Monday, March 12, 2012

አቡነ ገብርኤል "የተሰደደ የለም" ያሉት የሀዋሳ ሕዝብ፣ ታላቅና ደማቅ መንፈሳዊ ጉባዔ አካሄደ

ራሳቸውን ከአቡነ ገብርኤል አስተዳደር የለዩት ምዕመናን አሁንም ከአሳዳጆቻቸው ጋር ተፋጠዋል

በአቡነ ገብርኤል የመልካም አስተዳደር ብልሹነት ተማረውና ተቀጥቅጠው በዱላ ኃይል ከሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣  ከደብረ ሠላም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን እና ከደብረ ታቦር ቅዱስ ሩፋኤል ቅጥር ግቢ የተባረሩት ምዕመናን የራሳቸውን ታላቅ መንፈሳዊ ጉባዔ ማካሄዳቸው ዘጋቢዎቻችን አስታወቁ፡፡
 ዘጋቢዎቻችን በሥፍራው ተገኝተው እንዳረጋገጡት እነዚህ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንና ምዕመናት፣ ልዩ ልዩ ሥልጣነ ክህነት ያላቸው አገልጋዮችና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አቡነ ገብርኤል ከ"ማኅበረ ቅዱሳን"ና አሥር ከማይሞሉ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች እና ኃላፊነታቸውን ከዘነጉ ፖሊሶች ጋር በመተባበር ተከታታይና ኢሰብዓዊ ድብደባ፣ እሥራትና እንግልት ስላበዙባቸው ተማረው መውጣታቸው ታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የተሰደደው ሕዝብ ተበታትኖ ወደየቤቱ ከመግባት ይልቅ እየተሰባሰበ በግለሰቦች መኖሪያ ቅጥር ግቢ ውስጥ ወንጌል በመከታተል ላይ ሲሆን በአደረጃጀት እየጠነከረ በመምጣቱ እነ አቡነ ገብርኤል እንደስጋት እንደሚያዩት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህም የተነሳ በእነ አቡነ ገብርኤል ወገን ያለው አሳዳጅ ኃይል ግፉአኑን "ተሀድሶዎች" ናቸው፣ "መናፍቃን" ናቸው በማለት፣ ዐውደ ምሕረት ላይ የሐሰት ወሬ በማስተላለፍ ላይ ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን አሳዳጆቹ ወደ ፍትሕና ፀጥታ አካላት እንዲሁም ወደ ክልል መስተዳድር እና ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ዘወትር እግራቸው እስኪቀጥን ድረስ በመመላለስ እንዲያዙላቸው፣ እንዲታገዱላቸውና እንዲታሠሩላቸው በመወተወት ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Friday, March 9, 2012

የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እንዲከላከሉ ተወሰነባቸው!

 ሊቀ ትጉሃን ተሾመ ኃይለ ማርያም በ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሤራ በፖሊስ ተይዘው ወደ ነጌሌ ቦረና ተወሰዱ

በቆሞስ መልአከ ገነት አባ ሙሉጌታ ታዬ የክብረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ ከሸፈ

የካቲት 16 ቀን 2004 ዓ.ም በክብረ መንግሥት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የሚከበረውን የቅድስት ኪዳነ ምሕረት በዓለ ንግስ በመረበሽ ያስተጓጎሉት ሃያ አምስት የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና አፍቃሬ ማኅበረ ቅዱሳን ተከሳሾች ለመጋቢት 19 ቀን 2004 ዓ.ም ቀነ ቀጠሮ ቀርበው እንዲከላከሉ ተበይኖባቸዋል፡፡ ዐቃቤ ሕግ አሥራ ሦስት ምሥክሮችን ያሰማ ሲሆን ክሱን በጽሑፍ፣ በሰውና በምስል ማስረጃ አጠናቅሮ አስረድቷል፡፡ በተጨማሪም ሰባት ምሥክሮች ቃለ መሐላ ከፈጸሙ በኋላ ዐቃቤ ሕጉ በቃኝ ሳይሉ ምክንያቱ በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት ዳኛው አቶ ጉዩ እንዳይመሠክሩ አስቁመዋል ተብሏል፡፡  
በዚህም ሳቢያ ስምንት ቀንደኛ በጥባጮች በዚያው ዕለት 29/6/2004 ዓ.ም በነፃ አሰናብተዋቸዋል ተብሏል፡፡ ከነዚህ ስምንት ቀንደኛ መሪዎች ውስጥ መሪጌታ መዝገቡ ጌታነህ፣ ቄስ መኮንን ጉቴሳ (የአንድ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የታሪክ መምህር)፣ ወ/ሮ ሃይማኖት ጥላሁን፣ ወ/ሮ መቅደስ፣ ዲ/ን እንዳሻው፣ ዲ/ን ብንያም፣ ዮናስና ጌትነት የተባሉት መሆናቸው ታውቋል፡፡ በተለይም የእነዚህ ቀንደኛ በጥባጮች መለቀቅ፣ የከተማውን ኅብረተሰብ፣ የፍትሕና የፀጥታ አካላትን ማስቆጣቱ ተመልክቷል፡፡

Thursday, March 8, 2012

ትንቅንቅ!

 በእውነተኛ ራእይ ላይ የተመሠረተ፣

ርእስ- የመጨረሻው ትንቅንቅ
            ደራሲ- ሪክ ጆይነር
          ተርጓሚ ሰሎሞን አሰፋ
                                                            ናዝሬት፣ 2004 /
                          ክፍል ፩

የሲኦል ኃይላት እየተመሙ ናቸው

አጋንንታዊ ሠራዊቱ በዓይኔ ማየት እስኪሳነኝ ድረስ እጅግ ብዙ ሲሆኑ እያንዳንዳቸውም የተለያዩ ሰንደቅ ዓላማዎችን ተሸክሞ በተሰለፈ ክፍለ ጦር ስር ተከፋፍለው ተሰልፈው ነበር። ትላልቆቹ ክፍለ ጦሮች ትዕቢት፣ራስን ማጽደቅ፣ ስምን ማስጠራት፣ ራስ ወዳድነት፣ በጭፍን መፍረድና ቅናት የሚሉ ሰንደቅ ዓላማዎችን በያዘ ጦር ስር ተሰልፈው ነበር። በዓይኔ ማየት ከምችላቸው ከእነዚህም ሌላ እጅግ በርካታ ሌሎች ክፍለ ጦሮችም ተሰልፈው ነበር። ይሁንና ከገሃነም እየወጣ ከመጣው ከዚህ አስፈሪ መንጋ ፊት በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉት ግን እጅግ ኃያላን ይመስሉ ነበር። የዚህ ሠራዊት መሪ ደግሞ የወንድሞች ከሳሽ የሆነው ራሱ ሰይጣን ነበር።
ይህ መንጋ ሠራዊት የታጠቃቸው የጦር መሣሪያዎች በላያቸው ላይ ስሞቻቸው ተጽፎባቸው ነበር። ሰይፎቹም ዛቻ፣ ጦሮቹ ክህደት፣ ቀስቶቹ ሀሰት፣ ክስና ስም ማጥፋት ይባሉ ነበር። መራርነት፣ አለመቀባበል፣ ትዕግስት ማጣት፣ ይቅር አለማለት የተባሉ ስሞች ያሏቸው ጥቂት የአጋንንቱ ቡድን አባላትም ለዋናው ውጊያ ከዚህ ሠራዊት ፊት ቀድመው እንዲጓዙ ተልከው ነበር።

እነዚህ የአጋንንቱ ቡድን አባላት ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም ኃይላቸው ግን ከኋላቸው ተሰልፎ ከሚገሰግሰው በርካታ ክፍለ ጦር የሚተናነስ አልነበረም። ቁጥራቸው አናሳ የሆነው ደግሞ ለስልታዊ ምክንያት ብቻ ነበር። እነዚህ ጥቂት አጋንንታዊ ቡድኖች ልክ ዮሐንስ መጥምቁ ሕዝቡን በጥምቀት ለጌታ ለማዘጋጀት ብቻውን የተለየ ቅባት እንደተሰጠው ዓይነት እነዚህም ህዝቡን ለጥፋት ለማዘጋጀት «ብዙሃኑን ሕዝብ ለማጥመቅ» ልዩ አጋንንታዊ ኃይልን የለበሱ ነበሩ። አንዱ የመራርነት አጋንንት በሕዝብ ወገን ሁሉ ወይም ባህሎች ላይ እንኳን ሳይቀር መርዙን መርጨት ይችል ነበር። የርኩሰት አጋንንቱ ደግሞ ከአንድ የቴአትር፣ የፊልም ወይም የንግድ ምርት አስተዋዋቂ ተዋንያን ጋር ራሱን በማቆራኘት ቁጥሩ እጅግ በርካታ የሆነውን ሕዝብ እንደኤሌክትሪክ ያለ ኃይል እየላከ በመምታት ያፈዛቸውና ያደነዝዛቸው ነበር። ይሄ ሁሉ ደግሞ ቀጥሎ ለሚመጣው ለታላቁ የክፋት መንጋ መንገድ ጠርጎ ለማዘጋጀት ነበር።