አንዳንዶች ስለክርስቶስ የማማለድ ሥራ ለመቃወም ሲሉ መጽሐፍ ቅዱስን እስከመደለዝ ደርሰዋል። ሰብዓ ሊቃናትና ዐበይት የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤያት ያጸደቋቸውን የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ትርጓሜ በመሰረዝ የራሳቸውን ክልላዊ መጽሐፍ ቅዱስ እስከማሳተም የደረሱት የክርስቶስን ሥጋ የመልበስን ምስጢርና አሁንም በአብ ቀኝ የተቀመጠበትን አምላክ ሰው የሆነበትን ማንነት ለመጠበቅ ሲሉ የግሪኩንና እብራይስጡን ትርጉም ሰርዘውታል። በአንድ በኩል መናፍቃን ለራሳቸው እንዲያመቻቸው የወንጌል ቃልን ይሰርዛሉ፤ ይደልዛሉ እያልን በሌላ መልኩ ወቃሾች፤ የተወቃሾችን ታሪክ መድገም መደለዝ በመሠረቱ አሳዛኝ ነገር ነው። አበው ያቆዩትንና የተጻፈልንን እውነት ይዞ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ቃል ግልጽልጽ አድርጎ መመለስ ሲገባ፤ የተጻፈውን ሰርዞ፤ ከማስተማር ለመደበቅ መሞከር አስደንጋጭ ነው። ይህንን ከእውነት የመሸሽ ተግባር በማብራራት ከታች የቀረበው ጽሁፍ አንድ ነገር ይጠቁመናል። መሰረዛቸውን የማይክዱ ግን በመሰረዛቸው ከሲኖዶሳውያት ጉባዔያት ጋር ለምን እንደተለያዩ ማሳመን የማይችሉ ሰዎች ይህን ጽሁፍ ሲያነቡ ጆሮአቸውን ሊያስክክ፤ ዓይናቸውንም ሊያጨልም ይችላል።
የጽሁፉ ባለቤት «አድነው ዲሮ» ይሰኛሉ። መልካም ንባብ ይሁንልዎ!
I. መግቢያ፡-
የሰው ልጅ ውድቀት
የዚህ
ጽሁፍ አቢይ አላማ በየዕለቱ ስለ ሚገጥሙን የሕይወት ውጣ ወረዶች አንጻር፣ ስለታመሙ ሰዎች፣ በእስር ስላሉ ሰዎች፣ ስለ መሪዎች፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ አገር፣ ስለ አገልግሎት፣ ወዘተ አንዱ ለሌላው ወደ ፈጣሪው የሚያደርሰው የምልጃ ጸሎት፣ ክርስቶስ ለእኛ ባደረገው የማማለድ ሥራ ላይ ጥላውን እንዳያጠላበት ጥንቃቄ እንድናደርግ ለማሳሰብ ነው፡፡ እንደነዚህ አይነቶቹ - አንዱ ስለ ሌላው የሚጸልየው ጸሎት - ክርስቶስ ለእኛ ከፈጸመው የምልጃ ሥራ ጋር ምንም ዝምድና እንደሌለው ማሳሰብና እነዚህ ሁለት ነገሮች ሊነጻጸሩም ጭምር እንደማይገባ ማሳየት፣ የማንም ሰው የጸሎት ምልጃ የክርስቶስን የመስቀል ላይ ምልጃ ሊተካው እንደማይችል መግለጽ፣ እንዲያውም አንዳችን ለአንዳችን የመጸለይ (የመማለድ) ፈቃድ ያገኘነው በክርስቶስ የምልጃ ሥራ ከእግዚአብሔር ጋር ስለታረቅንና ከተቆጣን ፈጣሪ ጋር ሰላም ስለፈጠርን መሆኑን ማስገንዘብ የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይህንን አሳብ ለመገንዘብ ይረዳን ዘንድ ከችግሩ መነሻ ማለትም ከሰው ልጅ የውድቀት ታሪክ እንነሳና ጉዳዩን በጥልቀት እንመልከት፡፡
የሰው
ልጅ፣ አጽናፈ ዓለሙ፣ የምድር አራዊት፣ የሰማይ ወፎች፣ የባሕር ዓሶች ከተፈጠሩ በኋላ በፈጣሪው አምሳል በስድስተኛው ቀን የተፈጠረ ልዩ ፍጥረት ነው፡፡ ከእርሱ ቀድሞ የተፈጠሩትን ይገዛና ያስተዳድር ዘንድ ሃላፊነት ጭምር የተሰጠው ይህ ሰው፣ ይኖርበት ከነበረው ኤደን ገነት የአንዲቷን ዛፍ ፍሬ እንዳይበላ ከፈጣሪው ትእዛዝ ተሰጠው፡፡ በፈጣሪው ላይ መታመን ያልፈለገው የሰው ልጅ በትዕቢት ከፍሬዋ ቀጥፎ በላ፡፡ ከፍሬዋ በበላህ ጊዜ ሞትን ትሞታለህ ያለው አምላክም ጻድቅ ፈራጅ እንደ መሆኑ፣ የጽድቅ ብያኔውን በራሱ ላይ ተደግፎ ለመኖር በወሰነው በዚህ የሰው ልጅ ላይ አስተላለፈ፡፡ ከብያኔዎቹ መካከል አንዱ እንዲህ ይነበባል ፡- «... የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፣ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና፣ ምድር ካንተ የተነሳ የተረገመች ትሁን፤…´ (ዘፍ. 3፡17)፡፡
የሰውና
የፈጣሪ ጠብ እንግዲህ ከዚህ መጥፎ ጊዜ ይጀምራል፡፡ ከዚህች ቀንና ሰዓት ጀምሮ ሰውና ፈጣሪው ጥለኞች ሆኑ፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያዘጋጀውም መልካም ሃሳብ በሰይጣን ፈታኝነት፣ በሰው ልጅ ተባባሪነት እንቅፋት ገጠመው፡፡ አግዚአብሔር ሕግ ሰጠ፣ የሰው ልጅ ተላለፈው፣ ፈጣሪም የጽድቅ ፍርድ አስተላለፈ፡፡ ይህም ፍርድ ሞት ይባላል፡፡ የሰው ልጅ በሞት ፍርሃት ውስጥ እየማቀቀ ለበርካታ ዓመታት በምድር ላይ የስቃይ ኑሮ መግፋት ጀመረ፡፡
ይህን
ፍርድ ያስተላለፈው አምላክ ጻድቅ ብቻ ሳይሆን የፍቅር አምላክ በመሆኑ፣ ከእስትንፋሱ የተካፈለው ሰው በምድር ላይ ሲሰቃይ ማየት አላስቻለውም፡፡ በዚህም ምክንያት ጻድቅ ፈራጅነቱንና የፍቅር አምላክነቱን አዋህዶ የሚያሳይ ሌላ የደኅንነት መንገድ ለሰው ልጅ አዘጋጀ። ይህ የደኅንነት መንገድ ጽንፍ የሚመስሉትን የአምላክ ሁለት ባሕሪያት (ፍርድና ምሕረት) በአንድ መስመር ያገናኘ አስገራሚ ክስተት ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሰው ዘር ሁሉ ላይ ያሳለፈው ሊታጠፍ የማይችል የሞት ፍርድ ሳይቀለበስ የሰው ልጅ ከተቆጣው አምላኩ ጋር ታረቀ፡፡ የአገራችን የእምነት ሊቃውንት ይህንን ሁኔታ ግሩም በሆነ መንገድ እንዲህ በማለት ይገልጹታል፡፡ «እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ ተጠበበች፡፡´ የዚህ አስገራሚ ትእይንት ጀማሪና ፈጻሚው ደግሞ ምንም በደል ያልተገኘበት ኢየሱስ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሰው ልጅ ላይ የተቆጣውን ቁጣ በኢየሱስ ላይ አሳረፈው፤ ፍርዱን አሳየ፡፡ ኢየሱስ ስለ ኃጢአተኞቹ ስለ እኛ ሞተ፡፡ በእርሱም ምክንያት የሰው ልጅ ምሕረትን ተቀበለ፡፡ ከፈጣሪውም የፍርድ ቁጣ ተረፈ (ሮሜ. 5፡9)፡፡
የብሉይና
የሐዲስ ኪዳናት መሰረታዊ ጭብጥም ይኸው ታላቅ ሥራ ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን የሐዲሱ ኪዳን ጥላ/ምሳሌ እንደ መሆኑ፣ የሰው ልጅ የደኅንነት መሰረት የሆነው (1ቆሮ. 3፡10-11) ክርስቶስ ዘመኑ ደርሶ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እስኪመጣ ድረስ፣ የሰው ልጅ በታላቅ ምጥ ውስጥ ነበር፡፡ ጥላ የነበረውንና የሰውን ልጅ ፍጹም ሊያደርገው የማይችለውን የእርቅ ሥርዓት (ዕብ. 9፡9፣10) እየፈጸመ ከአምላኩ ጋር ሊያስታርቀው የሚችለውን የደኅንነት ተስፋ መጠበቅ ጀመረ፡፡ አንዳንዶች ይህን ተስፋ በሩቅ ተሳለሙት (ዕብ. 11፡13፣ 11፡49፣40)፤ ሊሎች ደግሞ ይህን ተስፋ በዓይናቸው አዩት (ሉቃስ 2፡29-32)፡፡ የዚህ ጽሑፍ አንባቢ እርስዎና እኔ ደግሞ በዚህ የምሕረት ዘመን ውስጥ ለመገኘት የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ሆነ፡፡
የሰው
ልጆች ሁሉ ተስፋ የነበረው፣ የዓለሙን ሁሉ ኃጢአት የሚቤዠው፣ ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያስታርቀው፣ የተዋረደውንና በውድቀት ከእግዚአብሔር ቁጣ ስር ለሞት የሚጠበቀውን የሰውን ዘር የሚታደገው ብቸኛ አዳኝ እስኪመጣ ድረስ፣ የሰው ልጅ የዚህን ፍጹም ተስፋ ጥላ እየተከተለ አካሉን ናፈቀ፡፡ ጥላው የነበረውን የብሉይ ሥርዓት እየፈጸመ የአካሉን መገለጥ ለእልፍ ምዕት ዓመታት በናፍቆት በጠበቅ ግድ ሆነበት፡፡ ከዚህ በታች ባሉት ጥቂት አንቀጾች ከሰው ውድቀት አንስቶ እስከ መሲሁ መምጣት ድረስ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ተቀባይነት ያለውን ሕብረት ለማድረግ፣ የኃጢአት ሥርየትን ለማግኘትና የምስጋና መሥዋዕት ለማቅረብ ምን ነገሮችን ይፈጽም እንደነበረ አለፍ አለፍ እያልን እናያለን፡፡ ይህ የብሉይ ሥርዓት ሊመጣ ያለው እውነተኛ አካል ጥላ/ምሳሌ እንደሆነ አንባቢ ልብ ይበል፡፡ በዚህ ስር የምናያቸው ቁም ነገሮች ግልጽ ከሆኑ፣ ኋላ ላይ የምናየው የሐዲስ ኪዳኑ አካል ፍሬ አሳብ ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡