መንበረ ፓትርያርክ ቅ/ማርያም ቤ/ክ 1921 ዓ/ም (ፎቶ ምንጭ፤ ሰሎሞን ክብርዬ)
በወቅቱ የሀ/ስብከቱን ክፍፍል በመቃወም ያወጣነውን ጽሁፍ ለማስታወስ ቀንጭበን ከታች አቅርበናል።
ከዚህ ውስጥ ዋነኛውና አስደናቂው ውሳኔ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ሰነጣጥቆ የማጠናቀቁ ሂደት አንዱ ነበር።
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ችግር ጠንቅቆ የሚያውቅ የሲኖዶስ አባል የለም። ጳጳሳቱ የተመደቡባቸውን ሀ/ስብከቶች ለሥራ አስኪያጆቻቸው አስረክበው ሁለትና ሦስት ወራት ከአዲስ አበባ ቤቶቻቸው መሽገው ወለተ ማርያምንና ገ/ማርያምን እያሳለሙ እንደሚቀመጡ ይታወቃል። ግድ እየሆነባቸው እንጂ ሐዋርያዊ ተልእኰ ለመፈጸም ዝግጁዎቹ ጥቂቶች ናቸው። ስለዚህ አብዛኛዎቹ ጳጳሳት በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለመመደብ ያላቸው ፍላጎት ጫን ያለ ነው። ይህንኑ ጽኑ ምኞት ለመተግበር የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ከፓትርያርክ ጳውሎስ ልዩ ሀ/ስብከትነት በማላቀቅ 4 ቦታ እንዲከፈልና 4 ሊቃነ ጳጳሳት ሊመደቡበት ይታገሉ እንደነበር ያለፉት ጉባዔያቶቻቸው ያስረዱናል። ተፈላጊው ነገር የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ችግሮች ምን እንደሆኑ በማወቅ መፍትሄ ለማምጣት ሳይሆን የአቡነ ጳውሎስን ስልጣን ከሀ/ስብከቱ ላይ በመቀማት 4 ጳጳሳት ተመድበውበት የሞቀ የደመቀውን በማግኘት ከክፍለ ሀገር ሀሩርና አቧራ ለመገላገል ብቻ ነበር። የሚገርመው ነገር ዛሬ አቡነ ጳውሎስ በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ ፍላጎታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ መቻላቸው ሳይሆን ለምን? እንዲከፈል እንደተፈለገ አለማወቃቸው ነው። ምክንያቱም ሀ/ስብከቱን እንደዓይናቸው አምሮት ከመሰነጣጠቃቸው በቀር ለምን መሰነጣጠቅ እንዳስፈለገ የተናገሩት አሳማኝና ጥናታዊ መረጃ ያለውን ዝርዝር ነገር ሲነግሩን አለመደመጡ ነው። እንደ ደጀብርሃን ብሎግ እምነት የአዲስ አበባ ሀስብከት መሰንጠቅ የተፈለገው በሁለት ምክንያት እንደሆነ ከፍላጎቶቻቸውና ከዓላማዎቻቸው አንጻር እንረዳለን።
1/ ከሚመጣው ፓትርያርክ ልዩ ሀ/ስብከትነት ነጻ በማውጣት ለሚመደቡ ጳጳሳት ልዩ የደስታ ግዛት ለመፍጠር፤
2/ ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአንድ ሰው ግዛት አድርጎ ከማቆየት ይልቅ ከፋፍሎ ለሌሎችም ቶሎ እንዲዳረስ ለማስቻል ነው ብለን እንገምታለን። ምክንያቱም መሰነጣጠቅ ያስፈለገው ምን ለማምጣት እንደሆነ አሳማኝ ነገር አለመቅረቡ ነው።
በኛ እምነት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት መሰንጠቅ ትክክለኛ ያልሆነ ውሳኔና የሀ/ስብከቱን ችግር ያልተመለከተ ስሜታዊ ውሳኔ ነው እንላለን። ምክንያቶቻችንም ለሀ/ስብከቱ የተሻለ መንገድ መኖሩን በማመላከት ይሆናል።
1/ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሀገሪቱና የአፍሪቃ ዋና ከተማ ከመሆኑም ባሻገር የቤተክርስቲያኒቱ ማእከላዊ ሀ/ስብከት በመሆኑ ሁኔታዎችን የገመገመና ወቅቱን ያገናዘበ ልዩ መተዳደሪያ ደንብ ሊኖረው የተገባ ነው።
2/ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት አወቃቀር የመንግሥትንና ዓለምአቀፍ ተቋማትን ደረጃ ያገናዘበ ዘመናዊ፤ ሙያዊና ችሎታን የተመረኮዘ የአስተዳደር መዋቅር የያዘ መሆን ይገባው ነበር።
3/ አሁን ያሉትን ስድስት ሥራ ፈት የወረዳ ጽ/ቤቶችን ወደ አራት በማጠቃለል በአውራጃ ጽ/ቤት ደረጃ ሥልጣንና ኃላፊነት ከሀ/ስብከቱ ከፍሎ በመስጠት እንደአዲስ ቢደራጅ ስልጣን የተሰበሰበበትን የሀ/ስብከቱን ማእከል ጫናና ድርሻ ከመቀነሱም በላይ ተጠያቂነት ያለው አሠራርን ማስፈን ይቻል ነበር።
4/ የሀ/ስብከቱ አድባራትና ገዳማት የአስተዳደር መዋቅር በሀ/ስብከቱ መተዳደሪያ ደንብ በትክክል የተቀመጠውን የተከተለ መሆን የሚገባው ሲሆን ሙያን፤ ችሎታን፤ ብቃትን፤ ልምድንና መልካም ሥነ ምግባር የተከተለ የአስተዳደር መዋቅር ሊፈጠርበት ይገባዋል።
5/ በየአድባራት ያሉትን ከመጠን በላይ ያለውን የሠራተኞች ቁጥር ወደሌላ የልማት ዘርፍ በመቀነስ እንደ አዲስ ማደራጀት የግድ መሆን አለበት።ይህ የልማት ዘርፍ ከደመወዝ ጠባቂነት ይልቅ አምራች ዜጋ እንዲኖርና የሚፈልሰውን ቅጥር ፈላጊ ለመከላከል የሚያስችል ነው።
6/ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት አድባራቱ በጋራ ያላቸውን ካፒታል በማሰባሰብ በሚያቋቁሙት የልማት ተቋም የገቢ አቅም እንዲፈጥሩና ከልመና ገንዘብ እንዲላቀቁ ማድረግ ይጠበቅበታል። ለምሳሌ በጋራ ገንዘባቸው፤ ማተሚያ ቤት ወዘተ ማቋቋም ይቻላል።
7/ ቤተክርስቲያኒቱ ብዙ ባለሙያና አዋቂ ምእመናንና ምእመናት እያሏት ከዳር ሆነው ድክመቷን እየተመለከቱ፤ እሷም ልትጠቀምባቸው ሳትችል መቅረቷ ይታወቃል። በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የሚደራጅ የምሁራን ልጆቿ የአማካሪ ቦርድ ቢኖረው ሀ/ስብከቱ ተጠቃሚ ይሆናል።
ሌሎች ተጨማሪና አስፈላጊ ነጥቦችን ለመፍትሄው በማስቀመጥ አሁን ያለውን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ችግር ማቃለል እየተቻለ ሲኖዶስ ሀ/ስብከቱን መሰነጣጠቅ መፈለጉ ትክክል አይደለም። የትኞቹን ችግር በየትኞቹ መንገዶች ለማቃለል ተፈልጎ ነው ሀ/ስብከቱን በብዙ ሊቃነ ጳጳሳት ስር መሰንጠቁ ያስፈለገው? ለሚለው ጥያቄ አሳማኝ መልስ የለም።
የአዲስ አበባ መስተዳደር እንኳን የሚተዳደረው በአንድ ከንቲባ ሥር ሆኖ ራሳቸውን ችለው በተወሰነ ሥልጣንና ኃላፊነት በተደራጁ ክ/ከተሞች እንጂ በልዩ ልዩ ከንቲባ ተሰነጣጥቆ አይታይም። የኛዎቹ በብዙ የሊቀ ጳጳስ ከንቲባ ሥር ሀ/ስብከቱን ከፋፍለው ሲያበቁ በሀ/ስብከቴ ጣልቃ አትግባ የሚል ድምጽ ለማስማትና አንድ ሠራተኛ ከአንድ ክፍል ውስጥ ወደ ሌላኛው ክፍል እንዳይዘዋወር የሚያደርግ ስለሆነ ይህንን መፈለጋቸው አስገራሚም አሳዛኝም ነው። ውጤቱም አሳዛኝ ከመሆን አይዘልም።
ለወትሮውስ ቢሆን ርዕይና ግብ ከሌለው ጉባዔ ከዚህ የተሻለ ምን ሊጠበቅ ኖሯል? ሲኖዶሱ ራሱ ተሰነጣጥቆ አዲስ አበባንም በፈቃዱ ሰነጣጥቆ አረፈው። የ10 ቀናት ውጤት ይህ መሆን ነበረበት? ለአንባቢዎች የምናስገነዝበው ጽሁፋችን ለነቀፋ ሳይሆን በተገቢ ሂስ፤ አሳማኝ መልስ የሚሰጥ ካለ ያንን ለማግኘት ሲሆን መሠረቱም በሚታይ ገሃዳዊ እውነታ ላይ ተመስርተን ብቻ መሆኑን እንድታውቁልን ነው።