ባልተዘጋጀችበትና በማትፈልገው ለውጥ የሚደርስባት ጉዳት ከባድ ነው!
ክፍል አንድ፤
ለውጥና የለውጥ አስተሳሰብ
ለውጥ የሂደት ውጤት ነው። ስለወደድነው አይመጣም፤ ስለጠላነው አይቀርም። አንዳንዶች ለውጥን ለማስቀረት ይታገላሉ፤ ወይም
በእነሱ ትግል የሚቀር ይመስላቸዋል። የለውጥ ህግጋት ግን አይቀሬ መሆኑን ስለሚያሳይ ይዘገይ እንደሆን እንጂ ያ የተፈራው ለውጥ
እንደሚሆን አድርገው ለመቀበል ካልፈለጉት እንደማይሆን ሆኖ ይመጣል። በዚህ ምድር ላይ ባለበት ችክ ብሎ የኖረ ነገር የለም። ድንጋይ
እንኳን ተፈረካክሶ አፈር ይሆናል። ፀሐይም በጭለማ ትጋረዳለች። በጋም በክረምት ይቀየራል። ብሉይም በሐዲስ ተሽሯል። ከእስራኤል
ዘሥጋ ይልቅ እስራኤል ዘነፍስ የጸጋ ፍሰት ደርሶታል።በመወለድና በመሞት፤በመምጣትና በመሄድ፤ በመፈጠርና በማለፍ መካከልም የለውጥ
ሕግጋት አለ። እግዚአብሔር ነገሮችን በጊዜ ዑደት ውስጥ እንዲያልፉ አድርጎ ፈጠረ እንጂ ባለበት ቆሞ እንዲቀር ያደረገው አንዳች
ነገር የለም። ሌላው ቀርቶ ያለንባት ሰማይና ምድር እንኳን በአዲስ ሰማይና ምድር ትለወጣለች። መቼም የማይለወጠው እግዚአብሔር ብቻ
ነው። ዘመን የማይቆጠርለትና የማይለወጥ እሱ ብቻ ስለሆነ ነብዩ ዳዊት እንዲህ አለ።
«አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም» መዝ 102፤27
የሀገራችን
ገበሬ ክረምት ከመድረሱ አስቀድሞ የወራቶችን ለውጥ አስልቶ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ መጻዒውን ጊዜ ይጠባበቃል። ዘመኑን ጠብቆ በሚመላለሰው
ለውጥ ውስጥ ራሱን አስማምቶና ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቱን በየተራ ካልፈጸመ በስተቀር የበጋው በክረምት መለወጥ
በራሱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖውን አሳርፎ ያልፋል። በሰለጠነው ዓለም ያሉ ምሁራን በማይቀረው የለውጥ ሂደት የተነሳ ስለለውጥ ያላቸው ግንዛቤ
ትልቅ ስለሆነ ሥራቸውን ከለውጥ ጠቀሜታና ተግዳሮት አንጻር ቅድመ ምልከታ በማድረግ ለምላሹ አስቀድመው ይዘጋጃሉ።