Thursday, November 5, 2015

መምህር ግርማ ተጨማሪ የተጠረጠሩበት ወንጀል ይፋ ሆነ



አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መምህር ግርማ ወንድሙ አዲስ የተጠረጠሩበት ወንጀል ይፋ ሆነ።

ይህ የተጠረጠሩበት ወንጀል ሀሰተኛ ሰነድ መገልገል የሚል ነው ብሏል የአዲስ አበባ ፖሊስ።

ጥቅምት 23 2008 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ባልሰጠኋቸው የስብከት እና የማጥመቅ ፈቃድ እንደሰጠኋቸው በማስመሰል በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር በቤተክርስቲያኒቱ ስም ሲያስተምሩ እና ሲያጠምቁ ቆይተዋል በማለት ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በፃፈው ደብዳቤ አሳውቋል።

ይህንን በተመለከተም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለ ቤተክርስቲያኒቱ እውቅና በህገ ወጥ መንገድ በሀሰተኛ ሰነድ ተጠቅመው ሲያገለግሉ ነበር በማለት ለመምህር ግርማ ወንድሙ የተፃፉ ሰባት ቅፅ ደብዳቤዎችን ጠቅላይ ቤተክህነት ለፖሊስ በመሸኛ ደብዳቤ ልኳል።

በዚህ መሰረት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ይህንን ምርመራ ለማከናወን 14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

ተጠርጣሪው መምህር ግርማ ወንድሙ በበኩላቸው ደቡብ ወሎን ጨምሮ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ቤተክህነት ደብዳቤ እየፃፈልኝ ነው ሳገለግል የሰነበትኩት ብለዋል።

ጠበቆቻቸውም እንዲሁ ሌላው ቢቀር እሳቸው በቋሚነት በሚያገለግሉባቸው የረር ስላሴ እና ጀሞ ሚካኤል እንኳን ህገ ወጥ ናቸው የሚል በቤተክህነት  የተላከ አንዳችም ደብዳቤ ያለመኖሩን እንዲሁም መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት ወንጀል ስላልሆነ ፍርድ ቤቱ የተጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ አቤቱታ ውድቅ አድርጎ ደንበኛችን የዋስትና መብታቸው ይከበርላቸው ሲል ጠይቋል።

የምርመራ ቡድኑ በበኩሉ የተጠረጠሩበት ወንጀል ሀሰተኛ ሰነድ መገልገል በመሆኑ ችሎቱ የጠበቆቹን ጥያቄ እንዳይቀበል ሲል አመልክቷል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀን የ7 ቀኑን ፈቅዷል።

ውጤቱን ለመጠባበቅ ለህዳር 3 ቀን 2008 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

በሌላ በኩል መምህር ግርማ ወንድሙ ባለፈው ሳምንት ከተጠረጠሩበት የማታለል ወንጀል ጋር በተያያዘ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ስራ አለኝ በማለት ከጠየቀው 14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ አምስት ቀን ብቻ ነው የፈቀደው።

ፖሊስ ድጋሚ ቀነ ቀጠሮ ለመጠየቅ ካቀረበው ምክንያት መካከል ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች አሉ፤ ከቤት ሽያጭ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪው ከሚኖሩበት ወረዳ የሰነድ ማስረጃ አልቀረበልኝም፤ ቤታቸው ላይ በተደረገው ብርበራ ስምንት ሲም ካርዶች የተገኙ በመሆኑ ሲም ካርዶቹ በማን ስም የወጡ ናቸው? እና በስልኩ ውስጥ የሚገኙ መረጃዎችን ኢትዮ ቴሌኮም አጥርቶ እንዲልክልን ደብዳቤ ፅፈን ውጤቱን እየተጠባበቅን ነው የሚሉት ይገኙበታል።

በዚህም ላይ የተጠርጣሪው ጠበቆች ሰው ታስሮ ሌላ ሰው ለመያዝ በሚል ተጨማሪ ቀን ሊጠየቅ አይገባም፤ ህጉም አይፈቅድም፤ እና ፖሊስ ምርመራውን ቀደም ሲል ያጠናቀቀ በመሆኑ ባለፈው በተሰጠው 7 ቀን የተጠርጣሪውን ቃል ተቀብሎ ክስ መመስረት ሲገባው ደንበኛችን ያለአግባብ እየታሰሩ ነው ብለዋል።

ችሎቱ ከኢትዮ ቴሌኮም የሚመጣውን መረጃ ለመጠባበቅ ከተጠየቀው 14 ቀን 5 ቀን ብቻ ፈቅዷል።

የዚህንም ውጤት ለመጠባበቅ ለጥቅምት 30 2008 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።


በጥላሁን ካሳ


Wednesday, November 4, 2015

የመጽሐፍ ሕግ ይከበር!!!


ልሳን በሚነገርበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሱ “በማኅበር መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር” እያለ (1ኛ ቆሮ 14፡28)፤ ፓስተር ዳዊት ደግሞ ያውም በመንፈስ ተመስጦ ሳይሆን ሰዓቱን እያየ በተናገረው ልሳን ላይ “እጅ ለእጅ ተያያዙ” እና “አንዴ ለሁለት ደቂቃ ሁሉም ሰው በልሳኑ ይጸልይ” በማለት ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ ሁሉም በማልሰማው ልሳን ይጮሁ ጀመር፤ ፓስተር ዳዊት እና መጽሐፍ ቅዱሱ የሚሉት ለየቅል ሆኖብኛል፡፡ ለመሆኑ በማኅበር መካከል ዝም ይበል እያለ የሚያዝዘው ትእዛዝ በእኛ ጉባኤ መቼ ነው የሚከበረው? ? ?
በመጽሐፍ ቅዱስ የሚነገር ልሳን እየተነገረን ከሆነ፤ እስቲ የፓስተር ዳዊትን ልሳን በ1ኛ ቆሮ 14፡27 “በልሳን የሚናገር ቢኖር ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በተራቸው ይናገሩ አንዱም ይተርጉም” ይላልና ትተረጉሙልኝ ዘንድ በትሕትና እጠይቃችኋለሁ ልሳኑ እነሆ፡-


1. አሞላቫንቶስሳክራቶሊያ
2. ሂላሞሪያማሳንቶኮትራቫሎዣንታ
3. ዚንትሮቪዲያሎማንቴስቴኬፕላዶራስ
4. ማዶሎሎስ ሲያማማንዶስሶኮዶጆኖሎሞስ
5. ኢንሞሎዲያናማሳንቶ
6. ኦላሪያማሴንታዲያካላቫሶንታ
7. ማርዶሎሞሲያናታኪቫ
8. ሃሊቮሪያማሳንቶ … ናሚያኖራሳንታ ….
9. ማትራቫዶላማንሳ
10. ሜሮቫንዶሶትራቮላ
11. አሪዞሞሜንቶኮትሬጅሪዮማንዴ
12. ዚልቮንቶቶድጄኔስቫፓሮዳ
13. አጉልቮኖንቴስቴቮዶሞሞንዶ
14. ሳልቬርኖማንቶሴትራዲያቮላ
15. ሀሞራማሺንዶሎሮሪያማንዳ
16. ዚላቮታካሮማንዲያላማሳ
17. አማሎናንቴኤልቬሌንቶስቶትሮቮሎኮዛ
18. አሙላዢቫዚያንዴ
19. ሪቫልዶሎትሮኮሎዞማንዳ
20. ኬልፕሮቫዶስ

መጽሐፍ ቅዱስ “አንዱም ይተርጉም” በሚለው መሠረት፤ ትርጉሙን በቁጥር በቁጥር ለሚተረጉምልኝ፤ አስቀድሜ ስለ ትብብሩ አመሰግናለሁ፡፡

Thursday, October 29, 2015

መምህር ግርማ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄም ወድቅ ተደርጓል።

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ትናንት በቁጥጥር ስር የዋሉት መምህር ግርማ ወንድሙ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

መምህር ግርማ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄም ወድቅ ተደርጓል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የፖሊስ መርማሪ ቡድን ዛሬ ግለሰቡን በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎት አቅርቧቸዋል።

ፖሊስ ግለሰቡ በተጠረጠሩበት የማታለል ወንጀል ቀሪ የምርመራ ስራ ስላሉብኝ ተጨማሪ 14 ቀን ይፈቀድልኝ ብሏል።

ተጠርጣሪው በራሳቸውና በጠበቃቸው በኩል ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ ጊዜ  በመቃወም የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

የፖሊስ የምርመራ ቡድን በበኩሉ እሳቸው ቢለቀቁ ሌሎች ተፈላጊዎችን እና የተለያዩ ሰነዶችን ስለሚያሸሹብን ጥያቄያቸው ውድቅ ይሁን ብሏል።

ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገን ክርክር መርምሮ ፖሊስ አብዛኛውን የምርመራ ስራ ያካሄደ በመሆኑ ለቀሪ የምርመራ ስራዎቹ ይረዳል በማለት ከጠየቀው የ14 ቀን ጊዜ ውስጥ 7 ቀን ብቻ ፈቅዷል።

ውጤቱን ለመጠባበቅም ለጥቅምት 25 2008 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

የወንጀሉ ዝርዝር

ፖሊስ መምህር ግርማ  በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ምክንያት የሆነው ወንጀል የተፈፀመው መስከረም 2006 ዓ.ም ነው ብሏል።

በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ወሰን ግሮሰሪ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩት አቶ በላይነህ ከበደ በመምህር ግርማ የማታለል ወንጀል የተፈጸመባቸው ግለሰብ ናቸው።

እንደ ፖሊስ የምርመራ መዝገብ እኚህ ግለሰብ ከትዳር አጋራቸው ጋር 400 ካሬ ሜትር ላይ ባረፈ መኖሪያ ቤታቸው ይኖሩ ነበር።

እንደ ምርመራ መዝገቡ መምህር ግርማ የግል ተበዳይን እምነት በመጠቀም የምትኖርበትን መኖሪያ ቤት እስከ ጥር 30 2006 ሽጠህ ካልወጣህ አስከሬንህ ይወጣል ይሏቸዋል።

የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደሚለው ልጅ ያልወለዱት ባልና ሚስት ከመሞት መሰንበት በማለት ይህንን ቤት በጣም በዝቅተኛ ዋጋ በ800 ሺህ ብር ይሸጡታል።

ቤቱ በዚህ ዋጋ እንዲሸጥ መምህር ግርማ በራሳቸው ሰዎች አማካኝነት ብዙ ያልተገባ ስራ ሰርተዋል ነው የሚለው የምርመራ መዝገቡ።

ከዚያም መምህር ግርማ በዚህ ብቻ ሳይመለሱ የግል ተበዳዩን ቦሌ አካባቢ በራዕይ ያየሁት ቦታ አለ እዚያ ነው ገዝተህ የምትኖረው ይሏቸውና ሌላ የማታለያ ዘዴ ቀየሱ ይላል ምርመራው።

ቤቱ የተሸጠበትን 800 ሺህ ብር አምጣና እንዲበረክትልህ ልፀልይበት ብለው በመውሰድ በዚያው ውለው አደሩ፤ የግል ተበዳዩም በእርሳቸው ላይ ያላቸው እምነት ባለመጥፋቱ በትዕግስት ስልክ ቢደውሉላቸውም ስልካቸው ዝግ ሆነባቸው፤ ይባስ ብሎ ከሀገር ወጡ ተባለ የሚለውም ተጠቅሷል።

የግል ተበዳይ ሁኔታው ማታለል መሆኑን ስለተረዱ 2007 መጋቢት ወር ገደማ ለፖሊስ ያመለከቱ ሲሆን፥ እርሳቸው ከሄዱበት እስኪመለሱ ፖሊስ የግል ተበዳዩን እና የምስክሮችን ቃል ተቀብሎ ቆይቶ ተጠርጣሪው መምህር ግርማ ወንድሙን ትናንት በቁጥጥር ስር አውሏቸው ነው ዛሬ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው።

ተጠርጣሪው እኔ የተባለውን ሰው ቀይ ይሁን ጥቁር አይቼው አላውቅም፤ ሆን ተብሎ ከጀርባ የተጠነሰሰብኝ ሴራ አለ በማለት ለችሎቱ አስረድተዋል።

ጠበቃቸውም የተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና የሚከለክል አይደለም፤ ፖሊስም የሚጠበቁ ምርመራዎቹን አጠናቋል፤ ደንበኛዬ የዋስትና መብታቸው ይከበርልኝ በማለት ጠይውቋል።

ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጓል።





በጥላሁን ካሳ