Thursday, June 6, 2013

የፕሬዚዳንት ሞርሲና የፓርቲዎች ጉባዔ በዐባይ ጉዳይ


መምሪ በተባለው የግብጽ ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት የተደረገ ውይይት) 

የነጻነትና ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር እንዲህ አሉ፤ 

«ድምጼን አሰምቼ በግልጽ መናገር የምፈልገው ነገር ሁሉም አማራጮች ለእኛ አስፈላጊዎች መሆናቸውን ነው። እናም ሁሉንም አማራጮች እንደግፋለን፤ ነገር ግን ሂደቱ በየደረጃው መሆን ይገባዋል። የንግግር ግንኙነታችን ሂደቱን መቀየር ካልቻለ ወደዓለም ዐቀፉ የግልግል አካል እናቀርበዋለን። ይህም ካልተሳካ ማንም ሊገምተው እንደሚችለው የውሃ ዋስትናችንን ለመከላከል ወደሌላ አማራጭ እንገባለን። ምክንያቱም የውሃ ዋስትና  ለእኛ የሞት ወይም የሕይወት ጉዳይ ነውና።


የአልኑር ፓርቲ ፓርቲ ሊቀመንበር በተራቸው እንዲህ አሉ፤

አሁን እየተካሄደ ባለው የዐባይ ስምምነት ማዕቀፍ ላይ ግብጽ ከተስማማች አደገኛ ስትራቴጂካዊ ስህተት መፈጸሟ ነው። ምክንያቱም በዚህ ጉዳይ ላይ አሜሪካ፤ እስራኤልና ኢትዮጵያ ከጉዳዩ ጀርባ አሉና። ምክንያቱም በዚህ ስምምነት ግብጽን በመጉዳት ርካሽ የፖለቲካ ጫና ለማሳረፍ ሲሉ ነው። እኛም እንደእነሱ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 35%  ኦሮሞ ስለሆነና ኦሮሞም ለመገንጠል የሚዋጋለት ኦነግ የሚባል ድርጅት ስላለው ለእሱ ሁለመናዊ ድጋፍ ማቅረብ አለብን። በሀገር ቤት ያለው ፖለቲካዊ የተቃውሞ መድረክ ደካማና ልፍስፍስ ስለሆነ ለመገንጠል በሚዋጉት እንደኦጋዴን ነጻነት ግንባር ያሉትን መደገፍ ይገባናል። ይህም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የተቀናጀ ጫና እንድናሳርፍ ያስችለናል። ይህ ሁሉ ተደርጎ  ውጤት ካላስገኘልን ሌላው አማራጭ ለግብጽ ኅልውና አደገኛ የሆነ ማንኛውንም ግድብ ለማውደም የምንችልበት ሁኔታ መፍጠር ነው። ለዚህም አስተማማኝ የደኅንነት መረጃ መኖር አለበት። ምክንያቱም አንዳንድ ጠበብቶች ግድቡን መጀመር በራሱ አደገኛና ጦርነት የማወጅ ያህል እንድንቆጥር በቂ ማስረጃ ነው እያሉን ነውና።

የአል አዝሃር ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት መምህር የሆኑት ደግሞ በተራቸው፤

አስታውሳለሁ፤ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግብጽ በመጣበት ወቅት በግብጽ ሕዝብ ላይ አላግጦ ነው የሄደው። ዐባይ ክንፍ የለውም፤ ወደእስራኤልም አይበርም አለ፤ ነገር ግን ማንኛውም ህዝብ እንደሚያውቀው የግብጽ ሕዝብም ያውቃል። የዓባይ ወንዝ በቀይባህር ስር የሚሄድበት የራሱ የቧንቧ መስመር ስውር ክንፍ አለው። ማንም ሀገር በቧንቧ መስመር ውሃ ወደሀገሩ እንደሚያስገባ ይታወቃል፤ ሲሉ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን በመቃወም ዐባይ ክንፍ አለው ብለዋል።  

የገድ አልተውራ ፓርቲ ሊቀመንበር ደግሞ ተራቸውን ጠብቀው እንዲህ አሉ፤

እንደዚህ ይባል ወይም አይባል እንደሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን አንዱ ጓደኛዬ ቅድም እንዳለው ኢትዮጵያ ብዙ ተቃዋሚዎች እንዳሏት ይታወቃል፤ እዚያም የተለየ እንቅስቃሴ እያየን ነው። የግብጽ ኤምባሲ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩ ምን ያደርግልናል? አስፈላጊ ነገር አሁን የፖለቲካና የመረጃ ክፍሎቻችን ብቻ ናቸው። በኢትዮጵያ ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመርኩዘን ሚና መጫወት አለብን። ይህንን ማስኬድ መቻል በትንሽ ወጪ ብዙ መስራት የሚያስችለን ሲሆን አጸፋዊ አደጋውም የቀነሰ ነው። በደንብ አድርገን በውስጥ ጉዳያቸው ብዙ መስራት ከቻልን ማዳከም ይቻለናል። አንድ የኢትዮጵያ ጋዜጣ እንዲህ አለ፤ ግብጽ የጦርነት ሃሳብ የላትም። ይህንን የማድረግ ብቃት የላትም፤ ሚሳይል የላትም፤ አውሮፕላን የላትም፤ ቢኖራትም ሱዳን በክልሏ ላይ ይህ እንዲደረግ አትፈቅድም ብሏል። በእርግጥም የሱዳኖች ሁኔታ ለእኛ በጣም የሚያሳምም ነው። ሁኔታዋ ማድረግ ከሚገባት አንጻር ሲታይ በጣም ደካማ ነው።  በእኛም በኩል መረጃ ፍሰት ችግር አለ።  ግብጽ የጦር አውሮፕላን ልትገዛ ነው፤ በአየር ላይ ነዳጅ መሙላት የሚችል አውሮፕላን አላት ወዘተ የሚሉት መረጃዎች መውጣት አለባቸው፤ በእርግጥ ባይሆንም እንኳን መረጃው በዲፕሎማሲያዊ ጥረታችን ላይ የራሱን ተጽዕኖ ያሳርፋል።

የሪፎርምና ደቨሎፕመንት ፓርቲ ሊቀመንበር ደግሞ ተራውን ተረክበው እንዲህ ዶለቱ፤

እኛ ባለን ግንዛቤ የብሔራዊ ቡድናችን ኢትዮጵያ ሄዶ ባደረገው ጫወታ ተጽእኖ በመፍጠር ማሸነፍ መቻሉን ነው። ብሔራዊ ቡድናችን የአፍሪካ ሻምፒዮን መሆኑና እጅግ በአመርቂ ውጤት ጫና መፍጠር መቻሉ በራሱ የሚያሳየው እውነትም ግብጻውያን ጫና የመፍጠር ጥበብ እንዳለን ነው። ትልቅም ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም አለን። የግብጽን ቤተክርስቲያንና የአልሃዛር ስኮላሮችን በዚህ ጉዳይ መጠቀም እንችላለን። አንዳንዶች የጦርነት አማራጮች ሊኖር እንደሚችል ያወራሉ። የሚወራውን ነገር ለመተግበር አስቸጋሪ ነው። እንደዚህ ዓይነቱን እሳቤ መነቀፍ ይገባዋል። ከዚህ ይልቅ የግንኙነት ምህዋራችንን ከኤርትራ፤ ከሶማሊያና ከጅቡቲ ጋር ብናደርግ ለደኅንነታችን ክፍሎች ትልቅ መስክ ነው።  ይህንን ማድረግ ጥሩ ከመሆኑም ባሻገር ግንኙነት የማድረግ መብታችንም እንደመጠቀም ስለሆነ ተገቢ ነው። ተስፋችን ሲጨልም ደግሞ ሃሳባችንን መፈጸም የምንችልባቸው በተዘዋዋሪ አንድ መቶ መንገዶች ስላሉን ሁሉንም እናደርጋለን።

የኢስላሚክ ሌበር ፓርቲ ሊቀመንበር ደግሞ ምኞታቸውን ከፍ አድርገው ተናገሩ፤

እኔ ከጠላቶቻችን ጋር ጦርነት የምናደርግበት ቀን ናፍቆኛል፤ በእርግጥም ከእስራኤልና ከአሜሪካ ጋር። ጦርነቱ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎ ተገቢውን ፍትህና እርጋታ የሚያመጣ መሆን ከቻለ። ምንም እንኳን ይህ ውይይት ምስጢራዊ ውይይት እንደመሆኑ ሁሉንም ነገር በምስጢር መያዝ ይገባናል። ውይይታችን ወደሚዲያ ሾልኮ መውጣት የለበትም። በእህታችን በባኪናም በኩል በግልጽ ከሚወጣው በስተቀር። ሕዝባዊ የሀገራዊ ደኅንነት እቅድ በግልጽ እንዲኖር እንፈልጋለን። እኛ እንዲህ ቢሆንም እንኳን………. (አቋረጡ) ቀጠሉና እሺ…..መልካም………እኔ የማነሳቸው ነጥቦች አግባብ ከመሆናቸው ጀርባ በእርግጥም ምንም ምስጢርነት የላቸውም። ውጊያችን ከአሜሪካና ከእስራኤል ጋር እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር አይደለም። ስለዚህ ውጊያችንን ለማስኬድ ፤ ይህ የኔ ሃሳብ ነው……….( ፕሬዚዳንት ሙርሲ ጣልቃ ገቡና፤ ይህ ውይይት እኮ በቀጥታ ስርጭት እየሄደ ነው ያለው! አሉ) የኢስላሚክ ፓርቲው ሊቀመንበርም፤ እኔም የምስጢር እቅድ ወይም ፕላን ማብራሪያ እየሰጠሁ አይደለም!  ሲሉ በጉባዔው ሳቅ ሆነ።  ቀጥለውም «እኔ ያልኩትን እኮ ማንም ሀገር የሚያደርገው ነው፤ በሌሎችም ሲባል የቆየ ነው» አሉ። (የጉባዔው ረጅም ሳቅ!!)
ማንም ሀገር ለከባቢያዊ ጥቅሙ የሚያደርገው ነው። እኔ ለግብጽ ሕዝብ የምለው ማንም ተነስቶ የውሃ አቅርቦትህን ሊዘጋ አይችልም ነው። የግብጽን ሕዝብ የዓለም አደገኛው የጽንፈኝነት መንገድ እንዲገባ ካልፈለጉ በስተቀር ይህን አያደርጉም። እስኪ አስቡት 80 ሚሊዮን ግብጻዊ ውሃ ሲዘጋበት በአሜሪካና በእስራኤል ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?

ፕሬዚዳንት ሙርሲ፤ የልባቸውን በልባቸው ይዘው፤ በዲፕሎማሲያዊ  ቋንቋ ደስ የተሰኙበትን ገታራ ውይይት አለዝበው እንዲህ ሲሉ ደመደሙ።  

«እኛ ለሰሜንና ደቡብ ሱዳናውያን የከበረና የተትረፈረፈ አክብሮት አለን» አሉና የሱዳንን ዳተኝነት ሸነገሉ። «ውሳኔዎቻቸውን ሁሉ እናከብራለን» ሲሉ በማሞካሸት ጠላት ማፍራት እንደማይገባ በውሰጠ ታዋቂ ጠቆሙ። እንደዚሁም ሁሉ «ለኢትዮጵያ ሕዝብም ያለን አክብሮት ተመሳሳይ ነው!» አሉና ዙሪያ ገባህን እሳት እንለኩሳለን ሲል ለቆየው ጉባዔ ማለስለሻ ቫዝሊን ቀቡት። እኛ የትኛውንም ጀብደንነት ጀማሪዎችና በማንም ላይ አሳቢዎችም አይደለንም አሉ። ነገር ግን አሉ ፕሬዚዳንት ሞርሲ፤ ነገር ግን መታወቅ ያለበት  እያንዳንዷን የዐባይ ውሃ ጠብታ ለመከላከል እጅግ የጠነከረ እርምጃ የምንወስድ መሆናችን ነው። ለእያንዳንዷ ጠብታ ውሃ!
(ተፈጸመ)