የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የምርጫ
ሂደት በ1957 ዓ/ም ተሻሽሎ የወጣ ነው። ምርጫው የቤተክርስቲያኒቱ አባል የሆነው በሙሉ ያካተተ እንዲሆን የተሞከረበት ህገ ደንብ
አለው። በእርግጥም ምርጫው በሲኖዶስ ፈቃድና እጣ የሚያበቃ ሳይሆን
ከየትኛውም ዘርፍ ያለውን አባሏን የሚያሳትፍ በመሆኑ እውነተኛ አባት ለመምረጥ አስቸጋሪ አልሆነባቸውም። ቢያንስ ቢያንስ አሁን ባለው
የፖፕ ሺኖዳ ምትክ ምርጫ ላይ እንኳን ወደ 14 ሰዎች በግልና በጥቆማ ከቀረቡት የፓትርያርክ እጩዎች ውስጥ የማይፈለጉ ሰዎች ወደዚያ
መንፈሳዊ ወንበር ሾልከው እንዳይወጡ ማስቀረት የሚችልበት የምርጫ ወንፊት ስላለው እስኪጣራ ድረስ ሂደቱን ሊያዘገይ አስችሎታል።
መዘግየቱ ለመንበረ ሥልጣኑ ክፍት ሆኖ መቆየት አስቸጋሪ መሆኑ ባይካድም ክፍት እንዳይቆይ ተብሎ በሆይ ሆይ ቢሾም ደግሞ የማይፈለጉ ሰዎች በቡድንና በድጋፍ ተጠግተው ሥልጣኑ ላይ ከወጡ በኋላ ሳያስለቅሱ
ማውረድ እንዳይቸግር ከወዲሁ በወንፊት የማበጠሩ ጉዳይ መኖሩ ኮፕቶችን ቢጠቅማቸው እንጂ አይጎዳቸውም። ከዚያው ያገኘናቸው መረጃዎች
የሚጠቁሙት ያንን ነው። እኛም የበሰለ ነገር ቢበሉት ሆድ አይጎረብጥምና ነገሩን አብስላችሁ ማቅረባችሁ ይበል የሚያሰኝ ነው እንላለን።
ወደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ስንመጣ የራሷን ፓትርያርክ ስትሾም እድሜው እንደጥንታዊነቷ አይደለም። የዚያን እንዴትነት እስከነ ሰፊ ታሪኩ ትተን ፓትርያርክ መሾም
ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ሁኔታ በግብጽ አጽዳቂነት የተከናወኑትን ስንመለከት የድክመቶቻችን ውጤት እንጂ ስኬታችን ትልቅነት
አድርጎ መመልከቱ ሚዛን አይደፋም። ራሳችን መሾም ጀምረናል ካልንበት ጊዜም ጀምሮ ቢሆን የመንግሥት እጅ በጓሮ በር ሳይገባበት የተከናወኑ
ምርጫዎችን ለማግኘት ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ስለሚሆን አልፈነዋል። እንደዚያም ሆኖ በመገዳደል፤ በመከፋፈልና በመሰነጣጠቅ፤ በመወጋገዝ የተሞላ መሆኑ የአሳዛኝ ገጽታው አንዱ ፈርጅ ሆኖ ዘልቋል። ዛሬም ከዚያ አዙሪት
ስለመውጣታችን እርግጠኞች አይደለንም። ቤተክርስቲያኒቱን በማስቀደም ሳይሆን የሥልጣን ጥምን ለመወጣትና የመንፈሳዊ ማንነት ጉድለቱ
ግዝፎ በመታየቱ ችግሮቻችን በአጭሩ የፕትርክና ታሪካችን ውስጥ የሺህ ዓመት ጥላሸትን አኑሯል።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
የፓትርያርክ አሿሿም ልምዷ ከጥንታዊነቷ ጋር የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ቢሆንም እንኳን ፓትርያርኳን ለመሾም የግድ የ1000 ዓመት ልምምድ ያስፈልጋታል ወይ?
ብለን እንጠይቃለን።
« ሞኝ ሰው ከራሱ ስህተት ይማራል፤ ብልህ ሰው
ግን ከሞኝ ሰው ስህተት ይማራል» እንዲሉ የሌሎችን ልምድ ቀምረን
እኛ የተሻለ ሥራ ለመስራት እንደብልሁ ሰው መሆን ባንችል እንኳን እንደሞኝ ሰው ከስህተቶቻችን መማር ለምን እንደከበደን ሳስብ ግራ
ይገባኛል።
በ21ኛው ክ/ዘመን ዲሞክራሲን ለመማር እንደአሜሪካ
200 ዓመት እስኪሞላ የምንጠብቅ ከሆነ ከሉላዊነት አስተሳሰብ ውጪ ነን ማለት ነው። አሜሪካ ውስጥ የተመረተ ሸቀጥ ኢትዮጵያ እስኪደርስ
200 ዓመት ይፈጅበታል ብሎ እንደማሰብ ይሆናል። እንደዚሁ ሁሉ ከኮፒቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የፓትርያርክ አሿሿም ሕገ ደንብ
ለመማር የግድ የግብጽ ጳጳሳት እንደገዙን 1600 ዓመት ልንጠብቅ አይገባም። የፓትርያርክነት የምርጫ አዙሪት በመገምገም መፍትሄው በቅርቡ ሊሆን ይችል ይሆን? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ሩቅ
ይሆንብኛል።
አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ሲሆኑ በምርጫው ላይ
የነበሩ ጳጳሳት ዛሬም አሉ። አቡነ መርቆሬዎስ ሲባረሩም፤ የመባረራቸውን ተገቢነት የደገፉ አሁንም አሉ። አቡነ ጳውሎስ በተባረሩት ምትክ ሲሾሙ የመረጡ አሉ። አቡነ ጳውሎስን
የመረጡ ተመልሰው የጠሏቸው፤ አሁን ሲሞቱ ደግሞ ተመልሰው ለመመረጥ ወይም ለመምረጥ ያሰፈሰፉ አሉ። እንግዲህ አቋሟቸው ለመገለባበጥ
እንጂ ሊኖር በሚገባ ሃይማኖታዊ ጽናት ለመቆም በማይችሉ ሰዎች በሞላበት ሲኖዶስ ተስፋ የሚጣልበትና እግዚአብሔር የወደደውን ምርጫ
ለማካሄድ ገና መቶ ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል። ለዚያውም ሰማይና ምድር ሳያልፉ ከጠበቀን ነው። ዛሬ እንኳን ለምርጫው በውስጠ ምስጢር
በመንግሥት በኩል የታለሙትና አውሬው ደግሞ በከተማይቱ እያስተጋባ የሚገኘውን ድምጽ ስናዳምጥ ነገም ልቅሶአችን ቀጣይ መሆኑን አመላካች
ነው። በዚህ ዓይነት መልኩ ከሄድን ደግሜ እላለሁ፤ ነገንም ከእንባ አንላቀቅም።
የኛ ጉዳይ እንደዚህ ነው። የሚሆነውንና የሚመጣውን
ከማያልቅበት እድሜ አይንፈገንና ሁሉን እናይ ይሆናል። እስከዚያው እስኪ ከኮፕቶች የፓትርያርክ ምርጫ ደንብ ጥቂት እንመልከት።
1/ ፓትርያርኩ ባረፉ በ7ኛው ቀን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና የጠቅላይ ምክር ቤት አባላት ባሉበት በጵጵስና ቀዳሚ
የሆነው ሊቀጳጳስ ዐቃቤ መንበር ሆኖ ይሰየማል። የዐቃቤ መንበሩ ምርጫ እንዳበቃ የፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ ይዋቀራል። አስመራጭ ኮሚቴው 18 አባላት ያሉት
ሆኖ 9 ጳጳሳት ከሲኖዶሱ፤ 9 አባላት ደግሞ ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ይመረጣሉ።
ጠቅላይ ምክር ቤት ማለት በፓትርያርኩ ሊቀመንበርነት የሚመራ በመንበረ ፓትርያርኩ ስር የተዋቀረ ሲሆን
የሲኖዶስ አባላት፤ ቤተክርስቲያኒቱን በገንዘብ፤ በጉልበትና በእውቀት
የሚደግፉ ምእመናን፤ አገልጋይ ካህናትና ዲያቆናት፤ የሰንበት ት/ቤት አባላት፤ ያሉበት የ24 አባላት ምክር ቤት ነው።