Monday, June 10, 2024
ካህን ማነው?
ካህን ማነው?
ካህን የሚለው ግስ ስርወ ቃሉ ዕብራይስጥ ሲሆን ኮሄን כהן (kohen) ከሚለው ቃል የመጣ ነው። አጭር ትርጉሙ "አገልጋይ" ማለት ሲሆን አቅራቢ፣ ሠራተኛ፣ የሚራዳ ማለትንም ያመለክታል። በቅዱስ መጽሐፋችን የመጀመሪያው ካህን የሳሌም ንጉሥ የነበረው፣ ትውልድና ዘር ያልተቆጠረለት መልከጼዴቅ ነበር። (ዘፍ 14:18) እሱም የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነበር። (ዕብ6:20) የመልከጼዴቅ ክህነት በኢየሱስ ክርስቶስ ምሣሌነት የተነገረበት ምክንያት የካህንነት ሹመቱ በነገድ አልተቆጠረም። የኦሪቱ የክህነት ሥልጣን ከሌዊ ነገድ በመወለድ የሚገኝ ቢሆንም ኢየሱስ ግን ሊቀካህን የሆነው ከይሁዳ ነገድ ነው። የኦሪቱ ክህነት ያለመሃላ የሚፀና ቢሆንም የኢየሱስ ክህነት እንደመልከ ጼዴቅ ክህነት በእግዚአብሔር በመሃላ የተረጋገጠ ነው። (ዕብ 7:20—21)
የዚህ ክህነት ዋና ምስጢር በአዲስ ኪዳን ከኢየሱስ በስተቀር በመሃላ እንደመልከ ጼዴቅ ለዘላለም ካህን ነህ ተብሎ የሚሾም ሌላ ካህን የለም ማለትን ያመለክታል። የኢየሱስ የካህንነት ምስጢር ራሱ መስዋእት፣ ራሱ መስዋእት አቅራቢ፣ በአብ የተወደደ መስዋእት ሆኖ በደሙ የዘላለም የኃጢአት ማስተሰሪያ መስዋእት ሆኖልን ስለእኛ ጸንቶ መቆሙን ያረጋግጥልናል።
“እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።” (ዕብ 7፥27)
የዚህ በመሃላ የተሾመው ሊቀካህን መስዋእት ወደእሱ የሚመጡትን ነፍሳት ሁሉ የሚቤዥ አንዴ የቀረበ፣ ሕያው የሥርየት መስዋእት ነው።
“ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”(ዕብ 7፥25)
ስለመልከጼዴቅ ከብሉይ ኪዳን የምናነበው ቃል ከአብርሃም ጋር ተገናኝቶ ከመባረኩ በስተቀር በፊት የት እንደነበረ፣ በኋላም ወዴት እንደሄደ የተነገረ ምንም ታሪክ የለም። ይህንን ታሪክ ኢየሱስ ራሱን በዘላለማዊ የማዳን የምልጃው ውስጥ መስዋእት ሆኖ ራሱን ሲገልጥ ብቻ ነው ለማየት የቻልነው። (ዕብራውያን ምዕራፍ 7ን ደግመው ያንብቡ)
ስለዘላለማዊ ሊቀካህን አገልግሎት ስንናገር ይሄንን ሥርዓት ኢየሱስ በራሱ መስዋእትነት የደመደመው ስለሆነ እኛ ክርስቲያኖች ከእንግዲህ ሌላ ምድራዊ ሊቀካህን ዛሬ የለንም። ምክንያቱም የሊቀካህን አገልግሎት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል፣ መካከለኛ አገልጋይ ሆኖ ሥርየትን ማስገኘት ነበር። በኦሪቱ የነበረውን የደም መስዋእት በራሱ ሕያው ሞትና ትንሣኤ ላመኑበት ሁሉ ሥርየትን ስላስገኘ ለክርስቲያን የሚሞትና ቢሞትም ሥርየትን ማሰጠት የሚችል ሰው የለምና ነው። እንኳን ለሌላው የኃጢአት ሥርየት መሆን ይቅርና ራሱን ለማዳን የሚበቃ ማንነት ያለው ሰው በምድር ላይ በጭራሽ የለም። በዚህ ዘላለማዊ ሊቀካህን ሞትና ትንሣኤ ያመንን እኛ በሱ የዘላለም ሕይወትን አግኝተናል።
“እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።”ዮሐ 6፥47
ሌላኛው የክህነት አገልግሎት ያለመሃላ የተሾሙይ የአሮን ዘሮች ነበሩ።
በብሉይ ኪዳን የካህናት ወገን መሆን የሚቻለው ከያዕቆብ ልጆች ሥስተኛ በሆነው ከሌዊ ዘር በመወለድ ብቻ የሚገኝ የአገልግሎት ክብር ነበር።(ዘዳ10:8) ሌዊ ማለት በዕብራይስጥ የተባበረ፣ የተያያዘ፣ የተገናኘ ማለት ነው። ምናልባትም የስሙ ትርጓሜ ከመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ጋር የተያያዘና በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል አገናኝ የሆኑበትን የክህነት አገልግሎት የሚያመለክት ስም ይሆናል። ሌዋውያን የመገናኛው ድንኳን አገልጋዮች ስለሆኑ ከ፲፩ዱ የእስራኤል ነገድ ጋር እንዳይቆጠሩ እግዚአብሔር አዘዘ።
(ዘኁ1:48—49) የሌዋውያን አገልግሎት የምስክሩን ድንኳን መጠበቅ (ዘኁ1:51) ሲንቀሳቀሱ መሸከም (ዘኁ1:53) በማረፊያቸው ደግሞ መትከል ሲሆን አሮንና ልጆቹ ደግሞ የመስዋዕቱን ሥርዓት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ማከነወን ነበር። (ዘጸ28:41) በኋለኛው ታሪክ እንደምናነበው ከሌዋውያኑ ወገን የሆኑት አሳፍና ወንድሞቹ ደግሞ በከበሮ፣ በጸናጽል፣ በመሰንቆ ይዘምሩ ነበር። (1ኛ ዜና 15:16—19)
ከክህነት አገልግሎቱ ጋር በተያያዘ ከሌዊ ወገን የሆኑ ካህናት በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ልዩ፣ ልዩ የአገልግሎት ድርሻ ነበራቸው። ሕዝበ እስራኤል ሲንቀሳቀስ የመገናኛውን ድንኳን በታዘዘው መሠረት ነቅለው ለሸክም የሚያዘጋጁ፣ የተዘጋጀውን ንዋያተ ቅድሳት ደግሞ የሚሸከሙ፣ በሚያርፉበት ቦታ ደግሞ ከተሸከሙት ተቀብለው በሥርዓቱ ተክለው ለአገልግሎት የሚያዘጋጁ፣ በተተከለው ድንኳን ውስጥ የማስተሰርያ መስዋዕቱን የሚያከናውኑ፣ ተሸክመው ሲሄዱም ሆነ ሲያርፉ በመዝሙርና በመሰንቆ እያሸበሸቡ የሚያገለግሉ መዘምራን ነበሩ። በዚህ የመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ውስጥ ከሌዊ ነገድ የተወለዱት ብቻ በአገልግሎት ተከፍለው በእግዚአብሔር የታዘዙትን አገልግሎት ሲፈፅሙ ኖረዋል። የዚህ ክህነት ባለሙሉ መብት ደግሞ በእግዚአብሔር የተመረጡት የእስራኤል ሕዝቦች ሲሆኑ ከእነርሱም መካከል የሌዊ ዘሮች ብቻ ነበሩ። ከሌዊ ዘሮችም ለድንኳኑ አገልግሎት የተለዩት የአሮን ልጆች ብቻ ናቸው። ስለዚህ፣
1/ በዚህ ዘመን እስራኤላውያን ብቻ ናቸው ለእግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቦች የሚል የአዲስ ኪዳን ትምህርት የለም። ስለዚህ ለተለየ ሕዝብ የተሰጠ የብሉይ ኪዳን የክህነት ሕግ በዚህ ዘመን የለም። አማኞች ሁሉ ካህናት ናቸው።
“መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፥ ታርደሃልና፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፥ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።” ራእይ 5፥9-10
2/ ሌዊ በሌለበት ሌዊ፣ መስዋዕትና ሥርየት አቅራቢው ኢየሱስ በሆነበት ራሱን የተለየ ካህን የሚያደርግ ቢኖር እሱ ምድራዊ ሥርዓት ነው።
እኛ በኢየሱስ ሊቀካህንነት ያመንን ሁላችን ለርስቱ የተለየን በደሙ የተዋጀን ካህናት ነን።
“እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤”
— 1ኛ ጴጥሮስ 2፥9
3/ ሌላ የምድራዊ ሹመት ሊቀካህን ይሁን ካህናት የማያስፈልገን ምክንያት ሁሉም ሰዎች በሞት የሚሸነፉና በኃጢአት የወደቁ ወይም ሊወድቁ የሚችሉ ደካማ ፍጥረቶች ስለሆኑ ነው።
ዕብ 7፣22—23 እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው።
ሥልጣነ ክህነት የሚባል መለኪያና መስፈሪያ የተዘጋጀለት የአገልግሎት መስፈርት በዚህ ዘመን አለ ቢሉ እሱ ከምድራዊ አስተምህሮ የመነጨ እንጂ ከሰማያዊ አገልግሎት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። በሰማይም፣ በምድርም ያለን ሊቀካህን አንድ ሲሆን እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ዕብራውያን 8፣ 1—2 ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።
በሊቀካህናችን በኢየሱስ መስዋዕትነት ያመንንና የኃጢአትን ሥርየት ከአብ የተቀበልን፣ እኛ አማኞች ሁላችን በኢየሱስ የተሾመን ካህናት ነን።
“መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።”
— ራእይ 1፥6
ማጠቃለያ፣
ካህን ማነው? ለሚለው ጥያቄ የማጠቃለያ መልሳችን በእስራኤል ዘሥጋ ዘመን ከ12ቱ ነገድ ለሌዊ ብቻ የተሰጠ ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን በመልከ ጼዴቅ ሥርዓት የዘላለም ሊቀካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን በእሱ ያመን እኛን በደሙ ተቀድሰን የመንግሥቱ ካህናት፣ የሰማያዊት ኢየሩሳሌም አገልጋዮች ሆነናል።
" ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል"
(ዕብ 12:22—24)
Monday, April 29, 2024
ጸጋ ምንድነው? (What is Grace?)
ጸጋ ምንድነው? (What is Grace?)
(ክፍል አምስት) የመጨረሻ—
ጸጋ ማለት በአጭር ቃል ያለዋጋ በነፃ፣ የማይገባህ ግን የተበረከተልህ ስጦታ ማለት ነው።
ጸጋ በቅዱሱ ወንጌል ውስጥ በሁለት ዋና ክፍሎች በኩል በእኛ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን የሕይወትና የኃይል ስጦታ ነው። አንደኛው፣ ሰጪውን አምኖ በመቀበል የሚገኝ የዘላለም ሕይወት ስጦታ ሲሆን ሁለተኛው የጸጋ ስጦታ አሠራር ደግሞ አምነን በተቀበልነው የዘላለም ሕይወት ውስጥ ለመኖር የዘላለም ሕይወት ሰጪውን ፈቃድና ዓላማ እየፈፀምን፣ እየተለማመድን የምንቆይበትን የኃይል ስጦታ ማለት ነው።
የመጀመሪያው ሰው ይኖርበት ዘንድ ከተዘጋጀለት ቦታ የአምላኩን ትዕዛዝ ጥሶ ከተገኘበት ቦታ ከወጣ በኋላ ወደዚያ የመመለሻ እድል አልነበረውም። ይሄንን ወደቀደመ ክብሩ የመመለስን ስጦታ ለአዳምና ለልጆቹ ያቀረበው እግዚአብሔር ራሱ ነው። ይሄ ስጦታ ከሰማይ ባይመጣ ኖሮ የሰው ልጅ ወደሰማይ መመለስ ባልቻለም ነበር። እግዚአብሔር ኮናኔ በጽድቅ፣ ፈታኄ በርትዕ አምላክ ስለሆነ የኃጢአት ዋጋ መከፈል ስለነበረበት አዳም የበደለውን የኃጢአት ዋጋ ለመክፈል ኢየሱስ የኛን ሥጋ ለብሶ፣ ኃጢአት ሳይኖርበት ለመስቀል ሞት የታዘዘ ሆነ። ይህ ለዘላለም እኛን የማዳን ዋጋ ጸጋ ይባላል።
“ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤” ኤፌሶን 2፥8
እኛ ስለበደላችን ልንከፍለው የሚገባን ዋጋ ቢሆንም ኃጢአተኛ በራሱ ሞት ራሱን ማዳን ስለማይችል ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ በኛ ምትክ ሞቶልን ከዘላለም ሞት ያዳነበት ምስጢር ነው። ይህ ስጦታ ዋጋ የተከፈለበት ነገር ግን እኛ ያልከፈልንበት፣ የማይገባን ሆኖ ሳለ አምነን እንድንበት ዘንድ በነጻ የተሰጠን ስጦታ ነው።
“ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤” ቲቶ 2፥11
የተገለጠው የማዳን ስጦታችን ኢየሱስ ነው። ያመኑበቱ ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያው ያገኛሉ። እንዲያው ማለት እኛ ሰርተን ያላገኘነው፣ በነጻ የተሰጠን ውድ ዋጋ ማለት ነው። የማዳኑን ጸጋ የትኛውም የኛ ዋጋ አይተካውም። ይህ ጸጋ በመላእክት፣ በጻድቃን፣ በቅዱሳን ወይም በሰማእታት ልመናና ምልጃ የሚገኝ አይደለም። እግዚአብሔር ራሱ በልጁ በኩል በነጻ የሰጠን የዘላለም ሕይወት ነው።
“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” ዮሐ 3፥16 ይህ ሁሉ የተደረገልን ከእግዚአብሔር ፍቅር የተነሳ ነው። ለዚህም ነው፣ ወንጌላዊው ዮሐንስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና ያለው። የሚያስወድድ ማንነት የሌለው የሰውን ልጅ በአምላካዊ ፍቅሩ እንዲሁ ወደደው።
“ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።”
— 1ኛ ዮሐንስ 4፥10
በጌታችን፣ በመድኃኒታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ያመነ ሰው ከሞት ወደሕይወት ተሸጋግሯል። አሁን አዲስ እንጂ አሮጌ ማንነት የለውም። ሁለንተናው ተቀድሷል። የእግዚአብሔር ጠላት የነበረው ሰው በኢየሱስ በኩል ልጅ ሆኗል። አባ፣ አባት ብሎ የሚጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብሏል። ከእንግዲህ ይሄ የንጉሡ ልጅ ቀሪ ዘመኑን የሚኖረው እንደንጉሡ ፈቃድና ሃሳብ ነው። ሰው በእምነቱ በኩል የመዳንን ጸጋ በነጻ እንደተቀበለ ሁሉ ከዚህ ምድር በሥጋ በሞት እስኪለይ ድረስ በእምነቱ ጸንቶ ለመኖር የጸጋ ኃይል ዕለት፣ ዕለት ያስፈልገዋል። አንዴ ድኛለሁ፣ ከእንግዲህ ምንም አያስፈልገኝም ሊል አይችልም።
" ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።" (2ኛ ጴጥ1፣5—7)
አንዴ የዳነ ሰው እምነቱ በበጎ ማንነት ሊገለፅ የግድ ነው። በጎ ማንነቱ የሚገለፀው ለመዳን ሳይሆን ስለዳነ ነው። የተተከለ ብርቱኳን የሚያፈራው ብርቱኳን ለመሆን ሳይሆን ብርቱኳን ስለሆነ ነው። አንድም ክርስቲያን የዳነው በእምነቱ ሲሆን እምነቱን በመልካም ሥራ የሚገልፀው ለመዳን ሳይሆን ስለዳነ ነው። ለመዳንም ሆነ ከዳነ በኋላ እምነቱን በሥራ ለመግለፅ ጸጋ የተባለ ኃይል የግድ ያስፈልገዋል። በባለፉት ዐራት ክፍሎች ላይ እንደገለፅነው ሦስቱን የኃጢአት በሮች መዝጋት የሚቻለው ጸጋ በተባለ ኃይል ስለሆነ የጸጋውን ኃይል መያዝ ይኖርብናል።
“እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” ዕብ 4፥16
ጸጋ፣ ቅዱሱን መጽሐፍ በመመርመር (2ኛ ጢሞ 3:15) በጸሎት (የሐዋ 1፣14) (የሐዋ 6፣4) (ማር 9፣29) ከነውር የፀዳች ሕሊና በመያዝ (የሐዋ 24፣16) በጽድቅ ንቁ በመሆን (1ኛ ቆሮ 15:34) ኃጢአትን ባለማድረግ (1ኛ ዮሐ 3:6) “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል።”
— 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥22
ከላይ እንደተጠቀሰው አንድ አማኝ ካመነ በኋላ ቀሪ ዘመኑን ተጠብቆ እንዲኖር በጸጋው ስጦታ ፊት ዕለት፣ ዕለት መኖር አለበት። ለአንድ አማኝ የሥጋውን መሻት፣ ዓለም የምታቀርብለትን ፈተና እና ከጠላት የተዘጋጀበትን ውጊያ አሸንፎ በእምነቱ ለመዝለቅ ጸጋ የተባለ የመከላከያ ጋሻ የግድ አስፈላጊው ነው። ያለጸጋው ኃይል መሸነፉ አይቀሬ ይሆናል። ብዙዎችም "ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል" (1ኛ ጢሞ 6፣ 9—11)
ማጠቃለያ፣
የእግዚአብሔር ጸጋ እኛን ለማዳን ተገልጿል። ደግሞም የዳንበትን እምነታችንን እስከመጨረሻው አጽንተን ለመጠበቅ የጸጋው ኃይል ተሰጥቶናል። ጸጋ ታላቅ በረከት ነው። ያለጸጋ ክርስትና የለም። ከጸጋው የጎደለ ሞቷል።
(ሮሜ 6፣ 22—23) አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።
Saturday, April 20, 2024
ጸጋ ምንድነው? (What is grace?)
ጸጋ ምንድነው? (What is grace?)
ክፍል ዐራት
በባለፉት ክፍሎች የተመለከትነው በኢየሱስ አምነን ለዳንን ሰዎች ሁሉ የጸጋ ኃይል የሚያስፈልገን ለምንድነው? ለሚለው ጥያቄ ሦስት የኃጢአት በሮችን ለመዝጋት ነው በሚለው ሃሳብ ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራሪያ ስንሰጥ መቆየታችን ይታወሳል። በዚሁ መሠረት ከሦስቱ የኃጢአት በሮች መካከል 1/ሥጋ 2/ ዓለም እንዴት ሊፈትኑን እንደሚችሉና ከሁለቱም የሚመጡ ፈተናዎች እንዴት መዋጋት እንደሚገባን ተመልክተናል። ሥጋ ማለት የተሸከምነውና የራሱ መሻት ያለው በነፍስ ሕያውነት የሚንቀሳቀስ አካላችን ሲሆን ይህም የሚኖረው በዚህች ምድር ላይ እንደመሆኑ መጠን ዓለም ሥጋን በባርነት እንዳትገዛ በሚዛን ለመኖር የሚያስችለን ጸጋ የሚባል ጉልበት እንደሚያስፈልገን አይተናል። ዛሬ ደግሞ ሦስተኛው ክፍል የሆነውንና የክፋት ሁሉ የኃጢአት ሹም ስለሆነው ስለወደቀው መልአክ እንመለከታለን።
ይህ ፍጥረት በትዕቢት፣ በተንኮልና በክፋት የተካነ ነው። ረጅም እድሜና ብዙ ልምድ ያለው የሰው ልጆች ሁሉ ጠላት ነው። የዚህ ዓለም ገዢ የተባለውም ዓለሙን ሁሉ በዐመፃና በኃጢአት ስለያዘው ነው። “ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።”1ኛ ዮሐ 5፥19
ይህ ጥንተ ጠላታችን ወደጥልቁ ወርዶ ለዘለዓለም እስኪታሰር ድረስ ለሰው ልጆች ምንም ዓይነት ርኅራኄ የለውም። ራእይ 20:10
የወደቀው መልአክ እብሪትና ትዕቢትን ሞሪስ የተባለ የነገረ መጻሕፍት ተርጓሚ “ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ።” ኢሳ 14፥14 ያለውን ቃል ሲተረጉም የወደቀው መልአክ ምኞቱ የመላእክት ሁሉ አለቃ መሆን ብቻ ሳይሆን አምላካዊ ሥፍራንም መፈለጉን ያሳያል ሲል ይፈታዋል።
የትኛውም ምኞትና አደገኛ የአምልኮ መሻት ሁሉ ምንጩ የዚህ የወደቀው መልአክ ውጤት ነው። የናቡከደነጾር የዱራ ሜዳ ሐውልት (ዳን3:1) የምናሴ የማመለኪያ አፀድ (2ኛ መዋዕል 33)፣ ዳጎን (መሣ16:23)፣ ቤል (ኤር 50:2) ወዘተ ሁሉም የወደቀው መልአክ ሥራዎች ናቸው። ይህንንም መዝሙረኛው እንዲህ ይላል። “የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።” መዝ 96፥5
ይህ የወደቀው መልአክ ለራሱ ብቻውን ወድቆ አልቀረም፣ የመጀመሪያዎቹንም የሰው ልጆች ጣለ እንጂ። የሚገርመው ነገር ሰዎቹ ሳይጠይቁት ራሱ ሰላማዊ ጠያቂ ሆኖ ነው የቀረበው። ከጠያቂነቱ ባሻገር እንዳይበሉ የተከለከሉት ተክል ስለመኖሩ እያወቀ፣ እንደማያውቅ ፍጥረት ሆኖ ነበር የቀረባቸው።
"...ሴቲቱንም፦ በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት።”ዘፍ 3፥1
ስለመከልከላቸው እውቀቱ ከሌለው ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? ብሎ ባልጠየቀም ነበር። በሚመልሱት መልስ ለማጥመድ ነው።
ይህንን በቃል የማጥመድ ተንኮል በኢየሱስ ላይም ሞክሮት ነበር።
“በሕዝቡም ፊት በቃሉ ሊያጠምዱት አልቻሉም በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ።”ሉቃ 20፥26
ሔዋን እንዳትበሉ አዝዞአልን? ብሎ ለጠየቃት የማጥመጃ ቃል የሰጠችው መልስ እንዲህ የሚል ነበር። (ዘፍጥረት 3:2—3)
ሴቲቱም ለእባቡ አለችው፦ በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እግዚአብሔር አለ፦ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም።
ሔዋን ሞትን ሞታ ስለማታውቅ ይሄ ጠላት በገዛ ቃሏ ምን እንደሚመስል ሊያሳያት ነው።
(ዘፍጥረት 3፣3—4)
እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።
ይህ ጠላት ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ይልቅ የሱ ድምፅ የተሻለ ፍቺና ምስጢር እንዳለው እየተናገረ ሰዎቹን ወደቤተ ሙከራ እየወሰዳቸው እንዳለ እናያለን። በሚያምረውና በሚያስጎመጀው የጠላት ቤተ ሙከራ የገቡት እንግዶች አብሯቸው የነበረው ፍሬ የተለየ ውበት እንዳለው ያንጊዜ እንደአዲስ የተገለፀላቸው ይመስል ነበር።
“ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።” ዘፍ 3፥6
የወደቀው ጠላት አዲሶቹንም ፍጥረቶች ይዞ ወደምድር ተፈጠፈጠ። ይሄንን ሀተታ እዚህ ላይ ማንሳት ያስፈለገው ለመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢያን ያልተነበበ ታሪክ ለመንገር ሳይሆን ይሄ ረጅም እድሜ፣ ልምድና ሁሉንም ክፋት የያዘ ፍጡር ዛሬም እየሰራ ያለ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው። ዛሬም ያማልላል፣ ያስጎመጃል፣ ያስመኛል፣ ያስፈፅማል፣ ያጋድላል፣ ያፋጃል፣ ሁሉንም ክፋት በሰው ልጆች መሀል ያስፈፅማል። ስለዚህ ይሄንን ባለብዙ ልምድ ጠላት ለመዋጋት "ጸጋ" የተባለ መመከቻ የእምነት ጋሻ የግድ ልንታጠቅ ይገባል። ያለበለዚያ የመጫወቻው ሜዳ ከመሆን ልታመልጥ አትችልም። ይህ ጸጋ እንዴት እንደሚሰራ የጳውሎስ ተማሪ የነበረው ቲቶ በመልእክቱ እንዲህ እያለ ይነግረናል።
“ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤” ቲቶ 2፥12-13
ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው የዳኑ ሰዎች የክርስቶስን መገለጥ እየጠበቁ፣ ራሳቸውን እየገዙ፣ በጽድቅና በቅድስና እየኖሩ ዘመኑን የሚሻገሩበት ሰማያዊ መሣሪያ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በጻፋቸው መልእክታት በሙሉ የመዝጊያ ቃል አድርጎ ከሚጠቅሳቸው የጸሎት መደምዲያው ክፍል "ጸጋ" ከእናንተ ጋር ይሁን እያለ ይለምን የነበረው አለምክንያት አልነበረም።
ሦስቱን የኃጢአት በሮች መዝጋት የሚቻለው ከእግዚአብሔር በሚሰጠን ጸጋ ብቻ ነው። ይህ ጸጋ እንዴት እንደሚገለጥና እንደሚሰራ እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር በቀጣይ ፅሑፋችን ለማየት እንሞክራለን።
Subscribe to:
Posts (Atom)