የታመመ ሰው ሕክምና የሚሄደው ለሕመሙ ተገቢውን
ህክምና ለማግኘት ነው። ሐኪሙ፤ ከታማሚው የሚያገኘውን የቃል መረጃና በምርመራ ያገኘውን ውጤት አንድ ላይ አዋሕዶ ካልሰራ በስተቀር
ፈዋሽ መድኃኒት ማዘዝ አይችልም። ቢያዝ እንኳን ለማያውቀውና መርምሮ ላልደረሰበት በሽታ የሚሰጠው መድኃኒት ከፈዋሽነቱ ይልቅ ጎጂ
እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ይሆናል።
እንደዚሁ ሁሉ በጥቅምት ወር 2004 ዓ/ም ላይ
የቤተክርስቲያን መሪዎች ሊቃነ ጳጳሳት ስብሰባ ተቀምጠው ነበር። ታማሚውን፤ የሕመሙን ዓይነትና ለሕመሙ የተስማማ መድኃኒት ለይቶ
ለመስጠት በተሰየመ አጀንዳ ላይ ውይይት አድርጎ ማዘዙን የተመለከተ መረጃ «አባ ሰላማ» በድረ ገጹ አስነብቦናል። ይህንኑ ተመልከተን
አንዳንድ ጥያቄዎችን አጫረብንና በዚያ ላይ የተድበሰበሰውን አካሄድ ለመግለጥና «ሲያውቅ የተኛ ቢጠሩት አይሰማም» እንዲሉ መደረግ የነበረበትን አካሄድ ሁሉ ለማኅበረ ቅዱሳን ደስታ ሲባል የተተወ መሆኑን
ብናውቅም ለታሪክና ለትውልድ ትልልቁን ግድፈት ለማሳየት ወደድን።
1/ የቀረበው ክስ ነው ወይስ ጥቆማ?
ሀ/ ክስ ፤/accusation/
ክስ /accusation/ በእንግሊዝኛው ፍቺ፤
አንድ ሰው ወይም ቡድን በሌላ ሰው ወይም ቡድን ላይ ሕገ ወጥ ነገር ፈጽሟል ብሎ የሚያቀርበው የሕግ መብትን የማስከበር አቤቱታ
ነው።
ይህንኑ ቃል አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ እንዲህ ሲሉ
በመዝገበ ቃላቸው ላይ ፈትተውታል።
«ከሰሰ- በዳኛ ተማጠነ፤ እገሌን
አቅርብልኝ፤ ዳኘን አለ። በደሉን፤ ግፉን ተናገረ፤ አመለከተ፤ ጠላቱን አሳጣ» በማለት ተርጉመውታል።
ክስ በሚለው ቃል ላይ እንደ አስረጂ በቀረቡት
ትርጉሞች ላይ ከተግባባን በማኅበረ ቅዱሳን ከሳሽነት እና በተከሳሽ
7 ድርጅቶችና 16 ግለሰቦች መካከል ለተቀደሰው ጉባዔ ቀርቦ የታየ ነገር ነበርን? ብለን ብንጠይቅ አዎ ለማለት
የሚያስችል ጭብጥ የለንም። ምክንያቱም «ክስ» የሚለውን ዐውደ ቃል ሊያሟላ የሚችል ሂደት አልነበርምና ነው። ይሁን እንጂ የሊቃነ
ጳጳሳቱ ስብሰባ የሰጠው ውሳኔ እንዲህ ሲል ይናገራል።
«………….7 ድርጅቶችና 16 ግለሰቦች የቀረበባቸው
ክስ በተጨባጭ በመረጋገጡ» ይላል። ማን ከሳሽ? ማን ተከሳሽ? ማን መርማሪ? ምን ዓይነት መልስና ማስረጃ ቀረቦ ታየ? የሚታወቅ
ነገር የለም። በክስ አግባብና አካሄድ ያልሄደ ሆኖ ሳለ እንዴት ነው
በተጨባጭ የሚረጋገጠው? እዚያው ፍጪው! እዚያው አቡኪው! ከመሆን የዘለለ አልነበረም። ስለዚህ በየትኛውም መመዘኛ «ክስ» የሚለውን
ስያሜ ለመያዝ የሚያበቃው ስላልሆነ ይህንን ስም ሲያነሱት ሊያፍሩ ይገባቸዋል። በዚህ ዘመን በተደበላለቀ ጫወታ/game/፤ ትላልቆች
የተቀመጡበትን ሥፍራ ለሌሎች ዓላማ መሳካት ማዋል ያስተዛዝባል። ያሳዝናልም።