Friday, June 20, 2014

ተአምረ ማርያም የተባለው መጽሐፍ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እናት የቅ/ማርያምን የቅድስና ባህርይ አይወክልም!

(እዝራ ስነጽሁፍ ዘላለም መንግሥቱ)

ካለፈው የቀጠለ (ክፍል ሁለት)

4.  ይህ  ደራሲ  ማርያምን  መለኮታዊ  ክብርን  ለማቀዳጀት  የጣረ  ወይም እንዲያደርግ  ያነሣሱት  ሰው  ነው።

 ምናልባት  መጽሐፉ  ስለራሱ እንደሚናገረው  ከግብጽ  ተገኝቶና  በዐረብኛ  ተጽፎ  ከሆነ  ክርስቲያኖች ማርያምን  እንደ  አምላክ  ያዩአታል  የሚያሰኝ  ዐረባዊ  ጫና  ሊኖርበትም ይችላል። ለምሣሌ፥ በኢስላም ግምት ክርስቲያኖች አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ  አንድ  አምላክን  ሳይሆን  ማርያምንና  ኢየሱስን  ከአላህ  ጋር  እኩል አድርገው  እንደሚያመልኩ  ይነገራል፥  ተጽፎአልም።  “የመርየም  ልጅ  ዒሳ ሆይ  አንተ  ለሰዎቹ፥  እኔንና  እናቴን  ከአላህ  ሌላ  ሁለት  አምላኮች አድርጋችሁ  ያዙ  ብለሃልን?  በሚለው  ጊዜ  (አስታውስ) . . .”( ቁርአን አልማኢዳህ ቁጥር 116)

   በተአምረ ማርያም  ደግሞ  ማርያም  ያላት  ሥልጣንና  የምታደርጋቸው  ትንግርቶች መለኮት  ብቻ  እንጂ  ማንም  ፍጡር  ሊያደርጋቸው  የማይችላቸው  ነገሮች ናቸውና እውነትም  ከመለኮት  ያልተናነሰ  ኃይልና  ችሎታ፥  ሞገስና  ክብር፥ሥልጣንና ስግደት ተጎናጽፋ ትገኛለች። እርግጥ  ነው  ጌታን  ያመኑና  የሚከተሉ  ተአምራትን  እንደሚያደርጉ ተጽፎአልና  በክርስትና  ታሪክ  ተአምራት  አዲስ  መሆን  የለባቸውም። የማርያም  ግን  የተለየ  ነው።  የሞተን  ማስነሣት  አንድ  ነገር  ነው፤  ግን፥ ለምሳሌ፥  በምዕራፍ  18  እና  19  ውስጥ  እንደሚነበበው  በደብረ  ምጥማቅ ተገልጣ  በዚያ  የነበሩ  ዘመዶቻቸውን  ብቻ  ሳይሆን  ጥንት  የሞቱትን ሙታን፥ አዳምና ሔዋንም ሳይቀሩ እያስነሱ አምጥቶ ለተመልካች ማሳየት መለኮትን  መጋራት  አይባልም?  ምክንያቱም  ትንሣኤ  የሰው  ሳይሆን የእግዚአብሔር  ብቻ  ሥራ  ነው።  ማርያም  ይህንና  ሌሎችንም  ሁሉ የምታደርገው  ደግሞ  እንደ  ጌታ  ደቀ  መዝሙር  በሕይወት  ሳለች  ሳይሆንከሞት  በኋላ  እየተገለጠችና  በአካል  እየመጣች  ነው።

  በዚህ  በተጠቀሰው ክፍል  እንደታየው  ያለ  ከሞተ  በኋላ  ከሞት  እየተነሣ፥  እየታየ፥  እየዳሰሰ፥ እያቀፈ፥  እየሳመ  ገባሬ  ተአምራት  ሆኖ  ከሰው  ጋር  የተባበረ  ኖሮ አያውቅም።  በመጽሐፍ  ቅዱስ  ውስጥ  የተጻፈ፥  በትንሣኤ  አካል  ከሞት የተነሣ  ጌታ  ክርስቶስ  ብቻ  ነው።  ከእርገቱ  በኋላ  እርሱ  ራሱም የተገለጠው  ለሁለት  ሰዎች  ብቻ  ነው፤  ለጳውሎስና  ለዮሐንስ።  ሁለቱም ባዩት  ጊዜ  ምን  እንደሆኑ  ተጽፎልናል፤  ሐዋ.  9  እና  ራእ.  1።  በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ትንሣኤ ሙታን እንደ ቁርስና ምሳ ተራ ጉዳይ ነው። በተአምረ  ማርያም  ጌታ  ኢየሱስ  በተጠቀሰባቸው  ቦታዎች  በ97  ወይም 98%  ያህሉ  ልጇና  ወዳጇ  ነው።  ፈጣሪዋ፥  አምላኳ፥  ጌታዋ  ከመሆኑ ይልቅ  ማለት  ነው።  ይህ  ፈጽሞ  አልተጠቀሰም  ማለት  ሳይሆን የተጠቀሰው  1  ወይ  2%  ብቻ  ነው።  በመጽሐፉ  የቀረቡት፥  ልክ  እንደ ስዕሉ  ሁሉ፥  የተሳሉት  እንደ  እናትና  ሕጻን ልጅ  ነው።  እናትና  ሕጻን ልጅ ብቻ  ሲታዩ  ክብደትና  ክብር  የተገባት  እናት  እንደምትሆን  ሆኖ  ነው አቀራረቡ።  ወደ  መጽሐፉ  መደምደሚያ  አንድ  ጊዜ  የ5  ዓመት፥  አንዴ የ8፥  አንዴ  የ12  ዓመት  የተጠቀሰ  ሲሆን  መጽሐፉ  ሲደመደም በመጨረሻው  ምዕራፍ  ኢየሱስ  የ18  ዓመት  ልጅ  ሆኖ  ገና  አሁንም የተጠየቀውን  አድራጊ  ሆኖ  ማርያም  የግሪክን  አገር  መጎብኘት  መፈለጓን ነግራው  እዚያ  ወስዷት  ታሪኩ  እዚያ  ይፈጸማል።  ከነዚህ  የመጨረሻ  4  ምዕራፎች  በቀር  በመጽሐፉ  ውስጥ  ኢየሱስ  በእናቱ  እቅፍ  ያለ  ሕጻን ነው። ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ እንኳ ሲታይ እንደ ሕጻን ሆኖ ነው።

5.  ይህ  ደራሲ  ወይም  ይህን  የመጽሐፉን  ይዘት  የተቀበሉትና  ያስጻፉት ሰዎች  በሰይጣን  የተታለሉ  ሰዎች  ናቸው።

 ይህ  ሁሉ  በመጽሐፉ  ውስጥ የተጠቀሱት  ነገሮች  ታይተዋል፤  ማርያምም  ተገልጣ  ተናግራቸዋለች፤ የተጻፈውም  ነገር  በትክክል  የታያቸውና  የተገለጠላቸው  ነው  ተብሎ ቢወሰድ  እንኳ  ከመጽሐፍ  ቅዱስ  ትምህርት  አንጻር  ሰዎችን  እውነትና መንገድ  ሕይወትም  ከሆነው  ከክርስቶስ  የሚያርቅ  ነገር  ስላስተላለፉ በማርያም  እየተመሰለ  የተገለጠ  ሰይጣን  ያሳታቸው  ሰዎች  ናቸው  ብሎ መደምደም  ይቻላል።  በ2ቆሮ. 11፥14  ሰይጣን  ራሱን  የብርሃንን  መልአክ እንዲመስል  እንደሚለውጥ  ተጽፎአል።  ይህች  ተገለጠች  የተባለችው  ማርያም ሐዋርያት የሰበኩትን  እውነተኛ ወንጌል እንኳ ብትሰብክ ይህንም መቀበል ግዴታ  አይሆንም፤ ምክንያቱም እውነተኛው  ወንጌል  ቀድሞውኑ ተሰብኮ፥  ተጽፎ  ተላልፎአላ!  በዚህ  መጽሐፍ  ውስጥ  የሚተላለፈው ትምህርት  ደግሞ  ከእውነት  ፈቀቅ  የሚያደርግ  ነው።  ይህን  በተመለከተ ጳውሎስ  በገላ.  1፥8  ነገር  ግን  እኛ  ብንሆን  ወይም  ከሰማይ  መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ  ወንጌል  የሚለይ  ወንጌልን  ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ  ይሁን አለ።  አዲስና  ወንጌል  የሚመስል  ግን  ያልሆነ  ነገር  የሚሰብክና  ታይቶ የሚገልጥ የዚህ ውግዘት ተሸካሚ ነው።

6. የተአምረ ማርያም ደራሲ  ደኅንነትን  የማያውቅ ሰው  ነው።

 በመጽሐፍ ቅዱስ  ውስጥ፥  በተለይም  በአዲስ  ኪዳን  በግልጽ  ተጽፎልን  የምናየው ደህንነት  ወይም  ድነት  ውብ  ነው!  የእግዚአብሔር  ድንቅ  የሆነው አሠራሩ፥  ኃጢአተኛውን  ሊያጸድቅ  አንድያ  ልጁን  መላኩ፥  ጌታችን መድኃኒታችን  ኢየሱስ  ክርስቶስም  በፈንታችን  በመስቀል  መሞቱና  እኛን ከዘላለም  ሞትና  ከኃጢአት  ባርነት  ነፃ  ማውጣቱ፥  ይህ  ድንቅና  ክቡር የሆነ  ግን  ግልጥና  ቀላል  ሆኖ  የቀረበው  ሥራው  አስገራሚ  ነው።  አቤት ደኅንነት  ውበቱ!  አቤት  ደኅንነት  ግልጽነቱና  ቀላልነቱ!  አቤት  ውስብስብ ያለመሆኑ!  አቤት  እርግጠኝነቱ!  ደህንነት  የሂደት ሳይሆን  የቅጽበት ለውጥ ነው።  ደኅንነት  ይታወቃል፤ አንድ  ኃጢአተኛ  ሲድን  መዳኑን  ያውቀዋል። እንዲያውቅ የሚያደርጉት ዋና ዋና ምስክሮች አሉ። 1ኛው የማይዋሽ ቃሉ ነው፤  በዳንንባት  ቅጽበት  የእግዚአብሔር  ልጆች  ሆነናል፤  ዮሐ. 1፥11-12፤
ልጁ  ያለው  ሕይወት  አለው፤  ይህ  ደግሞ  የሚታወቅ  ነው፤  1ዮሐ. 5፥12-13።  2ኛ  በዳንንባት  ቅጽበት  በውስጣችን  መኖር  የጀመረው  መንፈስ ቅዱስ  የእግዚአብሔር  ልጆች  መሆናችንን  ይመሰክርልናል፤  ሮሜ  8፥14-17።  3ኛው  ምስክር  የተለወጠ  ሕይወታችን  ነው።  ቀድሞ  የነበርነውን አይደለንም፤  ያልነበርነውን  ደግሞ  ሆነናል።  ሰው  ሲድን  አቤት  እረፍት!  አቤት  እፎይታ፥  አቤት  ሰላም!  አቤት  ነፃነት!  በመስቀል  ላይ  ከተፈጸመው የጌታ  ሥራ  የተነሣ  ደኅንነት  በእምነት  ብቻ  ነውና  በሥራ  እግዚአብሔርን አስደስቶ  መዳንንና  ጽድቅን  ለመቀዳጀት  መፍጨርጨር  የለም።  ይህ ደኅንነት  ደግሞ  ይጠፋል  ተብሎ  በስጋትና  በሰቀቀን  ሳይሆን  በታማኙ ታምኖ የሚኖሩት ኑሮ ነው። ክርስትና ይህ ቀላል የሆነ መዳን ነው። መ/ር ምህረተአብ  ምላሽ  በሰጠበት  ስብከት  ፓስተር  ዳዊት  “አታክብዱብን” ያለው  ይህንን  ነው።  መዳን  ይህንን  ያህል  ቀላል  ሆኖ  ነው  በአዲስ  ኪዳን የቀረበው።  ቀላል  ነው  ማለት  ግን  ርካሽ  ነው  ማለት  አይደለም።  ክቡር ዋጋ የተከፈለበት ነውና ርካሽ አይደለም፤ ግን ነፃ ነው! ነፃ! በተአምረ  ማርያም  ውስጥ  ግን  ይህንን  ነፃ፥  ቀላል፥  የሚያሳርፍ  ደኅንነት አናይም።  የማናይበት  ምክንያት  ግልጽ  ነው።  አንድ  ደራሲ  የሚያሳየው ያየውን  ነው።  እነዚህ  ሰዎች  ይህንን በጸጋው ብቻ  መዳንን  አልቀመሱም።
የተአምረ  ማርያሟ  ማርያም  የመጽሐፍ  ቅዱሷ  ማርያም  ከቶም አይደለችም።  ይህች  ማርያም  የክርስቶስ  ማዳን  እንዳይታይ  መጋረጃ ተደርጋለች።  ስለዚህ  ኢየሱስን  እስከ  መስቀሉ  እንኳ  ሳይሆን  እስከ አገልግሎቱም  ጅማሬ  ሳያደርሱት  በእናቱ  ስር  ያለ  ታዛዥ  ወጣት አድርገው  በ18  ዓመቱ  መጽሐፋቸውን  ደመደሙ።  ደኅንነት  ያለው መስቀሉ  ላይ  ነዋ!  በውስጡ  የሚታዩ  ሰዎችም  መዳንን  ያልተለማመዱ በነፍሳቸውም  የተቅበዘበዙ  ሰዎች  ናቸው።  በመጽሐፉ  ጥላቻ፥  ቂምና በቀል፥ መግደል፥ ፍርሃት፥ የሥልጣን ጥም፥ ውሸት፥ ወዘተ ይታዩበታል።  በምዕ.  61  ማርያምም  ውሸታም  ተደርጋ  ቀርባለች።  በአንዲት  ባልቴት ተመስላ  ወደ  አንድ  ሹም  ዘንድ  ሄዳ  የዋዳ  አገር  ሴት  መሆኗን  ነግራው ነበር።  የተአምረ ማርያሟ ማርያም መዋሸትም ትችላለች።

7.  ይህ ደራሲ  ያልተዋጣለት ልብ ወለድ ደራሲ  ነው። 

የተዋጣለት  ቢሆን መጽሐፉ ልብ ወለድ መሆኑን ይገልጥ ነበር። ነገር ግን፥ መጽሐፉ እውነት ሳይሆን  እውነት  ተደርጎ  ቀርቦአል።  እውነት  ያለመሆኑን  የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች በቀጣዩ  ንዑስ ርእስ  ይቀርባሉ። በመጽሐፉ  ውስጥ  ከእውነት ጋር የተጠጋጋው  ብቸኛ ክፍል በዘርዓ ያዕቆብ  ዘመን ለማርያምና ለስዕል፥ ለመስቀልም  ስግደት  የተገባ  አይደለም  ብለው  ስቃይ  የደረሰባቸው  ሰዎች  (ደቀ እስጢፋኖስ)  ጉዳይ  የተጻፈበት  ተአምር  24  ብቻ  ነው።  ለዚያውም ከተሰደዱቱ  አንጻር  ከተጻፈው  ጋር  ሲተያይ  በውስጡ  የተጠቀጠቁውሸቶችም  አሉበት።  በሌሎች  ምዕራፎች  የተጠቀሱ  ታሪካዊ  ሰዎችም እንኳ  በታሪክ  ማኅደር  ሲፈተሹ  በተአምረ  ማርያም  የሚታየው ማንነታቸው ከእውነተኛ ማንነታቸው ጋር አይገጥምም። ተረቶችና  የፈጠራ  ሥራዎች  የእውነት  መልክ  ሊይዙ  የሚችሉባቸው ዘመናት  ያኔ  ብቻ  አይደለም፤  ዛሬም  ያው  ነው።  ለምሳሌ፥  የዳቪንቺ  ኮድ ልብ  ወለድ  መጽሐፍ  ነው።  መጽሐፉ  ተናፍሶለት  ፊልምም  ሆኖ ለተመልካች  ሲበቃ  ያዩት  አላዋቂ  ሰዎች  ታሪኩ  እውነትና  ቤተ  ክርስቲያን እንዳይወጣ  ደብቃ  የያዘችው  ምስጢር  እንደሆነ  ሽንጣቸውን  ገትረው ተከራክረዋል።  በሕይወት  ያለው  ደራሲ  መጽሐፉ  ልብ  ወለድ  መሆኑን እየመሰከረም  እንኳ  ልብ  ወለዱን  እውነት  ነው  ብሎ  መከራከር  ጅልነት ሳይሆን  እብደት  ነው።  ተአምረ  ማርያምም  ሆን  ተብሎ  ባለበት  መልኩ ተጽፎ  ካልሆነ  ምናልባት  በመጀመሪያ  እንደ  አጫጭር  ተረቶች  መድብል ተጽፎ ኋላ ማርያማዊ  ቀለም የተቀባበት  ይመስላል፤ ሊሆንም ይችላል።
እነዚህ  ጥቂት  ነጥቦች  ከቁጥር  ሊገቡ  የተገባቸው  የደራሲዎቹ  ወይም የደራሲው  ባህርያት  ናቸው።  እንደ  ደራሲው  መጽሐፉ  ራሱ  ደግሞ ሲፈተሽ ይህ መጽሐፍ የራሱ ውስጣዊ ባህርያት አሉት።

የመጽሐፉ ባህርያት / ይዘት

ራሱን  በየጊዜው  ለማረምና  ለማስተካከል  ወይም  ከዘመኑ  ጋር ለመመሳሰል  ከሚጥር  በቀር  በየትኛውም  ሃይማኖትም  ይሁን  ፍልስፍና ዘንድ  አንድ  ዋና  መሠረታዊ  መጽሐፍ  ይኖራል።  ሌሎች  ጥቃቅን መጻሕፍትም  ደግሞ  ይኖራሉ።  ሁልጊዜ  ጥቃቅኖቹ  የዋናውን  አሳብና ፈለግ  እየተከተሉ  ያንን  ያጠነክሩታል፥  ያብራሩታል  እንጂ  አይጻረሩትም። ዋናው  መጽሐፍ  ስሕተት  ያለበትና  የሚስተካከል፥  ወይም  በየጊዜው የሚሻሻል  ሆኖ  ካልተገኘ  በስተቀር  በጥቃቅኖቹ  መጻሕፍት  ውስጥ የሚገኙት  አሳቦች  በሙሉ  ወይም  በከፊል  ስሕተት  የተገኘባቸው እንደሆነ፥  ወይም  ከዋናው  መጽሐፍ  ጋር  የተጋጩ  ሆነው  ቢገኙ  ዋናው ትክክል ጥቃቅኖቹ እንደ ስሕተተኛ ይቆጠራሉ። ወደ  ክርስትና  እምነት  ስንመጣ  ምንጩ  መንፈስ  ቅዱስ  የሆነ  አንድ  ዋና፥ የማይለወጥ፥  ትክክለኛ፥  ሙሉ  ሥልጣን  ያለው  መጽሐፍ  አለን።  ይህ መጽሐፍ  ማናቸውም  ሌላ  መጽሀፍ፥  ስብከት፥  እና  ትምህርት  ብቻ ሳይሆን  አኗኗርም፥  ልምምዶችም፥  የሚፈተሹበት  ነው።  ይህ  መጽሐፍ መጽሐፍ  ቅዱስ  ነው።  ማንም  ክርስቲያናዊ  ካባ  የደረበ  መጽሐፍ ከካባው በታች ያለው ሰውነቱ በዚህ መጽሐፍ መርማሪነት መፈተሽ አለበት።
ተአምረ  ማርያም  ምንጩ  ምንድርነው?  ትውፊት  ነው  ወይስ  አፈ  ታሪክ ወይስ  ተረት?  ለምን ምንጩ  መጽሐፍ  ቅዱስ አልሆነም? መጽሐፍ  ቅዱስ መጽሐፍ  ቅዱስ  የወጡ  ጥቂት  ምንባቦች  መጽሐፉን  ክርስትና  እንዲሸት ተብለው  ከዐውዳቸው  ተፈንቅለው  በውስጥ  ተስገዋል።  ይህን  የሚያህሉ ግዙፍ  ትምህርቶች  ሲሰጡ  በመጽሐፍ  ቅዱስ  መፈተሽ  አያስፈልግም ነበር? ሌሎችም መፈተሻዎች አሉ። መጽሐፉ እርስ በርሱ ይጋጫል ወይስ አይጋጭም?  ከሌሎች  መሰል  መጽሐፎች  ጋርስ  ይስማማል  ወይስ ይጣላል?  በአፈጣጠሩስ  ተዓማኒነትን  የጨበጠ  ነው?  ከታሪክና  ከተረት ወደ  የቱ  ይቀርባል?  ወደ  የቱስ  ያዘነብላል?  ታሪካዊ  ከሆነ  ታሪኩ  ከሌላ ምንጭ ጋር ሊስተያይ ይችላል?  ተአምረ  ማርያምን  አንብቤ  ከፈጸምኩ  በኋላ  በውስጡ  ካገኘኋቸው ሕጸጾች መካከል ዋና ዋና የምላቸው እነዚህ ናቸው፤
የደፈረሰ ምንጭ፥
የተቃለለ ክርስቶስ፥
የተጋነነች ማርያም፥
የተፈናቀለ ታሪክ፥
የተምታታ ሲዖልና መንግሥተ ሰማያት፥
የተጣረሰ ደኅንነትና የተቃወሰ ክርስትና፥
የተላቀቀ መልክዓ ምድር፥
የተዋረደ ጋብቻ፥
ያፈነገጠ ተፈጥሮ።

እነዚህን  ነጥቦች  በቀጣዮቹ  ገጾች  በነጥብ  አወሳቸዋለሁ።  እንዲህ የከፋፈልኩት  መጽሐፉን  በየምዕራፉ  ከመሄድ  ይልቅ  በነጥብ  መሄዱ የተሻለ  ሆኖ  ስላገኘሁት  ነው።  ከነጥቦቹ  አንድ  ሁለቱ  በቀደሙት  ገጾች የተነካኩ  ናቸውና  በነዚህ  እጀምራለሁ።  በየክፍሉ  ውስጥ  የተወሱት በአብዛኛው  ናሙና  ምሳሌዎች  ናቸው  እንጂ  ሕጸጾቹ  በሙሉ  ቢዘረዘሩ በትክክል ራሱን መጽሐፉን የሚያህል መጽሐፍ ይወጣዋል።

1.  የደፈረሰ  ምንጭ። 

ቀደም  ሲል  እንደተጠቀሰው  የእትሙ  አሳታሚው አይታወቅም።  መታወቁ  መልካም  የሚሆነው  ጥያቄንና  አጠያያቂ ጉዳዮችን  ለመነጋገር  እንዲያስችል  ነው።  አሳታሚውን  በተመለከተ መጽሐፉ  ከእትም  ወደ  እትም  የሚሸጋገረው  ከገቢ  ምንጭ  ጋር  በተያያዘ መልኩ  ሊሆን  ይችላል።  የደፈረሰው  ምንጭ  ግን  የመጀመሪያ  ደራሲውን የሚመለከት ነው።  የደፈረሰ  ሲባል  የጠራ  ነገር  ተቃራኒ  መሆኑን  ለማሳየት  ነው።  በዝርዝር እንደምናየው  መጽሐፉ  ከግብጽ  የመነጨ  ለመምሰል  ያልተሳካ  ሙከራ ያደርጋል።  በመምህር  ባዩ  ታደሰ  የተጻፈ  መጽሐፍ  ምንጩን  በተመለከተ፥ “በ1989  ዓ.ም.  የታተመው  ተአምረ  ማርያም  በዚህ  ጊዜ  ተጻፍሁ  ብሎ በግልጽ  ባይነግረንም  በውስጡ  ከያዛቸው  ዘመኑንን  ከሚያመላክቱ ታሪኮች  ተነስተን  ድምዳሜዎች  ላይ  መድረስ  የሚያስችሉንን  ፍንጮች ይዟል።”  ብሎ  ሦስት  ትልልቅ  ነጥቦችን፥  ማለትም፥  በዘመኑ  በርካታ መጻሕፍት  መደረሳቸውን፥  የተተረጎመበትን  የአባ  ሚካኤልንና  አባ ገብርኤልን  ዘመነ  ጵጵስና፥  በዘመኑ  የተደረገውን  የነአባ  እስጢፋ  ስደት ዘርዝሮ  ይህንኑ  አሳብ  ሲደመድም  እንዲህ  ይላል፥  “መጽሐፉን  ትኩረት ሰጥተን  ስንፈትሸው  ግን  በ15ኛው  ክፍለ  ዘመን  ጳጳሳቱ  ኢትዮጵያ  ውስጥ ከገቡ  በኋላ  አከናወኑት  የተባለውን  ኢትዮጵያዊ  ታሪክ  በውስጡ  ይዞ ስለሚገኝ  ከግብጽ  ነው  የመጣው  መባሉን  ለማመንና  ከዚያ  ክፍለ  ዘመን በፊት  የተጻፈ  ነው  ለማለት  የሚያስችለንን  ድፍረት  እንድናጣ ያደርገናል።"
ዲያቆን  ጽጌ  ሥጦታው  ባስተማራቸው  ትምህርቶች  ላይ  በኢኦተቤክ ቅዱስ  ሲኖዶስ  የሊቃውንት  ጉባኤ  በተደረገበት  ሃይማኖታዊ  ምርመራ ወይም  ክርክር  አንዱን  የክስ  ጥያቄ፥  “ተአምረ  ማርያም  የተጻፈው  አባ እስጢፋኖስን  ለመቃወም  ነው  ብለሃል  ተባልሁ”  በማለት  ያነሣና መጽሐፉ  በእርግጥ  የተሠራው  እዚሁ  አገር  ውስጥ  መሆኑን  በዝርዝር መልሶአል።  ይህንንና  ሌሎችንም  ተቀራራቢ  ጥያቄዎች  በጻፈው  መጽሐፍ ውስጥ አካትቶአል።
ተአምረ  ማርያም  በውስጡ  እንደተጻፈው  በእርግጥ  ከመንበረ  ማርቆስ ከተገኘ ከዚያ ወዲህ በመንበረ ማርቆስ ይህ መጽሐፍ መኖሩ የታወቀ ነው ይሆን?  ወደ  መንበረ  ማርቆስ  ከመግባቱ  በፊትስ  የት  ነበር?  ወይስ  እዚያ ነው  የመነጨው?  የግብጽ  ቤተ  ክርስቲያን  ይህ  መጽሐፍ  ኖሮአት ያውቃል? ወይም ይህን መጽሐፍ ንብረቴ ነው ብላ ታውቃለች? በዐረብኛ የተጻፈ  ብዙ  መቶዎች  ዓመታት  ያስቆጠረ  የምንጭ  መጽሐፍስ  አለ?

እንዲያው  በዐረብኛ  ተጽፎ  ከሆነ  ተብሎ  ከታሰበ  ለማለት  ነው  እንጂ የምንጩ  ጽሑፍ  በግብጽ  ስለመኖሩ  የሚናገር  ምንም  አመላካች  ነገር በመጽሐፉ  ውስጥ  የለም።  ከግብጽ  ውጪ  ስለመኖሩም  አመልካች  ነገር የለም። የምችለውን ያህል ውጪያዊ ምንጮችን ከመጻሕፍትም፥ ከመረጃ መረብም  በመፈለግ  ይህን  የአገራችንን  ተአምረ  ማርያም  የሚመስል ወይም  እንደ  ምንጭ  ሆኖ  ሊጠሩት  የሚቻል  ቀራቢ  ሰነድ  ላገኝ አልቻልኩም።  ተገልጠው  ከተሰደሩ  የግብጽ  ቤተ  ክርስቲያን  የሰነድ ስብስቦችም  ውስጥ  እንኳ  ይህ  ተአምር  የለም።  በዲያቆን  ጽጌ  መጽሐፍ በግብጽ  ውስጥ  ተአምረ  ማርያም  በግብጽ  አለመኖሩን  በተመለከተ  ብዙ ዓመታት (10 እና 13 ዓመታት) በዚያ ተቀምጠው የመጡ መነኮሳት ይህን መሳይ  ተአምር  [ተአምረ  ማርያም]  በግብጽ  ያለመኖሩን  ማረጋገጣቸውን ዘግቦአል። ምንጩ  ጠፍቶ  ቅጅው  ብቻ  ነው  አሁን  ያለው  ወይም  በዚህ ዘመን  የቀረው  ካልተባለ  ምንጩ  ካለበት  ተገኝቶ  ቢፈተሽ  ስለምንነቱ ከቅጅው ይልቅ እውነቱን የመግለጥ ጉልበት ይኖረዋል። ከሌለም፥ ‘ዋናው እነ  አባ  አብርሃም  የጻፉት  ከገጸ  ምድር  ጠፍቶ  አሁን  የሚገኘው  ይህ በእጃችን ያለው የኛ ቅጅ ብቻ ነው’ ተብሎም መገለጥ አለበት።  በሌላ  ገጽታው  ግን  ተአምረ  ማርያም  የተተረጎመ  ሳይሆን  በኢትዮጵያ ውስጥ  የተሠራ  አገር  በቀል  መጽሐፍ  መሆኑን  የሚገልጡ  እጅግ  በርካታ ማስረጃዎችን በውስጡ የታቀፈ ጽሑፍ ነው። ይህ ማለት የወዲያ ታሪኮች ከግብጽ  ከመጡት  የተሰሙ  ወይም  የተነገሩ  ሊኖሩ  መቻላቸው  ሳይዘነጋ ነው።  በግብጽ  ውስጥ  ያሉ  ገዳማትና  ግልጽና  የታወቁ  ያልሆኑ  ቦታዎችም ጭምር  ተጠቅሰዋል።  ግብጽና  ግብጻውያን  ግን  እየተደነቁ  ሳይሆን እየተወገዙ  የተነገረባቸው  ታሪኮች  ያይላሉ።  በአንጻሩ  ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን  እየተመሰገኑ  ተጽፈዋል።  ግብጻዊ  ምንጭ  ግብጽን ሲያኮስስና ሲያዋርድ፥ ኢትዮጵያን ሲያገንንና ሲያሞግስ ይነበባል። በግብጽ  ውስጥ  በዐረብኛ  ቋንቋ  ስለ  ማርያም  እየተጻፈ  የኢትዮጵያ ቦታዎች እጅግ ተዘርዝረው ተጽፈዋል። እነሽሬ፥ ተከዜ፥ ዋሊ (ዋልድባ?)፥ ሸዋ፥  ደዋሮ፥  ሙገር፥  ወግዳ፥  መርሐ  ቤቴ፥  ኢፋት፥  ትግራይ፥  የረር፥ አግዓዚ፥  ደብረ  ብርሃን፥  ዳሞት፥  ጎጃም፥  አክሱም፥  መጠራ፥  ጣና፥ ሀዘሎ፥ ደብረ ወገግ፥ ዝቋላ፥ ወዘተ፥ የኢትዮጵያ ሰዎች እነ ሠረቀ ብርሃን፥አስከናፍር፥  ዘሚካኤል፥  ዘርዑ፥  ያሬድ  (ባለ  መዝሙሩ  ያገራችን  ሰው)፥ ዘርዓ ያዕቆብ፥ ዘርዓ ክርስቶስ፥ ዘርዓ ሐዋርያት፥ ወዘተ፥ በኢትዮጵያ የሆነ ታሪካዊ  ክስተት  ለማርያምና  ለመስቀል መስገድ  የተገባ አይደለም ያሉ  የነ ደቀ  እስጢፋ  ዝርዝር  ታሪክ  ሁሉ  መጽሐፉ  ከውጭ  ሆኖ  ስለ  ኢትዮጵያ እየዘገበ  የነበረ  ሳይሆን  እውስጥ  ሆኖ  እየተናገረ  ያለ  መጽሐፍ  መሆኑን ይፋ ያደርገዋል።

የኢትዮጵያ  ግዛቶች  ስሞች  እነ  ማርያም  የኖሩባቸውና  ከሄሮድስ  ሸሽተው ወደ  ኢትዮጵያ  መጥተዋል  ተሰኝቶ  ነው።  ይህም  ራሱ  ራሱን  ማቆም እስከማይችል  ድረስ  የገዘፈ  ፈጠራ  ነው።  እውነተኛው  ታሪክ  የተጻፈው በማቴ. 2፥13-23  ብቻ  ሲሆን  በትንቢት  እንደተጻፈው  የሄዱትና  የቆዩት በግብጽ፥  የተመለሱትም  ከግብጽ  ነው።  ተአምረ  ማርያም  ኢትዮጵያ ውስጥ  በደብረ  መጠራ  ሳሉ  የሄሮድስ  ሞት  ተነገራቸው  የሚለው  ከአዲስ ኪዳን  ጋር  ይጋጫልና  ትልቅ  ውሸት  ነው።  ወደ  ኢትዮጵያ መጥተው  ኖሮ ቢሆን ማቴዎስ  ይህን ለምን አይነግረንም ነበር? ከሆነ ምንም አሳፋሪ ነገር የለበትም።  ይህ  የተሳገ  ትረካ  መጽሐፉ  እዚሁ  አገራችን  ተቦክቶ የተጋገረበት  አንድ  አመላካች  ነው።  መመለሳቸውን  በተመለከተ  ማቴዎስ ከግብጽ  ሲል  ተአምረ  ማርያም  ከመጠራ  (ኢትዮጵያ)፥  ማቴዎስ  ለዮሴፍ ተነገረው  ሲል  ተአምረ  ማርያም  ለማርያም፥  ማቴዎስ  መልአክ  በሕልም ነገረው  ሲል  ተአምረ  ማርያም  ገብርኤል  ለዮሴፍ  ነግሮት  ያረጋገጠላት ደግሞ  ልጇ  ኢየሱስ  ነው  ይላል።  እነዚህ  ሁለት  ምንጮች  እንዲህ ከተጣሉ  ማን  ይደመጥ?  ከተረት  የሚያንሱ  ነገሮች  የታጨቁበት  ተአምረ ማርያም ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ? እዚህ  ተደርሶ  ወደ  ዐረብኛ  ተተርጉሞ  እንደገና  ወደ  ግዕዝ  የተመለሰ የግብጽ  ደርሶ  መልስ  ቲኬት  ተቆርጦለት  ሄዶ  እንደመጣ  የተደረገ  ሥራ ካልሆነ  ወይም  የጥንት  ባላባቶች  የአገልግል  ምግብ  ሲያምራቸው  እቤት የተሠራ  የአገልግል  ምግብ  አገልጋይ  ተሸክማ  በፀሐይ  ስትዞር  ውላ  መልሳ ወደተሠራበት  ቤት  እንደምታመጣው  ዓይነት  ካልሆነ  በቀር  ተአምረ ማርያም  የአገር  ውስጥ  ሥራ  ነው።  ይህ  መጽሐፍ  የተፈጠረበት  ዘመን አምልኮተ  ማርያም  የገነነበት  መሆኑ  ይህን  አገር  በቀልነት  ግልጽ ያደርገዋል።  የአገሪቱ  ጳጳሳት  እየተሾሙ  ይመጡ  የነበረው  ከግብጽ በመሆኑ  ግብጻዊ  ተጋቦት  እንዳለው  አይካድም።  ግብጻዊ  ተጋቦትና ከውጪ  የተጫሩ  ‘ታሪኮች’  ይኑሩበት እንጂ ተተረጎመ  የተባለበት  [ወይም የተጻፈበት]  ዘመንና  ሁኔታ  ምንጩን  አገራዊ  ያደርገዋል።  ምንጩን አገራዊ  ከሚያደርጉት  ነገሮች  ሌላው፥  በሌሎች  አገሮችና  ሃይማኖቶች በአፍቅሮተ  ማርያምና  በአምልኮተ  ማርያም  በተጠመዱቱ  መካከል  እንኳ ይህ መጽሐፍ ያለመገኘቱ ነው።
የመጽሐፉ  ደራሲዎች  ሦስት  ሆኑና  ከዚህ  የተነሣ  መጽሐፉ  እርስ  በርስ የሚጋጩ  ብዙ  ነገሮች  ኖረውበታል።  ቅራኔዎቹና  ግጭቶቹ  ከመጽሐፍ ቅዱስ  ብቻ  ሳይሆን  እርስ  በርሱም  ከታሪክም  ጋር  ነው።  ምናልባት ሲጠናቀቅ  አንድ  ሰው  ነው  የደበለውና  ቅራኔዎቹን  ሳያስታርቅ፥ ግጭቶቹንም  ሳይከረክም  በእያንዳንዱ  ምዕራፍ  ጅማሬና  ድምዳሜ ተመሳሳይ አንቀጾችን መለጠፉ መጽሐፉ የአንድ ሰው እጅ እንጂ የማኅበር እንዳይመስል አድርጎታል።

 የተጻፈበት ዘመን የዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ነው። ቀደም ሲል  እንደጠቀስኩት  ተአምረ  ማርያም  ተተረጎመ  የተባለበት  የነገሠበት  7ኛ ዓመቱ  1434 ዓ.  ም.  መሆኑ  ነው።  ይህ  ዘርዓ  ያዕቆብ  የማርያምና የመስቀል  ስግደትን  ተግባራዊ  ያደረገ  ሰው  ነው።  ይህ  አዲስና  ኋላ  መጥ  ከመጽሐፍ  ቅዱስም  ያፈነገጠ  ትምህርት  መሆኑን  የተረዱና  እንቢ  ያሉ እስጢፋኖስ  በሚባል  መነኩሴ  የተመሩ  ሰዎች  መኖራቸው  አበሳጭቶት  ዘለፋ እስጢፋ  የሚባል  መጽሐፍም  የጻፈ ንጉሥ  ነው።  እነ  እስጢፋኖስን  በመቃወም  ብቻ  ሳይሆን  ሕዝቡንም  በጠንካራ  ማስፈራራት  ለመጠፈር  የማርያም  አምልኮ  አዋጅ  ታወጀ። አዋጁ  ደቂቀ እስጢፋን  የተቀበለ በቤቱ  ያኖረ  ርስት  ያለው  ከርስቱ  ሊነቀል፥  ሹሙ  ከሹመቱ  ሊሻር፥  እነዚህ  ደቀ እስጢፋ  ለድንግል  ማርያምና  ለአንድ  ልጇ  መስቀል  እንቢ  ያሉ ናቸውና አይሁድ  እንደሆኑ  ቅጣታቸውም  ሞት  መሆን  እንዳለበት  ነው።
እውነትም  አዋጁ  ገዳይ  ብቻ  ሳይሆን  አሰቃይቶ  ገዳይ  ሆነ።  አፍንጫ  እየተፎነነ፥  ምላስ  እየተቆረጠ፥  በግርፋትና  የከብት  አጎዳ  በላያቸው እየተነዳ፥  በድንጋይ  እየተወገሩ  ብዙዎች  በስቃይ  ተሰዉ።  ሃይማኖታዊ  ጥያቄዎችን  ለመጠየቅ  በቂ  እውቀት  ከሌለ፥  ቃሉን  አንብበው  መንፈሳዊ  ዓይናቸው  በርቶ  እውቀቱን  ያገኙትም  ሲጠይቁ  ወይም  ሲቃወሙ በንጉሥ ሥልጣንና  አቀነባባሪነት  ይህ  ግድያ  ከተፈጸመባቸው  ሕዝቡ  በመንፈሳዊ  ጨለማ እየዳከረ ቢኖር ምን ያስገርማል?

ለእንዲህ  ያለው  አምልኮተ  ማርያም  ቀዳሚው  ሁኔታ  ምን  ነበር  የሚለው ጥያቄ  ጥናት  የሚፈልግና  ከዚህ  መጣጥፍ  አሳብ  ያለፈ  ጉዳይ  ነው። በአጭር  ቃል  ግን  ስለ  ማርያምና  ወላጆቿ፥  ስለ  ኢየሱስ  ሕጻንነትና  ከዚያ ጋር  ስለተያያዙት  ነገሮች  የተጻፉት  በታሪክ  የሚታወቁት  መጻሕፍት የተጻፉት  ማርያም  ካረፈች  ከ100 ዓመታት በኋላ ነው። ታሪኩን  የሚናገሩ  በሌሉበት  የተፈጠረ  ሥራ  ነው።  ተአምረ  ማርያምማ  ራሱም  ስለ  ራሱ እንደሚመሰክረው  ከዚያ  መደብ  የሚገባም  አይደለም።  ማርያም በሕልምና  በራእይም እየተገለጠች  ያስጻፈችው ነውና። በዐፄ  ዘርዓ  ያዕቆብ  ዘመን  ከዚያ  ዘመን  በፊት  ኖሮ  ያልታወቀ  እንዲህ የመሰለ  መጽሐፍ  ቢጻፍ  ወይም  ቢተረጎም  ግን  አይደንቅም።  የዐፄ  ዘርዓ ያዕቆብ  ዘመን  ከሚታወቅባቸው  መልኮች  አንዱ  የስነ  ጽሑፍ  ፍንዳታ ነው።  ራሱ  ንጉሡም  አስቀድሞ  በገዳም  የኖረ  መነኩሴ  ሲሆን  መንግሥት በአጭር  ጊዜ  ከአባቱ  ሞት  በኋላ  ወደ  ወንድሞቹ  እየተላለፈ  ኋላ ከወንድም  ወደ  ወንድም  ልጅ  ሲያልፍ  ቆቡን  ጥሎ  ዘውድ  ሊደፋ ከምንኩስና  ወደ  ንግሥና  የመጣ  ሰው  ነው።  እንደ  ክርስቲያን  የተቀደሰ ኑሮ  በመኖር  ምሳሌ  የሆነ  ሰው  ሳይሆን  ደርቦ  እያገባና  እንደወደደ  የኖረ፥ እንደ  ክርስቲያን  በእግዚአብሔር  በመታመን  ሳይሆን  ጥንቆላን በመፍራትና በመሳቀቅ የኖረ ሰው ነው። እንደ  ገዳም  ሰውም  እንደ  ንጉሥም  ራሱም  እየጻፈም  ሌሎችንም እያስጻፈና  ከሌሎች  ቋንቋዎች  እየተተረጎመም፥  ዜጋው  በግዴታ የሃይማኖትና  የኅሊና  ጫና  እየተደረገበትም  ብዙ  ሠርቶአል።  ከእርሱ ዘመን  ቀደም  ሲል  መጡ  የተባሉ  ስዕሎችና  ግማደ  መስቀልም  ገናና ሆነዋል።  በዚህ  ጊዜ  ነው  ለማርያም  ስዕል  መስገድ  የመንግሥት  ግዴታ የሆነው።  እነ  መጽሐፈ  ምዕላድ፥  አርጋኖነ  ድንግል፥  ይኸው  በዚህ መጣጥፍ  የምንመለከተው  ተአምረ  ማርያም፥  ይህን  አዲስ  ጫና ላለመቀበል  በቆረጡት  ላይ  የተጻፈ  ዘለፋ  እስጢፋ፥  መጽሐፈ  ብርሃን እና መጽሐፈ  ጽልመት  ሌሎችም  ብዙ  በዚህ  ዘመን  ተጽፈዋል።  ነገረ ማርያምን  በተመለከተ  እንዲህ  የበዙ  መጻሕፍት  በተደረሱበት  ዘመን  ላይ ይህም መጽሐፍ ተተረጎመ ሳይሆን ተደረሰ ቢባል ተገቢ ነው። ሃይማኖቱ የንጉሥ  ጫና  ያለበት  ሲሆንና  ንጉሡ  ራሱም  ደራሲ  ይህን  መሳይ  ጽሑፍ የሚያስሸልምና  ባለሟል  የሚያስደርግ  ከሆነ  ለመጽሐፉ ፈጣሪዎችም  ይህ ዘመን ምቹ ዘመን ነው።

ይቀጥላል,,,,,,,,,,,,,,,,,,
ማሳሰቢያ፤
 በመልእክት ሳጥናችን ገንቢ ያልሆኑና ስህተት ካለ ለእርማት የማያመቹ አስተያየቶችና ስድቦች እየደረሱን ነው። ጸሐፊው የተሳሳተው ነገር ካለ ወይም ጽሁፉ በቀረበበት ርዕስ ላይ በቂ ምላሽ መስጠት የፈለገውን በቀጥታ ለጸሐፊው በማቅረብ ወይም በመካነ ጦማራችን ላይ በማውጣት ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን እየገለጽን ለጸያፍ ቃላት ከተዘጋጀ የስመ ክርስትና አንደበት በመራቅና  ከኔ ወዲያ እውነተኛ ጸዳቂ  የለም!  ከሚል ሌላውን የመኮነን ግብዝነት መለየት የተሻለ እንደሆነ እንመክራለን ። ከዚያ በተረፈ  ብንቀበለውም፤ ባንቀበለውም ያለው እውነት በወንጌል የተነገረላት የክርስቶስ ኢየሱስ እናት ቅ/ማርያምና በተአምረ ማርያም ያለችቱ ማርያም አንድ አይደሉም። የክርስቶስ እናት ድንግል ማርያም ሁሉን ነገር በትዕግስትና በትህትና ትጠብቅ የነበረች ፍጹም ትሁትና የመሀሪ እናት ስትሆን (ሉቃስ 2፤19) የተአምረ ማርያሟ ማርያም ግን ሲኦል የምታወርድ፤ የምትሰነጥቅ፤ እንደእንጨት የምታደርቅ፤ የሰባት ዓመት መንገድ ያህል የሰው ሬሳ እንዲገማ የምታደርግ፤ ሥሉስ ቅዱስን የሚክድ የምትወድ፤ ጥላዋን ጥላ ሚዛን የምትሸውድ፤ ስሟንና ሀገሯን ሳይቀር በመደበቅ የምትዋሽ፤ እሁድ እሁድ ተአምሯን ያልሰማውን የምታወግዝና በአጠቃላይ አንዳችም ክርስቲያናዊ ጠባይ የሌለባት፤ ከክርስቶስ ይልቅ እኔ ልግነን የምትል፤ ጭካኔ የሚታይባት ናት። ይህች ኢትዮጵያ ውስጥ በዘርዓ ያዕቆብ የተፈጠረችው ማርያም፤ በየትኛውም መንፈሳዊ መመዘኛ መንፈስ ቅዱስ ያነጻትና የቀደሳት ድንግል ማርያምን አትወክልም።