሴውን በቀጥታ ስርጭት ይከታተል የነበረው ሁሉ በየቤቱ አነባ። አዎ ፓትርያርኩ ብዙ ምስጢራቸውን፣ችግራቸውንና ስለቤተክርስቲያን ያላቸውን ጭንቀት የመፍትሄ ባለቤት ለሆነው ለክርስቶስ ይነግሩ ነበር። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያቀርቧቸው ሃሳቦቻቸው መካከል «ክርስቶስ የሰጠን አንዲቱን ቤተክርስቲያን ሆኖ ሳለ እኛ ተለያይተን እንዴት ክርስቶስን በእውነት እናመልካለን፣ ክርስቶስን ይህን እያየ ዝም የሚለው እስከመቼ ነው?» እያለ እለት እለት የሚያሳስባቸውን የቤተክርስቲያን ጉዳይ የሚያነሱ ባለትልቅ ራእይ አባት ነበሩ።

Saturday, March 17, 2012

ያኔ ሲኦልም ቢሆን የመረጡ ዛሬ ደግሞ ጳውሎስ ነን ይላሉ!

 
(ከደጀብርሃን) ዘመድኩን ከሐዋርያው ጳውሎስና ከሲላስ ጋር አይመሳሰልም!
«ለራስ ሲቆርሱ፣ አያሳንሱ» ማንም ወዳጁን ወይም ራሱን ሲክብና ሲያሞካሽ ይህ ቃል ይነገራል። ደጀ ሰላም የተባለው መካነ ጦማር ግን እሱ የጠላውን ሲያክፋፋና ስሙን ጥላሸት ሲቀባው ወዳጆቹን ደግሞ በማሞካሸት ጳውሎሳዊና ሲላሳዊ ዓይነት የወንጌል ተጋዳይ አድርጎ ሲያቀርብ እንኳን እንደሃይማኖት ሠራተኛነት፣ እንደሥጋውያን ሰዎች ይህንን ለማለት የሚያስችለውን አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ አለመቻሉ አስገራሚ ይሆንብናል።
ደጀ ሰላም እንዲህ ሲል ስለነዘመድኩን ጽፎልናል።
«ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ ከግንድ ተጠርቀው በታሰሩበት ወኅኒ ቤት የወኅኒውን መሠረት ያናወጠውን፣ ምድርን ያንቀጠቀጠውን፣ ወህኒ አዛዡንና ቤተ ሰዎቹን ካለማመን ወደ ማመን የመለሰውን መዝሙራቸውንና ትምህርታቸውን፤ ቅዱስ ጳውሎስ በእስራቱ ዓመታት የከተባቸውን መልእክታት፤ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በግዞቱ ሓላፊያትን፣ ማእከላውያንን፣ መፃዕያትን ያየበትን ራእዩን ያስታውሷል»
እንግዲህ ዘመድኩንን ከሲላስና ከጳውሎስ ጋር ለማመሳሰል የሚያስችለው መነሻ ምንድነው? ብለን ለመጠየቅ የምንገደድ ሲሆን ደጀ ሰላም የወደደውን እንኳን ጳውሎስና ሲላስ ከፈለገም ከሰማይ የወረደ መልአክ ከማድረግና የጠላውን ደግሞ ቤተክርስቲያን እንደተገኘች ውሻ እንደሚያሳድድ ስለምናውቅ እኛው ራሳችን አባባሉን «ለራስ ሰው ሲቆርሱ አያሳንሱ» ብለን ሀሰተኛነቱን ለማሳየት እንሞክራለን።

Thursday, March 15, 2012

ወሲብን መፈለግና ውጤቱን መጥላት አይቻልም!

ዝሙትና ማመንዘር፣ዘርን መዝጋትና ወሲብ እፈልጋለሁ! በስጋም ሆነ በነፍስ የሚታጨደውን ዋጋ ግን አልፈልግም?
«እንጀራ እበላለሁ፣ ውሃን  መጠጣት ግን  አልፈልግም»እንደማለት ነው።
ይሄ ነገር ይቻል ይሆን? እስካሁን እኔ አልሰማሁም፣ አላነበብኩምም። የቻለ ካለ ወይም  ወይም በዓለም አስደናቂ ታሪኮች መዝገብ ላይ ሰፍሮ አይቻለሁ የሚል ጽፎልን ሊያስደንቀን ይችላል። በእርግጥ ቢጽፍልንም አናምነውም። ምክንያቱም የሰው ሰውነት 66% የተገነባው በደም ነው። ደም ደግሞ ያለውሃ ደም ሳይሆን እንጨት ነው። ይደርቃል ማለት ነው። ስለዚህ «እንጀራ እበላለሁ፣ ውሃ ግን መጠጣት  አልፈልግም» የሚል ቢኖር ጤንነቱን ልንጠራጠር የግድ ይሆናል። እናንተስ ምን ትሉት ይሆን? ለመንደርደሪያ ተጠቀምኩኝ እንጂ  ስለእንጀራ መብላትና ውሃን ለመጠጣት አለመፈለግ ጉዳይ ሳይንሳዊ ትንተናን ለመስጠት የጽሁፌ ዓላማ አይደለም። ግን እንደዚያ ከማለት ተለይቶ የማይታይ  ሃሳብን በአንጻራዊነት ለመቃኘት በመፈለግ ነው። ልክ «እንጀራ እበላለሁ፣ ውሃ ግን መጠጣት አልፈልግም» እንደማለት ዓይነት የሚነገር የሰው ሃሳብ!! ይህን ሃሳብ ብዙ መንፈሳውያን ሰዎች ሲያስተምሩት አይሰማም። ምናልባትም በእነሱም ዘንድ አለመነሳቱ እነሱም ይህንኑ ሃሳብ በሕይወታቸው ውስጥ እየተለማመዱት ይሆናል። ታዲያ ምን እንበል? እግዚአብሔር እንድንበላ ፈቅዶ ውሃ መጠጣትን የሚከለክል እቅድ የለውም፣ አልነበረውም። በሰዎች ዘንድ እየሆነ ያለው መንፈሳዊ ጥፋት ይህንን የሚናገር ነው። እስኪ ወደጉዳዩ እንግባ።
1/ ዝሙትና ማመንዘር(Fornication & Adultery)
ማመንዘር  ሰው ከጋብቻ በፊት የሚፈጽሙት ተራክቦ  ነው። ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ሥራ ነው።ዝሙት ደግሞ በጋብቻው ውስጥ እያለ ከሌላ ሰው ጋር የሚፈጽመው ተግባር ነው።
ሮሜ 618
«ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል»