Tuesday, June 17, 2014

ተአምረ ማርያም የተባለው መጽሐፍ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እናት የቅ/ማርያምን የቅድስና ባህርይ አይወክልም!

(እዝራ ስነ ጽሁፍ፤ ዘላለም መንግሥቱ)

ተአምረ  ማርያም  የተባለው  መጽሐፍ  እንደ  ስያሜው  ሁሉ  ማርያም እንዳደረገቻቸው  የሚነገሩ  የብዙ  ተአምራት  መድብል  ነው።  ከተአምራቱ በጣም  ጥቂቱን  ሕጻኑ  ኢየሱስ  ያደረጋቸው  ሲሆኑ  ብዙዎቹን  ማርያምና የማርያም  የተለያዩ  ስዕሎች  ናቸው  ያደረጉት።  አንዳንዱ  ምዕራፍ  ምንም ተአምርነት  የሌለበት  የተደረጉ  ነገሮች  የተዘገቡበት  ዘገባ  ቢሆኑም በእያንዳንዱና  በሁሉም  ምዕራፎች  መግቢያ  ወይም  አናት  ላይ  ማርያም ያደረገቻቸው  ተአምራት  እንደሆኑ  በቀይ  ቀለም  እየተጻፈ  በአንቀጽ ተቀምጦአል።  ተአምር  ባልሆኑት  ላይ  በአናቱ  ላይ  የማርያም  ተአምር መሆኑን  መጻፉ  የግድ  መሆን  ስላለበት  የተደረገ  ይመስላል።  ለምሳሌ፥ ሁለተኛው  ተአምር  ወይም  ምዕራፍ  ማርያም  ስለ  መጸነሷና  ስለ  ልደቷ የተነገረ  ሲሆን  ያው  የግዴታ  ልማድ  ሆኖ  ክብርት  እመቤታችን ያደረገችው ተአምር ተብሎ ተጽፎአል። ያለዚያ እንደ ምዕራፍ 2 መግቢያ ማርያም  ገና  ከመጸነሷና  ከመወለዷ  በፊትም  ተአምር  ታደርግ  ነበርና ከልደቷ  በፊትም  ቀዳሚ  ኅልውና  ነበራት  ማለት  ይሆን?  አጻጻፉ ይመስላል። ከሆነ ዘላለማዊት ናት ሊሰኝ ይመስላል።  የመጽሐፉ አሳታሚና ባለቤት ማን ነው? ይህኛውን  (እኔ  ያነበብኩትን)  እትም  ያተመው  ተስፋ  ገብረ  ሥላሴ ማተሚያ  ቤት  ሲሆን  አሳታሚው  አልተጻፈም።  ከመግቢያው እንደሚነበበው  ግን  አሳታሚው  ተስፋ  ገብረ  ሥላሴ  ዘብሔረ  ቡልጋ ነው።  ይህ  መጽሐፍ  በኢኦተቤክ  ሰፊ  ተቀባይነት  ያለው  የነገረ  ማርያም ሰነድ  መሆኑ  አጠያያቂ  ባይሆንም  በማን  ቡራኬ  መታተሙ  አልተጻፈም። በበርካታ የኢኦተቤክ መጽሐፎች እንደሚታየውም የሊቀ ጳጳስ ምስል እና መልእክትም  የለበትም።  ስለዚህም  አይቶ፥  መርምሮ  አጽድቆ  ለአንባቢ የተገባ  ነው  ብሎ  ያሳለፈ  ተጠያቂ  አካል  የለውም  ማለት  ነው።  በእውኑ የኢኦተቤክ  ይህን  መጽሐፍ  እንደ  ቅዱስ  መጽሐፍ  አድርጋ  ትቀበለዋለች?  መቼም  ከተቀበለችው  በቂ  የሆነ  ታሪካዊ  ምንጭ  ያለው  ሆኖ  መገኘት አለበት?  ከመጽሐፍ  ቅዱስ  ጋርም  መጋጨት  የለበትም።  ምክንያቱም ማንም  ክርስቲያናዊ  መጽሐፍ  አስተምህሮአዊ  ተደርጎ  ከተወሰደ  ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለበት። ታሪካዊ ከሆነ ደግሞ ታሪካዊ ብቻ ነውና ሥልጣን  ያለው  መጽሐፍ  መሆን  የለበትም።  ደግሞም  ከዋናው ክርስቲያናዊ  መጽሐፍ  ከመጽሐፍ  ቅዱስ  ጋር  ተያይቶ  ሊቀበሉት  ወይም ሊጥሉት የተፈቀደ መሆን የተገባው ነው። የኢኦተቤክ ይህን መጽሐፍ የኔ ብላ ትቀበለው ወይም አትቀበለው እንደሆነም  ግልጽ  አይደለም። በአንድ ድረ  ገጽ  ላይ  በቅርብ  ያነበብኩት  ሁለቱ  ሲኖዶሶች  ከሚነጋገሩባቸው ነጥቦች አንዱ ይህ መጽሐፍ እንደሆነም ነው። መጽሐፉ  አሁን  በታተመበት  ቅርጹ  አማርኛው  ከግዕዙ  ጋር  ጎን  ለጎን በመሆን  ተጽፎአል።  አንዳንዱ  የአማርኛ  ቃላት  ሆን  ተብለው  የተለሳለሱ ሲመስሉ  አንዳንዱን  አማርኛ  ለመረዳት  ደግሞ  ራሱ  ግዕዙ  ለዘመናችን አማርኛ  የቀረበ  የሚመስልባቸው  ቦታዎችም  አሉ።  አንዳንዱ  ጥቅስ ከትርጉም  ይልቅ  ማብራሪያ  የሚመስልባቸው  ቦታዎችም  ብዙ  ናቸው። የተአምራቱ  ቁጥራቸውም  ከአንዱ  እትም  ወደ  ሌላው  ይለያያል  ይባላል። እኔ  ባነበብኩት  መጽሐፍ  (የŦ ŹƃƂƆ  ዓመተ  ምሕረት  እትም)  ተአምራቱ ወይም  ምዕራፎቹ  123  ናቸው።  አንዳንድ  ተአምራት  ወይም  ምዕራፎች በአንዱ  የመጽሐፉ  እትም  ይገኙና  በሌላው  እትም  የማይገኙ  ከሆኑ መጠኑና ይዘቱ ከእትም እትም ይለያያል ማለት ነው። በመምህር  ባዩ  ታደሰ  መጽሐፍ ውስጥ  ከተቀነሱት  ተአምራት  አንዱን ‘ተአምር  97’  የተባለውን  በመጥቀስ  ከቀድሞዎቹ  እትሞች  በአንዱ (ለምሳሌ፥  ከ1924ቱ  እትም)  ተጽፎ  ከኋለኞቹ  እትሞች  (ለምሳሌ፥ ከ1989ኙ እትም) እንደቀረ በማውሳት ይህ የሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በግልጽ  በመጋጨቱ  ምክንያት  እንደሆነ  ታትቶ  ቀርቦአል።  ለውጥ የሌለበት  ለማስመሰል  ግን  ‘በድጋሚ  የታተመ’  እየተባለ  መቅረቡተወስቶአል። በሌላ  አንድ  መጽሐፍ  ውስጥ  የተጠቀሰ  ተአምረ  ማርያም ደግሞ  ተአምራቱ  አንድ  መቶ  አሥራ  አንድ  መሆናቸውን  ይጠቅሳል። ቁጥሩ  ወጣ  ገባ  ነው።  በአንድ  ድረ  ገጽ  ስለ  ተአምረ  ማርያም  በተጻፈ አጭር  መልእክት  ላይ  ምላሽ  ከሰጡት  ሰዎች  አንዱ  ተአምር  19  ላይ  ስለ መሐመድ  የተጻፈ  ነገር  እንዳለበት  ጠቅሶአል። እኔ  ባነበብኩት  ምዕ. 19ማርያም  ሙታንን  እያስነሳች  ለሰዎች  ስታሳይ  ነው  የተጻፈው  እንጂ  ይህ ስለሌለ  በድረ  ገጹ  የተጻፈው  ትክክል  ከሆነ  ምዕራፎቹ  ተሸጋሽገው፥ ታጥፈው፥ ወይ ተሰርዘው ይሆናል? ምናልባት አንዳንዱ እትም ምዕራፎቹ እየተመረጡና  የሚያጠያይቁት  እየተነቀሱ  የታተመ  ሊሆን  ይችላል፤  ግን ከላይ  እንደተጠቀሰው  ‘በድጋሚ  የታተመ’  እየተባለ  ከውስጡ  እየተገመሰ ከቀረ ይህ ስነ ጽሑፋዊ እብለትና አንባቢን መደለል ነው።

 የመጽሐፉ ምንጭ / ደራሲው ማን ነው?

ተአምረ ማርያም በመጀመሪያ በግብጽ አገር ከመዓልቃ ከመንበረ ማርቆስ (መንበረ  ማርቆስ  በእስክንድርያ  ነው  የሚገኘው)  የተገኘ  በዐረብኛ  ቋንቋ የተጻፈና  በኋላ  ወደ  ግዕዝ  ተተረጎመ  የተባለ  መጽሐፍ  ነው።  የጻፉት  አባ አብርሃም፥  አባ  ማርቆስና  አባ  ማቴዎስ  የተባሉ  [መነኮሳት]  ሲሆኑ የጻፉትም  ማርያም  አንዳንዴ  ራሷ  እየተገለጠች፥  ሌላ  ጊዜ  በሕልም፥  ሌላ ጊዜ  በራእይ  እየታየች  እየተነጋገረቻቸው  እንደሆነም  በመቅድሙ ተጽፎአል።  እነዚህ  ሦስት  መነኮሳት  እነማን  ስለመሆናቸው፥  መቼ ስለመኖራቸው፥  የት  ስለመኖራቸው፥  የምን  አገር  ወይም  የየትኛው ዐረብኛ  ተናጋሪ  አገር  ሰዎች ስለመሆናቸው የሚናገርም ምንም  ማብራሪያ በመጽሐፉ  የለም።  እነዚህ  ጸሐፊዎች  እነማን  ናቸው  ቢባል መታወቂያቸው  ቢያንስ  በመጽሐፉ  ውስጥ  የሚገኝ  መሆን  ነበረበት፤  ግን የለም። በምዕ.  1  ደቅስዮስ  የተባለ  ሰው  ታሪኳን  ሲሰበስብ  እንደተገለጠችለትና ስለጻፈላት  እንዳመሰገነችውም  ተጠቅሶአል።  ይህ  ደቅስዮስ  ሰብሳቢም ጸሐፊም  ተብሎአልና  እንደ  ሰብሳቢ  ብቻ  ሳይሆን  ከነአባ  አብርሃም  ጋር እንደ  ጸሐፊም  የሚቆጠር  ነው።  በምዕ.  6  ደግሞ  አንድ  ሰው  ሌላ መጽሐፍ፥ የፍልሰት መጽሐፍ እንዳገኘ ይናገራል። ቁ. 23 ላይ ይህን የጻፈ ዮሐንስ ነውም  ይላል።  ቁ. 18  ላይ እርሱ ራሱ  የጻፈውን ነገረኝም ይላል። ስለዚህ  ከነአባ  አብርሃም  በፊት  የተጻፈ  ያውም  በሐዋርያው  ዮሐንስ የተጻፈ  የፍልሰት  መጽሐፍም  የነበረ  ይመስላል።  በምዕ.  7  ደግሞ ስንክሳርን  በመጥቀስ  ያንንም  እንደ  ምንጭ  በመጥቀስ  የማርያምን  ዕርገት ይተርካል።  ስለ  ደራሲዎቹ  ከስማቸው  ውጪ  ከመጽሐፉ  ውስጥ  የምናገኝላቸው  ነገር የለም።  ስምና  ማዕረግ  ብቻ  ‘አባ  እገሌ’  ተብሎ  ከመጠቀሱ  በቀር  ሌላ ያለመኖሩ  ምንጩን  ሆን  ተብሎ  የተድበሰበሰ  ያደርገዋል።  ‘አባ  እገሌ’ ደግሞ  የመነኩሴ  ሁሉ  መጠሪያ  ነው።  በማን  ዘመን  መንግሥት  ወይም በማን  ዘመነ  ጵጵስና  ነበሩ?  የት  ነበሩ?  እነዚህ  ሴዎች  ሌላ  ምን  ጻፉ?  ቢባል  አጥጋቢ  ቀርቶ  የማያጠግብም  ማስረጃ  አይገኝም።  ምናልባት  ኖሮ ቢሆን  ከዚያ  በመንደርደር  የዘመኑን  ታሪካዊ  ስነ  መለኮት  በመቃኘት ነባራዊ  እውነታ  መጨበጥ  ይቻል  ነበር፤  ወይም  ሌላ  የጻፏቸው  ሥራዎች ቢኖሩ  የሰዎቹን  ስነ  መለኮታዊ  አቋም  በንጽጽር  መገምገም  ይቻል  ነበር። ግን እነዚህ ነገሮች የሉም። የዐረብኛው  የምንጭ  ጽሑፍም  መቼ  እንደተጻፈ  የሚያረጋግጥ  ውጪያዊ ምስክር  ወይም  ውስጣዊ  ማስረጃ  አይገኝለትም።  ከመጽሐፉ  መግቢያ እንደሚገመተው  የመጀመሪያውን  የጻፉት  በዐረብኛ  ሳይሆን  አይቀርም። እንደሚገመተው  ያልኩት  ግዕዙ  ተተረጎመ  የተባለው  ከዐረብኛ  መሆኑ እንጂ  የምንጭ  ቋንቋው  ዐረብኛ  ይሁን  ወይም  ራሱ  ዐረብኛው  ከሌላ ቋንቋ  የተተረጎመ  መሆኑን  ስለማይናገር  ነው።  ከሆነ  ዐረብኛ  የግብጽ ቋንቋ የሆነውና ቅብጥ ወደ ኋላ ተገፍቶ ከመነጋገሪያ ቋንቋነት የተወገደው ከእስልምናና  የዐረቦች  ወረራና  መስፋፋት  በኋላ  ስለሆነ  ከ8ኛው  ምዕት  ዓመት  በኋላ  ይሆናል  ማለት  ነው።  እንግዲህ  በዐረብኛ  መጻፋቸውና የተገኘው  ከግብጽ  መሆኑ  የኢትዮጵያና  የግብጽ  አብያተ  ክርስቲያናትን ቁርኝት  ተንተርሶ  አገሩን  ግብጽ፥  ዘመኑንም  ከእስልምና  ወረራ  በኋላ ጀምሮ እስከ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ባለው ጊዜ ነው ብሎ ሰፊ ግምት መቸር ይቻላል።  በመቅድሙ  ይህ  የተተረጎመው  መጽሐፍ  የተገኘው  ከመንበረ ማርቆስ መሆኑ ተነግሮአል።  ተአምረ  ማርያም  ተተረጎመ  የተባለበት  ዘመኑም  ተጽፎአል።  ግን  ዋናው ከተጻፈ  ከስንት  ዘመናት  በኋላ  ስለመተርጎሙ  ግምትም  እንኳ  መገመት አይቻልም።  ተርጓሚዎቹ  አባ  ሚካኤልና  አባ  ገብርኤል  የተባሉ  ናቸው። አሁንም  ከስማቸው  ውጪ  ስለሰዎቹ  ከመጽሐፉ  ውስጥ  የምናገኘው ማንነታቸውን  ገልጦ  የሚያስረዳ  ነገር  የለም።  ተረጎሙት  የተባለበት  ጊዜ “ቆስጠንጢኖስ  የተባለ  ንጉሣችን  በዘርዓ  ያዕቆብ  ዘመን  በነገሠም  በ፯ ዓመት”  ተብሎ  ተጠቅሶአል።  ቆስጠንጢኖስ  ወይም  ዐፄ  ዘርዓ  ያዕቆብ የነገሠው በኛ አቆጣጠር ከ 1427-1461 ዓመተ ምሕረት ነው። የነገሠ 7ኛ  ዓመቱ  1434  ዓ.  ም.  ነው  ማለት  ነው።  በኋላ  ላይ  የምንጩን ድፍርስነት  በተመለከተ  አወዛጋቢና  አጠያያቂ  ነጥቦች  አነሣለሁ።  በአጭሩ ግን  በመጽሐፉ  ውስጥ  ከተጻፈው  የሚገኘው  የተአምረ  ማርያም  ምንጭ፥ መነሻና ዘመን ይህ ነው።

የጸሐፊው / የጸሐፊዎቹ ባህርያት

በአንዳንድ  መጽሐፎች  አንዳንዴ  እውስጡ፥  አንዳንዴ  በሽፋኑ  ስለ ደራሲው የተጻፈ አጭር ወይም ረጅም ታሪክ ወይም ግለ ታሪክ ይገኛል። ከመጽሐፉም  ከሌላ  ስፍራም  ካልተገኘ  በመጽሐፉ  ውስጥ  ከተነገሩት ነገሮች  በመነሣት  አንባቢው  የደራሲውን  የተለያዩ  የእምነትና  ማኅበራዊ አቋሞች እንዲሁም ስነ ልቡናዊ ከባቢና ስፍራ ማወቅ ይችላል።  በተአምረ  ማርያም  ውስጥ  ስለመጽሐፉ  ደራሲዎችም  ሆነ  ተርጓሚዎች ማንነት፥  አገልግሎት፥  እምነት፥  ዘመን፥  ገጠመኝ፥  ቦታ፥  ቤተ  ሰብ  ወዘተ የተጻፈ  ነገር  የለም።  ከመጽሐፉ  በመነሣት  ግን  ተአምረ  ማርያምን  የጻፉት ደራሲዎች  ወይም  ደራሲ  እምነቱ፥  የመጽሐፍ  ቅዱስ  መረዳቱ፥  የታሪክ እውቀቱ፥  ከክርስቶስ  ቁርኝቱ፥  ወዘተ፥  ምን  እንዲመስል  መገንዘብ ይቻላል። ጥቂቶቹ እነዚህ ናቸው።

 1.  የተአምረ  ማርያም  ደራሲ  እግዚአብሔርን  የሚንቅ  ሰው  ነው።

እግዚአብሔር  በነቢዩ  ኢሳይያስ  አድርጎ፥  እኔ  እግዚአብሔር  ነኝ ስሜ  ይህ ነው  ክብሬን  ለሌላ፥  ምስጋናዬንም ለተቀረጹ  ምስሎች  አልሰጥም  ብሏል፤ ኢሳ.  42፥8።  ክብሩን  ለሌላና  ለተቀረጹ  ምስሎች  አሳልፎ  አለመስጠት ብቻ ሳይሆን የተቀረጹ ምስሎች መደረግም የለባቸውም። ከ10ቱ ትእዛዛት 2ኛው  ይህ  ነው፤  በላይ  በሰማይ  ካለው፥  በታችም  በምድር  ካለው፥ ከምድርም  በታች  በውኃ  ካለው  ነገር  የማናቸውንም  ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም  ምስል  ለአንተ  አታድርግ፥  አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም።  ዘጸ.  20፥4።  የዚህ  መጽሐፍ  ጸሐፊ  ግን  በግልጽ ይህንን  አምላካዊ  ትእዛዝ  በመተላለፍ  የእግዚአብሔርን  ክብር  ለሌላ፥ ማለትም፥  በፈጣሪ  ለተፈጠረች  ለማርያም  እና  በሰዎች  እጅ  ለተሳሉ የማርያም ስዕሎች ሸንሽኖ አሳልፎ ይሰጣል። በመጽሐፉ  ውስጥ  እግዚአብሔር  የተገለጠበትን  ክብር  እና  ማርያምየተገለጠችበትን  ክብር  ስናነጻጽር  በጉልህ  እግዚአብሔር የማርያም ፈቃድ ፈጻሚ  ነው።  ወሳኟ፥  አድራጊዋ፥  ቀጪዋ፥  ሸላሚዋ፥  ተበቃይዋ፥  ወደ ሲዖል  አውራጇ፥  ከሲዖል  ነጣቂዋ  እርሷ  ናት።  አዳምና  ሔዋን  እና  ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር ሳይሆን ለእርሷ ክብር እንደተፈጠሩ ይናገራል መጽሐፉ።  በመጽሐፉ  ውስጥ  የሚታዩት  የማርያም  ስዕሎች  እጅ  ዘርግተው የመሥራትና  የማድረግ፥  አፍ  ከፍቶ  ድምጽ  አውጥቶ  የመናገር፥  ብያኔ የመስጠት፥  ሲወጉት  የመድማት፥  ተመልሰው  ሲለጠፉ  ጠባሳ  ሆኖ የመቅረት  ባህርይ  ያላቸው  ምስሎች  ናቸው።  ተአምራት  ማድረግ የእግዚአብሔር  ሀብት  ቢሆንም  በዚህ  መጽሐፍ  ውስጥ  እግዚአብሔር ሳይሆን  ማርያም  እና  ምስሎቿ  ናቸው  ተአምር  አድራጊዎቹ።  ከእግዚአብሔር  ኃይል  እና ከጌታ  ከኢየሱስ ስም  ሥልጣን ውጪ  ተአምር ከተደረገ  የዚያ  ተአምርና  ምልክት  ምንጭ  እግዚአብሔር  ሳይሆን  ሰይጣን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል።

2.  ይህ  ደራሲ  መጽሐፍ  ቅዱስን  የማያውቅ  ሰው  ነው። 

በጣም  በጥቂት ቦታዎች  አልፎ  አልፎ  የተጠቀሱ  የመጽሐፍ  ቅዱስ  ክፍሎች  አሉ።  እነዚህ የተጠቀሱ  ጥቂት  ጥቅሶች  የተጠቀሱት  ያለቦታቸው  በመሆኑ  ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩና የሚጣሉ ነገሮች ናቸው። መጽሐፉ የተደመደመው ኢየሱስ  18  ዓመቱ  ሆኖ  በግሪክ  ሳለ  ሲሆን  በወንጌል  ውስጥ  ያደረጋቸው አንዳንድ  ነገሮች  ገና  አገልግሎቱን  ሳይጀምርም  እንደተፈጸመ  ሆነው ተጠቅሰዋል።  የደራሲው  ከመጽሐፍ  ቅዱስ  ጋር  ያለው  ግንኙነት  እነዚህን ጥቅሶች ለመውሰድ ብቻ ይመስላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና መልእክት ሰው ንጹሕ ሆኖ ተፈጥሮ ሳለ ኃጢአተኛ መሆኑና  እግዚአብሔር  ይህን  የወደቀ  ሰው  ለማዳን  በብሉይና  በአዲስ ኪዳን ያደረገው  ነገር  ነው።  ይህ ደግሞ በጣም  ግልጽ  ተደርጎ  ተጽፎአል። በብሉይ  ዘመን  ከሲና  ኪዳን  በፊት  በልቡና  ሕግ፥  ከሕገ  ልቡና  ዘመን በኋላ ደግሞ  ሕግ  ተሰጥቶ  ሰዎች  የመዳንን መንገድ  የሚሄዱበት  ያን  ሕግ በመፈጸም ሆነ። ሕጉም ራሱ ሊመጣ ያለው ነገር ምሳሌና ጥላ ነው እንጂ በዘላቂነት  ተጠብቆ  የሚዳንበት  አልነበረም።  ያ  ሁሉ  መስዋዕት  ጥላ  ሆኖ የሚያመለክተው  አካል  ነበረ፤  ያም  በመስቀል  ላይ  የሞተው  የክርስቶስ መስዋዕትነት  ነው።  ወንጌል  በአንድ  ጥቅስ  ቢጠቀስ  በዮሐ.  3፥16  የተጻፈው፥  በእርሱ  የሚያምን  ሁሉ  የዘላለም  ሕይወት  እንዲኖረው  እንጂ እንዳይጠፋ  እግዚአብሔር  አንድያ  ልጁን  እስኪሰጥ  ድረስ  ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና የሚል ነው።  የተአምረ  ማርያም  ደራሲ  የሸፈነው  ትልቅ  እውነት  ይህ  አንጡራው ወንጌል  ነው።  ተአምረ  ማርያም  በመጽሐፍ  ቅዱስ  ውስጥ  እንደተጻፈው የሰውን  ልጆች  ለማዳን  እግዚአብሔር  ያደረገውን  እውነት  የጋረደ መጽሐፍ  ነው።  በዮሐ.  14፥6  ጌታ፥  እኔ  መንገድና  እውነት  ሕይወትም ነኝ፤  በእኔ  በቀር  ወደ  አብ  የሚመጣ  የለም  ያለውን  የተጻረረ  መጽሐፍ ነው።  በሮሜ  10፥13፥  የጌታን  ስም  የሚጠራ  ሁሉ  ይድናልና  የሚለው የምሥራች  በሌላ  ጫና  ተተካ።  መንገዱ  ኢየሱስ  ሳይሆን  ማርያም፥ መጠራት  ያለበት የጌታ  ሳይሆን የማርያም ስም  ተደረገና  ተለወጠ።  ለዚህ ነው  ይህ  ደራሲ  ደኅንነት  የሚገኝበትን  መንገድ  ያልተገነዘበ፥  መጽሐፍ ቅዱስን  የማያውቅ  ሰው  ነው  ያልሁት።  ካወቀ  ደግሞ  ሳያውቅ  የዘላበደ ሳይሆን አውቆ ያሳተ አሳች ነውና የባሰ አጥፊ ነው።  ይህ  መጽሐፍ  የተጻፈበት  ዘመን  ምእመናን  መጽሐፍ  ቅዱስን  እንደልብ የማያገኙበትና  የማያስተያዩበት  ዘመን  ነውና  የተነገረውን  ሁሉ  እንደ እውነት  ለመቀበል  ሃይማኖታዊና  ስነ  ልቡናዊ  ጫና  የሚደረግባቸው ስለሆነ  እውን  ከመጽሐፍ  ቅዱስ  ጋር  ይጋጫል  ወይስ  አይጋጭም የሚለውን  የሚጠይቅ  አይኖርም።  የተማሩት  የሚባሉት  አለማሳወቃቸው ግን  የአዋቂ  አጥፊ  ያደርጋቸዋል።  ባለፉት  300  ዓመታት  ተራው  ሕዝብ ሊገባው  በሚችለው  ቋንቋ  መጽሐፍ  ቅዱስን  እንዲያገኝ  በመርዳትና  በማስተርጎም ፈንታ  ሌሎች  ጥረው  የተረጎሙት እንኳ  እንዳይደርስ  ታላቅ ተጋድሎ  ታደርግ  የነበረችው  ቤተ  ክህነት  መሆኗም  አስተዛዛቢ  ጉዳይ ነው።  ይህ  ራሱን  የቻለ  ሌላ  ጉዳይ  ቢሆንም  እዚህ  ያነሣሁት  ከሕዝብ መጽሐፍ  ቅዱስን  አለማወቅና  የተጻፈውን  ሳያስተያዩ  ከመቀበል  ጋር መነሣት  ስለተገባው  ነው።  እስከ  ቅርብ  ዓመታት  ድረስ  በኢኦተቤክ ስብከትና  ትምህርት  ለተራው  ምእመናን  በሚገባቸው  ቋንቋ  አይሰበክም ነበር።  ያኔ  ይህ  መጽሐፍ  በተጻፈበት  ዘመንማ  ሰው  በተስኪያን  ገብቶ ግድግዳ  ላይ  የተሳሉ  ስዕሎችን  ‘አንብቦ’  ነበር  የሚመለሰው  እንጂ  ሮሜ 10፥17  እንግዲያስ  እምነት  ከመስማት  ነው  መስማትም  በእግዚአብሔር ቃል  ነው  የሚለውን  አምኖ  እንዲድን  ሊሰማ  አልተደረገም።  የምእመናኑ አለማወቅ  ብቻ  ሳይሆን  ያውቃሉ  ተብለው  ሊያሳውቁ  የሚጠበቁትም ከቃሉ  ጋር  ጀርባና  ጀርባ  የሆነ  እንደዚህ  ያለ  መጽሐፍ  ሲያቀርቡ  አሳዛኝ ታሪክ  ነው።  ምን  ይደረግ!  ቃሉን  አያውቁትም።  ቢያውቁት  ኖሮ አይቃረኑትም ነበር።

3.  ይህ  ደራሲ  ክርስቲያንና  የክርስቶስ  ምስክር  ያልሆነ  ሰው  ነው።

በተአምረ  ማርያም  ውስጥ  ክርስቲያናዊ  ባህርያት፥  ቃሉን  ማንበብ፥ እግዚአብሔርን  በመንፈስና  በእውነት  ማምለክ፥  ወንጌልን  ላልዳኑት ማሳወቅ፥  ክርስቶስን  መምሰል፥  የደቀ  መዝሙርነት  ኑሮ፥  የመንፈስ  ፍሬ፥ ጠላትን  መውደድ፥  የቅዱሳን  በቅድስና  መኖርና  በእምነት  መጽናት፥ ወዘተ፥  አይታዩበትም።  ይልቁን  በቀል  ይታይበታል።  የማያምኑትን መበቀል፥  በወንጌል  እውነት ተመርተው ሊኖሩ የሚወድዱትንም  መበቀል ይታዩበታል።  ክርስቲያን  ክርስቲያን  የተባለው  የክርስቶስ  ስለሆነ  ነው። አዳኙ፥  መሪው፥  ጌታው  ክርስቶስ  ነው።  በዚህ  መጽሐፍ  ግን  ማርያም አዳኝ፥  ኮናኝ፥  አጽዳቂ፥  ወደ  ሲዖል  አውራጅ፥  ወደ  መንግሥተ  ሰማያት አስገቢ፥  እየተገለጠች  መመሪያ  የምትሰጥ  ናት።  ይህ  እርሷን  ያለምንም ጥያቄ የሚከተል ሰው ክርስቲያን ነው መባል ያለበት ወይስ  ‘ማርያን’? ክርስቶስን  የሚያውቅ  ክርስቲያን  ያለ  ልክ  ከፍ  ያለውን  ጌታ  ስላወቀ በፊል. 2፥11  መላስም  ሁሉ  ለእግዚአብሔር  አብ  ክብር  ኢየሱስ  ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው እንደተባለ እርሱን የሚመሰክር ነው። ደግሞም  ጌታ  ከማረጉ  በፊት  በመጨረሻ  የተናገረው  ቃል፥  ምስክሮቼ ትሆናላችሁ  የሚል  ነው፤  ሐዋ. 1፥8።  ክርስቲያን  የክርስቶስ  ምስክር  ነው እንጂ  የሌላ  የማንም  ምስክር  አይደለም፤  ሊሆንም  የተገባ  አይደለም። እንዲህ  ያለ  መጽሐፍን  የጻፉና  ያስጻፉ፥  ከተጻፈ  በኋላም  የሚያሳትሙና የሚያሰራጩ  ክፉኛ  የሳቱት  ክርስቲያን  የማን  ምስክር  የመሆኑን  እውነት ባለመረዳት  ነው።  ይህ  ብቻ  ሳይሆን  የክርስቶስ  ሳይሆን  የሌላ  ምስክር መሆን  የሐሰት  ምስክር  ሆኖ  መገኘት  መሆኑን  ባለመረዳት  ወይም  አውቆ ከሐሰት ጋር ለመቆም ነው።  ምስክር  ያየውንና  የሰማውን  የሚናገር  እንጂ  ያዩና  የሰሙት  የጻፉትን የተነገረውን  እውነት  የሚሸፍን  አይደለም።  በዚህ  መጽሐፍ  ውስጥ  ግን ጌታ  ክርስቶስ  ተለጣፊ  ሆኖ ነው  የሚታየው። ጌታ ከራሱ  ጋር  ሌላ  ደባል የሚያቆምና  የሚጋራ  አምላክና  አዳኝ  አይደለም።  በነዚህ  ጥቂት  ጥቅሶች ውስጥ  “ብቻውን”  የሚሉትን  ቃላት  እናጢን፤  ብቻውን  አምላክ  ለሚሆን ለማይጠፋው  ለማይታየውም  ለዘመናት  ንጉሥ  ምስጋናና  ክብር  እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን። 1ጢሞ. 1፥17። ያንም መገለጡን በራሱ ጊዜ ብፁዕና  ብቻውን  የሆነ  ገዥ፥  የነገሥታት  ንጉሥና  የጌቶች  ጌታ፥  ያሳያል። 1ጢሞ. 6፥15።   ከብዙ  ጊዜ  በፊት  ለዚህ ፍርድ የተጻፉ  አንዳንዶች  ሰዎች ሾልከው  ገብተዋልና፤  ኃጢአተኞች  ሆነው  የአምላካችንን  ጸጋ  በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ።  .  .  .  ብቻውን  ለሆነ  አምላክና  መድኃኒታችን  ከዘመን  ሁሉ በፊት  አሁንም  እስከ  ዘላለምም  ድረስ  በጌታችን  በኢየሱስ  ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤  አሜን።  ይሁ. 1፥4፥25።  ይህ ብቻውን  የሚል  ቃል  (movnoß)  የሚጋራው፥  የሚዳበለው፥  አብሮት የሆነ  የሌለ  መሆኑን  ገላጭ  ቃል  ነው።  ለደኅንነት  ኢየሱስን  ከማርያምም ሆነ ከሌላ ከማንም ማዳበል ፍትሕ ሳይሆን ክህደት ነው።

ይቀጥላል,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,