(የደጀብርሃን ልዩ ዘገባ) ፖፕ ሺኖዳ ሳልሳዊ አረፉ! ፎቷቸው ላይ ሀገሬ በሰማይ ነው የሚሉ ይመስላሉ!
የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ሆነው ከ1971(እ ኤ አ) ጀምሮ በማገልገል ላይ የነበሩት ፖፕ ሺኖዳ ሳልሳዊ
በፕሮስቴት ካንሰር፣ በጉበትና ሳንባ በሽታ ለዓመታት ሲሰቃዩ ቆይተው በተወለዱ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ፖፕ ሲኖዳ በኮፕት ክርስቲያን ልጆቻቸው ዘንድ እጅግ በጣም ተወዳጅና ተፈቃሪ የነበሩ ሲሆን በበሽታ እየተሰቃዩ ከወንጌል
አስተምህሮ ሳይለዩ፣ ቅዳሴ ሳያቋርጡ፣ በሐዋርያው ጉብኝቶቻቸው፣ አድባራትና ገዳማቶቻቸውን በማጽናናት ሌሊትና ቀን ደክመው አገልግሎታቸውን
ለግብጽ ቤተክርስቲያን በትጋት ፈጽመው ያለፉ ታላቅ አባት ነበሩ። «ባባ ሹኑዳ» እያሉ የሚጠሯቸው ልጆቻቸው አስተምህሮአቸውን ለመስማት
ሲሽቀዳደሙ፣እግሮቻቸውን፣ እጆቻቸውን ለመሳለም ሲሰለፉ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም። ይህ ሁሉ ለክርስቶስ ቤተክርስቲያን የተሰለፉበትን
አባታዊ ተልእኰ በመፈጸም እድሜአቸውን ሙሉ ባበረከቱት ትጋት የተነሳ የተሰጣቸው ትልቅ ክብር እንጂ ለውዳሴ ከንቱ እንዳልሆነ ሁላችንም
የምንመሰክረው ሐቅ ነው። በአንድ ወቅት በቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ትምህርተ ወንጌል አስተምረው የተናገሩትና
እሳቸው አልቅሰው ምእመናኑን ሁሉ ያስለቀሱት መቼም አይረሳም።
እንዲህ አሉ! «ልጆቼ ካስተማርኳችሁ ሁሉ ያልነገርኳችሁ ብዙ ነገር በልቤ ውስጥ አለ፣ እሱን ለእናንተ አልነግርም ፣
የልቤን ለሚያውቅ ለኢየሱስ ለክርስቶስ ትቼዋለሁ» ሲሉ ቁጭ ባሉበት ስቅስቅ ብለው አለቀሱ።ቤተክርስቲያኑን የሞላው ሕዝብ ተከትሎ
አለቀሰ። ቅዳሴውን በቀጥታ ስርጭት ይከታተል የነበረው ሁሉ በየቤቱ አነባ። አዎ ፓትርያርኩ ብዙ ምስጢራቸውን፣ችግራቸውንና ስለቤተክርስቲያን
ያላቸውን ጭንቀት የመፍትሄ ባለቤት ለሆነው ለክርስቶስ ይነግሩ ነበር። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያቀርቧቸው ሃሳቦቻቸው መካከል «ክርስቶስ
የሰጠን አንዲቱን ቤተክርስቲያን ሆኖ ሳለ እኛ ተለያይተን እንዴት ክርስቶስን በእውነት እናመልካለን፣ ክርስቶስን ይህን እያየ ዝም
የሚለው እስከመቼ ነው?» እያለ እለት እለት የሚያሳስባቸውን የቤተክርስቲያን ጉዳይ የሚያነሱ ባለትልቅ ራእይ አባት ነበሩ።