Friday, March 21, 2014

የአቶ ግርማ ወንድሙ የማጭበርበር ጥምቀት የተፈቀደ አይደለም!



  

ግርማ ወንድሙ አጠምቃለሁ፤ ሰይጣንም አስወጣለሁ እያለ ማጭበርበርና ገንዘብ መዝረፍ ከጀመረ ሰነባብቷል። ማታለል በሀገሪቱ ህግ ወንጀል ቢሆንም ይህንን አታላይ የሚዳኝ ህግ እስካሁን አልተገኘም።  ከሁሉም የሚያሳዝነው ደግሞ ሊቃነ ጳጳሳቱም ከእነዚህ ዓይነቶች አጭበርባሪዎች ጋር ግንባር ፈጥረው ቤተ ክርስቲያኒቱ እመራበታለሁ ከምትለው የሥልጣነ ክህነት የአሰጣጥ ሂደት በተቃራኒው ግርማ ወንድሙ ለተባለው ነፍሰ በላ ወታደር  የቅስና ማዕርግ ሰጥተውት «ይፍታህ» እያለ ኃጢአት ሲደመሰስ እንደሚውል መዝጊያ የሚያክል መስቀል ጨብጦ እያየን ነው። ከስጋ ለባሽ መካከል ኃጢአትን የሚያስተሰርይ ቢገኝ ኖሮ የክርስቶስ ሰው መሆን ባላስፈለገም ነበር። 
  ዳሩ ግን እንኳን የሌሎችን ኃጢአት ሊያስተሰርይ ይቅርና ከማጭበርበር ዓለም ወጥቶ ራሱን መግዛት ያልቻለው ግርማ ወንድሙ መውጊያ በሚያክል የብረት መስቀል «ይፍታሽ፣ ይፍታህ» እያለ እንዲደበድብ ጳጳሳቱ ቅስና ሰጥተውታል። ጳጳሳቱ ገንዘብና የሚቀበላቸው ካገኙ እንኳን ቅስና ጵጵስናም ከመስጠት አይመለሱም። የትም ሳይማሩ የክብር ዶክተሬት ዲግሪ እንደሚሰጠው ሁሉ «ፈቀደ እግዚእ» ብለው የሰኞ ውዳሴ ማርያምን መዝለቅ ለማይችሉ ሁሉ የክብር የቅስና ማዕርግ ሲሰጥ እያየን ነው።  እስካሁን በአደባባይ የክብር የቅስና ማዕርግ እንደምትሰጥ ከቤተ ክርስቲያኒቱ በኦፊሴል ባንሰማም በተግባር ግን የማይሰራበት የክብር የቅስና ማዕርግ ይዘው ያሉ እንዳሉ እናውቃለን። ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ በዚህ መልኩ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። የሚያገለግሉበት ወይም ያገለገሉበት ደብርና ገዳም ሳይኖር ወይም ለማገልገል የሚያበቃ ሙያ ወይም ትምህርት ሳይኖራቸው ቅስናና ዲቁና አለን ብለው በእጃቸው ትላልቅ መስቀል ጨብጠው መንገድ የሚያጣብቡ ሁሉ ለወደፊቱ መለየት አለባቸው።
 ይህንን የዲቁና፤ የቅስናና ሌሎች ማዕርጋት ልክ የንግድ ፈቃድ እድሳት እንደሚደረገው የእድሳት ዘመን ተደርጎለት ማዕረጉን ከየት እንዳገኘው? የት እንደሚያገለግልበትና ምን እንደተማረ? እየተመረመረ ተገቢ ሆኖ ያልተገኘው ሁሉ እንዳጭበረበረ ተቆጥሮ ወዳቂ ካልተደረገ በየሜዳው «ቀሲስ» የሚባሉ ጩልሌዎችን አደብ ማስገዛት አይቻልም። ከእነዚህም የክብር የቅስና ማዕርግ ተሸካሚ አንዱ አቶ ግርማ ወንድሙ ነው። ሌሎቹም ቢሆኑ ሙያውና እውቀቱ እያላቸው ነገር ግን ሥነ ምግባርና ለተመደቡበት ማዕርግ የሚያበቃ ማንነት የሌላቸው ዲያቆናት፤ ቀሳውስትና መነኮሳት ከዚሁ ጋር ተያይዞ ካልታየ በስተቀር የዝቅጠትና የውርደት መለያ ሆኖ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ውድቀት አስተዋጽኦ ማድረጉ አይካድም። ምዕመናንና ምዕመናት በእንደዚህ ዓይነቶቹ ተቆጣጣሪ አልባ ባለማዕርጋት ስርዓተ አልበኝነት የተነሳ በሀፍረት ተሸማቀው  እንደሚገኙም ይታወቃል።

   ከእነዚህኞቹ አንዱ የሆነው አቶ ግርማ ወንድሙ በስመ ማጥመቅ የሚሊዮን ብሮች ባለቤት መሆኑ ሳያንስ ከዚህ ዓይነቱ ተግባር እንዲላቀቅ ቤተ ክርስቲያኒቱ ብትመክረውም ለመስማት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ( እሱ ይሁን ወዳጆቹ) ማን እንዳስጻፈው ያልታወቀ የማጥመቅ ፈቃድ አውጥተው እንደነበር አይዘነጋም። ( ደብዳቤውን ለማንበብእዚህ ይጫኑ )

  ይሁን እንጂ በአባ ገሪማ ፊርማ ቅዱስ ፓትርያርኩ የማጥመቅ ፈቃድ ሰጥተውታል የተባለበት ደብዳቤ ከቤተ ክህነቱ ደርሶ ኖሮ ሲመረመር የሀሰትና የማጭበርበር ተግባር መሆኑ በመረጋገጡ ቤተ ክህነት ይህንኑ ለማሳወቅ ተገዷል። በዚሁ መሠረት ለአቶ ግርማ ወንድሙ የማጥመቅ ሥራ ምንም ዓይነት ፈቃድ እንዳልተሰጠና ፈቃድ የተሰጠው በማስመሰል የተበተነው ወረቀት የማጭበርበር ውጤት እንጂ የቤተ ክህነቱን የፕሮቶኮል ቁጥር የያዘ እንዳይደለ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገልጿል። በአባ ገሪማ የተጻፈውን ደብዳቤ ለማንበብ  ( እዚህ ላይ ይጫኑ ) 

አቶ ግርማ ድሮም አጥማቂ አልነበረም፤ አሁንም አጥማቂነት እንዳልተፈቀደለት ተረጋግጧል።  ግርማ ወንድሙ ከእጁ በምን ዓይነት ተአምር ሊለያት በማይፈልጋት መቁጠሪያ ሰይጣናዊ አስማት የሚጠቀም አስመሳይ እንጂ አጥማቂ አይደለም። ስለዚህ አፍቃሬ ግርማ ወንድሙ የሆናችሁ ሁሉ እርማችሁን አውጡ።

 ዳሩ በማስመሰል የሚያጠምቀው ግርማ ወንድሙ ይቅርና «እኔ ጥቁሯ ድንግል ማርያም ነኝ» እያለች ስታጭበረብር የነበረችው ሴት እንኳን ብዙ ተከታዮች ማፍራቷን አይተናል፤ ከእሷ አታላይነትም የበለጠ «ጥቁሯ ድንግል ማርያም» እንደሆነች አምነው የሚከተሏት ሰዎች ያስገረመን ጉዳይ ሆኖ አልፏል። ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን እንጂ የወንጌልን ቃል ስለማይመረምር ለእንደዚህ ዓይነት ትንግርቶች ተጋላጭ ነው።  

«በዚያን ጊዜ ማንም እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፤ ወይም ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ»    ማቴ 24፤23-25

Saturday, March 15, 2014

«ቅዱስ ኤልያስ ይዞት የመጣውን መጽሐፍ” ቤተ ክርስቲያን እንድትቀበል ተጠየቀ»

 (ምንጭ፤አዲስ አድማስ)
መጽሐፉ ለአቡነ ማትያስና ለጠ/ሚ ኃይለማርያም እንዲደርሳቸው ተደርጓል
ደብዳቤው ለእስራኤሉ ጠ/ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታናሁ እና ለተመድ ተልኳል

       ከተፃፈ ከ2 ሺህ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል የተባለውንና ስለ ቅዱስ ኤልያስ መምጣት ምስጢር የሚተነትነውን መጽሐፍ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተቀብላ ወደተለያዩ ቋንቋዎች በማስተርጎም ምዕመናኖችን እንድታስተምር፣ “ማህበረ ሥላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ” ለቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በጻፈው ደብዳቤ ጠየቀ፡፡
ማህበሩ፤የመጽሐፉን ኮፒዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ እና ለብፁዕ አቡነ ማትያስ  ህዝቡን እንዲያስተምሩበት ከሚያሳስብ ደብዳቤ ጋር መላኩን አስታውቋል፡፡
አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን አባል የሆነችበት ማህበረ ሥላሴ፤“ቅድስት ቤተ-ክርስቲያን ለሁለት ሺህ ዘመን ስትጠብቀው የቆየችውን ምስጢራዊ መጽሐፍ በአደራ የመረከብና ለዓለም ሁሉ የማሳወቅ ፅኑ ኃላፊነትን ይመለከታል” በሚል ርዕስ ለፓትርያርኩ፣ በግልባጭ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲሁም ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትናሁ እና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት በፃፈው  ደብዳቤ “ማህፈድ ብርህት ዘዲዮስቆሮስ አንበሳ” በሚል ርዕስ በግዕዝ ቋንቋ የተፃፈውን መጽሀፍ፣ የቤተ-ክርስቲያኗ ሊቃውንት ተቀብለው ምእመናኑን ስለ ቅዱስ ኤልያስ እና ትክክለኛይቱ ሰንበት እንዲያስተምሩበት አሳስቧል፡፡
ደብዳቤው ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የተላከው ኢትዮጵያና እስራኤል በመንፈሣዊ አሰራር አንድ ስለሚሆኑበት ሁኔታ ለማመልከት ነው ያሉት የማህበሩ አመራሮች፤ለተባበሩት መንግሥታት የተላከውም መልእክቱ ለዓለም ሁሉ እንዲዳረስ ስለሚፈለግ ነው ብለዋል፡፡
ከ2 ሺህ ዓመታት በፊት እንደተፃፈ የሚነገርለት መጽሐፉ፤ ስለ ቀዳሚት ሰንበት ምንነትና ዘለዓለማዊነት በግልፅ እንደሚያብራራ እንዲሁም የኢትዮጵያና የእስራኤልን አንድነትና ትንሳኤ ምስጢር ተንትኖ እንደሚያስረዳ ተጠቁሟል፡፡
ማህበሩ በላከው መልዕክት፣ ቅዱስ ኤልያስ ከብሄረ ህያዋን ይዞት የመጣውን መጽሀፍ፣ የቤተ-ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት እንዲመረምሩት፣ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲተረጎምና እንዲታተም፣ ምዕመናንም እንዲያነቡት የማድረግ ግዴታ ፓትርያርኩ እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ “ይህ ሳይሆን በእንቢተኝነትና በቸልታ ለዘመናት በተስፋ የተጠበቀውን ይህን መጽሀፍ እንዳይቀርብ ቢያደርጉ፣ ከብሄረ ህያዋን የመጣው ቀናኢ ነቢይ ዓለምን ሁሉ እየገሰፀ ባለበት ኃያል፣ ስልጣኑ ፅኑ ፈራጅነቱና ቁጣው የሚፈርድ መሆኑን አረጋግጠን እንነግርዎታለን” ብሏል፡፡ “ለቤተ-ክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ እና ካህናት ጥፋትና የመጨረሻው ውድቀት ነው” ሲልም ለመፅሃፉ ትኩረት እንዲሰጥ ማህበሩ  አበክሮ አሳስቧል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የፓትርያርኩን ጽ/ቤት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጽ/ቤት በስልክ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

Wednesday, March 12, 2014

የደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል የሰንበቴ ማኅበራት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተወከለውን ኦዲተር የኦዲት መርኃ ግብር በመቃወም ህገወጥ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ

በአዲስ አበባ የደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል የሰንበቴ ማኅበራት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተወከለውን ኦዲተር የኦዲት መርኃ ግብር በመቃወም ህገወጥ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ፡፡ በተለያየ መጥፎ ሥነ ምግባርና ድርጊት ከካቴድራሉ ሰንበት ትምህርት ቤት የተባረሩ ሁለት አባላትን ይዘው በካቴድራሉ ሁለተኛ ሰንበት ትምህርት ቤት ለማቋቋም ከጉርድ ሾላ እና አካባቢ የሰበሰቧቸው ወጣቶች ስለ ሰንበት ትምህርት ቤት አመሰራረት ግንዛቤ የሌላቸው በመሆናቸው የአዲሱ ሰንበት ትምህርት ቤት ምስረታ አልተሳካም፡፡  ቀደም ሲል የሰንበቴ ማኅበራቱ ከሀገረ ስብከቱም ሆነ ከካቴድራሉ አስተዳደር እውቅና ውጪ የሚሸጡትንና በወር እስከ 300.000.00 (ሦስት መቶ ሺህ ብር) ገቢ የሚያገኙበት የቀብር ፉካ ሽያጭ እና የአዳራሽ ኪራይ ንግድ ወይ ለቤተክህነቱ ፈሰስ እንዲያደርጉ አልያም ንግድ ፈቃድ አውጥተው ለመንግሥት ግብር እንዲከፍሉ በሀገረ ስብከቱ የቀረበውን ሐሳብ አልተቀበሉትም፡፡ እናም በመስከረም ወር 2006 ዓ.ም ከጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ፤ የቅዱ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በተገኙበት ተመርጦ ሥራ የጀመረውን ሰበካ ጉባዔ አይመራንም፤ እነርሱ ባቀረቡት ጥቆማ መነሻነት ከመንግሥት እና ከገለልተኛ አካላት የተዋቀረው የኦዲት  ኮሚቴ እኛን (የሰንበቴ ማኅበራቱን እና እንደ አቶ ወልዴ የሺጥላ አይነት በሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ ገንዘብ ጉድለት የተገኘባቸውንና በቤተክርስቲያኑ ግቢ በቤተልሔሙ ጎን 26 ፉካ በመስራት መናፍቅ ልጆቻቸውን ወራሽ በማድረግ ሕገ ወጥ ሰነድ ያዘጋጁትን) ኦዲት ሊያደርጉ አይገባም በሚል ነጻና ገለልተኛ ቤተክርስቲያን እንመሰርታለን የሚል ፖስተር በመያዝ  እሑድ የካቲት 2 ቀን ጠዋት በቅዳሴ ሰዓት የቅዳሴ ሥነ ሥርዓቱን ለማስተጓጎል ሞክረዋል፡፡
በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የሴት ሰባኪ የሆነችውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕጋዊ ባሏን ጥላ   ወልዴ የሺጥላ የተባለውን የቀድሞ የህንጻ ኮሚቴ ሊቀ መንበር የወሸመችው እራሷን የዘመኑ የወንጌል አብሳሪ በመንፈስ ቅዱስ የተቀባሁ ጳውሎሳዊት ነኝ በማለት ጸሎተ ፍትሐት አያስፈልግም እኔ በፍትሀቱ ፋንታ ጸሎት አድጋለሁ አስተምራለሁ በማለት ምንፍቅና የምታስፋፋው  ቅድስት አሳልፍ ወደ ቤተክርስቲያኑ ድንጋይ እንዲወረውሩ ተሰብሳቢዎቹን ስታግባባ ነበር፡፡
ከካቴድራሉ ሰንበት ትምህርት ቤት ሴት አባላትን በመተናኮልና ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ በሕግ ተከሶ የተቀጣውና ከሰንበት ትምህርት ቤት በዚህ ቅሌት የተባረረው ሰለሞን አጥሌ የተባለው የታክሲ ሾፌርና የሰንበት ትምህርት ቤቱን ገንዘብ በተለያየ ወቅት በመውሰድ በሌብነት ወንጀል ተከሶ ከሰንበት ትምህርት ቤት የተባረረውና ዲቃላ ልጁን ደብቆ ሁለተኛ ሚስት በተክሊል ያገባው የሰለሞን አጥሌ ወያላ የሆነው ሲሳይ አፈወርቅ የተባሉት ሁለት ግለሰቦች መናፍቃንን በማሰባሰብ ሁለተኛ ሰንበት ትምህርት ቤት ለማቋቋም ያደረጉት እንቅስቃሴ አልተሳካላቸውም፡፡
ከዚህ ቀደም በዋነኛነት የሰንበቴ ማኅበራቱንና በመንግሥት ላይ ያኮረፉትን እንደነ ታዋቂውና ጨካኙ የደርግ የምስራቅ  ጎጃም ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪና የደርጉ አባል አንሙት ክንዴን አይነት ሰዎችን በማሰባሰብ የደርግ ሥርዓተ ማኅበርን በቤተክርስቲያን ለመመስረት የሚታገለው የደርግ የስለላ ሹም የመቶ አለቃ አባቡ ታከለው በአጣዳፊ ህመም ከሰልፉ ላይ ወጥቶ ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን ህመሙ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ እለቱን ኦፕራሲዎን መደረጉንና እስካሁን ከሰመመን እንዳልነቃ ታውቋል፡፡
የካቴድራሉ አስተዳደር በሰንበቴ ማኅበር ስም ተደራጅተው የሚነግዱትን አንዳንድ የደርግ ጡረተኞችና የሰንበቴ አላማ ጠላ ማንቃረርና ቆሎ ማሸርደም የሚመስላቸው ሥራ ፈት አባወራዎችንና የሚገስጻቸው ያጡ ባሎቻቸው የዘነጓዋቸውን እንደነ ቅድስት አይነት መናፍቃንን በቅጡ በመቃወሙና በፍርድ ቤት በተወሰነ ቤተክርስቲያኒቱ  ባወጣችው ሕግ ሕገወጥ ንግድ እና የቦታ ወረራ በመቃወሙ በመረጃ ባልተረጋገጠ ሙስና እና ስም ማጥፋት ሆ ብለን በመጮህ  ከሰን እናስወግዳለን ከሚመጣውም ጋር በመደራደር የፉካ ንግዳችንን እንቀጥላለን በማለት  ለሀገረ ስብከቱ ቅሬታቸውን በሕጋዊ ሽፋን ቢያቀርቡም ሀገረ ስብከቱ በቦታው ያለውን ችግር በዘላቂ ሁኔታ ለመፍታት ከመንግሥትና ከገለልተኛ አካላት  የተመደበው አጣሪ ግን በተጨባጭ በደረሰው መረጃ  እና በተለያዩ ጊዜያት በሰንበቴ ማኅበራቱ በቤተክርስቲኗ የድንጋይ  መአድን ሽያጭ  ባገኙት ገንዘብ በገዟቸው የቢራ አክስዮኖች ባለቤትነት ጉዳይ እንዲሁም እነ ወልዴ የሺጥላ የህንጻ ኮሚቴ ሊቀመንበር መሆናቸውን ሽፋን በማድረግ በሌሎች አብበያተክርስቲያናት ባልተለመደ መልኩ በቤተክርስቲያኗ ግቢ መኖሪያ ቤት በመገንባት እና ለግላቸው 26 ፉካ በመገንባት ለፈጸሙት ምዝበራ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ኦዲት ለማድረግ በማሰብ ያዘጋጀውን የጊዜ አጠቃቀም መመሪያ በመቃወም ሰልፉን አደራጅተዋል፡፡
 ቁጥራቸው 60 የሚደርሱት እነዚሁ ሰልፈኞች ከያዟቸው መፈክሮች መካከል መንግሥትን የሚተቹ እና አመጹን በማስፋፋት ልክ በእስልምና እምነት በመስኪዶች አካባቢ እንዳለው አይነት ውጥረት ለመፍጠር ቢያስቡም ፖሊስ ደርሶ ሰልፉ እንዲበተን አድርጓል፡፡ በቅርቡ ከአሜሪካ የመጣውና የደህንነት አባል ነኝ በማለት አመጹን የሚያስተባብረው አለማየሁ ከልል  ክሰ ቢመጣ አዘጋላችኋለሁ በማለት ቃል እንደገባላቸው የሰንበቴ ማኅበራቱ አመራሮች አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉት ዋናዎቹ ግለሰቦች የተለያየ ችግር ያለባቸው ሲሆኑ አንዳንዶቹ በአጫሽነት ፤ ሰካራምነት ፤ በቃሚነት የሚታወቁ እና በአካባቢ ማኅበረሰብ የእንጨት ሽበት ተብለው የተናቁ ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ ይህን አጋጣሚ እንደ መልካም የቆጠሩት አንዳድ ፖለቲካ ኃይሎች ሰልፉን ለማጠናከርና ወደ ውጪ በመውጣት ህዝብን ቀልብ ለመሳብ ቢያስቡም ፖሊስ ግን ይህንን ሊፈቅድ አልቻለም፡፡ ከትግራይ የተመረጠ ፓትርያርክ ቤተክርስቲያኗን ሊመራ አይችልም መንግሥት እጁን ከቤተክርስቲያናችን ላይ ያንሳ ትግሬ ተወላጅ ሰራተኞች ይውጡ በማለት በዋናነት መፈክር ሲያሰሙ የዋሉት አንሙት ክንዴ፤ አስማረ ዋሴ ፤ ባዬ ባዘዘው፤ወልሴ የሺጥላ፤ አበበ ደስታ ፤ መልአከ ኃይሌ ፤ ታደሰ  ፤ ቅድስት አሳልፍ፤ ደሳለኝ ፋንታቢል፤ ወልደኢየሱስ በሻህ ፤ሙሉ በለጠ ሲሆኑ ከወጣቶቹ ደግሞ ሴሰኛው ታክሲ ሾፌር  ሰለሞን አጥሌ እና ሌባው ሲሳይ አፈወርቅ ሲሆኑ እነዚህ የግል ጥቅም ያሳወራቸውና እምነትና ፖለቲካ የተቀላቀለባቸው ግለሰቦች በፖሊስ ክስ እንደተመሰረተባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሰአሊተ ምህረት ያለው የሰንበቴ አካሄድ ገና ከጅምሩ በ34ኛው አጠቃላይ መንፈሳዊ ሰበበካ ጉባዔ ታላቅ ተቃውሞ የገጠምውና ሲኖዶሱ እልባት እንዲሰጠው በተሰብሳቢዎቹ አቋም የተያዘበትቤተክርስቲያን የምትመዘበርበት መንገድ ነው፡፡ የሰንበቴ ማኅበራቱ ወደ እድርነትና እክስዮን ማኅበርነት በመለወጣቸው እና ከቀብር ፉካና ከአዳራሽ ኪራይ ያገኙትን ገቢ የቢራ አክስዮኖችን በመግዛት ከመንፈሳዊ ተግባት ውጪ የሚያውሉት ሲሆን ለረፈደበት የፖለቲካ ዓላማ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያንቀሳቅሱ ማወቅ ተችሏል፡፡ የዚህ ድርጊት ዋነኛ መሪ ወልዴ የሺጥላ በኢትዮ ቴሌኮም ሲሰራ በጽዳት ሰራተኞች ላይ በፈጸመው የወሲብ ትንኮሳ በአስተዳደር ተከሶ ከቅርንጫፍሥ አስኪጅነት ወደ ሽያጭ ሰራተኛነት የወረደ ግለሰብ መሆኑ ስለርሱ የሚያውቁት ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡
በካቴድራሉ ጉብኝት ያደረጉት ቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁአን ሊቃነጳጳሳት በሰንበቴ ማኅበራ የተወረረውንና ለብዝኃኑ ጥቅም መስጠት ያለበትን ቦታ እና ግንባታ ተመልክተው ማዘናቸው ታውቋል፡፡ የደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ሰፊ የልማት ቦታና በሰንበቴ የተወረረ የቀብር ስፍራ እንዲሁም በሰንበቴ ማኅበራ ቁጥጥር ሥር የሆነ በብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመት የድንጋይ ማእድን ሐብት እና ከ100.000 በላይ አማንያን ያሉበት ሲሆን በሰንበቴ የጥቅም ሰንሰለት የተደራጁ ከ60 የማይበልጡ ግለሰቦች ምክንያት ሰላሙን አጥቶ የቆየ ደብር ነው፡፡

Monday, March 10, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን የፓትርያርኩን እጅ የመጠምዘዝ፤ እምቢ ካሉም የማስወገድ ትግሉን አጠናክሮ ቀጥሏል!! (ከማን ጋር ሊሰሩ ነው? » አባ ኤልሳዕ


የአሀዳዊ መዋቅር ምንጭ በሆነው ሲኖዶስ የምትተዳደር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን ምኗ ነው? 
በአንድ ወቅት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ «በመንግሥት ሌቦች እጃችን ታስሯል» ማለታቸው አይዘነጋም። ከትንሹ በቀቀን ካድሬ አንስቶ እስከ ትልቁ ዓሳ ነባሪ/አንበሪ/ ሹመኛ ድረስ የመዋጥ፤ የመሰልቀጥ ተግባሩን ተመልክተው «የመንግሥት ሌባ እጃችንን አስሯል» ማለታቸው ይህንን ሁሉ በአንዴ ለማስቆም አለመቻላቸውን መግለጻቸው ብቻ ሳይሆን ከስፋቱ አንጻር ለማስቆም መሞከር ውጤቱ አደገኛ ሊሆን መቻሉን ለማመልከት« እጃችን ታስሯል» በማለት የችግሩን ስር መስደድ በአጭር ዐረፍተ ነገር ለመግለጽ ሞክረዋል። እዚያ አደገኛ ደረጃ ላይ የተደረሰው ግን በአንድ ጀምበር ሳይሆን ቀስ በቀስ አንዱ አንዱን እየዋጠና እየፋፋ እንደመሆኑ መጠን እጅ ከመታሰሩ በፊት አስቀድሞ ትንሽ በትንሹ እርምጃ ቢወሰድ ኖሮ አስጊነቱ ያን ያህል ባላሳሰበ ነበር።  ስርቆት ምንጊዜም ከክፉ ሰዎች ልቡና በሚመነጭ ሃሳብ የሚፈጸም ተግባር ነው። ክፉ ሰዎች ደግሞ ሰውን ከመግደል ወደኋላ አይመለሱም። እግዚአብሔርን ማወቅ ከሰዎች ኅሊና ውስጥ ሲጠፋ ጭካኔ ይስፋፋል። እርግማን፤ ግዳይ፣ ስርቆት፤ ደም ማፍሰስ ይበዛል።
በአንድ ወቅት የእስራኤል ልጆች ኃጢአት በመብዛቱና የካህናቱ ርኩሰት መጠን ከማጣቱ የተነሳ እግዚአብሔር አዝኖ የሥራቸውን ዋጋ ይቀበሉ ዘንድ ጥፋት እንደተዘጋጀባቸው መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል።( ሆሴዕ ምዕ 4 እና 5) ሌብነትን መዋጋት ህግን እንደማስከበር ብቻ ሳይሆን መታየት ያለበት ደም ለማፍሰስ የማይመለሱ ሰዎችን ከኅብረተሰቡ ውስጥ እንደማውጣት ይቆጠራል።
እንደዚሁ ሁሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፓትርያርኩ ጀምሮ እስከ አጥቢያው አገልጋይ ካህን ድረስ እጃቸውን ወደኋላ አስሮ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም እየነገደ የፈረጠመውና በመዋቅሩ የዓሳ ነባሪ ያህል የገዘፈው ማኅበረ ቅዱሳን መሠረታዊ ጥቅሙን ለማስከበር ሲል ብቻ ከዚህ በፊት ለፓትርያርኩ ይሰጥ የነበረውን የምስጋና ካባ አውልቆ እጃቸውን ወደመጠምዘዝ ተግባር መሸጋገሩን እየተመለከትን እንገኛለን። የዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት በጥቅሙ መስመር ላይ የሚቆም ማንም ሰው የጥቅሙ ጠላት በመሆኑ አስቀድሞ እጁን በመጠምዘዝ ወደቀድሞ አስተሳሰቡ ለመመለስ በየትኛውም መልኩ መታገል፤ ካልተቻለ ደግሞ ከቆመበት የጥቅሙ መስመር ላይ ማጥፋትና ማስወገድ የጥቅመኛ መዳረሻ ግቡ ነው። ምን ጊዜም በማግበስበስ የበለጸጉ ሰዎች ጥቅማቸውን የማያስጠብቀውን አመራር ለማስወገድ እረፍት የሌላቸው መሆኑ ታሪክ ያስተምረናል። ሰሞኑን  የማኅበረ ቅዱሳንና የተባባሪ ጳጳሳቱ ጩኸት አቶ መለስ እንዳሉት የፓትርያርኩን እጅ የመጠምዘዝና ወደኋላ በማሰር ወደቀድሞ የማኅበሩን ጥቅም የማስከበር መስመር የመመለስ ትግል ተጠናክሮ መቀጠሉን እያየን ሲሆን ችግሩ በዚህ የማይፈታ ከሆነና ከቀጠለ ፓትርያርኩን የማስወገድ እርምጃ እንደሚከተል ሳይታለም የተፈታ ነው። እንዴት ይፈጸማል? የሚለውን ወደፊት የምናየው ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ግን ክፉ ሰዎች / ክፉ መሪዎች/ ክፉ ሀገራት/ ወዘተ ምን ጊዜም የማይስማማቸውን ከመግደል እንደማይመለሱ በእርግጠኝነት ልንናገር እንችላለን።
«ክፉ ካላደረጉ አይተኙምና፤ ካላሰናከሉም እንቅልፋቸው ይወገዳልና» ምሳሌ 4፤16
በዚሁ አጋጣሚ የምናሳስበው ነገር እውነተኛን የሚጠብቅ እግዚአብሔር እንደማያንቀላፋ ቢታወቅም  በተሰጠን ልቡና ራሳቸንን እንዳንጠብቅ የሚያዘናጋን ባለመሆኑ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በሚበሉት፤ በሚጠጡትና በሚለብሱት ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ማስገንዘብ እንወዳለን።  እውነት ነው! «ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ» ማቴ 10፤28 በማለት እንደተናገረው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ብቻ በሕይወታችን በማስቀደም ማገልገል እንደሚገባ እንጂ የሚያሳስበን በስጋ መሞት እንደማያስፈራን ይታወቃል።
ፓትርያርክ ማትያስ ከማኅበረ ቅዱሳን እስራት ነጻ ሰው መሆናቸውን መግለጽ በጀመሩ ማግስት፤ እስራታቸውን አምነው እንዲቀበሉ የማኅበሩ እስረኝነታቸውን ያረጋገጡ ጳጳሳት ቢቻል በምክር ሽፋን እጃቸውን እንዲሰጡ አለሳልሰው በማባበል፤ ፓትርያርኩ የአቋም ሰው በመሆን ከቀጠሉ ግፋ ሲል ደግሞ ወደፊት በማስፈራራት፤ አድማ በመምታትና በስመ ድምጽ ብልጫ የፓትርያርክነቱን ሥልጣን በመቀማት እግር ተወርች የማሰሩ ዘመቻ በእርግጥ ይቀጥላል። አባ ጳውሎስንም እንዲሁ ነበር ያዋከቡት።
ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ እንጂ የማኅበረ ቅዱሳን ፓትርያርክ የመሆን ግዴታና ውል የለባቸውም። እኛም እንደተለመደው የምንጠይቀው ነገር ቢኖር አንድና አንድ ብቻ ነው።
የአሀዳዊ መዋቅር ምንጭ በሆነው ሲኖዶስ የምትተዳደር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን ምኗ ነው? የሲኖዶስ አባላት ጳጳሳቱ የሚያገለግሉት ለማኅበረ ቅዱሳን ወይስ ለቤተ ክርስቲያን?

Saturday, March 8, 2014

«እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል» ዮሐ 8፤32


ሐዋርያቱ ጌታችንን ከጠየቁት አስደናቂ ጥያቄዎች አንዱ «የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?» በማለት ያቀረቡለት ጥያቄ ነው። ከክርስቶስ ዳግም መምጣት በፊት የሚሆነውን የዓለሙን ነገር ከተናገራቸው መካከል አንዱ ደግሞ የመንግሥት ወንጌል በዓለሙ ሁሉ እንደሚሰበክ የተናገረው ይገኝበታል። ማቴ 24፤14
መንግሥተ ሰማያት የሚያስገባውና ዳኝነት የሚያሰጠው የሕግ መጽሐፍ ወንጌል በመሆኑ ማንም ቢሆን ይህንን ቃል እንዲሰማ በመጨረሻውና በክርስቶስ መምጫው መዳረሻ ላይ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ እንደሚሰበክ የተናገረው ምልክት እነሆ በዓለሙ ሁሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ እየተሰበከ መገኘቱ እውነት ነው። በንግግር፤ በጽሑፍ፤ በምስል፤ በድምጽ፤ በምልክትና የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ወንጌል እየተሰበከ ይገኛል። በእርግጥ ወንጌልን የሚሰብኩ ሁሉ እውነተኞች፤ እንዲሁም ወንጌል የሰማ ሁሉ ይድናል ማለት አይደለም። የተጠሩ ብዙዎች፤ የተመረጡት ግን ጥቂቶች በመሆናቸው ለመዳንም ይሁን በፍርድ ለመውደቅ ድርሻው የእያንዳንዱ ሕይወት ከወንጌል ቃል መስማማቱ ነው። ወንጌል ሕጋችን ነው የሚሉ እነዚህ በሁለት ይመደባሉ።
1/ ወንጌል የሚናገረውን የእውነት ቃል አምነው እንደቃሉ የሚኖሩ
2/ ወንጌል የሚናገረውን የእውነት ቃል አምነው እንደራሳቸው የሚኖሩ ናቸው።
ወንጌል የሚናገረውን የእውነት ቃል አምነው እንደቃሉ የሚኖሩ በመልካም መሬት ላይ እንደተዘራ ዘር የወንጌልን ቃል አፍርተው ለብዙዎች መዳንና ወደእውነት መድረስ መንገድ የሚሆኑ ናቸው። ለዚህ አብነት ሆኖ የሚጠቀስ የመልካም መሬት ዘር ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። ሐዋርያው መንፈሳዊ ትግሉ ምንጊዜም ሰዎች የክርስቶስ ብቻ ሆነው መልካም ፍሬ ያፈሩ ዘንድ ይተጋ ነበር።
«እንዲሁ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ ደግሞ በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ ተገድላችኋል፤ ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ፥ እናንተ ለሌላው፥ ከሙታን ለተነሣው፥ ለእርሱ ትሆኑ ዘንድ» ሮሜ 7፤4
እኛ በወንጌል አምነን በቃሉም የምንኖር ለሕግ ሞተን፤ ለክርስቶስ የሆንን የሌላ የማንም ፍሬ አይደለንም። የተክልዬም አይደለንም። የአቦዬም አይደለንም። የሚካኤልም አይደለንም። የማርያምም አይደለንም። የማንም ጻድቅ አይደለንም። የየትኛውም ቅዱሳን አይደለንም ማለት ቅዱሳንን እንደማቃለል አድርገው የሚመለከቱ አሉ። ከክርስቶስ በቀር የሞተልን፤ ከሞት የታደገንና ያዳነን ማንም የለም ማለት ነው። ጳውሎስ እንደተናገረው «ከሙታን ለተነሳው ለእሱ ትሆኑ ዘንድ» እንዳለው የእግዚአብሔር ብቻ እንደሆንን ይነግረናል። ወንጌል በክርስቶስ ብቻ ድነን የክርስቶስ እንሆን ዘንድ ሲያዘን ለቅዱሳን ያለንን ክብር የገለጽን እየመሰለን በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በመረጃ መረቦች ላይ «እኔ የማርያም ነኝ፤ እናንተስ? እኔ የተክልዬ ነኝ፤ እናንተስ? ያለድንግል ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም! የሚል ጥሪ ወንጌልን አመንን ከሚሉ ነገር ግን የወንጌል ቃል ተቃራኒ ድምጾች ይስተጋባሉ።  እውነቱን ስንነጋገር ዓለም የዳነው መቼ ነው? ዓለሙን ሁሉ ያዳነው ማነው? እግዚአብሔር አብ ዓለሙን ለማዳን አንድያ ልጁን ሲልክ የማን አማላጅነት እረፍት ስለነሳው ነው?
በጣም አሳዛኝና ወንጌልን የሚጻረር ድምጽ እየሰማን እንገኛለን። ቅዱሳንን በማክበር ሽፋንና ቅዱሳን በመቀበል ከለላ «ዓለም ያለቅዱሳኑ አማላጅነት አይድንም» ማለት ፈጽሞ ክህደት ነው ።  የእግዚአብሔር ፍርዱን ማን ሊመረምር ይችላል? ጳውሎስ እንዳለው።
«የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም።የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው?ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው?ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን» ሮሜ 11፤33-36
ወንጌልን አምነው ነገር ግን  እንደራሳቸው ቃል የሚኖሩት ደግሞ የራሳቸው የሆነ ፍሬ አላቸው። ፍሬአቸው ከወንጌል ቃል ጋር ፈጽሞ አይስማማም።  ለአብነትም ይህንን እውነት ከታችኛው ምስለ ድምጽ በማስረጃ ያመሳክሩ!!







Monday, March 3, 2014

ግብፅ ስትደነፋ መለስ ዜናዊ ናፈቁኝ!! When I hear Egypt's Rhetoric over Nile, I miss Meles Zenawi


ፎቶ፦ ናሳ ሳተላይት    
  ጽሁፍ በአማኑኤል ዊንታ
በሌሊት የተነሱ የግብፅ የሳተላይት ፎቶዎችን በአትኩሮት ብታዩ ፍንትው ያለና የማያወላዳ እውነትን ይጋፈጣሉ ከታላቁ የአስዋን ግድብ በካይሮ አድርጐ እስከ ሜዲትራንያን ባህር ድረስ 84 ሚሊዮን የሚጠጋው አጠቃላይ የግብፅ ህዝብ በጣም በሚገርም ሁኔታ የአባይን ዳር ለዳር ተጠግቶ ይኖራል፡፡ ይህም ግብፅን በአለም ላይ ካሉ ሀገራት ሁሉ እራሷን ሙሉ በሙሉ ለጥፋት አደጋ ያመቻቸች ብቸኛ ሐገር ያሰኛታል፡፡
ታላቁ የአስዋን ግድብ ያቋተው ውሃ የናስር ሐይቅ የሚባለውን ሰው ሰራሽ ሐይቅ ለመፍጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ የናስር ሰው ሰራሽ ሐይቅ 547 ኪ.ሜ ርዝመት 35 ኪ.ሜ ስፋትና 110 ሜ ከፍታ አለው፡፡ ይህ የተፈጥሮ ሐይቅ ቢመታና ውሃው ቢፈስ በሰዓታት ውስጥ ግብፅ ያለምንም ጥርጥር ከጫፍ እስከ ጫፍ ተጥለቅልቃ ትጠፋለች ይህ ሳይንሳዊ ሐቅ ነው፡፡

በቅርቡ የካይሮና የአዲስ አበባ መሪዎች የተለያዩ የተካረሩ ቃላቶችን ሲወራወሩ አይተናል ሰምተናል፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ውስጤን ቆፍጠን! በሸቅ! ነደድ! የሚያደርግ ነገር ወረረኝ፡፡ አይ ወይኔ ይሄኔ ነበር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ በኖሩልን ብዬ  የተመኘሁት በደንብ አርገው ግብፅን ያቀምሱልኝ ነበራ፡፡ አሐ እሳቸው እንዲሁ ነብሳቸውን ይማርና እንኳን የግብፅን የአሜሪካና የአውሮፓ ድንፋታንም ከቁብ አይቆጥሩት እኔ በግሌ የእሳቸው ፓርቲ አባል አይደለሁም ፓለቲካም አልወድም አባቴ ይሙት! ጀግና ናቸው እረ በጣም አዋቂም ናቸው፡፡ ናፈቁኝ ከምር ናፈቁኝ፡፡ ምን ዋጋ አለው “የማንም ልቅምቅም የሰው ልክ አያውቅም!” አለ ያገሬ ሰው፡፡ ግብፆች ደነፋብን የግብፅ ኘሬዝዳንት ሙሐመድ ሙሪሲ ለህዝባቸው የሚከተለውን ድስኩር አሰሙ፡፡
“በእውነቱ እኔ ጦርነት ይጀመር እያልኩ አይደለም ግን በእርግጠኝነት ቃል እገባላችኋለው የግብፅ የውሃ ፍላጐት በማንም በምንም አደጋ ላይ አይወድቅም! አሉ ቀጠሉናም
“የግብፅ የውሃ ፍላጐትና ደህንነት መቸም ቢሆን ጥያቄ ውስጥ አይገባም በማንም አይሞከርም እንደ ግብፅ ኘሬዝዳንትነቴ እማረጋግጥላችሁ ነገር ቢኖር ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው ይተገበራሉም!” አሉ
ከዛም ቀጠሉና ተረት ተረት የሚመስለውን ግን እርር ድብን ያረገኝን ቀጣዮቹን ሁለት ንግግሮች ቀጠሉ “ግብፅ የአባይ ስጦታ ናት ካልን አባይም የግብፅ ስጦታ ነው!” በማለት ከድሮ ጀምሮ ሲባል የነበረውን አባባል በቴሌቪዥን ሕዝባቸውን ሆ አስባሉበት ቀጠሉናም ደነፉ፡፡
“የግብፃውያን ሕይወት ከአባይ ጋር ብቻ የተያያዘ ነው…. እንደ አንድ ታላቅ ህዝብ ደግሞ አንዲት ጠብታ ውሃ ከአባይ ላይ ሳትመጣ ብትቀር አማራጫችን አንድና አንድ ነው ደማችን ይፈሳል!” አሉና ፈገግ ጀነን ደንደን አሉ፡፡
እኔም እርር ድብን! ቆጣ! በስጨት! አልኩና ለማን ልተንፍሰው? ኮከቤ ደግሞ ታውረስ በሬው ነውና ለመዋጋትም፣ ይለይልን ኑ ውጡ! ለማለትም አማረኝ ግን አንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ መሆኔ ሁሉንም አገደኝ ግን ከምር አንድ ግብፃዊ መንገድ ዳር ላይ ባገኝ ያን ቀን በስሱ በቴስታ ነበር አፍንጫውን ብየ ደም እያሉ ኘሬዝዳንት ሙርሲ የደነፉበትን ደም የማየው በእውነት ምን ችግር አለው በስሱ አንድ ቴስታ ባቀምሰው? ምንም፡፡
ኘሬዝዳንት ሙርሲም ሲያጠቃልሉ “ግብፅ ሁሉንም የአባይ ተፋሰስ ሐገራት ኢትዮጵያንም ጨምሮ በወንዙ ላይ ለሚሰሩት የልማት ኘሮጀክቶች ተቃውሞ የላትም፡፡ ነገር ግን የልማት ኘሮጀክቶች የግብፅን ህጋዊም ሆነ ታሪካዊ መብቶች የሚነኩም የሚያስተጓጉሉም መሆን የለባቸውም፡፡” አሉና ፖለቲካቸውን ቦተለኩ፡፡
የግብፅ የተለያዩ ፖለቲከኞችም የሙርሲን አባባል እያነሱ እያወደሱ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብቅ እያሉ እንዳውም ታላቁን የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ከፍ ሳይል ባጭር እንቅጨው የጦር እርምጃ እንውሰድበት እያሉ ቀባጠሩ፡፡
ታዲያ መለስ ዜናዊ ቢናፍቁኝ ትፈርዱብኛላችሁ? አሃ ሌሎችንማ አየናቸው እኛ ላይ ሲሏችሁ ነው እንጂ የምትደነፉት ጠላት ሲመጣማ ጭጭ ምጭጭ፡፡ ባይሆን በኢቲቪ ወጣ ብላችሁ “ግብፅ ብትደነፋም በኩርኩም ነው የምንላት!” ምናምን እያላችሁ አታፅናኑንም? ድንቄም ፖለቲከኛ! እኔ በእውነት በጣም ተሰምቶኛል ወይ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ፖለቲከኞቻችን መድረሱን ለጀግኖች ለመከላከያ ሰራዊታችን ለቀቅ አድርጉላቸውና በሚዲያችን ዛቻና ድንፋታ እንስማበትና ወንዱ! አንበሳው! እንባባል፡
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ይህንን ሁሉ ችግር የፈጠረው የእኛ የፖለቲከኞች ችግርና ጥበብ ማነስ ነው ግድቡ የኢህአዴግ ብቻ ይመስል ለግንቦት 20 በአል አከባበር ታላቅ ድምቀት ብላችሁ የልደት ኬክ ይመስል አባይን ቦታውን አስቀይሳችሁ በሌላ አቅጣጫ እንዲፈስ አደረጋችሁ ወይም በሳይንሳዊ አገላለፁ (Diversion) ተሰራ፡፡ ግን ይሄ መሆን ያለበት የግብፅም ሆነ ሌሎች የአባይ ተፋሰስ ሐገራት ቅድሚያ አውቀውትና ተስማምተው መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ግድቡ ሲጀመርም እኮ አብዛኞቹ ሐገራት ተስማምተዋል፡፡ መመካከር ማንን ይጐዳል? ነው ወይስ አባይን ለፖለቲካ ቅስቀሳ ጥቅም ብቻ ነው የገነባችሁት? አባይ የዚህ ወይም የዛ ፓርቲ አባል ነው የሚል ፓርቲ ካለ ከግብፅ ጐን መሰለፍ ይችላል፡፡ አባይ በተለይም ጥቁር አባይ የኢትዮጵያዊያን በሙሉ ነው፡፡ ለዛም ነው ህዝቡ በጉልበቱም በገንዘቡም ሆ ብሎ እየገነባው ያለው የሚገነባውም! እና እንደ ምክር ወይ እንደተግሳፅ ፖለቲከኞቻችን እዩትና እባካችሁ ለሐገራችን የሚጠቅመውን አድርጉ አዋቂና ጥበበኞችም ሁኑ አንብቡ ተማሩ ተመራመሩ፡፡ መለስ የናፈቁኝ አንባቢ መሪና ተመራማሪ ስለነበሩ ነው፡፡ እንደውም አሁን አሁን በየቀበሌው በየቢሮው የመለስን ራዕይ እናሳካለን እያላችሁ በለጠፋችሁት ወረቀት ስር ይህንንም የምንተገብረው እንደሳቸው በማንበብና በመፃፍ በመማርና በመመራመር ነው በሉበት፡፡ በእውነት እውነቴን ነው፡፡ እኔ ይህንን ጽሑፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ስልጣን ፈላጊ ሆኘ አይደለም ሐገሬን አንድ ግብፃዊ ስነ-ህዝቡ በአደባባይ ሲዘልፋት ሰምቸ ተናድጀና ተቆጥቸ እንጅ አንድ ተራ ሰላማዊ ዜጋ ነኝ ግን እንደኔ ይህንን ስሜት የሚጋሩ ብዙ ኢትዮጵያዊያን አይጠፉምና አስቡበት፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ግብፅ በ2011 ላይ ደርሶባት ስለነበረው የእርስ በእርስ ግጭትና የግብፅን የአሁን ሁኔታ በመላው አለም ላይ ተሰራጭቶ የተለያዩ ኤክስፐርቶች አስተያየት የሰጡበትን መረጃ በመመርኮዝ ለሐገራችን ሕዝቦች ለመንግስታችንና ለሐገር መከላከያ ሰራዊታችን አቀርባለሁ፡፡
ልብ በሉ ግብፅ በታሪኳ ብዙ ጦርነቶችን አድርጋለች ታላላቅ ጦርነቶችን ግን ተሸንፋለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት የጦር ኃይሏ በአፍሪካ አንደኛ በአለም አስረኛ ነው፡፡ በአሜሪካ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከሚያገኙ ሐገራት ከእስራኤል ቀጥሎ ሁለተኛ ናት፡፡ አሜሪካ የእኔ ብቻ ናቸው ሌላ ሐገራት ቴክኖሎጂውን እንዳይሸጡት በሽያጭ አላቀርባቸውም የምትላቸው የብቻዋ ቴክኖሎጂ የሆኑ የተለያዩ ቀላልና ከባድ የጦር መሳሪያዎች ሄልኮኘተርና ጀቶችን ጨምሮ ግብፅን አስታጥቃታለች፡፡ በአጭሩ ግብፅ በአፍሪካ ቁንጮ ላይ ከአቅሟ በላይ የታጠቀች ጉረኛ ሐገር ናት ማለት ይቻላል፡፡
በአንድ ቀላል ምሳሌ እንኳን ለማስረዳት እስራኤልን ከምድረ ገፅ አጠፋለሁ ብላ ከሶስት ሐገራት ጋር ተባብራ በታሪክ የ“6 ቀኑ ጦርነት” የሚባለውን ልትተገብር ስትነሳ፣ ገና ሳይነሱ እስራኤል አጋየቻቸው እንጅ 300 የጦር አውሮኘላኖችን ቦምብና ሚሳኤል አስታጥቃ እስራኤልን ልትወርና ልታጠፋ የሞከረች ሐገር ናት፡፡ ይህም ምን ያህል ድንፋታም ነገር ግን ጥበብ የጐደላት ሀገር መሆኗን በቀላሉ ያስረዳል፡፡
ብዙ አወራሁ ወደ ተሰራጨ ያልኳችሁ ፅሑፍ ልግባና በመፅሐፍ ቅዱስ ትንቢተ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 29 እና 30 ላይ የግብፅን ቅጣት ስለሚያትተው ትንቢት የተሰራጨ አንድ ጽሑፍ ነበር ጽሑፉንም የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች አስተያየታቸውን አስፍረውበት ነበር ከአስተያየቶቹ መካከልም አይ ይህ ትንቢት እኮ ድሮ ገና ድሮ ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት በ572 ቅ.ል.ክ አካባቢ በናቡከነፃር ጊዜ ተፈፅሟል ያሉም ነበሩ፡፡ በዚህ አሁንም ድረስ እያነጋገረ ባለ ፅሑፍ ተነስተን እስኪ በደንብ ትንቢቱን በጥሞና እንየው፡፡
በደንብ መታየት ያለበት ነገር የግብፅ የቅርብ ጊዜ እርስ በእርስ መባላት በየአደባባዩ ጐራ ለይቶ መወራወር ከቱኒዚያ በተነሳው የጐዳና ላይ ግጭት ቀጥሎ የአለምን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ የግብፃዊያኑ አመፅ ዋናው አላማም ለ30 አመት ግብፅን አንቀጥቅጦ የገዛውን የሆስኒ ሙባረክን መንግስት መገልበጥ ነበር፡፡ በአሜሪካ መንግስትና በአንዳንድ የምዕራቡ ሐገራት ባለስልጣናት ግፊትም ሆስኒ ሙባረክ ስልጣናቸውን በፌቡራሪ 12 ቀን መልቀቂያ ጠይቀው ለግብፅ ጦር ሰራዊት አስረከቡ፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ በግብፅ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስልጣን ሽኩቻና ብጥብጥ ተፋፍሟል ዋናው ግፊትም ያለው ግብፅ በሐይማኖት መሪዎች የምትመራ ጠንካራና እስላማዊ ሐገር ሆና እንድትቀጥል ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው፡፡
ተራማጅ እስላም በሚል መፈክር ስርም ከጀርባ ሁኖ ማርሹን በመቀያየር የሚገኘው “ሙስሊሞቹ ወንድማማቾች” (Muslim brotherhood) የሚባለው ድርጅት እንደሆነ የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ ቀስ በቀስም በጥበብ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን እየያዘ ገና እየወጣ የሚገኝ ፓርቲ ነው ዋናው አላማውም ግብፅን ጠንካራ የሙስሊሞች ሐገር እንድትሆን ማስቻል ነው፡፡ በቅርቡ የሚታየው ሁኔታ እንደሚያመለክተውም የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ በግብፅ ጦር ውስጥ ያሉ ቁልፍ ሰዎችን እያዳከመና ወደ ፓርቲው እየቀላቀለ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ቀን ከሌት እየሰራ ይገኛል፡፡
ባጭሩ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚገልፁት በጣም የጦፈ የስልጣን መያዝ ፉክክር እንደሚደረግና የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ እንደሚያሸንፍና ተራማጅ እስላም ስልጣን ላይ እንደሚሆን ይገልፃሉ፡፡
ሙባረክ ስልጣኑን ባስረከቡ ማግስት ነው እንግዲህ እስራኤላውያን ነቃ ብለው የግብፅን ሁኔታ በጥሞና ማዳመጥ የጀመሩት የስለላ ኤክስፐርቶቻቸውንም ያሰማሩት፡፡ ምክንያቱም እ.ኤ.አ ማርች 31,1979 ጀምሮ ከ30 አመታት በላይ ያስቆጠረ የሰላም ስምምነት ከሙባረክ ጋር እስራኤል አድርጋ ነበር ሙባረክ ሲወድቅም ስምምነቱ ተቋረጠ፡፡ ባለፉት 30 አመታት ምንም እንኳ ግብፅ በጨቋኙ የሆስኒ ሙባረክ አገዛዝ ስር ብትሆንም እንኳ ግብፅ ለእስራኤል ደቡባዊ ድንበር መጋጋት የሆስኒ ሙባረክ ወታደሮች ከፍተኛ ጥበቃ ያደረጉ ነበርና ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ያ አስተማማኝ ጥበቃ የለም ስለዚህ እስራኤል ሆየ ነቃ! ብላ ነገሩን መከታተል ጀመረች፡፡
ይህ የእስራኤል ስጋትም ሳይውል ሳያድር እውን መሆኑ ተረጋገጠ ሁለቱ በተባበሩት መንግስታት አሸባሪ ተብለው የተፈረጁትና እስራኤልን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ሙሉ ጊዜአቸውን ሰውተው የሚንቀሳቀሱት የአሸባሪ ቡድኖቹ የሐማስና የፋታህ መሪዎች ሳይውል ሳያድር ግብፅ ካይሮ ላይ በሚያዚያ 26 ተገናኙና ጦራቸውን አንድ በማድረግ እስራኤልን ለመዋጋት ተፈራረሙ፡፡
የአሸባሪ ቡድኑ ፋታህ ኘሬዝዳንት ሞሐመድ አባስም ንግግራቸውን አሰሙ፡፡
“እኛ ፍልስጤማውያን ከዛሬ ጀምሮ ያንን ጥቁር የልዩነት ዘመናችንን አጠናቀናል! ሐማስ የፍልስጤም ሕዝብ አባልና አካል መሆኑን አውጀናል፡፡ እንግዲህ እስራኤል ከሰፈራ ኘሮግራም ወይም ከሰላም አንዱን መምረጥ አለባት!” ሲሉ ተኮፈሱ፡፡
አሁን በእርግጠኝነት ለመናገር ከዚህ በኋላ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል የሚደረግ የሰላም ስምምነት ሊኖር አይችልም፡፡ ቀዩ መስመር ይሉሐል ይሄኔ ነው! ፍልስጤም የምትባል ሐገርን ለማቋቋምና እውቅናን ለመስጠት ፋታህ እና ሐማስ መሞከራቸው አይቀሬ ነው ከዚች ቀን ደቂቃና ሰከንድ ጀምሮም ነበር እስላሞቹ ወንድማማቾችና እስራኤል አይጥና ድመት የሆኑት፡፡
እንግዲህ ቅድም የገለፅኩት የግብፃዊያን ትንቢት በትንቢተ ሕዝቅኤል ላይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል ያልኩት ከፅሑፉ ተነስቸ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕዝቅኤል በግልፅ ግብፆች የሚቀጡት ከእስራኤል ጋር አልተባበርም በማለታቸው ነው ይላል፡፡ “ግብፅ ለወደፊቱ አይቀጡ ቅጣት ነው የሚደርስባት ፍርዱም የቆሻሻ መጣያ ቦታ እስክትመስል በግብፅ ይታያል እያለ ቃል በቃል የሚከተሉትን የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ያትታል፡፡

 ሕዝቅኤል 29 (6:12)
በግብፅም የሚኖሩ ሁሉ ለእስራኤል ቤት የሸንበቆ በትር ሆነዋልና እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ”
“በእጅ በያዙህ ጊዜ ተሰበርህ ጫንቃቸውንም ሁሉ አቆሰልህ በተደገፈብህ ጊዜ ተሰበርህ ወገባቸውንም ሁሉ አንቀጠቀጥህ”
“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እነሆ ሰይፍ አመጣብሃለሁ ሰውንና እንስሳንም ከአንተ ዘንድ አጠፋለሁ፡፡”
“የግብፅ ምድር ባድማና ውድማ ትሆናለች እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ አንተ ወንዙ የእኔ ነው የሰራሁትም እኔ ነኝ ብለሀልና”
“ስለዚህ እነሆ በአንተና በወንዞችህ ላይ ነኝ የግብፅንም ምድር ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔና እስከ ኢትዮጵያ ዳርቻ ድረስ ውድማና ባድማ አደርጋታለሁ፡፡”
“የሰው እግር አያልፍበትም የእንስሳም ኮቴ አያልፍባትም እስከ 40 አመትም ድረስ ማንም አይኖርባትም፡፡”
“ባድማም በሆኑ ምድሮች መካከል የግብፅን ምድር ባድማ አደርጋታለሁ ባፈረሱትም ከተሞች መካከል ከተሞችዋ 40 አመት ፈርሰው ይቀመጣሉ ግብፃውያንንም ወደ አህዛብ እበትናቸዋለሁ በአገሮችም እዘራቸዋለሁ፡፡”

 በአሁኑ ሰአት ያለምንም ጥርጥር ግብፅ እስራኤልን ለማጥፋት ለብዙ አመታት ቀን ከሌሊት ሲማስኑ ከኖሩ ሙስሊም አሸባሪዎች ጋር ህብረት ፈጥራለች፡፡
ይህ የአሸባሪነት ትብብርም በቅርቡ እንደ ሰደድ እሳት መቀጣጠሉና ብዙ አሸባሪዎችን በህብረት አሰባስቦ እስላማዊ ወንድማማቾችን አሁን ጊዜው ደርሷል እስራኤል ትወረር ማስባሉ የማይቀር ሐቅ ነው፡፡
ብዙ ሰዎች ከላይ የጠቀስኩትን የሕዝቅኤል 29 ትንቢት ገና ወደፊት አለም ስትጠፋ የሚፈፀም ትንቢት ነው እንጅ አሁን ጊዜው ገና ነው እያሉ ይቃወማሉ፡፡
አንዳንዶቹ ደግሞ ትንቢቱ እኮ ድሮ ገና ድሮ በባሊሎናዊያን ጊዜ ተፈፅሟል ይላሉ፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ ልብ ያላሉት ነገር ቢኖር የሕዝቅኤል ትንቢት ስለፍፃሜው ሲተነብይ እሚያወራው ሴዌኔ ስለሚባል ቦታ የሚደርስበትን የወደፊት መከራ ነው የሚዘረዝረው፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ከላይ የዘረዘርኩት የመፅሐፍ ቅዱስ ቃል እንደሚያትተው ግብፅ በታሪኳ መቸም ቢሆን ለ40 አመታት ያህል ሰው የሌለባት ምድረ በዳ ሆና አታውቅም ይህም ትንቢቱ ገና ወደፊት ለመሆኑ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡
ለብዙ አመታት ስናምንበት የኖርነው የሕዝቅኤል ትንቢት በተፈጥሮው ቅኔያዊ ይዘቱ ያይላል፡፡ ይህንን ለማለት ያስቻለኝ ምክንያትም ሕዝቅኤል ትንቢቱን ሲፅፈው በዛ ጊዜ “የሴዌኔ ማማ” የሚባል ነገር ወይም ቦታ የለም አልነበረም እንደውም እ.ኤ.አ እስከ 1967 ጊዜ ድስ ይህ ቦታ አልተሰራም በ1967 ግን ይህ ቦታ በሚደንቅ ሁኔታ ታላቁ የአስዋን ግድብ ሆኖ ብቅ አለ፡፡ በግብፅ ደቡባዊ በኩል አባይን ተከትሎ ተገነባ፡፡ “ሴዌኔ” የሚለው ስም የመጣው ሲቭኔ ከሚለው የሒብሩ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም “መግቢያ” ወይም “ቁልፍ” ማለት ሲሆን ይህም ስም የጥንት ግብፃውያንን መግቢያ ያመላክታል፡፡ ከደቡባዊ ግብፅ ወይም ከኢትዮጵያ ተነስቶ አንድ ሰው ወደ ግብፅ ሲገባ የሚያየውን መግቢያ ወይም ቁልፍ በግልፅ ያትታልና፡፡
በጣም ብዙና የተለያዩ ታሪካዊ መረጃዎችን ብናገላብጥ የመፅሐፍ ቅዱስ ሴዌኔ በእርግጥም አስዋን ግድብ ነው ይላሉ፡፡ ከነዚህ መረጃዎች መካከል አንዱ በ1966 እ.ኤ.አ በኬል እና ዳልሽ የተፃፈው የብሉይ ኪዳን ጥናትና አስተያየት የሚለው መፅሐፍ ይገኝበታል፡፡ ግንኙነቱንም ሲያጠናክረው በግሪኮች “ሴዌኔ ብሩዳሽ” እንደፃፈው “ሴርቱዋጅንት” ወይም የመጨረሻዋ የግብፅ ደቡባዊ ከተማ ከኩሽ ማለትም ኢትዮጵያ አቅጣጫና ጐን ናት ይላል፡፡ አሁንም ድረስ ከአባይ ምስራቃዊ ቦታዎች አካባቢ የሚታዩ ኢትዮጵያዊ የሆኑ አንዳንድ የጥንት ስልጣኔ መገለጫዎች በግብፅ ደቡባዊ አዋሳኝ ከተማ ሴርቱዋጅንት አካባቢ ይገኛሉ፡፡
የሚገርመው ነገር ኬል እና ደልሽ በ1866 የብሉይ ኪዳን ጥናትና አስተያየት ሲፅፉ አስዋን ላይ ምንም አይነት ማማ አልነበረም ሕዝቅኤል ትንቢቱን በ570 ቅ.ክ.ል በፊት ሲፅፈውም ምንም አይነት ማማ አልነበረም፡፡ እውነታው ግን ታላቁ የአስዋን ሐይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ በግብፃውያንና በራሻውያን ተሰርቶ በ1967 እ.ኤ.አ እስከሚጠናቀቅበት ቀንና ደቂቃ ጊዜ ምንም አይነት ማማ በአስዋን ላይ አልነበረም፡፡
አሁን ግን ይህ ግድብ ሲጠናቀቅ በአካባቢው ያለው ብቸኛ ማማና ወደ ላይ የተራራ ያህል ገዝፎ የሚታየው የአስዋን ግድብ እራሱ ነው፡፡ ለዛም ነው ይህ “ሴዌኔ” እየተባለ በትንቢት ሲገለፅ የነበረው ቦታ በአሁኑ ሰአት አስዋን እየተባለ የሚጠራው ቦታ መሆኑን አጋግጠናል የሚሉት፡፡ ግብፃውያኑ የራሽውያንን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ግድባቸውን በተሳካ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ሲያጠናቅቁም ተኮፈሱና እስከ ዛሬ ድረስ የሚመፃደቁበትን አባባላቸውን ለልጅ ልጅ እንዲወረስ እያደረጉ እንደ ምሳሌያዊ አነጋገር ይጠቀሙበታል፡፡

“ወንዙ የእራሴ ነው የሰራሁትም እኔ ነኝ” ግብፃውያን

 ሕዝቅኤል 29 (2-5)
“የሰው ልጅ ሆይ ፊትህን በግብፅ ንጉስ በፈርኦን ላይ አድርግ በእርሱና በግብፅ ሁሉ ላይም ትንቢት ተናገር፡፡”
“እንዲህም በል - ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላላ በወንዞች መካከል የምትተኛና ወንዙ የእኔ ነው ለራሴም ሰርቸዋለሁ የምትል ታላቅ አዞ የግብፅ ፈርኦን ሆይ እነሆ በአንተ ላይ ነኝ፡፡”
“በመንጋጋህ መቃጥን አገባብሃለሁ የወንዞችህንም አሶች ወደ ቅርፊትህ አጣብቃለሁ ከወንዞችህም መካከል አወጣሀለሁ የወንዞችህም አሶች ሁሉ ወደ ቅርፊትህ ይጣበቃሉ፡፡
“አንተና የወንዞችህን አሶች ሁሉ ወደ ምድረ በዳ እጥላለሁ በምድርም ፊት ላይ ትወድቃለህ እንጅ አትከማችም አትሰበሰብም መብልም አድርጌ ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች ሰጥቼሃለሁ፡፡”
ትንቢቱ ዝም ብሎ በመጀመያ ሲታይ የሚመስለው ለግብፅ ንጉስ ፈርኦን ፓሮህ የተፃፈ ይመስላል ቀስ እያላችሁ በደንብ መፈተሽ ስትጀምሩ ግን ትንቢቱ የተፃፈው “በባህር ላይ ስለሚኖረው” ታላቅ አዞ መሆኑን ታውቃላችሁ፡፡
ቀጥሎም አንተና የወንዞችህ ወይም የአባይ አሳዎች ሁሉ ወደ ምድረ በዳ እጥላለሁ ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎችም መብል አደርግሃለሁ እያለ ያትታል፡፡
አባይ በየአመቱ እየተንደረደረ በከፍተኛ ሙላት ነበር ወደ ግብፅ የሚገባው ነገር ግን ግድቡ ከተሰራ በኋላ ሰጥ ለጥ ብሎ ነው ግብፅ ውስጥ የሚጓዘው በትንቢቱ እንደተገለፀው አባይን እንደገና በከፍተኛ ሙላት እያስጋለቡ በግብፅ ውስጥ ለማስጓዝ ብቸኛው መንገድ አንድ እና አንድ ብቻ ነው ግድቡን ማፍረስ፡፡
ሌላው አስደናቂ ነገር ይህ ታላቅ ግድብ የተገነባው በጣም በትልልቅ ብረቶችና ኮንክሪቶች ተጠፍጥፎ ከመሆኑ የነሳ የዘርፉ ባለሙያዎች የአስዋን ግድብ በምንም አይነት ቦምብ ቢመታ ሊፈርስ አይችልም፡፡ ከኒውክሌር ቦምብ በቀር ማለታቸው ትንቢቱን ገና ያልተፈፀመ ስለመሆኑ ያረጋግጣል፡፡ ኒውክሌር ቦምብ የአሁን ቴክኖሎጂ ነውና፡፡

 እስራኤላዊያን ጠበብቶች ምን አሉ?

በ2002 የእስራኤል የፓርላማ አባል የነበረ አቪጐር ሊበርማን የተባለ ሰው ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ይህች በየጊዜው ለእስራኤል ችግር መነሻ እየሆነች ላስቸገረችው ግብፅ የምትባል ሐር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚሆን መፍትሄ አግኝቻለሁ ብሎ ንግግሩን ያሰማው፡፡
“እስራኤል በቀላሉ ግብፅን በአንድ ኒውክሌር ቦምብ ድምጥማጧን ማጥፋት ትችላለች አለ” ልብርማን ስለ ግድቡ በደንብ ነበር ያጠናው ያሰማራቸው ረዳቶችም አስዋን ግድብ በጣም ትልቅና ግዙፍ ከመሆኑ የነሳ በተራ ቦምብ እንደማይፈርስ ተረድቶ ነበርና ኒኩሌየር ቦምብ ብቸኛ አማራጭ መሆኑን ተንትኖ አስረዳ፡፡
ሌላኛው የፓርላማ አባል ይጋል አሎን ቀጠለና ይህንን ጥሩ ዜና የምስራች ለእስራኤላዊያን በአደባባይ አበሰረ፡፡ እነዚህ ሁለት ጀግኖች አብዛኞቹ እስራኤላዊያን የሚያውቁትን ነገር ግን በውስጣቸው አምቀው የያዙትን እውነት በአደባባይ ያበሰሩ ጀግኖች አደረጋቸው፡፡ ሊበርማን ከእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስከ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ድረስ፣ ይጋል ደግሞ ለሰባት አመታት በሚኒስቴርነት ሐገራቸውን አገልግለዋል፡፡
ሊበርማንና ይጋል እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ ግብፃውያን አንገታቸውን ደፍተው እድሜልካቸውን መፍትሄ የማያገኙለትን የቤት ስራ ሰጥተዋቸዋል፡፡
እነኚህ ሁለት እስራኤላዊያን ሲናገሩም የእስራኤል የማንነት ጥያቄ በግብፃውያን ወረራ የሚስተጓጐል ከሆነ ጨዋታው የሚሆነው እንደዛ በምትመፃደቁበት ግድባችሁ ላይ ይሆናል በማለት አስረገጡ፡፡
“በኑክሊር ቦምብ አስዋንን እናፈርሰዋለን፡፡ በውሃውም በሰዓታት ሰምጣችሁ ታልቃላችሁ አርፋችሁ ቁጭ በሉ፡፡ “ይኸው እነሱም አርፈው እስከ ዛሬ ቁጭ ብለዋል፡፡

 የሚከተሉት የማጠቃለያ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በመጨረሻው ቀን ላይ ያተኩራሉ ልብ ብላችሁም አስተውሉ የሴዌኔ ማማም ተጠቅሷል፡፡

 (ሕዝቅኤል 30 1፡6)
“የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ የሰው ልጅ ሆይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል”
“ጌታ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል” ዋይ በሉ ለቀኑ ወዮ ቀኑ ቅርብ ነው የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው የደመና ቀን የአህዛብ ጊዜ ይሆናል፡፡
“ሰይፍ በግብፅ ላይ ይመጣል ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል የተገደሉትም በግብፅ ውስጥ ይወድቃሉ ብዛትዋንም ይወስዳሉ መሰረቷም ይፈርሳል፡፡”
“ኢትዮጵያና ፋጥ ሎድም የደባለቀም ሕዝብ ሁሉ ኩብም ቃል ኪዳንም የገባችው ምድር ልጆች ከእነሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ፡፡”
“እግዚአብሄር እንዲህ ይላል ግብፅን የሚደግፉ ይወድቃሉ የሐይሏም ትእቢት ይወርዳል ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔ ድረስ በእርስዋ ውስጥ በሰይፍ ይወድቃሉ ይላል ጌታ እግዚአብሄር፡፡”

ለዚህም ነው ግብፅ ለመኖሪያ የማትመች የተንኮለኞችና የእግዚአብሔር ቃል ተቃዋሚዎች ሐገር በመሆኗ ለ40 አመት ያህል ማንም የማይኖርባት ምድረ በዳ አደርጋታለሁ ያለው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በሕዝቅኤል 38 ላይ እስራኤልን ተባብረው ከሚያጠቋት የጐግ ሐይሎች ጋር ግብፅ ያልተጠቀሰችውም እኮ ስለማትኖር ነው እንጂ ብትኖርማ የመጀመያ ቋሚ ተሰላፊ ነበር እኮ የምትሆነው፡፡
በራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገር በተበከለ ውሃ የተጥለቀለችን አንድ ሐገር ለማፅዳት የሚፈጀውን ሐይልና ገንዘብ አስቡትና ምን ያህል አስቸጋሪ ነው ብላችሁ እራሳችሁን ጠይቁ፡፡ ወይም ከመጨረሻው ቀን በኋላ በእግዚአብሄርና በተከታዮቹ የሚፀዳው ቦታ ግብፅ ይሆነ ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል? እባካችሁ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖችም በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ነገር በሉ “ግብፅ ሆይ አርፈሽ ቁጭ በይ! በእሳት አትጫወች! ግድባችንን እንዳንሰራ ወንድ የሆነ ያስቆመናል! አለዛ በደህና ጊዜ የሰራሽውን የአስዋን ግድብ መጥፊያሽ ይሆናል! አሁን ያለው ኢትዮጵያዊ ትውልድ ከምታስቢው በላይ ነቃ ያለ ነው እንኳን ለወደፊቱ ድሮ ለሄደብን አፈርም ካሳ መጠየቁ አይቀርም” እኔስ እችን ፅፌ ትንሽ ንዴቴ ተንፈስ አለልኝ! እናንተስ?

 የምወዳትን ኢትዮጵያ እግዚአብሔር ይባርካት፡፡

                              አመሰግናለሁ፡፡

                       አማኑኤል ዊንታ

                   ባህር ዳር ሰኔ 2005

Sunday, February 23, 2014

ጾም


(ነብዩ ዮናስ በነነዌህ የሥዕል ምንጭ ባይብል ጌት ዌይ)
(የጽሁፍ ምንጭ፦ የዲያቆን አሸናፊ መኮንን ገጽ)

ጾም ለመንፈሳዊው ዓለም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ቁርጥ ልመናን ለማቅረብ፣ እውነተኛ ንሰሐን ለመፈጸም፣ የዕንባ መሥዋዕትን ለማቅረብ፣ በትሕትና ጸጋን ለመቀበል ጾም አስፈላጊና ግዴታ ነው፡፡
ጾም አዋጅና በአዋጅ ሊደረግ የሚገባው ነው፡፡  በስውር የሚደረግ ጾም አለ፡፡  ግለሰቡ ጉዳዩን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብበት፣ መጾሙንም የማያሳውቅበት ነው፡፡  የማኅበር ጾም ግን በአዋጅ የሚደረግ፣ ስለ አገርና ስለ ወገን የእግዚአብሔር ማዳን የምንጠባበቅበት ነው፡፡  ጾምን ሰው ለራሱ ያውጃል፣ ቤተ ክርስቲያንም ታውጃለች፡፡
ጾም ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት የምናዋርድበት ነው፡፡  በተሰበረ ልብ የሚቀርብ ልመና ግዳጅን ይፈጽማል፡፡  ፈጽሞም መልስ ያገኛል፡፡  ጾም ለትሑት ጸሎት እጅግ ይረዳል፡፡  ሥጋን በማድከም ወደ ነፍስ ልዕልና የምንቀርብበት ምሥጢር ነው፡፡  ጾም የርኅራኄ መገኛ፣ የዕንባ ምንጭ፣ የትሕትና መፍለቂያ ናት፡፡  ራሳችንን በጾም ስናዋርድ እግዚአብሔር ከፍ ያደርገናል፣ ምሪትን ይሰጠናል (ዕዝ. 8÷21)::
ጾም አዋጅን የሚሽር አዋጅ ነው፡፡ በመጽሐፈ አስቴር ላይ እንደምናነበው በአይሁድ ላይ የታወጀው የሞት አዋጅ ወደ ሹመትና ክብር የተለወጠው በጾምና በጸሎት ነው (አስቴ. 4÷3)፡፡  የተዘጉ ደጆች እንዲከፈቱ፣ በአገር በወገን ላይ የመጣ የክፉ አዋጅ ማለት ሞት፣ መከራ፣ በሽታ እንዲወገድ ጾም ጸሎት ትልቅ መሣሪያ ነው፡፡  የጾምና የጸሎት ትጥቅ አይታይም፣ የሚታየውን ጠላት ግን ያሸንፋል፡፡  
ጾም ይቅር ብለን ይቅርታ የምንለምንበት ነው፡፡  እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን (ይቅርታን) ይወዳል (ማቴ. 9÷13)፡፡  በጾም በጸሎት የእግዚአብሔርን ይቅርታ ስንለምን ይቅር እያልን፣ በረከቱን ስንለምን ለተራቡት እያበላን ሊሆን ይገባዋል፡፡ አማኝ ከጫጫታ ስፍራ ገለል ብሎ፣ ከዘፈን ይልቅ ዝማሬን መርጦ፣ ከወሬ ይልቅ በጸሎት ተጠምዶ እንዲባረክ ጾም ቀስቃሽ ደወል ነው፡፡
ዘፈንና ዝሙት እንዲሁም ስካር በአገር ሲበዛ ቀጥሎ ትልቅ ጥፋትና ልቅሶ ይኖራል፡፡  "የዘፈን ቤት ሳይፈርስ አይቀርም" እንዲሉ ዘፈን ሲበዛ መጾምና ማልቀስ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾም የበሬ ሥጋን ከመብላት መከልከልን ብቻ ሳይሆን ከሰው ሥጋም እንድንርቅ ነው፡፡  ያለ ቢላዋ በሐሜት የሰውን ሥጋ መብላት ጾምን እንደ መግደፍ ነው፡፡  እኛ ግን የበሬ ሥጋ እንጂ የሰው ሥጋ አንተውም፡፡ ሠራተኞቻችንን እያስለቀስን፣ ደመወዛቸውን እየበላን፣ ቂምን በልባችን ሞልተን የምንጾመው ጾም የረሃብ አድማ እንጂ ጾም አይባልም (ኢሳ. 58÷5-6)፡፡ የጾም መሰናዶው ነጠላን ማጽዳት ሳይሆን ልብን ማጽዳት፣ በየልኳንዳ ቤት ደጆች መሰለፍ ሳይሆን ንስሐ መግባት፣ ዕቃን ማጣጠብ ሳይሆን ከቂም መጽዳት ነው፡፡  የጾምን መረቁን እንጂ ሥጋውን አልበላንምና ከንቱ ልፋተኞች ሆነናል፡፡ ምክንያቱም ለጾማችን የምናደርገው ዝግጅት ሜዳዊ እንጂ ውስጣዊ አይደለምና፡፡ ትልቁ ጾም ከኃጢአት መከልከል ነው፡፡  ቅበላና ፋሲካ የሌለው ጾም ኃጢአት ነው፡፡  በአገራችን በጾም መግቢያና መውጫ ስካርና ዝሙት ይደራል፡፡  ቅበላውና ፋሲካው በኃጢአት በመሆኑ ከጾም የሚገኘውን በረከት ማግኘት አልቻልንም፡፡
ጾም ለእግዚአብሔር እንጂ ለታይታ አይደለም (ዘካ. 7÷5)፡፡  ከማኅበረሰቡ ላለመለየት፣ ሆዳም ላለመባል፣ ዶሮ ለመባረክ መጾም ከንቱ ጾም ነው፡፡ የምንጾመው ከእግዚአብሔር ዋጋ ለማግኘት እንጂ ጾመኛ ለመባል መሆን የለበትም፡፡ የጾምና የጸሎት ዋጋ ያለው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡ “በጾም አፌ ክፉ አታናግሩኝ” ለማለት መጾም አይገባንም፡፡  ባንጾምም ክፉ መናገር አይገባንም፡፡  በጾማችን የሚታየን እግዚአብሔር ነው?  ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል፡፡
ጾም እውነትና ሰላም ያለበት ነው፡፡  በጾማችን ወራት ከድሆች ጋር ማሳለፍ፣ ብድር መመለስ ለማይችሉ ቸርነት ማድረግ ይገባል፡፡ እኩያን ሲጠሩ መኖር እውነተኛነት አይደለም፡፡ ከእኛ ባነሰ ኑሮ ለሚኖሩት እጅን መዘርጋት ግን የጾም መገለጫው ነው፡፡  ጾም ሁለት እጆች አሏት፡፡  አንደኛው የጾም እጅ ጸሎት፣ ሁለተኛው የጾም እጅ ምጽዋት ነው፡፡  ጾም ሁለት አንደበት አሏት፡፡  አንደኛው ቃላችን ሲሆን ሁለተኛው ዕንባችን ነው፡፡ ጾም እውነትን ትፈልጋለችና ለተጨቆኑ ምስኪኖች፣ ፍርድ ለተጓደለባቸው እስረኞች፣ በግፍ ከገዛ አገራቸው ለሚሰደዱ አቤት የምንልበት፣ ግፍ አድራጊዎችን በቃችሁ ብለን የምንገስጽበት የእውነት ሰይፍ ነው፡፡ ጾም ሰላም ስለሆነ ግለሰብ ከግለሰብ፣ ማኅበራት ከማኅበራት፣ አገር ከአገር ጋር የሚታረቁበት፣ እንዲታረቁም ጥረት የምናደርግበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ እርቅን የጠሉና የገፉ የሃይማኖት አባቶች ጾምን የማወጅ አቅም የላቸውም፡፡ ስለዚህ ታርቀው የሚያስታርቁበት እንዲሆን ሊያስቡ ይገባቸዋል፡፡ የጾም የመጨረሻው ውጤት ወይም በዓሉ እግዚአብሔር በሚሰጠን መልስ ሆታና ደስታ ነው፡፡  መልስ እንዲመጣ ግን እውነትና ሰላም መርጋት አለባቸው፡፡ ግፈኞች፣ የሌላውን ድርሻ እየነጠቁ የሚበሉ፣ ለሀብታም እያደሉ በድሃ የሚፈርዱ ሊገሰጹ፣ ንስሐ ሊገቡ ይገባል፡፡  ያ ሲሆን የጾም ዳርቻው ተድላና ደስታ ይሆናል (ዘካ. 8÷19)፡፡
 የነነዌ ሰዎች ምሕረትን የተቀበሉት በሦስት ቀን ጾምና ጸሎት ነው፡፡  የመጣው መዓት የተመለሰው፣ የራቀው ምሕረት የቀረበው በአንድ ልብ ሆነው አቤት በማለታቸው ነው፡፡  እኛ ግን ዓመት ሙሉ እየጾምን ለምን በረከት ራቀን? ብለን ጠይቀን አናውቅም፡፡ 

እንደጸሎታችን መብዛቱ ረሃብና ቸነፈር፤ ስደትና እንግልት፤ የሰላምና ፍቅር እጦት፤ አንድነትና ኅብረት አለመኖር የሚያጠቃን ለምንድነው? የጾም ጸሎት ምላሹ ይህንን ለማስቀረት ካልሆነ የጾምና የጸሎታችን ጉዞ የተተከለ ደንብ ከመፈጸም ውጪ ከእግዚአብሔር ሀሳብ ጋር አልተገናኘም ማለት ነው። ስለዚህ ይህን ዐቢይ ጾም ስንጾም፡-
    1.     ርዕስ ልንይዝ
    2.    ይቅር ልንባባል
    3.    ንስሐ ልንገባ ይገባናል፡፡
ብዙ አንገብጋቢ ርዕሶች አሉን፡፡ የቤተ ክርስቲያን ለሁለት መከፈል፣ በመንፈሳዊ ቦታ መንፈሳዊ ያልሆኑ ሰዎች መቀመጣቸው፣ እርቅን የማይወዱ ሰዎች መሙላታቸው፣ በአገር ያለው የኑሮ ውድነት፣ ድሆች በደንብ እየደኸዩ መሆናቸው፣ ፍትሕና ፍቅር መጥፋቱ፣ የገንዘብ ጣኦት በምድራችን መቆሙ፣ የዝናብ መታጣት፣ የበሽታ መበርከት፣ የአንድነት መጥፋት፣ የትዳር መናጋት፣ የልጆች ዋልጌነት፣ የሐሰት መምህራን መብዛት፣ እግዚአብሔርን መርሳት…….  ይህ ሁሉ የጾምና የጸሎት ርዕሳችን ነው፡፡  ክርስቲያን መንፈሳዊ ኃይልን አጥተóል፡፡  በየደረሰበት ውጊያ አሸናፊ ሳይሆን ተሸናፊ ሆኗል፡፡
ይኸውም፡-
    -      ቃሉን ስለማያጠና
    -      የጸሎት ሰዓቱ ስላልተከበረ
    -      ጾምና ጸሎትን ስለተወ
    -      ምጽዋትን ስላስቀረ
    -      የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር መስጠት ስላልቻለ …. ነው፡፡
በእውነት ጾመን በዓሉ ተድላ እንዲሆን፣ በጾም ዘርተን በፈውስ እንድናጭድ እግዚአብሔር ይርዳን!

Sunday, February 16, 2014

ዕርቅና ሰላም፤ የሕይወት ቅመም


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እንደውለታ ቢስ ለሚቆጥሩ ወገኛ ሁሉ መልስ የሚሆን ጽሁፍ እነሆ!
በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ 
 
   አንድ ጥናት ሳነብ፥ ምናልባት እናንተም አንብባችሁት ይሆናል፥ የተፈጥሮ ሀብት ባላት ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከተራቡ፥  የማሰብ ችሎታቸው ዝቅተኛ ቢሆን ነው ሲል አገኘሁት። "ጥልቀት የሌለው ረጋ-ሠራሽ ጥናት ነው" ብዬ ጣልኩት። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ባለጠጋ መሆኗን እርግጥ ባለሞያዎች የመሰከሩት ነው። ማዳበሪያ የማያስፈልገው መሬት ታርሶ አያልቅም። የወንዞቿ ውሀ ለጎረቤት አገሮች ሳይቀር ይተርፋል። ይኸንን እውነታ በቀጥታ ከተመራማሪዎቹ  አፍ ለመስማት የፈለገ ፕሮፌሰር ስዩም ገላየን ማዳመጥ ይችላል።  
   እንዲህ ከሆነ፥ ትኩረቱ በኢትዮጵያውያን የማሰብ ችሎታ ላይ ሊሆን ነው። እውነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተመጽዋች ሆኖ የቀረው የማሰብ ችሎታው ዝቅተኛ ሆኖ ነው? አይመስለኝም።  ሰውየው ጥናቱን ማስተካከል አለበት። አለዚያ፥ ከዚያ ቀጥሎ፥ "አንድ ሰው እሱቁ ውስጥ ከመስተዋቱ በስተኋላ ድፎ ዳቦ እያየ ከተራበ የአስተሳሰብ ችሎታው ዝቅተኛ ቢሆን ነው" ሊለን ነው። ምንም ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ቢኖረው፥ ዳቦውን እንደማያገኘው ለማንም ግልጽ ነው። 
  እርግጥ ነው፥ በአስተሳሰብ ደከም የሚል ሰው ሊጎዳ ይችላል። ሌላው ቢቀር፥ የብልሁ ጓደኛውን ያህል አይደላውም።  ግን በከፍተኛ ደረጃ የማሰብ ችሎታ ያለው ሰውም ሊቸገር ይችላል።  ስንቶች ናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በችግር የሚኖሩ፥ መውጫ ቢያገኙ ግን ለሌላው ሳይቀር የሚተርፉ? በአፍሪካ፥ በአውሮፓ፥ በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በማስተማርና በምርምር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቊጥር ቀላል አይደለም። በንግዱ ዓለምም ቢሆን፥ "የሺ ብር ጌቶችን" ጓዳ ይቊጠራቸው። 
የለም፥ የተፈጥሮ ሀብት ባለጠጋ የሆነች ኢትዮጵያ ብልሁ ሕዝቧ ለምን እንደሚራብ የተከበረ ጥናት መደረግ አለበት። ዋና ዋናዎቹን ምክንያቶች ፕሮፌሰር ስዩም ገላየ ደርድሯቸዋል። አንዱ፥ የመሬት ይዞታ መበላሸት ነው ይለናል። "የመሬት ላራሹ" ጩኸት ውጤቱ "መሬት ለነጋሹ" ሆኗል፤ ለገበሬው የታሰበውን መሬት ወያኔ ወሰደው። የዱሮ ንጉሣዊ ገዢዎቿ ቤተ ሰቦች ስለነበሩ በቊጥራቸው ማነስ ምክንያት እነሱን በማር ግብር ለማጥገብና በሰላም ለመኖር ቀላል ነበረ። የዛሬዎቹ ገዢዎች ብሔረ ሰቦች ስለሆኑ እነሱን ሁሉ በሚሊዮን ዶላር ማጥገብ መራቆትን አስከትሏል። ሌላው፥ አገሪቱ በክልል መከፋፈል ነው። ማንም ሰው በገዛ ሀገሩ ከመሰለው ክፍለ ሀገር ሄዶ በሰፊው ማረስ አይችልም። ዛሬ ኢትዮጵያ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ሙሉ በሙሉ አገሩ አይደለችም። ኢትዮጵያ ለልጆቿ እናትነቷ በሙሉ ሰውነቷ እንዳይሆን ተከልክላለች። 
 የታሪክ ተመራማሮዎችም ያዩት ምክንያት ይኖራቸዋል። ክርስቲያኖችና እስላሞች፥ ኦሮሞዎችና ሌሎች መሆናችንን ዐውቀን በብልህነት አለማስተናገዳችን ጒዳት እንዳመጣብን ይናገራሉ። ሁላችንም የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች፥ አንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብንሆን ኖሮ ከምሰሶ ጋር በእግር ብረት እንደተቈራኘ ሰው እጃችንን ብቻ ወደ እግዚአብሔር እያደረስን አንድ ዘመን ላይ ቆመን አንቀርም ነበር ይላሉ።  
  በሃይማኖት አንድ ባለመሆናችን ያስከተለውን ጕዳት ለማሳየት የአክሱምን ሥልጣኔ ያከሰመውን የጉዲትን አመፅና የአምሐራን ("የአማራን" ማለቴ አይደለም)ሥልጣኔ እሳት የለቀቀበትን የግራኝን ወረራ ይተርካሉ።

እነዚህ ሁለት ሥልጣኔዎች ኢትዮጵያን በዚያ ዘመን ከገነኑ አገሮች እኩል አስሰልፈዋት ነበረ፤ ጠፉ፤ ባለንበት ቆመን ቀረን። 
ዛሬ ስለሁለቱ ሥልጣኔዎች የምናውቀው ከመጥፋታቸው በፊት ከተጻፈው ታሪካቸውና ከጥፋት ካመለጠው  ርዝራዣቸው ነው። ሀገሪቱ ከግራኝ ምች ልታንሰራራ አልቻለችም። የግራኝ ምች የምለው እስላሞች በዓሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት በክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን ጒዳት ነው;ታሪኩን ክርስቲያኖቹ በሐዘን፥እስላሞቹ በደስታ መዝግበውታል፤ ዛሬም በዚያው ስሜት ያስታውሱታል። የደረሰው የሰውና የንብረት ጥፋት ሁሉ የሚያሳዝን ቢሆንም፥ሁልጊዜ የሚታወሱኝ ቅጂ ያልተገኘላቸው ስማቸው ብቻ የቀረልን ብርቅ ድርሰቶች ናቸው።
እስላሞቹ ክርስቲያኖቹን ለማጥፋት ከጂሃድ በቀር ሌላ ምንም ምክንያትአልነበራቸውም። መንግሥቱን ተወደደም ተጠላ ያቋቋሙት ክርስቲያኖቹ  ነበሩ። ከሀገሪቱ ክፍል ሱማሌዎችና ይፋቴዎች እንደሚኖሩባቸው አንዳንድ ክፍሎች ሲሰልሙ፥ በኢትዮጵያ ስር ሆነው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ሙሉ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበረ። በዛሬው ዓይናችን እንኳ ስናየው፥ የንጉሣዊው መንግሥት ከዚህ የተሻለ ሌላ ምን አማራጭ አገዛዝ ነበረው? የጂሃዱ መንሥኤ ኦርቶዶክሱን ሕዝብ በሞላ አስልሞ በሸሪዓ ሕግ መግዛት  ነበር። 
እስላሞቹ፥ "መንግሥቱን ወስደን፥ ክርስቲያኖቹ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ እናደርጋለን" ቢሉ እንኳን ያባት ነበር። ኦሮምኛ ተናጋሪዎችና ሌሎች መሆናችን ያስከተለውን ጕዳት ለማሳየት ደግሞ የኦሮምኛ ተናጋሪ ጎሳዎችን ወደማህል ኢትዮጵያ የመፍለስ ታሪክ ይተርካሉ። ለአባ ባሕርይና የዘመኑን ነገሥታት ታሪክ ለጻፉ፥ በተለይም ለተክለ ሥላሴ ጢኖና ለተክለ ኢየሱስ ዋቅጂራ ምስጋና ይድረሳቸውና የኦሮሞ ጎሳዎች ወደማህል ኢትዮጵያ ፍልሰት ያስከተለው የሥልጣኔ ውድመት ከብዙው በጥቂቱ ተመዝግቧል። ኦሮምኛ የሚናገሩ ጎሳዎች የእስላሞቹ አመፅ በተገታ ማግስት ፈልሰው፥ ከእስላሞቹ የተረፈውን የሥልጣኔ ምልክት ጠራረጉት። ጋዳ በሚሉት ሁሉን ለጦርነት በሚያሰልፍ የማፊያ ሥርዓት በውትድርና ተደራጅተው፥ በግብርና፥ በንግድ፥ በድብትርና ("በዕውቀትና በምርምር"ማለቴ ነው) የሚተዳደረውን ሰላማዊ ሕዝብ አረዱት፤ ንብረቱን አወደሙት። በእርሻው፥ በሰብሉ ላይ ከብታቸውን አስሠማሩበት። በባህላቸው መሠረት፥ ክርስቲያን ያልገደለ በቅማል ይሰቃያል እንጂ ራሱን አይላጭም ነበር። ሸዋን፥ ጎንደርን፥ ጎጃምን፥ አምሐራን (የዛሬውን ወሎ) ደመሰሷቸው።  
እስላሞቹ የክርስቲያኖቹን ሥልጣኔ አጥፍተው በራሳቸው ሥነ ጽሑፋዊ ሥልጣኔ ሊተኩት አስበው ነበረ። ኦሮምኛ ተናጋሪዎቹ ግን እረኞች ስለነበሩ ሥልጣኔን በሥነ ጽሑፋዊ ሥልጣኔ የመተካት ግዴታ አልነበረባቸውም። ግን በባህል ረገድ ከወረሩት ሕዝብ አብዛኛውን እንደነሱ ኦሮምኛ ተናጋሪ፥ የቀረውን ገበር (አሽከር) አደረጉት። እስላሞቹና ኦሮምኛ ተናጋሪዎቹ ሰውና ቅርስ ባወደሙበት ቦታ ሁሉ ሐውልት ቢቆም ሀገሪቱ "ሀገረ ሐውልት" ትሆን ነበረ።  
  ከግድያቸው ሰለባቸው ይብስ ነበረ። ባለቅኔው፥ "ጃዊ ቀደደ ሆድ ሆድሆዶሙ ወሰለቦሙ እስከ ሕምብርት" (ጃዊ ሆድ ሆዳቸውን ቀደደው፤ እምብርታቸው ድረስ ሰለባቸው) ያለው በጎንደር ዘመነ መንግሥት የደረሰውን መቅሠፍት አይቶ ነው። የሆነውን በታሪክ ዓይን አይቶ በማለፍ ፈንታ፥ ዛሬ አቻው እንዲሆን ታስቦ ያልሆነ፥ ያልተደረገ የአረመኔነት ታሪክ ለራስ ጎበና ዳጨ ወታደር መፍጠር፥ ግፋ ቢል ሞኞችን በሞኝነታቸው እንዲኖሩ ከማድረግ የበለጠ አገልግሎት አይኖረውም። ውሸት ታሪክ አይሆንም።  
  ማንም መጥቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሰፍር የኢትዮጵያ ነገሥታት አይከለክሉም ነበር። ሰው የሌለበት ሰፊ ቦታ ስለሞላ ማንም ከዚያ ቢሰፍር ማን ነህ የሚለው አልነበረም። ችግሩ፥ ኦሮምኛ  ተናጋሪ ጎሳዎች ከአንድ ቦታ ፈልሰው ከባዶ ቦታ በመስፈር ፈንታ፥ ሌሎች ያቀኑትን ቦታና ያተረፉትን ቅርስና ውርስ እንንጠቅ ማለታቸው ነበር። በዚያ ላይ፥ ማህል ኢትዮጵያን ከያዙ በኋላ፥ ለኢትዮጵያ መንግሥት አንገብርም ማለትን አመጡ። በዚህ ጊዜ የንጉሣዊው መንግሥት ምርጫ ምን መሆን ነበረበት?  

  
ያምናው በሽታ፤ 

  በዚህ እኛ ባለንበት ዘመን፥ እስላሞች ቤተክርስቲያን ሲያቃጥሉ፥ አንዳንድ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ሰላማዊውን ሰው በሕይወት ገደል ሲሰዱ፥ በ ዩቲዩብ  (youtube) ሳይ፥ ሰውየው፥ "ኧረ እናንተ ሰዎች ሰው አይድንም ታሞ፤ ያምናው በሽታየ አገረሸ ደግሞ፡" ያለው ትዝ አለኝ። በሽታውን ማስገርሸት አንዱን ጠቅሞ ሌላውን አይጐዳም። ሁሉም ተጐጂ ነው የሚሆነው። ሁል ጊዜ ሳይሞቱ መግደል አይቻልም። 
ሌላውን የሚገድሉት እየሞቱ ነው። በዚያ ላይ በማህል ቤት የሚሆነውን ማንም አያውቀውም። ለምሳሌ፥ የኦሮሞን አመፅ ይመሩ የነበሩ የወለጋ ፕሮቴስታንቶች እንደነበሩ ይታወሳል። አሁን አመፁን ከነሱ ተቀብለው በኦሮሞ ስም የሚያካሂዱት፥ "ከኦሮሞው ሕዝብ አርባ በመቶው እስላም ነው" የሚሉ የኦሮሞ እስላሞች ናቸው። ቊጥራቸውን ቢያጋንኑትም፥ እስላሞቹ ከፕሮቴስታንቶቹ መብለጣቸው አያጠራጥርም።  እንግዲህ፥ የፕሮቴስታንት ክርስቲያኖች በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች መንግሥት  ላይ  ያካሄዱት ትግል በፍትሐ ነገሥት ቀርቶ በሸሪዓ ሕግ በሚያምኑ ወገኖች ለመተዳደር ሊሆን ነው።  የግብጽ ክርስቲያኖች የመለካውያን ክርስቲያኖችን የበላይነት በመጥላት አገሪቷን ዐረቦች እንዲወስዷት ረድተው፥ ዋጋ ከሌለው ጸጸት ላይ እንደወደቁ የምናየው ነው። 


 የመጀመሪያው እርምጃ፤ 

ከላይ እንደገለጥኩት፥ እስላሞችና ኦሮምኛ ተናጋሪ ጎሳዎች ኢትዮጵያን እንዴት እንዳቈረቈዟት ታሪኩ እንዳይፋቅ ሆኖ ተጽፏል፤ የሚፈለገው ግን ዕርቅና ሰላም እንዲወርድ ነው።ዕርቅና ሰላም የሚወርድ ከሆነ፥ታሪኩ ባይፋቅም ተከቶ ከድንቊርናና ከረኀብ የምንላቀቅበትንና ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ እንዳለን የምናስመሰክርበትን ብልሀት ልንፈልግ እንችላለን።ለዚህም መሆን ያለበት የመጀመሪያው እርምጃ አባቶቻችንን እንወክላለን የሚሉ እስላሞችና ኦሮሞዎች የአባቶቻቸውን ጥፋት ከመቀጠል አባቶቻችው በኢትዮጵያ ላይ ላደረሱት መጠን አልባ ጥፋት የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ ይሆናል። 
የጥፋቱን ታሪክ ጸሐፊዎቹ ለወገኖቻቸው እያዳሉ ጽፈውታል እንዳይሉ፥የጻፉት ራሳቸው እስላሞቹ እነሽሀብ እዲን ዐረብ ፈቂህ፥ የአማራውና የኦሮሞ ተወላጆች እነ አባ ባሕርይ፥ እነ ተክለ ሥላሴ ጢኖ፥ እነ ተክለ ማርያም ዋቅጂራ ናቸው። ታሪካችንን ደብተራዎች አይጽፉትም የሚሉ ካሉ፥ የጸሐፊዎቹን ማንነት ባለማወቅ ሊሆን ይችላል። የሌሎችም ታሪክ ጸሐፊዎች ስማቸውና ሥራቸው "የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፤ ኦሮሞችን ከሚመለከቱ ሌሎች ሰነዶች ጋራ"  በተባለው መጽሐፌ ውስጥ ተዘርዝሯል።  ይህን መጽሐፍ ብዙ ሰው ስለሚፈልገው፥ ማንም ሰው  እያወረደና እያተመ  እንዲያነበው በማሰብ፥ www.ethiopiawin.net or www.ethiopiawin.org  ብለን ካቋቋምነው ድረ ገጽ ላይ ተለጥፏል። ኢትዮጵያን ለማገልገል ላቋቋምነው ድርጅት እርዳታ የሚሆን በፈቃድ ከሚሰጥ ገንዘብ በቀር የመጽሐፉን ዋጋ አንጠይቅም።  

ሁለተኛው እርምጃ፤ 

ሁለተኛው እርምጃ ኦሮምኛ ተናጋሪዎችን የሚመለከት ነው፤ አፄ ምኒልክና ራስ ጎበና ዳጨ ስፍር ቊጥር በሌለው ጎሳ የተበታተኑትንና እርስ በርሳቸው የሚባሉትን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች አንድ ያደረጉበትን ቀን በየዓመቱ ማክበር አለባቸው። ግን ሁሉንም አንድ ያደረጉት በአንድ ቀን ድል ስላይደለ፥  የትኛውን ቀን እንደሚያከብሩ በጨፌያቸው ሊወስኑት ይችላሉ። ሆኖም በአፄ ምኒልክ ሐውልት ስር አበባ ማስቀመጥ የበዓሉ ክፍል መሆን አለበት። ራስ ጎበና ሐውልት ስለሌላቸው፥ ሳይውል ሳያድር ከተከበረ አደባባይ ላይ የጎላ ሐውልት እንዲተከልላቸው ባለውለታዎቹ መገፋፋት ይኖርባቸዋል።        

ሶስተኛው እርምጃ 

ሶስተኛው እርምጃ አስተሳሰብን ከሰብአ ትካት አስተሳሰብ ወደ ሰብአ ዘመን አስተሳስብ ማራመድ ነው። '"ሰብአ ትካት" በእንግሊዝኛ  primitive people የሚባሉት ናቸው። አስተሳሰባቸው ከመንደራቸው ርቆ አይሄድም፤ የዚያኛው መንደር ሰው ጠላታቸው ነው፤ የዚያኛው ብሔረ ሰብ አባል ባለጋራቸው ነው። "ሰብአ ዘመን" modern man ነው። መንደሩ ጠቅላላዋ ሀገር ነች። በሰብአ ዘመን አስተሳሰብ የዚያ መንደር ወይም የዚህ መንደር ነባር መሆንና የዚያ ቋንቋ ወይም የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን ዋጋ ሊሰጠው የማይገባ አጋጣሚ ነው። የሰብአ ዘመን አስተሳሰብ ከዚያም መጥቆ ሄዶ ዓለም አቀፍ ላይ ይድርሳል። በሰብአ ትካት አስተሳሰብ ያሉ ብሔርተኞችን በአንድ ጊዜ ወደዓለም አቀፍ አስተሳሰብ ይሸጋገራሉ ብለን አንገምትም፤ ለጊዜው ፍላጎታችንም አይደለም። ግን በሰላምና በብልጽግና ለመኖር ከብሔርተኛነትና ከሰብአ ትካት አስተሳሰብ ወጥቶ ዲሞክራት መሆን አማራጭ የሌለው እርምጃ ነው። በአካል የሰብአ ዘመን አባል ሆኖ በአስተሳሰብ ሰብአ ትካት መሆን፥ "የሚራቡት የማሰብ ችሎታቸው ዝቅተኛ ቢሆን ነው"  ለሚለው ጥናት ማስረጃ መሆን ነው። እንደማየው፥ ብሔርተኞች ከዲሞክራሲ ጋር ያላቸው ግንኙነት በፍቅርና በጥላቻ የተሳሰረ ነው። የዲሞክራሲ ዋና መለዮ ሰብአዊ መብቶችን ማስከበር ነው። በአሁኑ ሰዓት ከገዢዎቹና ከደጋፊዎቻቸው በቀር ይኸንን የማይቀበል ያለ አይመስለኝም። እዚህ ላይ ብሔርተኞችና ዲሞክራሲ ፍቅረኞች ናቸው። ግን  ሰብአዊ መብቶች የሚባሉት የግለሰብ ብቻ ናቸው ወይስ ማኅበሮችና ብሔረ ሰቦችም ሰብአዊ መብቶች አሏቸው? የላቸውም ከተባለ፥ ብሔርተኞች ዲሞክራሲን አይቀበሉም።  

መብት በመሠረቱ የግለሰብ ነው። ሆኖም ብሔረሰቦች በደፈናው መብት የላቸውም አይባልም። አቅም ካላቸው ቋንቋቸውንና ሌላ ሌላ ባህላቸውን ማዳበር መብታቸው ነው። ይኸንን በሥራ ላይ ለማዋል ሲሰበሰቡ ጸጥታቸውን መንግሥት ያስከብርላቸዋል። የአንድ ሀገር ሕዝብ ሆኖ ብሔረሰባዊ  ፓርቲ መመሥረት ግን ከሌላው ብሔረ ሰብ ጋር የጋራ ጥቅም የለንም ማለት ይሆናል። የፓርቲ መሠረቱ የግለሰብን ሕይወት በኢኮኖሚ እድገት ማሻሻል ነው። ለዚህ ዓላማ ፓርቲው ጉራጌ፥ አደሬ፥ ጉጂ፥ ወዘተ መሆን የለበትም።  ሆኖም፥ የብሔረሰብ አባላት በይፋ አድመው ድምጻቸውን ይጠቅመናል ለሚሉት ፓርቲ ሊሰጡ ይችላሉ። በዲሞክራሲ አስተዳደር ብሔርተኞች ብሔራቸውን የሚጠቅሙት በዚህ መንገድ ብቻ ነው።            
 
 

Saturday, February 15, 2014

ፓትርያርኩ ማኅበረ ቅዱሳን የጠራውን ሀገራዊ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጉባዔ ማገዳቸው ትክክል ነው!!


«መታገድ» የሚለውን ቃል በአሉታዊ ምልከታ ለማራገብ ካልተሞከረ በስተቀር ባለእባብ ዓርማው ማኅበረ ቅዱሳን የጠራውን ስብሰባ መታገድ በተመለከተ የሚያሳየው  የትርጓሜ እውነታ ግን በትክክለኛነቱ ተቀባይነት ያለው ውሳኔ ነው። ለዚህም ከበቂ በላይ ምክንያቶች አሉን።
1/ ማኅበረ ቅዱሳን የተባለውን ማኅበር ቤተ ክርስቲያኗ ያላቋቋመችውና ከብላቴ ጦር ምላሽ በጎ ፈቃደኞች የመሠረቱት ሲሆን የቤተ ክርስቲያኗ የውክልና ድርሻ ስለሌለው የትኛውንም የቤተ ክርስቲያን አባል በመጥራት መሰብሰብ አይችልም።
2/ ማኅበረ ቅዱሳን በጥቂት ደጋፊዎቹ ተነስቶ የሲኖዶስ አባል የሆኑትን ጳጳሳት በመጠምዘዝ፤ በማስፈራራትና በጥቅማ ጥቅም በማታለል ለራሱ ብቻ የሚጠቅመውን መተዳደሪያ ደንብ በማስጸደቅ ቤተ ክርስቲያንን ተለጥፎ በሕይወት ለመቆየት ከመቻሉ በስተቀር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደልማት ማኅበር ወይም እንደ በጎ አድራጊ ድርጅት ወይም እንደመንፈሳዊ ተቋም የመሠረተችው አይደለም። ስለዚህ አሀዳዊትና ሐዋርያዊት በሆነችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌላ ማኅበር ሊኖር ስለማይገባው ማኅበረ ቅዱሳን ማንንም የቤተ ክርስቲያን አባል በማደራጀት መንቀሳቀስ አይችልም።
3/ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከቅዱስ ሲኖዶስ አንስቶ በሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ የሀገረ ስብከት ጽ/ቤቶች በተዋረድ ያላት ተቋም ሆና ሳለ በሽብልቅ የገባው ማኅበር ይህንን የመዋቅር ሰንሰለት በጥሶ ለራሱ ዓላማና ግብ በመንፈሳዊ ካባ ተጠልሎ ስብሰባ የማካሄድ፤ የመጥራት፤ የማደራጀት፤ የመምራት ስልጣን የለውም።

4/ ማኅበረ ቅዱሳን በልማት ማኅበር ወይም በእርዳታ ድርጅት ወይም ራሱን በቻለ መንፈሳዊ ተቋምነት ወይም በሌላ መሰል ስያሜ የሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው አግባብ እውቅና አግኝቶ የተፈቀደለትንና የሚችለውን ሀገራዊና መንፈሳዊ ዓላማ ከማከናወን በስተቀር በሲኖዶስና በማኅበር የሚመራ ሁለት አስተዳደር ቤተ ክርስቲያኒቱ መሸከም የለባትም። ስለሆነም የፓትርያርኩ እግድ የስልጣን ተዋረድንና ኃላፊነትን ያገናዘበ በመሆኑ ትክክለኛ ውሳኔ ነው።
5/ ለወደፊትም ቢሆን ቁርጡ በታወቀ ቁመና የማኅበረ ቅዱሳን ማንነት መታወቅ አለበት። ስለሆነም እጅ እየጠመዘዘ ያስጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ ቀሪ ሆኖ በራሱ ግዘፈ አካል፤

   ሀ/ በሰንበት ትምህርት ቤቶች አወቃቀር የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበር ለመሆን ከፈለገ ያለውንና ያፈራውን ሀብትና ንብረት ለቤተ ክርስቲያኒቱ በማስረከብ ለሰንበት ተማሪዎች በተሰጠው የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ መመሪያ መሰረት መተዳደር አለበት።
  ለ/ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ለማደራጀት በወጣው ህገ ደንብ የመተዳደር ፈቃደኝነቱ ከሌለው የአባልነት ምልመላ፤ የገንዘብ አቅምን የማጎልበት፤ አስተዳደራዊ መዋቅሩን የመዘርጋትና የማንነት አቅም ማጎለበቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውጪ የመሆን አዝማሚያ እንዳለው እያየን ነውና ሀገሪቱ በምትሰጠው መብት በፍትህ ሚኒስትር ተመዝግቦ ሊንቀሳቀስ ይገባዋልና ቅዱስ ፓትርያርኩ የጀመሩትን መልክ የማስያዝ ጅማሮ ከፍጻሜ እንዲያደርሱ እንጠይቃለን።