Thursday, June 6, 2013

የፕሬዚዳንት ሞርሲና የፓርቲዎች ጉባዔ በዐባይ ጉዳይ


መምሪ በተባለው የግብጽ ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት የተደረገ ውይይት) 

የነጻነትና ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር እንዲህ አሉ፤ 

«ድምጼን አሰምቼ በግልጽ መናገር የምፈልገው ነገር ሁሉም አማራጮች ለእኛ አስፈላጊዎች መሆናቸውን ነው። እናም ሁሉንም አማራጮች እንደግፋለን፤ ነገር ግን ሂደቱ በየደረጃው መሆን ይገባዋል። የንግግር ግንኙነታችን ሂደቱን መቀየር ካልቻለ ወደዓለም ዐቀፉ የግልግል አካል እናቀርበዋለን። ይህም ካልተሳካ ማንም ሊገምተው እንደሚችለው የውሃ ዋስትናችንን ለመከላከል ወደሌላ አማራጭ እንገባለን። ምክንያቱም የውሃ ዋስትና  ለእኛ የሞት ወይም የሕይወት ጉዳይ ነውና።


የአልኑር ፓርቲ ፓርቲ ሊቀመንበር በተራቸው እንዲህ አሉ፤

አሁን እየተካሄደ ባለው የዐባይ ስምምነት ማዕቀፍ ላይ ግብጽ ከተስማማች አደገኛ ስትራቴጂካዊ ስህተት መፈጸሟ ነው። ምክንያቱም በዚህ ጉዳይ ላይ አሜሪካ፤ እስራኤልና ኢትዮጵያ ከጉዳዩ ጀርባ አሉና። ምክንያቱም በዚህ ስምምነት ግብጽን በመጉዳት ርካሽ የፖለቲካ ጫና ለማሳረፍ ሲሉ ነው። እኛም እንደእነሱ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 35%  ኦሮሞ ስለሆነና ኦሮሞም ለመገንጠል የሚዋጋለት ኦነግ የሚባል ድርጅት ስላለው ለእሱ ሁለመናዊ ድጋፍ ማቅረብ አለብን። በሀገር ቤት ያለው ፖለቲካዊ የተቃውሞ መድረክ ደካማና ልፍስፍስ ስለሆነ ለመገንጠል በሚዋጉት እንደኦጋዴን ነጻነት ግንባር ያሉትን መደገፍ ይገባናል። ይህም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የተቀናጀ ጫና እንድናሳርፍ ያስችለናል። ይህ ሁሉ ተደርጎ  ውጤት ካላስገኘልን ሌላው አማራጭ ለግብጽ ኅልውና አደገኛ የሆነ ማንኛውንም ግድብ ለማውደም የምንችልበት ሁኔታ መፍጠር ነው። ለዚህም አስተማማኝ የደኅንነት መረጃ መኖር አለበት። ምክንያቱም አንዳንድ ጠበብቶች ግድቡን መጀመር በራሱ አደገኛና ጦርነት የማወጅ ያህል እንድንቆጥር በቂ ማስረጃ ነው እያሉን ነውና።

የአል አዝሃር ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት መምህር የሆኑት ደግሞ በተራቸው፤

አስታውሳለሁ፤ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግብጽ በመጣበት ወቅት በግብጽ ሕዝብ ላይ አላግጦ ነው የሄደው። ዐባይ ክንፍ የለውም፤ ወደእስራኤልም አይበርም አለ፤ ነገር ግን ማንኛውም ህዝብ እንደሚያውቀው የግብጽ ሕዝብም ያውቃል። የዓባይ ወንዝ በቀይባህር ስር የሚሄድበት የራሱ የቧንቧ መስመር ስውር ክንፍ አለው። ማንም ሀገር በቧንቧ መስመር ውሃ ወደሀገሩ እንደሚያስገባ ይታወቃል፤ ሲሉ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን በመቃወም ዐባይ ክንፍ አለው ብለዋል።  

የገድ አልተውራ ፓርቲ ሊቀመንበር ደግሞ ተራቸውን ጠብቀው እንዲህ አሉ፤

እንደዚህ ይባል ወይም አይባል እንደሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን አንዱ ጓደኛዬ ቅድም እንዳለው ኢትዮጵያ ብዙ ተቃዋሚዎች እንዳሏት ይታወቃል፤ እዚያም የተለየ እንቅስቃሴ እያየን ነው። የግብጽ ኤምባሲ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩ ምን ያደርግልናል? አስፈላጊ ነገር አሁን የፖለቲካና የመረጃ ክፍሎቻችን ብቻ ናቸው። በኢትዮጵያ ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመርኩዘን ሚና መጫወት አለብን። ይህንን ማስኬድ መቻል በትንሽ ወጪ ብዙ መስራት የሚያስችለን ሲሆን አጸፋዊ አደጋውም የቀነሰ ነው። በደንብ አድርገን በውስጥ ጉዳያቸው ብዙ መስራት ከቻልን ማዳከም ይቻለናል። አንድ የኢትዮጵያ ጋዜጣ እንዲህ አለ፤ ግብጽ የጦርነት ሃሳብ የላትም። ይህንን የማድረግ ብቃት የላትም፤ ሚሳይል የላትም፤ አውሮፕላን የላትም፤ ቢኖራትም ሱዳን በክልሏ ላይ ይህ እንዲደረግ አትፈቅድም ብሏል። በእርግጥም የሱዳኖች ሁኔታ ለእኛ በጣም የሚያሳምም ነው። ሁኔታዋ ማድረግ ከሚገባት አንጻር ሲታይ በጣም ደካማ ነው።  በእኛም በኩል መረጃ ፍሰት ችግር አለ።  ግብጽ የጦር አውሮፕላን ልትገዛ ነው፤ በአየር ላይ ነዳጅ መሙላት የሚችል አውሮፕላን አላት ወዘተ የሚሉት መረጃዎች መውጣት አለባቸው፤ በእርግጥ ባይሆንም እንኳን መረጃው በዲፕሎማሲያዊ ጥረታችን ላይ የራሱን ተጽዕኖ ያሳርፋል።

የሪፎርምና ደቨሎፕመንት ፓርቲ ሊቀመንበር ደግሞ ተራውን ተረክበው እንዲህ ዶለቱ፤

እኛ ባለን ግንዛቤ የብሔራዊ ቡድናችን ኢትዮጵያ ሄዶ ባደረገው ጫወታ ተጽእኖ በመፍጠር ማሸነፍ መቻሉን ነው። ብሔራዊ ቡድናችን የአፍሪካ ሻምፒዮን መሆኑና እጅግ በአመርቂ ውጤት ጫና መፍጠር መቻሉ በራሱ የሚያሳየው እውነትም ግብጻውያን ጫና የመፍጠር ጥበብ እንዳለን ነው። ትልቅም ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም አለን። የግብጽን ቤተክርስቲያንና የአልሃዛር ስኮላሮችን በዚህ ጉዳይ መጠቀም እንችላለን። አንዳንዶች የጦርነት አማራጮች ሊኖር እንደሚችል ያወራሉ። የሚወራውን ነገር ለመተግበር አስቸጋሪ ነው። እንደዚህ ዓይነቱን እሳቤ መነቀፍ ይገባዋል። ከዚህ ይልቅ የግንኙነት ምህዋራችንን ከኤርትራ፤ ከሶማሊያና ከጅቡቲ ጋር ብናደርግ ለደኅንነታችን ክፍሎች ትልቅ መስክ ነው።  ይህንን ማድረግ ጥሩ ከመሆኑም ባሻገር ግንኙነት የማድረግ መብታችንም እንደመጠቀም ስለሆነ ተገቢ ነው። ተስፋችን ሲጨልም ደግሞ ሃሳባችንን መፈጸም የምንችልባቸው በተዘዋዋሪ አንድ መቶ መንገዶች ስላሉን ሁሉንም እናደርጋለን።

የኢስላሚክ ሌበር ፓርቲ ሊቀመንበር ደግሞ ምኞታቸውን ከፍ አድርገው ተናገሩ፤

እኔ ከጠላቶቻችን ጋር ጦርነት የምናደርግበት ቀን ናፍቆኛል፤ በእርግጥም ከእስራኤልና ከአሜሪካ ጋር። ጦርነቱ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎ ተገቢውን ፍትህና እርጋታ የሚያመጣ መሆን ከቻለ። ምንም እንኳን ይህ ውይይት ምስጢራዊ ውይይት እንደመሆኑ ሁሉንም ነገር በምስጢር መያዝ ይገባናል። ውይይታችን ወደሚዲያ ሾልኮ መውጣት የለበትም። በእህታችን በባኪናም በኩል በግልጽ ከሚወጣው በስተቀር። ሕዝባዊ የሀገራዊ ደኅንነት እቅድ በግልጽ እንዲኖር እንፈልጋለን። እኛ እንዲህ ቢሆንም እንኳን………. (አቋረጡ) ቀጠሉና እሺ…..መልካም………እኔ የማነሳቸው ነጥቦች አግባብ ከመሆናቸው ጀርባ በእርግጥም ምንም ምስጢርነት የላቸውም። ውጊያችን ከአሜሪካና ከእስራኤል ጋር እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር አይደለም። ስለዚህ ውጊያችንን ለማስኬድ ፤ ይህ የኔ ሃሳብ ነው……….( ፕሬዚዳንት ሙርሲ ጣልቃ ገቡና፤ ይህ ውይይት እኮ በቀጥታ ስርጭት እየሄደ ነው ያለው! አሉ) የኢስላሚክ ፓርቲው ሊቀመንበርም፤ እኔም የምስጢር እቅድ ወይም ፕላን ማብራሪያ እየሰጠሁ አይደለም!  ሲሉ በጉባዔው ሳቅ ሆነ።  ቀጥለውም «እኔ ያልኩትን እኮ ማንም ሀገር የሚያደርገው ነው፤ በሌሎችም ሲባል የቆየ ነው» አሉ። (የጉባዔው ረጅም ሳቅ!!)
ማንም ሀገር ለከባቢያዊ ጥቅሙ የሚያደርገው ነው። እኔ ለግብጽ ሕዝብ የምለው ማንም ተነስቶ የውሃ አቅርቦትህን ሊዘጋ አይችልም ነው። የግብጽን ሕዝብ የዓለም አደገኛው የጽንፈኝነት መንገድ እንዲገባ ካልፈለጉ በስተቀር ይህን አያደርጉም። እስኪ አስቡት 80 ሚሊዮን ግብጻዊ ውሃ ሲዘጋበት በአሜሪካና በእስራኤል ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?

ፕሬዚዳንት ሙርሲ፤ የልባቸውን በልባቸው ይዘው፤ በዲፕሎማሲያዊ  ቋንቋ ደስ የተሰኙበትን ገታራ ውይይት አለዝበው እንዲህ ሲሉ ደመደሙ።  

«እኛ ለሰሜንና ደቡብ ሱዳናውያን የከበረና የተትረፈረፈ አክብሮት አለን» አሉና የሱዳንን ዳተኝነት ሸነገሉ። «ውሳኔዎቻቸውን ሁሉ እናከብራለን» ሲሉ በማሞካሸት ጠላት ማፍራት እንደማይገባ በውሰጠ ታዋቂ ጠቆሙ። እንደዚሁም ሁሉ «ለኢትዮጵያ ሕዝብም ያለን አክብሮት ተመሳሳይ ነው!» አሉና ዙሪያ ገባህን እሳት እንለኩሳለን ሲል ለቆየው ጉባዔ ማለስለሻ ቫዝሊን ቀቡት። እኛ የትኛውንም ጀብደንነት ጀማሪዎችና በማንም ላይ አሳቢዎችም አይደለንም አሉ። ነገር ግን አሉ ፕሬዚዳንት ሞርሲ፤ ነገር ግን መታወቅ ያለበት  እያንዳንዷን የዐባይ ውሃ ጠብታ ለመከላከል እጅግ የጠነከረ እርምጃ የምንወስድ መሆናችን ነው። ለእያንዳንዷ ጠብታ ውሃ!
(ተፈጸመ)

Wednesday, June 5, 2013

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት እንዲሰነጣጠቅ ሲኖዶስ የወሰነው ለምንድነው?( ከዚህ በፊት የቀረበ ጽሁፍ)

            መንበረ ፓትርያርክ ቅ/ማርያም ቤ/ክ 1921 ዓ/ም (ፎቶ ምንጭ፤ ሰሎሞን ክብርዬ) 
          
ይህንን ጽሁፍ በጥቅምት/2004 ዓ/ም ሲኖዶስ ማብቂያ ላይ በዚሁ መካነ ጦማራችን አውጥተን ነበር። ዛሬ እንደገና መድገም ያስፈለገን በወቅቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን አራት ቦታ መከፋፈሉን በመቃወም ፤ ተገቢ እንዳልሆነና ጥናት ያልተደረገበት አሠራር ስለሆነ ውጤቱ ኪሳራ መሆኑን አመልክተን የነበረው በትክክል እንዳልነው ውጤቱ ኪሳራ ሆኖ በመገኘቱ ቅ/ሲኖዶስ በ2005 ዓ/ም ጉባዔው  ከግብታዊ ውሳኔው በመውጣት ሀገረ ስብከቱን ወደነበረበት ሲመልስ በማየታችን ነው። አሁንም ደግመን የምንለው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ወደነበረበት የቀድሞ ተቋማዊ መልኩ መመለስ ብቻ ሳይሆን የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖረው ማስቻል ገና የሚቀረው ሂደት ነው እንላለን። ይኸውም የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በሠራተኛ ብዛት፤ በገቢ አቅም፤ በማዕከላዊ ተቋምነቱ ሠፊና ትልቅ ሀ/ስብከት ስለሆነ ሥልጣንን ሁሉ አንድ ቦታ ሰብስቦ እንዲይዝ የሚያደርገው ሁኔታ ስላለ ከሙስና፤ ከአድልዎ፤ ከፍትህና ውሳኔ አሰጣጥ መዛባት አንጻር ለቁጥጥር የማያመች፤ የአሰራር ዝርክርክነት የሚያስፋፋ ችግር እንደበፊቱ ተመልሶ ሊመጣ ስለሚችል ሥልጣን መከፋፈል አለበት እንላለን። ይህንንም የሥልጣን ክፍፍል በታወቀና በተወሰነ የአሠራር ደንብ ላይ ተመርኩዞ በወረዳዎች ደረጃ ወደታች መውረድ ይኖርበታል። ስለሆነም እንደእኛ እምነት ሀገረ ስብከቱን በአራት የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በተሟላ አደረጃጀት አዋቅሮ ሥልጣን  መውረድ ካልቻለ ከችግሮች አዙሪት አለመውጣት ብቻ ሳይሆን ሀ/ስብከቱ የትናንሽ መንግሥታት ቢሮ ከመሆን አይዘልም። ሀገረ ስብከቱን ወደነበረበት ተቋማዊ አደረጃጀቱ መመለስ  ማለት የሥልጣን ጡንቻውን እንደገና አንድ ቦታ ማፈርጠም ማለት ሳይሆን ሥራን ከፋፍሎ ለመሥራት ያለመና የተሻለ ርእይ የያዘ መሆን ስለሚገባው አሁንም ይህ ይፈጸም ዘንድ ከችግሮች በፊት አበክረን እናሳስባለን።
በወቅቱ የሀ/ስብከቱን ክፍፍል በመቃወም ያወጣነውን ጽሁፍ ለማስታወስ ቀንጭበን ከታች አቅርበናል።

 ከዚህ ውስጥ ዋነኛውና አስደናቂው ውሳኔ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ሰነጣጥቆ የማጠናቀቁ ሂደት አንዱ ነበር።
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ችግር ጠንቅቆ የሚያውቅ የሲኖዶስ አባል የለም። ጳጳሳቱ የተመደቡባቸውን ሀ/ስብከቶች ለሥራ አስኪያጆቻቸው አስረክበው ሁለትና ሦስት ወራት ከአዲስ አበባ ቤቶቻቸው መሽገው ወለተ ማርያምንና ገ/ማርያምን እያሳለሙ እንደሚቀመጡ ይታወቃል። ግድ እየሆነባቸው እንጂ ሐዋርያዊ ተልእኰ ለመፈጸም ዝግጁዎቹ ጥቂቶች ናቸው። ስለዚህ አብዛኛዎቹ ጳጳሳት በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለመመደብ ያላቸው ፍላጎት ጫን ያለ ነው። ይህንኑ ጽኑ ምኞት ለመተግበር የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ከፓትርያርክ ጳውሎስ ልዩ ሀ/ስብከትነት  በማላቀቅ 4 ቦታ እንዲከፈልና 4 ሊቃነ ጳጳሳት ሊመደቡበት ይታገሉ እንደነበር ያለፉት ጉባዔያቶቻቸው ያስረዱናል። ተፈላጊው ነገር የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ችግሮች ምን እንደሆኑ በማወቅ መፍትሄ ለማምጣት ሳይሆን የአቡነ ጳውሎስን ስልጣን ከሀ/ስብከቱ ላይ በመቀማት 4 ጳጳሳት ተመድበውበት የሞቀ የደመቀውን በማግኘት ከክፍለ ሀገር ሀሩርና አቧራ ለመገላገል ብቻ ነበር። የሚገርመው ነገር ዛሬ አቡነ ጳውሎስ በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ ፍላጎታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ መቻላቸው ሳይሆን ለምን? እንዲከፈል እንደተፈለገ አለማወቃቸው ነው። ምክንያቱም ሀ/ስብከቱን እንደዓይናቸው አምሮት ከመሰነጣጠቃቸው በቀር ለምን መሰነጣጠቅ እንዳስፈለገ የተናገሩት አሳማኝና ጥናታዊ መረጃ ያለውን ዝርዝር ነገር ሲነግሩን አለመደመጡ ነው። እንደ ደጀብርሃን ብሎግ እምነት የአዲስ አበባ ሀስብከት መሰንጠቅ የተፈለገው በሁለት ምክንያት እንደሆነ ከፍላጎቶቻቸውና ከዓላማዎቻቸው አንጻር እንረዳለን።
1/ ከሚመጣው ፓትርያርክ ልዩ ሀ/ስብከትነት ነጻ በማውጣት ለሚመደቡ ጳጳሳት ልዩ የደስታ ግዛት ለመፍጠር፤
2/ ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአንድ ሰው ግዛት አድርጎ ከማቆየት ይልቅ ከፋፍሎ ለሌሎችም ቶሎ እንዲዳረስ ለማስቻል ነው ብለን እንገምታለን። ምክንያቱም መሰነጣጠቅ ያስፈለገው ምን ለማምጣት እንደሆነ አሳማኝ ነገር አለመቅረቡ ነው።
በኛ እምነት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት መሰንጠቅ ትክክለኛ ያልሆነ ውሳኔና የሀ/ስብከቱን ችግር ያልተመለከተ ስሜታዊ ውሳኔ ነው እንላለን። ምክንያቶቻችንም ለሀ/ስብከቱ የተሻለ መንገድ መኖሩን በማመላከት ይሆናል።
1/ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሀገሪቱና የአፍሪቃ ዋና ከተማ ከመሆኑም ባሻገር የቤተክርስቲያኒቱ ማእከላዊ ሀ/ስብከት  በመሆኑ ሁኔታዎችን የገመገመና ወቅቱን ያገናዘበ  ልዩ መተዳደሪያ ደንብ ሊኖረው የተገባ ነው።
2/ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት አወቃቀር የመንግሥትንና ዓለምአቀፍ ተቋማትን ደረጃ ያገናዘበ ዘመናዊ፤ ሙያዊና ችሎታን የተመረኮዘ የአስተዳደር መዋቅር  የያዘ መሆን ይገባው ነበር።
3/ አሁን ያሉትን ስድስት ሥራ ፈት የወረዳ ጽ/ቤቶችን ወደ አራት በማጠቃለል በአውራጃ ጽ/ቤት ደረጃ ሥልጣንና ኃላፊነት ከሀ/ስብከቱ  ከፍሎ በመስጠት እንደአዲስ ቢደራጅ ስልጣን የተሰበሰበበትን የሀ/ስብከቱን  ማእከል ጫናና ድርሻ ከመቀነሱም በላይ ተጠያቂነት ያለው አሠራርን ማስፈን ይቻል ነበር።
4/  የሀ/ስብከቱ አድባራትና ገዳማት የአስተዳደር መዋቅር በሀ/ስብከቱ መተዳደሪያ ደንብ በትክክል የተቀመጠውን የተከተለ መሆን የሚገባው ሲሆን ሙያን፤ ችሎታን፤ ብቃትን፤ ልምድንና መልካም ሥነ ምግባር የተከተለ የአስተዳደር መዋቅር ሊፈጠርበት ይገባዋል።
5/ በየአድባራት ያሉትን ከመጠን በላይ ያለውን የሠራተኞች ቁጥር  ወደሌላ የልማት ዘርፍ በመቀነስ እንደ አዲስ ማደራጀት የግድ መሆን አለበት።ይህ የልማት ዘርፍ ከደመወዝ ጠባቂነት ይልቅ አምራች ዜጋ እንዲኖርና የሚፈልሰውን ቅጥር ፈላጊ ለመከላከል የሚያስችል ነው።
6/ የሀ/ስብከቱ  ጽ/ቤት አድባራቱ በጋራ  ያላቸውን ካፒታል በማሰባሰብ በሚያቋቁሙት የልማት ተቋም የገቢ አቅም እንዲፈጥሩና ከልመና ገንዘብ እንዲላቀቁ ማድረግ ይጠበቅበታል። ለምሳሌ በጋራ ገንዘባቸው፤ ማተሚያ ቤት ወዘተ ማቋቋም ይቻላል።
7/ ቤተክርስቲያኒቱ ብዙ ባለሙያና አዋቂ ምእመናንና ምእመናት እያሏት ከዳር ሆነው ድክመቷን እየተመለከቱ፤ እሷም ልትጠቀምባቸው ሳትችል መቅረቷ ይታወቃል። በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የሚደራጅ የምሁራን ልጆቿ የአማካሪ ቦርድ ቢኖረው ሀ/ስብከቱ ተጠቃሚ ይሆናል።
ሌሎች ተጨማሪና አስፈላጊ ነጥቦችን ለመፍትሄው በማስቀመጥ አሁን ያለውን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ችግር ማቃለል እየተቻለ ሲኖዶስ ሀ/ስብከቱን መሰነጣጠቅ መፈለጉ ትክክል አይደለም። የትኞቹን ችግር በየትኞቹ መንገዶች ለማቃለል ተፈልጎ ነው ሀ/ስብከቱን በብዙ ሊቃነ ጳጳሳት ስር መሰንጠቁ ያስፈለገው? ለሚለው ጥያቄ  አሳማኝ መልስ የለም።
የአዲስ አበባ መስተዳደር እንኳን የሚተዳደረው በአንድ ከንቲባ ሥር ሆኖ ራሳቸውን ችለው በተወሰነ ሥልጣንና ኃላፊነት በተደራጁ ክ/ከተሞች እንጂ በልዩ ልዩ ከንቲባ ተሰነጣጥቆ አይታይም። የኛዎቹ በብዙ የሊቀ ጳጳስ ከንቲባ ሥር ሀ/ስብከቱን ከፋፍለው ሲያበቁ በሀ/ስብከቴ ጣልቃ አትግባ የሚል ድምጽ ለማስማትና አንድ ሠራተኛ  ከአንድ ክፍል ውስጥ ወደ ሌላኛው ክፍል እንዳይዘዋወር የሚያደርግ ስለሆነ ይህንን መፈለጋቸው አስገራሚም አሳዛኝም ነው። ውጤቱም አሳዛኝ ከመሆን አይዘልም።
ለወትሮውስ ቢሆን ርዕይና ግብ ከሌለው ጉባዔ ከዚህ የተሻለ ምን ሊጠበቅ ኖሯል? ሲኖዶሱ ራሱ ተሰነጣጥቆ አዲስ አበባንም በፈቃዱ ሰነጣጥቆ አረፈው። የ10 ቀናት ውጤት ይህ መሆን ነበረበት? ለአንባቢዎች የምናስገነዝበው ጽሁፋችን ለነቀፋ ሳይሆን በተገቢ ሂስ፤ አሳማኝ መልስ የሚሰጥ ካለ ያንን ለማግኘት ሲሆን መሠረቱም በሚታይ ገሃዳዊ እውነታ ላይ ተመስርተን ብቻ መሆኑን እንድታውቁልን ነው።

Tuesday, June 4, 2013

በሰማንያ ወአሀዱ ሽፋን የተፈጸመው የጠላት ሴራ ሲገለጥ ( ክፍል ፪ )


( ክፍል ፪ )
ከዚህ በፊት በክፍል ፩ ለመግለጽ እንደሞከርነው ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉም ውስጥ እጁን በማስገባት የራሱን ዓላማ በእግዚአብሔር ቃል ሽፋን ሲፈጽም መቆየቱን ለማብራራት ሞክረናል። ክርስቲያኖች እውነቱን አውቀው እግዚአብሔርን ወደማምለክና በአንድያ ልጁ በኩል የተደረገውን የማዳን ሥራ በቂ እንዳልሆነና ልዩ ልዩ የድኅነት/ የመዳን/ መንገዶች መኖራቸውን በማሳየት መመለሻ ወደሌለው ጥፋት ለመውሰድ ሌሊትና ቀን የማይደክም ብርቱ ጠላት መሆኑ «የሚውጠውን የሚፈልግ አንበሳ» የተባለው ቃል ያረጋግጥልናል።

ብፁዕ አቡነ ሺኖዳ የቅብጥ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ከጻፏቸው በርካታ መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነውና «diabolic war» /ዲያብሎሳዊ ውጊያ/ በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ ዲያብሎስን ጠንካራ የሚያደርገው መልካም ነገር አለ ብሎ ባሰበበት ቦታ ሁሉ ከፍተኛ ውጊያ ቢገጥመው እንኳን ተስፋ ቆርጦ ስለማይሄድ ክፉ ጠላት በማለት ይገልጹታል። ሲሸነፍ አሜን ብሎ እጁን የሚሰጥ ሳይሆን ጊዜ እየጠበቀ እስከመጨረሻው ድረስ ያለመታከትና ያለመሰልቸት መዋጋት መቻሉ የክፋቱን ልክ ያሳያል ይላሉ። በእርግጥ ዲያብሎስ ከክብሩ የወደቀና የተሸነፈ መልአክ ነው። ቢሆንም ያለው ከሙሉ ኃይሉ ጋር ስለሆነ  ውጊያው ቀላል ስላይደለ እምነታችንን እንዳይጥልብን አጽንተን እንጠብቅ ዘንድ ይመክሩናል። 

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6፥12
«መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ»

ስለዚህ ጠላታችን ኃይለኛ ተዋጊ እንጂ የወደቀ ነው ተብሎ የሚናቅ ስላይደለ አብያተ ክርስቲያናትን አጥብቆ መዋጋቱን መዘንጋት ተገቢ አይደለም። ግለሰቦችን ተዋግቶ ከማሸነፍ ይልቅ ግለሰቦች የተሰባሰቡባትን ቤተክርስቲያን የምትመራበትን ቃል መጠምዘዝ መቻል ሁሉንም ከእውነተኛው መንገድ ላይ ማስወጣት መቻል መሆኑ አሳምሮ ስለሚያውቅ  ይህንኑ በትጋት ይፈጽማል።ከዚህም የመዋጊያ ስልቱ መካከል ቅዱሱን የእግዚአብሔር ቃል ባደረባቸው ሰዎች በኩል ማጣመም፤ መሸቃቀጥ፤ ብዙ የመዳን መንገዶች እንዳሉ ማሳየት፤ የኢየሱስ ክርስቶስን ብቸኛና ብቁ መድኃኒትነት በልዩ ልዩ መድኃኒቶች መተካት ዋናው ስራው ነው። ይህንንም በተግባር ሲሰራ ቆይቷል። ለዛሬም ጥቂቱን በማሳየት እንዴት እንደተዋጋን ለማሳየት እንሞክራለን።

1/ የመጽሐፍ ቅዱስን ቁጥር ማዛባት የጠላት ዋነኛ ሥራው ነው..

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የጻፉት መሆኑ አያጠያይቅም። ቀደምት አበውም የመጽሐፍ ቅዱስን ቅደም ተከተል፤ ምዕራፍና ቁጥር የተነተኑትም በመንፈስ ቅዱስ መርምረው መሆኑንም እናምናለን። ችግሩ የሚነሳው በዚህ ዘመን ላይ እንደመጽሐፍ ቅዱስ አካል የሚቆጠሩት የቀደምት መጻሕፍት አካል የሆኑት የትኞቹ ናቸው? የሚለው ጥያቄ ነው። ለማሳየነትም በቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለ1600 ዓመት ስትመራ ቆይታለች እየተባለ የሚነገርላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ቁጥርና ዝርዝር በፍጹም አይመሳሰልም። ለምን? ሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት የመጽሐፍ ቅዱስ ቁጥርና ዝርዝር አንድ ካላደረጋቸው አንድ ነበሩ ሲያሰኝ የቆየው ታዲያ ምን ነበር? እነአትናቴዎስን ከፍ ከፍ የምታደርገው በምን መለኪያ ነው? በዋናው የእግዚአብሔር ቃል ልዩነት ካላቸው በሃይማኖት አይመሳሰሉም ማለት ነው። የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በዕብራውያን እጅ ያሉትን 39 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንደትክክለኛ የእግዚአብሔር እስትንፋስ መጻሕፍት አድርጋ ትቀበላለች። ካርቴጅ  በተደረገው ጉባዔ መጻሕፍት አምላካውያት ላይ ቀኖና ሲደነገግ እነቅዱስ አትናቴዎስ 39ኙን የዕብራውያን መጻሕፍት አጽድቀዋል። ኮፕትም ይህንኑ ተቀብላ እስከዛሬ አለች። እንደዕብራውያን መጻሕፍት የማይቆጠሩና በተጨማሪ ቀኖናተ መጻሕፍት የተያዙ /Deutrocanonical/ መጻሕፍትን ለብቻ መዝግባለች። 
እነዚህም 1/ እዝራ ሱቱኤል (አንድና ሁለትን) እንደአንድ መጽሐፍ 2/ ጦቢት 3/ ዮዲት 4/ ጥበበ ሰሎሞን 5/ ሲራክ 6/ ባሮክ 7/ መቃብያን (አንድና ሁለት) እንደአንድ መጽሐፍ መያዟ ይታወቃል። እነዚህም መጻሕፍት ቢሆኑ ድምራቸው ከዕብራውያን መጻሕፍት አይደሉም።  መጽሐፈ ሔኖክ፤ 3ኛ መቃብያን ፤ 4ኛ መቃብያን የሚባሉትን መጻሕፍት እንደትርፍ መጻሕፍት አድርጋ አትቀበልም።  መቃብያን አንድና ሁለት ራሱ ከኢትዮጵያው መቃቢያን ጋር ምንም የሃሳብና የመንፈስ ግንኙነት የሌለው በመሆኑበሁሉም  በመጽሐፈ መቃብያን በኩል ቅብጥና ኢትዮጵያ ልዩነታቸው የሰማይና የምድር ያህል ይርቃል። ለምን?

ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደቅዱሳት መጻሕፍት አድርገው ያልቆጠሯቸውን መጻሕፍት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከማን አግኝታ ተቀበለቻቸው? ለመቀበል ያስቻላት መመዘኛ ምንድነው? እስክንድርያ እናቴ፤ ማርቆስ አባቴ ስትል የቆየችባቸው ዘመናት የክርስትና ሕይወትና ዓምድ በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ አንድነት ከሌላት መነሻው ምንድነው? ኮፕት 66ቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደአበው ቅዱሳት መጻሕፍት ድንጋጌ ስትቀበል፤ በትርፍነት እንደሕጻናት የመንፈሳዊ ትምህርት ማጎልመሻ መጻሕፍትነት 7 በተጨማሪ ወይም በዲቃላ መልክ ይዛ ትገኛለች። 

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ግን ዲድስቅልያ፤ አብጥሊስ፤ትዕዛዝ፤ ሥርዐተ ጽዮን፤ ግጽው፤ ቀሌምንጦስ፤ ዮሴፍ ወልደኮርዮን ወዘተ ሳይቀሩ በ4ኛውና በ5ኛው ክ/ዘመን የተጻፉትን ሳይቀር የቅዱሳት መጻሕፍት አካል አድርጋ መቁጠሯ ለምን ይሆን?
ሰማንያ ወአሀዱ ተብለው በተለምዶ ቢጠሩም እነሱም እስከ 85 ይደርሳሉ። አንዳንዴ የግድ የተለመደው 81ን እንዳያልፍ ሲባል ሁለቱን በአንድ እስከመጨፍለቅ ይደረሳል። ቀሌምንጦስ የሐዋርያው ጴጥሮስ ደቀመዝሙር የእጣ ክፍሉ በነበረችው በኮፕት ቤተክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ያበረከተ ብዙ መጻሕፍትን የጻፈ ቢሆንም ኮፕት የሱን መጻሕፍት እንደመጽሐፍ ቅዱስ አካል አድርጋ ያልተቀበለችው ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የኔ ሰማንያ አሀዱ በማለት በግድ የምትቆጥረው ምን ቁጣ ወርዶባት ይሆን? ከዘመነ ሐዋርያት በኋላ የተጻፉ መጻሕፍት ከመማሪያነትና በመንፈሳዊ እውቀት ከማነጽ ባሻገር እንደወንጌል ቃል ሊቆጠሩ ይችላሉ? የኛ ሰማንያ ወአሀዱ ይህንን ሁሉ ግሳንግስ ይዟል። ለምን? በምን መለኪያ? ቅዱሳት መጻሕፍትን በፈለጉበት ጊዜ እያነሱ መጨመር ይቻላል?

በዚህም ተባለ በዚያ አበው ሊቃውንት እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለባቸው ናቸው በማለት በቅደም ተከተል ያስቀመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን የማይታወቁ፤ ያልተመረመሩ፤ አበው በቀኖናቸው ያልያዟቸው፤ ብዙ ትርፍ መጻሕፍትን ይዛ መገኘቷ እንደቅርስ ካልሆነ በስተቀር እንደቅዱሳት መጻሕፍት ስብስብ ሊያስቆጥራቸው የሚችል አንዳችም አስረጂ አይቀርብባቸውም።
እስኪ ግብጽ/ቅብጥ/ እንደትርፍ መጻሕፍት የምትቆጥረውንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ግን እንደዕብራውያን መጻሕፍት እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያስጻፈው ነው ብላ የምታምንበትን 1ኛ መቃብያንን ምዕ 1፤1 በንጽጽር እንመልከት።

የቅብጥ ቤተክርስቲያን መቃብያን 1፤1

After Alexander son of Philip, the Macedonian, who came from the land of Kittim, had defeated Darius, king of the Persians and the Medes, he succeeded him as king. (He had previously become king of Greece.)

ተዛማጅ ትርጉም፤ «ከምድረ ኪቲም የመጣው መቄዶንያዊው የፊልጶስ ልጅ ፤ የፋርሱንና የሜዶኑን ንጉሥ ዳርዮስን አሸነፈ።ራሱንም ንጉሥ አድርጎ  ሾመ፤ ቀድሞም የግሪክ ንጉሥ ነበር»   (መቃብያን ቀዳማዊ 1፤1)

ይህ  ታሪክ ስለታላቁ እስክንድር የሚተርክ የታሪክ ክፍል ነው። ታላቁ እስክንድር ደግሞ የኖረበትን የታሪክ ዘመን ስንመረምር በ3ኛው መቶ አጋማሽ ዓመተ ዓለም የነበረ ጦረኛ ተዋጊ መሆኑን መረጃዎች ያሳዩናል። ከዚህ ተነስተን ስለ እስክንድር ታላቁ የሚተርከው ይህ የመቃብያን መጽሐፍ ታላቁ እስክንድር ካለፈ በኋላ እሱን በሚያውቁ ወይም ታሪኩን በሰሙ ሰዎች የተጻፈ ስለመሆኑ የጽሁፉ ይዘት ይጠቁመናል። ለጽሁፉም መነሻ ምክንያት የሆነው ኢየሩሳሌምን ጨምሮ ከፋርሶች እጅ ነጻ በማውጣቱ ምናልባትም የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊዎች የጻፉት ሊሆን እንደሚችል የነገረ መለኮት ታሪክ አዋቂዎች ይገምታሉ።  ግብጻውያንም እንደቅዱሳት መጻሕፍት ያልቆጠሩበት መነሻ ምክንያትም እስክንድር ቅድመ ክርስትና የነበረ ሰው ሲሆን በእምነትም አይሁዳዊ ባለመሆኑ የተነሳ ነው። በማታትያስና አምስት ልጆቹ ያለውን በሜዲተራንያን  አካባቢ በግሪኮች ላይ የተደረገውን የዐመጽ ትርክርት የሚናገር መጽሐፍ ነው። ዛሬም አይሁዳውያን እንደመንፈሳዊ መጽሐፍ ሳይሆን ከታሪክ መጽሐፍነት የበለጠ ስፍራ አልሰጡትም።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መቃብያን በተመሳሳይ(ምዕ 1፤1) ከኮፕቱ ጋር ሲተያይ፤

«ስሙ ጺሩጻይዳን የሚባል ኃጢአትንም የሚወዳት አንድ ሰው ነበር። በፈረሶቹም ብዛት፤ ከሥልጣኑ በታች፤ በጭፍራዎቹም ጽናት ይመካ ነበር» (መቃብያን ቀዳማዊ 1፤1)

የሃሳብ፤ የመልዕክት ግንኙነት ምንም የለውም። ይህ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መቃብያን ስለማታትያስና አምስት ልጆቹ የዐመጽ ታሪክ ምን አይናገርም። ይልቁንም የሜዶን ንጉሥ ሳይሆን ግሪኮች መካከለኛው ምሥራቅን ሲገዙ የነበሩበትን ዘመን ትቶ ወደኋላ በመሄድ ስለሜዶኖች ይተርካል። እንግዲህ ይህንን ዓይነት የመጻሕፍት ልዩነት መኖሩ መነሻው ምንድነው? ብለን ብንጠይቅ ጠላት እያሰረገ በቅዱሳት መጻሕፍት ሽፋን ያስገባው እንጂ   በሁለት አፍ የሚናገር ቃለ እግዚአብሔር ለክርስቲያኖች የተሰጠ  ሆኖ አይደለም።

2/ መጽሐፈ መቃብያን ያላቸው ተቀባይነት ፣

፩ኛና ፪ኛ መቃብያን በካቶሊክ፤ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶችና ኮፕት ኦርቶዶክስ ዘንድ እንደተጨማሪ መጻሕፍት ሲቆጠሩ በአይሁዶችና በፕሮቴስታንቶች ዘንድ እንደ እግዚአብሔር እስትንፋስ ስለማይቆጠር ተቀባይነት አላገኘም።  ፫ኛ መቃብያን በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች ዘንድ ብቻ ተቀባይነት ሲያገኝ በካቶሊክ፤ በኮፕት፤ በአይሁዶችና በፕሮቴስታንቶች  ዘንድ እንደ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ተደርጎ አይቆጠርም። ፬ኛ መቃብያን ደግሞ ከጆርጂያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብቻ እንጂ በየትኞቹም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። 

በመቃብያን ስም የሚጠራ ነገር ግን ከላይ ከተዘረዘሩት አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፈ መቃብያን ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ሦስት የመቃብያንን መጻሕፍት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና የኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው መቃብያን ይዘው ይገኛሉ። ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የማይቀበሉት በተለይም ከአይሁድ የኦሪት መጻሕፍት ውስጥ እንደአንዱ የማይቀጠርና ወዳጅ ቤተክርስቲያን የተባለችው የኮፕት ቤተክርስቲያን ጭምር የማትቀበለውን ይህንን የመቃብያን መጻሕፍት መቀበላችን ምክንያቱ ምንድነው?

ለኢትዮጵያውያን ለብቻችን ከሰማይ የወረደ ልዩ መጽሐፍ ስለሆነ ይሆን? በበፊቶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ እንደመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሳይቆጠር /Apocrypha/  ተብሎ ለብቻው የተቀመጠውን በ2000 ዓ/ም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን እንደቅዱሳት መጻሕፍት ቆጥራው መዝግባው መገኘቷ አስገራሚ ሆኗል። እቀበለዋለሁ በምትላቸው የኒቂያ፤ የኤፌሶንና የቁስጥንጥንያ ጉባዔያት ውስጥ ከቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የሌሉትን በ2000 ዓ/ም እትም ውስጥ ማስገባትዋ የጤንነት ነው? በእርግጥም ጠላት ቤተክርስቲያኒቱን በእውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እንክርዳዱን በደንብ መዝራት መቻሉን ያረጋገጠ ሆኗል።

3/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መቃብያን ግልጽ ስህተቶች፤ 

መቃብያን ምንጩ ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከሰዎች ልብ መንጭቶ የተጻፈ ስለመሆኑ ብዙ ግድፈቶችን ማቅረብ ይቻላል። ለምሳሌ ያህል በ1ኛ መቃብያን 10፤ 1-2 ያለውን እስኪ እንመልከት። እንዲህ ይላል።
«ነገር ግን እንዲህ ካልሆነ የቀደሙት ሰዎች ከአዳም ጀምሮ ከሴትና ከአቤል፤ ከሴምና ከኖኅ ከይስሐቅና ከአብርሃም ከዮሴፍና ከያዕቆብ፤ ከአሮንና ከሙሴ ጀምሮ በአባቶቻቸው መቃብር ይቀበሩ ዘንድ ነው እንጂ በሌላ ቦታ ይቀበሩ ዘንድ ያልወደዱ ለምንድነው? በትንሣዔ ጊዜ በአንድነት ሊነሱ አይደለምን? አጥንታቸውስ ጣዖት ከሚያመልኩ ከክፉዎች ከአረማውያንም አጥንት ጋራ እንዳይቆጠር አይደለምን?» 

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረን አሮን የሞተው በሖር ተራራ ላይ ርስት ምድር ሳይገባ በሞዓባውያን ሀገር ነው። ዘኁል 20፤25-26 ሞዓብ ደግሞ ጣዖት አምላኪያውያን ናቸው እንጂ እስራኤላውያን አልነበሩም። መጽሐፈ መቃብያን ግን የሌለውን ታሪክ በመለፍለፍ አሮን  ከአባቶቻቸው መቃብር ከተቀበሩት አንዱ እንደሆነ ውሸት ይተርክልናል። የአብርሃምና ሚስቱ ሣራ እስከዛሬም  መቃብራቸው ያለው በኬብሮን ነው።  ዘፍ 23፤19-20  ኬብሮን ደግሞ ከደቡባዊ እስራኤል ከተማ አንዷ ናት። በአሮንና በአብርሃም መቃብር መካከል ያለው የቦታ ልዩነት ሩቅ ነው።  ሙሴ እስከዛሬ ድረስ መቃብሩ የት እንደሆነ እንደማይታወቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የሞተው ግን በናባው ተራራ ላይ ነው። መቃብሩ በሞዓብ ሸለቆ ውስጥ ቢሆንም መቃብሩ አልተነገረም። ታዲያ የሙሴን መቃብር የት እንደሆነ አውቆ ነው መቃብያን ከአባቶቻቸው ጋር ለትንሣዔ ቀን እንዲያመች  አንድ ቦታ ተቀበሩ የሚለን? መቃብያን ስማቸውን በመጥራት ሁሉ አንድ ቦታ እንደተቀበሩና ይህም የሆነው መቃብራቸው ከጣዖት አምላኪዎች ጋር እንዳይቀላቀል፤ በትንሣዔ ቀንም አብረው እንዲነሱ ሲሉ ነው የሚለን ትንሣዔን የቦታ ርቀት ይከለክለዋል? 

በጣዖት አምላኪ መካከል መቀበር ሟችን የኃጢአት ተጋሪ እንዲሆን ያደርገዋል? መቃብያን አስገራሚ ትንተናና ልብወለዳዊ ትረካውን በመስጠት አንድ ላይ ያልተቀበሩትን መተረኩ ያስደንቃል። ስለዚህ መቃብያን የተጻፈው በእግዚአብሔር መንፈስ አይደለም። ቦታ አያውቅም፤ ታሪክ አያውቅም፤ የእግዚአብሔርንም የትንሣዔ አሠራር አያውቅም። ይህንን ዓይነት መዛነፍ በማስከተል በቀደምት አበው ተሸፍኖ መቃብያን ከቅዱሱ የእግዚአብሔር ቃል ጋር እንዲቆጠረው ያደረገው ጥንተ ጠላታችን መሆኑን ከመቀበል ውጪ ያፈጠጠውን እውነት መካድ የሚቻል አይደለም።
(ይቀጥላል)