ራሳቸውን ከአቡነ ገብርኤል አስተዳደር የለዩት ምዕመናን አሁንም ከአሳዳጆቻቸው ጋር ተፋጠዋል
በአቡነ
ገብርኤል የመልካም አስተዳደር ብልሹነት ተማረውና ተቀጥቅጠው በዱላ ኃይል ከሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል
ገዳም፣ ከደብረ ሠላም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን እና ከደብረ ታቦር ቅዱስ ሩፋኤል ቅጥር ግቢ የተባረሩት
ምዕመናን የራሳቸውን ታላቅ መንፈሳዊ ጉባዔ ማካሄዳቸው ዘጋቢዎቻችን አስታወቁ፡፡
ዘጋቢዎቻችን በሥፍራው ተገኝተው እንዳረጋገጡት እነዚህ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንና ምዕመናት፣ ልዩ ልዩ ሥልጣነ ክህነት ያላቸው አገልጋዮችና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አቡነ ገብርኤል ከ"ማኅበረ ቅዱሳን"ና አሥር ከማይሞሉ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች እና ኃላፊነታቸውን ከዘነጉ ፖሊሶች ጋር በመተባበር ተከታታይና ኢሰብዓዊ ድብደባ፣ እሥራትና እንግልት ስላበዙባቸው ተማረው መውጣታቸው ታውቋል፡፡
ይሁን
እንጂ ይህ የተሰደደው ሕዝብ ተበታትኖ ወደየቤቱ ከመግባት ይልቅ እየተሰባሰበ በግለሰቦች መኖሪያ ቅጥር ግቢ ውስጥ
ወንጌል በመከታተል ላይ ሲሆን በአደረጃጀት እየጠነከረ በመምጣቱ እነ አቡነ ገብርኤል እንደስጋት እንደሚያዩት
ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህም የተነሳ በእነ አቡነ ገብርኤል ወገን ያለው አሳዳጅ ኃይል ግፉአኑን "ተሀድሶዎች" ናቸው፣ "መናፍቃን"
ናቸው በማለት፣ ዐውደ ምሕረት ላይ የሐሰት ወሬ በማስተላለፍ ላይ ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን አሳዳጆቹ ወደ ፍትሕና
ፀጥታ አካላት እንዲሁም ወደ ክልል መስተዳድር እና ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ዘወትር እግራቸው እስኪቀጥን ድረስ
በመመላለስ እንዲያዙላቸው፣ እንዲታገዱላቸውና እንዲታሠሩላቸው በመወተወት ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡