የአቡነ ገብርኤል የገጽታ ግንባታ ተግባር!
የተሰደዱት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ጉባዔውን ለማደናቀፍ ምንም ዓይነት ዕቅድ እንደሌላቸው አስታወቁ
በሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ከመጪው የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ መንፈሳዊ ጉባዔ ሊዘጋጅ እንደሆነ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ስምዓ ጽድቅ ተከፋይ ዐምደኛ መልአከ ብርሃን ይትባረክ ታጠቅ ድምፅ ማጉያ ይዘው በሹሽሹክታ ለሕዝብ መናገራቸውን መግለጻችን ይታወሳል፡፡ በሀዋሳ
ዳቶ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ለእመቤታችን በዓለ ንግሥ ለተሰበሰበው ሕዝብ ዳንኤል ክብረት፣ ዘመድኩን በቀለና
ዘማሪ ቴዎድሮስ ዮሴፍ ሄደው እንደሚያስተምሩ መናገራቸውን ጭምር መግለጻችን አይዘነጋም፡፡ ሆኖም አሁን በደረሰን
መረጃ ሄደው የሚያስተምሩት መ/ር ዘበነ ለማ ከአሜሪካ፣ ዳንኤል ክብረት፣ መ/ር ምሕረተአብ አሰፋ፣ ዘማሪ ቴዎድሮስ
ዮሴፍና ሌሎችም ስማቸው ያልተገለጹ ሰዎች እንደሆኑ ታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ የመ/ር ዘበነ ባይታወቅም ዳንኤል ክብረት ከፍተኛ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አመራር፣ እንዲሁም መ/ር ምሕረተ አብ አሰፋ የ"ማኅበሩ" አባልና ደጋፊ በመሆናቸው ሄደው ለማስተማር ቀደም ሲል የተላለፉ መመሪያዎች እንደማይፈቅዱላቸው ታውቋል፡፡ እነዚህም:-
- ክቡራን የመንግሥት ሚኒስትሮች በታዛቢነት በተገኙበት አቡነ ገብርኤል ራሳቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ሆነው መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም በተካሄደው የሠላም ጉባዔ የወሰኑትና የፈረሙበት "ማኅበረ ቅዱሳን" በማናቸውም የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅሮች ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ ጥቅምት 6 ቀን 2002 ዓ.ም በቁጥር 44/70/2002 መመሪያ ወጥቷል፡፡
- የሀዋሳን ግጭት ለማብረድ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የተመራው አጣሪ ቡድን ያቀረበው ሪፖርት ግጭቱ የተከሰተው ተስፋ ኪዳነ ምሕረትና ፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ማኅበር እና "ማኅበረ ቅዱሳን" ባስነሱት ሁከት መሆኑን ይገልጽና ተስፋ ኪዳነ ምሕረት ማኅበርን ጨምሮ "ማኅበረ ቅዱሳን" እንደማንኛውም ተቋምና ግለሰብ አስቀድሶና ተገልግሎ ከመውጣት በስተቀር በቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡና በዐውደ ምሕረት ላይ እንዳያስተምሩ፣ የካቲት 2 ቀን 2003 ዓ.ም በቁጥር 92/54/2003 ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት መመሪያ ተላልፏል፡፡