Tuesday, June 4, 2013

በሰማንያ ወአሀዱ ሽፋን የተፈጸመው የጠላት ሴራ ሲገለጥ ( ክፍል ፪ )


( ክፍል ፪ )
ከዚህ በፊት በክፍል ፩ ለመግለጽ እንደሞከርነው ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉም ውስጥ እጁን በማስገባት የራሱን ዓላማ በእግዚአብሔር ቃል ሽፋን ሲፈጽም መቆየቱን ለማብራራት ሞክረናል። ክርስቲያኖች እውነቱን አውቀው እግዚአብሔርን ወደማምለክና በአንድያ ልጁ በኩል የተደረገውን የማዳን ሥራ በቂ እንዳልሆነና ልዩ ልዩ የድኅነት/ የመዳን/ መንገዶች መኖራቸውን በማሳየት መመለሻ ወደሌለው ጥፋት ለመውሰድ ሌሊትና ቀን የማይደክም ብርቱ ጠላት መሆኑ «የሚውጠውን የሚፈልግ አንበሳ» የተባለው ቃል ያረጋግጥልናል።

ብፁዕ አቡነ ሺኖዳ የቅብጥ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ከጻፏቸው በርካታ መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነውና «diabolic war» /ዲያብሎሳዊ ውጊያ/ በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ ዲያብሎስን ጠንካራ የሚያደርገው መልካም ነገር አለ ብሎ ባሰበበት ቦታ ሁሉ ከፍተኛ ውጊያ ቢገጥመው እንኳን ተስፋ ቆርጦ ስለማይሄድ ክፉ ጠላት በማለት ይገልጹታል። ሲሸነፍ አሜን ብሎ እጁን የሚሰጥ ሳይሆን ጊዜ እየጠበቀ እስከመጨረሻው ድረስ ያለመታከትና ያለመሰልቸት መዋጋት መቻሉ የክፋቱን ልክ ያሳያል ይላሉ። በእርግጥ ዲያብሎስ ከክብሩ የወደቀና የተሸነፈ መልአክ ነው። ቢሆንም ያለው ከሙሉ ኃይሉ ጋር ስለሆነ  ውጊያው ቀላል ስላይደለ እምነታችንን እንዳይጥልብን አጽንተን እንጠብቅ ዘንድ ይመክሩናል። 

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6፥12
«መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ»

ስለዚህ ጠላታችን ኃይለኛ ተዋጊ እንጂ የወደቀ ነው ተብሎ የሚናቅ ስላይደለ አብያተ ክርስቲያናትን አጥብቆ መዋጋቱን መዘንጋት ተገቢ አይደለም። ግለሰቦችን ተዋግቶ ከማሸነፍ ይልቅ ግለሰቦች የተሰባሰቡባትን ቤተክርስቲያን የምትመራበትን ቃል መጠምዘዝ መቻል ሁሉንም ከእውነተኛው መንገድ ላይ ማስወጣት መቻል መሆኑ አሳምሮ ስለሚያውቅ  ይህንኑ በትጋት ይፈጽማል።ከዚህም የመዋጊያ ስልቱ መካከል ቅዱሱን የእግዚአብሔር ቃል ባደረባቸው ሰዎች በኩል ማጣመም፤ መሸቃቀጥ፤ ብዙ የመዳን መንገዶች እንዳሉ ማሳየት፤ የኢየሱስ ክርስቶስን ብቸኛና ብቁ መድኃኒትነት በልዩ ልዩ መድኃኒቶች መተካት ዋናው ስራው ነው። ይህንንም በተግባር ሲሰራ ቆይቷል። ለዛሬም ጥቂቱን በማሳየት እንዴት እንደተዋጋን ለማሳየት እንሞክራለን።

1/ የመጽሐፍ ቅዱስን ቁጥር ማዛባት የጠላት ዋነኛ ሥራው ነው..

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የጻፉት መሆኑ አያጠያይቅም። ቀደምት አበውም የመጽሐፍ ቅዱስን ቅደም ተከተል፤ ምዕራፍና ቁጥር የተነተኑትም በመንፈስ ቅዱስ መርምረው መሆኑንም እናምናለን። ችግሩ የሚነሳው በዚህ ዘመን ላይ እንደመጽሐፍ ቅዱስ አካል የሚቆጠሩት የቀደምት መጻሕፍት አካል የሆኑት የትኞቹ ናቸው? የሚለው ጥያቄ ነው። ለማሳየነትም በቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለ1600 ዓመት ስትመራ ቆይታለች እየተባለ የሚነገርላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ቁጥርና ዝርዝር በፍጹም አይመሳሰልም። ለምን? ሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት የመጽሐፍ ቅዱስ ቁጥርና ዝርዝር አንድ ካላደረጋቸው አንድ ነበሩ ሲያሰኝ የቆየው ታዲያ ምን ነበር? እነአትናቴዎስን ከፍ ከፍ የምታደርገው በምን መለኪያ ነው? በዋናው የእግዚአብሔር ቃል ልዩነት ካላቸው በሃይማኖት አይመሳሰሉም ማለት ነው። የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በዕብራውያን እጅ ያሉትን 39 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንደትክክለኛ የእግዚአብሔር እስትንፋስ መጻሕፍት አድርጋ ትቀበላለች። ካርቴጅ  በተደረገው ጉባዔ መጻሕፍት አምላካውያት ላይ ቀኖና ሲደነገግ እነቅዱስ አትናቴዎስ 39ኙን የዕብራውያን መጻሕፍት አጽድቀዋል። ኮፕትም ይህንኑ ተቀብላ እስከዛሬ አለች። እንደዕብራውያን መጻሕፍት የማይቆጠሩና በተጨማሪ ቀኖናተ መጻሕፍት የተያዙ /Deutrocanonical/ መጻሕፍትን ለብቻ መዝግባለች። 
እነዚህም 1/ እዝራ ሱቱኤል (አንድና ሁለትን) እንደአንድ መጽሐፍ 2/ ጦቢት 3/ ዮዲት 4/ ጥበበ ሰሎሞን 5/ ሲራክ 6/ ባሮክ 7/ መቃብያን (አንድና ሁለት) እንደአንድ መጽሐፍ መያዟ ይታወቃል። እነዚህም መጻሕፍት ቢሆኑ ድምራቸው ከዕብራውያን መጻሕፍት አይደሉም።  መጽሐፈ ሔኖክ፤ 3ኛ መቃብያን ፤ 4ኛ መቃብያን የሚባሉትን መጻሕፍት እንደትርፍ መጻሕፍት አድርጋ አትቀበልም።  መቃብያን አንድና ሁለት ራሱ ከኢትዮጵያው መቃቢያን ጋር ምንም የሃሳብና የመንፈስ ግንኙነት የሌለው በመሆኑበሁሉም  በመጽሐፈ መቃብያን በኩል ቅብጥና ኢትዮጵያ ልዩነታቸው የሰማይና የምድር ያህል ይርቃል። ለምን?

ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደቅዱሳት መጻሕፍት አድርገው ያልቆጠሯቸውን መጻሕፍት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከማን አግኝታ ተቀበለቻቸው? ለመቀበል ያስቻላት መመዘኛ ምንድነው? እስክንድርያ እናቴ፤ ማርቆስ አባቴ ስትል የቆየችባቸው ዘመናት የክርስትና ሕይወትና ዓምድ በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ አንድነት ከሌላት መነሻው ምንድነው? ኮፕት 66ቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደአበው ቅዱሳት መጻሕፍት ድንጋጌ ስትቀበል፤ በትርፍነት እንደሕጻናት የመንፈሳዊ ትምህርት ማጎልመሻ መጻሕፍትነት 7 በተጨማሪ ወይም በዲቃላ መልክ ይዛ ትገኛለች። 

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ግን ዲድስቅልያ፤ አብጥሊስ፤ትዕዛዝ፤ ሥርዐተ ጽዮን፤ ግጽው፤ ቀሌምንጦስ፤ ዮሴፍ ወልደኮርዮን ወዘተ ሳይቀሩ በ4ኛውና በ5ኛው ክ/ዘመን የተጻፉትን ሳይቀር የቅዱሳት መጻሕፍት አካል አድርጋ መቁጠሯ ለምን ይሆን?
ሰማንያ ወአሀዱ ተብለው በተለምዶ ቢጠሩም እነሱም እስከ 85 ይደርሳሉ። አንዳንዴ የግድ የተለመደው 81ን እንዳያልፍ ሲባል ሁለቱን በአንድ እስከመጨፍለቅ ይደረሳል። ቀሌምንጦስ የሐዋርያው ጴጥሮስ ደቀመዝሙር የእጣ ክፍሉ በነበረችው በኮፕት ቤተክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ያበረከተ ብዙ መጻሕፍትን የጻፈ ቢሆንም ኮፕት የሱን መጻሕፍት እንደመጽሐፍ ቅዱስ አካል አድርጋ ያልተቀበለችው ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የኔ ሰማንያ አሀዱ በማለት በግድ የምትቆጥረው ምን ቁጣ ወርዶባት ይሆን? ከዘመነ ሐዋርያት በኋላ የተጻፉ መጻሕፍት ከመማሪያነትና በመንፈሳዊ እውቀት ከማነጽ ባሻገር እንደወንጌል ቃል ሊቆጠሩ ይችላሉ? የኛ ሰማንያ ወአሀዱ ይህንን ሁሉ ግሳንግስ ይዟል። ለምን? በምን መለኪያ? ቅዱሳት መጻሕፍትን በፈለጉበት ጊዜ እያነሱ መጨመር ይቻላል?

በዚህም ተባለ በዚያ አበው ሊቃውንት እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለባቸው ናቸው በማለት በቅደም ተከተል ያስቀመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን የማይታወቁ፤ ያልተመረመሩ፤ አበው በቀኖናቸው ያልያዟቸው፤ ብዙ ትርፍ መጻሕፍትን ይዛ መገኘቷ እንደቅርስ ካልሆነ በስተቀር እንደቅዱሳት መጻሕፍት ስብስብ ሊያስቆጥራቸው የሚችል አንዳችም አስረጂ አይቀርብባቸውም።
እስኪ ግብጽ/ቅብጥ/ እንደትርፍ መጻሕፍት የምትቆጥረውንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ግን እንደዕብራውያን መጻሕፍት እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያስጻፈው ነው ብላ የምታምንበትን 1ኛ መቃብያንን ምዕ 1፤1 በንጽጽር እንመልከት።

የቅብጥ ቤተክርስቲያን መቃብያን 1፤1

After Alexander son of Philip, the Macedonian, who came from the land of Kittim, had defeated Darius, king of the Persians and the Medes, he succeeded him as king. (He had previously become king of Greece.)

ተዛማጅ ትርጉም፤ «ከምድረ ኪቲም የመጣው መቄዶንያዊው የፊልጶስ ልጅ ፤ የፋርሱንና የሜዶኑን ንጉሥ ዳርዮስን አሸነፈ።ራሱንም ንጉሥ አድርጎ  ሾመ፤ ቀድሞም የግሪክ ንጉሥ ነበር»   (መቃብያን ቀዳማዊ 1፤1)

ይህ  ታሪክ ስለታላቁ እስክንድር የሚተርክ የታሪክ ክፍል ነው። ታላቁ እስክንድር ደግሞ የኖረበትን የታሪክ ዘመን ስንመረምር በ3ኛው መቶ አጋማሽ ዓመተ ዓለም የነበረ ጦረኛ ተዋጊ መሆኑን መረጃዎች ያሳዩናል። ከዚህ ተነስተን ስለ እስክንድር ታላቁ የሚተርከው ይህ የመቃብያን መጽሐፍ ታላቁ እስክንድር ካለፈ በኋላ እሱን በሚያውቁ ወይም ታሪኩን በሰሙ ሰዎች የተጻፈ ስለመሆኑ የጽሁፉ ይዘት ይጠቁመናል። ለጽሁፉም መነሻ ምክንያት የሆነው ኢየሩሳሌምን ጨምሮ ከፋርሶች እጅ ነጻ በማውጣቱ ምናልባትም የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊዎች የጻፉት ሊሆን እንደሚችል የነገረ መለኮት ታሪክ አዋቂዎች ይገምታሉ።  ግብጻውያንም እንደቅዱሳት መጻሕፍት ያልቆጠሩበት መነሻ ምክንያትም እስክንድር ቅድመ ክርስትና የነበረ ሰው ሲሆን በእምነትም አይሁዳዊ ባለመሆኑ የተነሳ ነው። በማታትያስና አምስት ልጆቹ ያለውን በሜዲተራንያን  አካባቢ በግሪኮች ላይ የተደረገውን የዐመጽ ትርክርት የሚናገር መጽሐፍ ነው። ዛሬም አይሁዳውያን እንደመንፈሳዊ መጽሐፍ ሳይሆን ከታሪክ መጽሐፍነት የበለጠ ስፍራ አልሰጡትም።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መቃብያን በተመሳሳይ(ምዕ 1፤1) ከኮፕቱ ጋር ሲተያይ፤

«ስሙ ጺሩጻይዳን የሚባል ኃጢአትንም የሚወዳት አንድ ሰው ነበር። በፈረሶቹም ብዛት፤ ከሥልጣኑ በታች፤ በጭፍራዎቹም ጽናት ይመካ ነበር» (መቃብያን ቀዳማዊ 1፤1)

የሃሳብ፤ የመልዕክት ግንኙነት ምንም የለውም። ይህ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መቃብያን ስለማታትያስና አምስት ልጆቹ የዐመጽ ታሪክ ምን አይናገርም። ይልቁንም የሜዶን ንጉሥ ሳይሆን ግሪኮች መካከለኛው ምሥራቅን ሲገዙ የነበሩበትን ዘመን ትቶ ወደኋላ በመሄድ ስለሜዶኖች ይተርካል። እንግዲህ ይህንን ዓይነት የመጻሕፍት ልዩነት መኖሩ መነሻው ምንድነው? ብለን ብንጠይቅ ጠላት እያሰረገ በቅዱሳት መጻሕፍት ሽፋን ያስገባው እንጂ   በሁለት አፍ የሚናገር ቃለ እግዚአብሔር ለክርስቲያኖች የተሰጠ  ሆኖ አይደለም።

2/ መጽሐፈ መቃብያን ያላቸው ተቀባይነት ፣

፩ኛና ፪ኛ መቃብያን በካቶሊክ፤ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶችና ኮፕት ኦርቶዶክስ ዘንድ እንደተጨማሪ መጻሕፍት ሲቆጠሩ በአይሁዶችና በፕሮቴስታንቶች ዘንድ እንደ እግዚአብሔር እስትንፋስ ስለማይቆጠር ተቀባይነት አላገኘም።  ፫ኛ መቃብያን በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች ዘንድ ብቻ ተቀባይነት ሲያገኝ በካቶሊክ፤ በኮፕት፤ በአይሁዶችና በፕሮቴስታንቶች  ዘንድ እንደ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ተደርጎ አይቆጠርም። ፬ኛ መቃብያን ደግሞ ከጆርጂያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብቻ እንጂ በየትኞቹም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። 

በመቃብያን ስም የሚጠራ ነገር ግን ከላይ ከተዘረዘሩት አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፈ መቃብያን ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ሦስት የመቃብያንን መጻሕፍት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና የኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው መቃብያን ይዘው ይገኛሉ። ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የማይቀበሉት በተለይም ከአይሁድ የኦሪት መጻሕፍት ውስጥ እንደአንዱ የማይቀጠርና ወዳጅ ቤተክርስቲያን የተባለችው የኮፕት ቤተክርስቲያን ጭምር የማትቀበለውን ይህንን የመቃብያን መጻሕፍት መቀበላችን ምክንያቱ ምንድነው?

ለኢትዮጵያውያን ለብቻችን ከሰማይ የወረደ ልዩ መጽሐፍ ስለሆነ ይሆን? በበፊቶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ እንደመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሳይቆጠር /Apocrypha/  ተብሎ ለብቻው የተቀመጠውን በ2000 ዓ/ም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን እንደቅዱሳት መጻሕፍት ቆጥራው መዝግባው መገኘቷ አስገራሚ ሆኗል። እቀበለዋለሁ በምትላቸው የኒቂያ፤ የኤፌሶንና የቁስጥንጥንያ ጉባዔያት ውስጥ ከቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የሌሉትን በ2000 ዓ/ም እትም ውስጥ ማስገባትዋ የጤንነት ነው? በእርግጥም ጠላት ቤተክርስቲያኒቱን በእውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እንክርዳዱን በደንብ መዝራት መቻሉን ያረጋገጠ ሆኗል።

3/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መቃብያን ግልጽ ስህተቶች፤ 

መቃብያን ምንጩ ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከሰዎች ልብ መንጭቶ የተጻፈ ስለመሆኑ ብዙ ግድፈቶችን ማቅረብ ይቻላል። ለምሳሌ ያህል በ1ኛ መቃብያን 10፤ 1-2 ያለውን እስኪ እንመልከት። እንዲህ ይላል።
«ነገር ግን እንዲህ ካልሆነ የቀደሙት ሰዎች ከአዳም ጀምሮ ከሴትና ከአቤል፤ ከሴምና ከኖኅ ከይስሐቅና ከአብርሃም ከዮሴፍና ከያዕቆብ፤ ከአሮንና ከሙሴ ጀምሮ በአባቶቻቸው መቃብር ይቀበሩ ዘንድ ነው እንጂ በሌላ ቦታ ይቀበሩ ዘንድ ያልወደዱ ለምንድነው? በትንሣዔ ጊዜ በአንድነት ሊነሱ አይደለምን? አጥንታቸውስ ጣዖት ከሚያመልኩ ከክፉዎች ከአረማውያንም አጥንት ጋራ እንዳይቆጠር አይደለምን?» 

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረን አሮን የሞተው በሖር ተራራ ላይ ርስት ምድር ሳይገባ በሞዓባውያን ሀገር ነው። ዘኁል 20፤25-26 ሞዓብ ደግሞ ጣዖት አምላኪያውያን ናቸው እንጂ እስራኤላውያን አልነበሩም። መጽሐፈ መቃብያን ግን የሌለውን ታሪክ በመለፍለፍ አሮን  ከአባቶቻቸው መቃብር ከተቀበሩት አንዱ እንደሆነ ውሸት ይተርክልናል። የአብርሃምና ሚስቱ ሣራ እስከዛሬም  መቃብራቸው ያለው በኬብሮን ነው።  ዘፍ 23፤19-20  ኬብሮን ደግሞ ከደቡባዊ እስራኤል ከተማ አንዷ ናት። በአሮንና በአብርሃም መቃብር መካከል ያለው የቦታ ልዩነት ሩቅ ነው።  ሙሴ እስከዛሬ ድረስ መቃብሩ የት እንደሆነ እንደማይታወቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የሞተው ግን በናባው ተራራ ላይ ነው። መቃብሩ በሞዓብ ሸለቆ ውስጥ ቢሆንም መቃብሩ አልተነገረም። ታዲያ የሙሴን መቃብር የት እንደሆነ አውቆ ነው መቃብያን ከአባቶቻቸው ጋር ለትንሣዔ ቀን እንዲያመች  አንድ ቦታ ተቀበሩ የሚለን? መቃብያን ስማቸውን በመጥራት ሁሉ አንድ ቦታ እንደተቀበሩና ይህም የሆነው መቃብራቸው ከጣዖት አምላኪዎች ጋር እንዳይቀላቀል፤ በትንሣዔ ቀንም አብረው እንዲነሱ ሲሉ ነው የሚለን ትንሣዔን የቦታ ርቀት ይከለክለዋል? 

በጣዖት አምላኪ መካከል መቀበር ሟችን የኃጢአት ተጋሪ እንዲሆን ያደርገዋል? መቃብያን አስገራሚ ትንተናና ልብወለዳዊ ትረካውን በመስጠት አንድ ላይ ያልተቀበሩትን መተረኩ ያስደንቃል። ስለዚህ መቃብያን የተጻፈው በእግዚአብሔር መንፈስ አይደለም። ቦታ አያውቅም፤ ታሪክ አያውቅም፤ የእግዚአብሔርንም የትንሣዔ አሠራር አያውቅም። ይህንን ዓይነት መዛነፍ በማስከተል በቀደምት አበው ተሸፍኖ መቃብያን ከቅዱሱ የእግዚአብሔር ቃል ጋር እንዲቆጠረው ያደረገው ጥንተ ጠላታችን መሆኑን ከመቀበል ውጪ ያፈጠጠውን እውነት መካድ የሚቻል አይደለም።
(ይቀጥላል)