(ክፍል አንድ)
በዓለማችን
ላይ ባሉ በኦርቶዶክሳዊያንና በካቶሊካዊያን ቤተ እምነቶች ውስጥ ከሰማያውያን ፍጥረቶች ውስጥ መላእክት በእምነት ህግጋቶቻቸው ከፍተኛውን ስፍራ
ይዘው ይገኛሉ። እንደጥንታውያኑ ቤተ እምነቶች አይሁን እንጂ በወንጌላውያን
ቤተ እምነቶችም ውስጥ ከተወሰኑቱ በስተቀር ስለመላእክት ያላቸው እምነትና እውቀት ጥቂት አይደለም። የሰው ልጆች ስለቅዱሳን መላእክት ያለን እውቀት ከፍ እንዲልና ትኩረት እንድንሰጥ
የሚያደርገን ምክንያት መኖሩ እርግጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችንም ስለመላእክት ምንነትና ተግባር በብዙ ቦታ ላይ ጠቅሶ የሚገኘው ያለምክንያት ባለመሆኑ በዚያ መነሻነት ስለመላእክት
ያለን ግምት ከፍ ቢል የሚያስደንቅ አይሆንም። እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ ውስጥ ይህንን ዓይነት መልእክት ማስቀመጡም ስለመላእክት
ያለን ግንዛቤ እንዲያድግ ስለፈለገ በመሆኑ ዘወትር ቃሉን በማንበብ እንመረመራለን። መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን መገለጥም ስለመላእክት
ያለን እውቀት ከፍ ይላል። ምክንያቱም በሰው ልጆችና በመላእክት መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ የጠበቀ በመሆኑ ስለመላእክት ማወቁ
እጅግ ጠቃሚ ነው።
በተመሳሳይ
መልኩም ስለመላእክት ያለን እምነትና በቅዱስ ቃሉ ላይ ያልተመሠረተ እውቀት እንደዚሁ የሚኖረንን ግንኙነት ከማበላሸቱም በላይ የሰው
ልጆችንም ይሁን መላእክትን በፈጠረው በእግዚአብሔር ላይ ያለንን የአምልኰ መንገድ ከመስመሩ ሊያወጣ ስለሚችል እጅግ ብርቱ ጥንቃቄ
የሚያስፈልገው ነገር መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል። የአምልኰ ስህተት እንደጊዜያዊ እክል የማይታይና በቀላሉ ሊታረም እንደሚችል የሚታሰብ
ባለመሆኑ ስህተቱ ዘላለማዊነት ባላት በነፍስ ላይ ዘላለማዊ ዋጋን የሚያስከፍል ጉዳይ ስለሆነ እጅግ ብርቱ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል።
ስለሆነም የእግዚአብሔርን
ቃል መሠረት ባደረገ መልኩ ስለመላእክት ያለን እውቀት መልካም የመሆኑን ያህል ቃሉን በሳተ መንገድ ያለን እውቀትም በተቃራኒው የጎደለ
ከሆነ ጎጂነቱ የከፋ መሆኑን ለማስገንዘብ እንዲቻል በተለያየ አቅጣጫ ስለመላእክት የሚሰጠውን ትርጉምና የእምነት አስተምህሮን በተመለከተ
ቅዱስ መጽሐፍን ዋቢ በማድረግ ለማሳየት እንሞክራለን።
1/ ስለመላእክት ማወቅ ለምን አስፈለገ?
እግዚአብሔር
በቃሉ አማካይነት ያስተምረናል። የቃሉ ምንጭ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ
ውስጥ ስለመላእክት እግዚአብሔር በብዙ ቦታ ተናግሯል፤ ተግባራቸውንም በተወሰነ መልኩ አሳይቶናል። እግዚአብሔር በቃሉ የሚነግረን
ለእኛ እንዲበጀን ስለሆነ ስለመላእክት እንድናውቅለት ይፈልጋል ማለት ነው። በመሆኑም ስለመላእክት ማወቅ ያስፈለገን እግዚአብሔር
በቃሉ አማካይነት ስለመላእክት እንድናውቅ ስለነገረን ነው። ስለመላእክት
ማንነትና ተግባር የነገረንን ካወቅን እግዚአብሔር ለምን እንደፈጠራቸው እንረዳለን። በዚህም የተነሳ ስህተት ላይ ከመውደቅ እንጠበቃለን።
ስለመላእክት ነግሮን ሳለ በእኛ ስህተት የተነሳ ከእውቀት ብንጎድል እግዚአብሔር ስላልነገረን ሳይሆን ቃሉን ለመስማት ካለመፈለጋችን
የተነሳ ይሆናል ማለት ነው። ማንም ስህተትን ቢያደርግ በተሰጠው ቃል መሠረት ተጠያቂነት አለበት። ስለሆነም ከተጠያቂነት ለመዳን
ስለመላእክት ማንነት ማወቅ ያስፈልገናል። ችግሩ ስለመላእክት ያለን ስህተት የሚነሳው እግዚአብሔር በቃሉ ከተናገረው ውጪ የራሳችንን
ግምትና ስሜት ስንጨምርበት ነው። ስለዚህ በዚህ ጽሁፍ የሚዳሰሰው ክርስቲያኖች ሁሉ በእጃቸው የያዙትን መጽሐፍ ቅዱስ ዋቢ በማድረግ
ነው። ሌላ የትኞቹም ስለመላእክት የተጻፉ አስረጂዎች መነሻቸው ወይም መለኪያቸው ቅዱሱ መጽሐፍ ከሆነ ስለመላእክት የሚኖረው እውቀት
ያልተዛነፈ ይሆናል።
«ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል አንተም እውቀትን ጠልተሃልና» ሆሴዕ 4፤6 እንዳለው እንዳንጠፋ ስለመላእክት ማንነትና
ምንነት ማወቅ አለብን።
2/ የመላእክት ተፈጥሮ
የመላእክትን
ተፈጥሮ በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ሰፊ የሆነ ማብራሪያ አይሰጠንም።
ያ ማለት ግን ስለመላእክት ተፈጥሮ ለአማኞች የሚበቃ ትምህርት
የለውም ማለት አይደለም። በመሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ የዘመን መነሻና ፍጻሜ ከሌለው ከእግዚአብሔር እውቀት ውስጥ ለሰው ልጅ በሚመጥነው
መልኩ የተሰጠው ቃል በመሆኑ ብዙ ማብራሪያ መስጠት አይጠበቅበትም። በዮሐንስ ወንጌል ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ዓለም ራሷ ሰሌዳ፤ ውቅያኖሶች
ሁሉ የብርዕ ቀለም ቢሆኑ መያዝ እንደማይችሉ ያስረዳናል።
ዮሐ 21፥25 «ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም
ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል»
ስለዚህ
የመላእክትን ማንነትና ተፈጥሮ ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስ የነገረንን ይዘን እየተማርን፤ ያልነገረንን ደግሞ በእምነት እንደተነገረን ያህል
ተቀብለን እንጓዛለን እንጂ ያልተነገረውን ለመናገር የግድ የራሳችንን ስሜቶችና ፍላጎቶች በመናገር በማንወጣው አዘቅት ውስጥ ገብተን
አንዳክርም። «ለጠቢብሰ አሐቲ ቃል ትበቍዖ» እንዲሉ።
ስለዚህ መላእክት በቁጥር ስንት ናቸው? አፈጣጠራቸው እንዴት ነው? ሥልጣናቸው? ስማቸው? ወዘተ የተመለከተውን ነጥብ ከተወሰኑት በስተቀር መጽሐፍ ቅዱስ ዝም ስላለ እኛም ዝም እንላለን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ያልጠራቸውን በጕስአተ ልብ አንጠራቸውም። ይልቅስ መጽሐፍ ቅዱስ የነገረንን መረጃ እንመልከት። በመዝሙረ ዳዊት ላይና
በዕብራውያን መልእክት ላይ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ስለመላእክት ተፈጥሮ ያስተምረናል።
መዝ 104፥4 «መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፥
አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል»
ዕብ 1፥7 «ስለ መላእክትም። መላእክቱን
መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ» ይላል።
ከዚህ
የእግዚአብሔር ቃል ተነስተን መላእክቱ መንፈስና የእሳት ነበልባል መሆናቸውን እንረዳለን። መናፍስትም፤ የእሳት ነበልባልም ያደረጋቸው እግዚአብሔር ነው። እነዚህ መንፈሳውያንና
እሳታውን መላእክት ከፍጥረታት መካከል አንዱ ክፍል ናቸው ማለት ነው። መላእክቱ መናፍስት (ረቂቃን) እና እሳታውያን መሆናቸው የሚያሳየን ነገር ቢኖር እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በፈጠረበት መንገድ
አልፈጠራቸውም ማለት ነው። መንፈስም፤ እሳትም በመሆናቸው መላእክት
እንደሥጋውያን እርጅናና ሞት አያገኛቸውም።
ኢዮብ 34፥15 «ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት ይጠፋል፥ ሰውም ወደ አፈር ይመለሳል» እንዳለው።
በሌላ
ቦታም መላእክት ሕያው መንፈሳዊ ፍጥረታት መሆናቸውን ቅዱስ ቃሉ ሲነግረን፤
ሥጋውያን የሆንን እኛ ትንሣዔ ሙታን እንደማይመለከታቸው እንደመላእክት
እንደምንሆን ተነግሮናል።
ማር 12፥25 «ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ
መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፥ አይጋቡምም»
ስለመላእክት አፈጣጠር የሚናገር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ውስጥ በተለምዶ «አክሲማሮስ» ወይም በመጠሪያው «ሔክሳሄሜሮስ» የተባለ መጽሐፍ አለ። በስድስት ቀን ውስጥ እግዚአብሔር
ስለፈጠራቸው ሃያ ሁለቱ ስነፍጥረታት አመጣጥ የተነገረበት ይህ መጽሐፍ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ያልተነገረውን በዝርዝር ይተርካል። በጽርዕ ቋንቋ «ሔክሳ» ማለት «ስድስት» ማለት ሲሆን «ሄሜር» ማለት «ቀን»
ማለት ነው። ይህም የስድስቱ ቀናት ሥነ ፍጥረትን ለማመልከት የገባ ቃል ነው። ሔክሳ ሄሜሮስን የበረሺት መጽሐፍ ባለቤቶች የሆኑቱ ዕብራውያን የማያውቁትን ይህን ከ4ኛው ክ/ዘመን በኋላ የተጻፈውንና ስለሥነ
ፍጥረት የሚናገረውን መጽሐፍ መጠቀም ሳያስፈልግ እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ በገለጠው በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ መላእክት ሞት የማያገኛቸው፤ እሳታውያንና መንፈሳውያን ፍጥረቶች ናቸው
ብሎ አፈጣጠራቸውን በአጭር ቃል መግለጽ ይቻላል።
3/ የመላእክት ጠባይና ግብር
ከላይ
ባነሳናቸው ርእሶች ላይ ስለመላእክት ማወቅ የሚገባንን ምክንያትና የመላእክትን ተፈጥሮ ከተረዳን ዘንዳ በቀጣይነት ሥራቸውን ልናውቅ
ይገባል። ይህም ማንነታቸውንና ከሰው ልጆች ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን እንደሆነ እንድናውቅ ያግዘናል። በዚህ መጠይቃዊ ርእስ ስር
የሚካተቱ ንዑስ ርእሶች አሉን።
ሀ/ የመልአክ ስማዊ ትርጉም
ቁጥራቸውን
ብዙ መሆኑን ለማመልከት «መላእክት» የምንላቸው ፍጥረቶች በነጠላ
ስያሜ «መልአክ» ስንል ምን ማለታችን ነው? የሚለውን መረዳት ይገባናል። ይህም የመላእክትን ሥራ ለማወቅ ይጠቅመናል።
ሥራቸውን ካወቅን መላእክት ከእኛ ጋር እኛም ከመላእክቱ ጋር ያለንን ግንኙነት ለመለየት ያግዘናል። ያለበለዚያ ከላይ ስናነሳ የቆየንባቸው
የማወቅ እድላችን እርስ በእርሱ ይምታታና ባለማወቅ ውስጥ ሆነን የምናውቅ ሊመስለን ይችላል። ይህም ትልቅ ጉዳት ያስከትላል።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (በማኅበረ ቅዱሳን ተሃድሶ ተብለዋል) «መጽሐፈ፡ሰዋስው፡ወግስ፡ወመዝገበ፡ቃላት፡ሐዲስ»
በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ 549 ላይ እንዲህ ሲሉ ስለ«መልአክ»
ግሳዊ ትንታኔን አትተዋል።
ድርጊቱን
ሲገልጡልን «ልኢክ፤ ልኢኮት(ለአከ፤ይልእክ) መላክ፤መስደድ» ማለት እንደሆነ በመግለጽ
አድራጊውን ሲነግሩን «ለአኪ ማለት ላኪ ወይም ሰዳጅ ማለት ነው ይሉናል። ተደራጊውን ደግሞ «መልአክ ማለት በቁሙ ሹመኛ፣ አለቃ ሲሆን የእግዚአብሔር መላእክቶችን ነጠላ የወል
ስም «መልአክ» የሚለው
እንደሚወክል
ያብራሩልናል።
በሌላ ቦታም የሰባ ሊቃናት ትርጉም እንደሚያስረዳን «ἄγγελος»
የሚለው የልሳነ ጽርዕ ትርጉም «ኤንጄሎስ»
ማለት «መልእክተኛ» ማለት እንደሆነ እናገኛለን። ዕብራይስጡም «מלאך אלהים » «ሜሌኽ ኤልሂም» ይለዋል። የእግዚአብሔር
መልዕክተኛ ማለት ነው።
ከዚህ የትርጉም ጽንሰ ሃሳብ የምንረዳው መላእክት ማለት የሚላኩ፣ የሚታዘዙ ፍጥረታት ሲሆኑ ላኪያቸው ወይም ሰዳጃቸው የፈጠራቸው እግዚአብሔር ነው ማለት ነው። ስለዚህ መልአክ
ማለት የሚላክ፤ የሚታዘዝ፤ ተላኪ፤ አገልጋይ፤ አመስጋኝ ማለት ነው። የአለቃ ኪዳነ ወልድ ትርጉም ከጽርዑና ከዕብራይስጡ ጋር ይስማማል።
ለ/ መላእክት
በሁሉም ሥፍራ በአንድ ጊዜ መገኘት ይችላሉን?
መላእክት ፍጡራን ናቸው ካልን ከፍጡርነት
ባህርይ አንጻር ውሱንነት መኖሩ እርግጥ ነው። በዚያ ላይ የሚላኩ፤ የሚታዘዙ፤ አገልጋዮች መሆናቸው በራሱ መነሻና መድረሻ እንዳላቸው
ያሳያል። መልእክት ከሚቀበሉበት መንበረ ጸባዖት ተነስተው ከሚደርሱበት የተልእኰ ሥፍራ ድረስ መውጣትና መውረድ አለባቸው ማለት ነው።
መላእክት የሚወጡበትና የሚወርዱበት መሰላል የእግዚአብሔር ኃይል እንደመሆኑ
መጠን መላእክቱን የፈጠረ አምላክ እንዲህ ሲል ይነግረናል።
ዮሐ1፥52 «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው
ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው»
በሁሉም ሥፍራ በአንድ ጊዜ የመገኘት ብቃት
ስለሌላቸው የመውጣትና የመውረድ አገልግሎት ይፈጽማሉ ማለት ነው። መላእክቱ ከታዘዙበት ሲወጡ ከነበሩበት ሥፍራ ለቀው ወደሌላ ሥፍራ ይሄዳሉ። ስለዚህ ለቀው ከወጡ በኋላ በምስጋና ከተማቸው ውስጥ በመልአካዊ ባህርያቸው አይገኙም
ማለት ነው። ከተልእኮአቸውም ሲመለሱ ከፈጸሙበት ሥፍራ ወደቀድሞ ቦታቸው ይመለሳሉ እንጂ በምስጋና ከተማቸውም ሆነ በተልእኰ ስፍራቸው
በአንድ ጊዜ የመገኘት ብቃት የላቸውም። ይህንን በደንብ የሚገልጽን የትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ነው።
አንድ ስሙ ያልተገለጸ የእግዚአብሔር መልአክ
በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ ሳለ ወደነብዩ ዳንኤል በተላከ ጊዜ የፋርስ መንግሥት አለቃ (የፋርስ መንግሥትን የያዘ ተቃዋሚ መንፈስ ማለት
ነው) ከተላከው መልአክ ጋር ለ21 ቀናት በመዋጋት ከዳንኤል ዘንድ ቶሎ እንዳይደርስ አግዶት ነበር። በኋላም ቅዱስ ሚካኤል ሊረዳው
ከመጣ በኋላ ከሌሎች የፋርስ መንግሥታት መናፍስት ጋር ሚካኤልን በዚያ ትቶት ወደተልእኰ ሥፍራው ወደ ነብዩ ዳንኤል መሄዱን ይነግረናል።
ዳን 10፤12-14 «እርሱም እንዲህ አለኝ። ዳንኤል ሆይ፥ አትፍራ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት
ይዋረድ ዘንድ ካደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ። የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሀያ
አንድ ቀን ተቋቋመኝ እነሆም፥ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት። ራእዩም
ገና ለብዙ ዘመን ነውና በኋለኛው ዘመን ለሕዝብህ የሚሆነውን አስታውቅህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ»
(የፋርስ መንግሥት አለቃ ማለቱ በፋርስ መንግሥት ላይ አድሮ ዳንኤልንና ወገኖቹን
የሚዋጋው መንፈስ አለቃ ማለት ነው) የዚህን እንዴትነት ወረድ ብለን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ እንመለከታለን።
ነገር ግን ከላይኛው ጥቅስ ውስጥ የምንረዳው
ቁም ነገር፤
* የተላከው መልአክ ለ21 ቀናት በውጊያ ላይ በመዘግየቱ ወደተላከበት ሥፍራ ለመድረስ አለመቻሉ፤
* ሚካኤል ለእርዳታ ከመጣለት በኋላ ወደዳንኤል ከመሄዱ በስተቀር ከሚካኤል ጋር በውጊያውም እየተሳተፈ፤ ወደዳንኤልም መልእክት እያደረሰ ባንድ
ጊዜ በሁለቱም ሥፍራ አለመገኘቱ የመላእክትን ውሱንነት ይገልጥልናል።
«ሚካኤልን በዚያ ተውኩት» ማለቱ የነበረበትን
ሥፍራ ለቆ መሄዱን ይገልጣል። ስለዚህ መላእክት በሁሉም ሥፍራ አይገኙም። መእክተኛ እንደመሆናቸውም መጠን ሳይላኩ አይሄዱም። በሁሉም ሥፍራ በአንድ ጊዜ መገኘት /Omnipotent/ የእግዚአብሔር የብቻው
ባህርይ ነው።
መላእክት የእግዚአብሔር ፍጥረት እንደመሆናቸው
መጠን ሁሉን የማወቅ ሥልጣን አልተሰጣቸውም፤ በሁሉም ሥፍራ በአንድ ጊዜ የመገኘት ብቃትም የላቸውም። በፈጣሪያቸው ሲላኩ ወይም ሲታዘዙ
ለአገልግሎት የሚሄዱት እግዚአብሔር ብቻ ስለሚያውቀው ሃሳብና ዓላማ ብቻ በመሆኑ ነው። የእግዚአብሔርነት ሙላት በሆነው ባህርይ መሠረት ሁሉን የመስማት፤ ሁሉን የማየት፤
ሁሉን የማወቅ ብቃት የላቸውም። ይልቁንም መላእክቱን በነዚህ ሦስት
ጥቅሶች ምስጋናን፤ ተአዝዞንና ተልአኪነትን ሲፈጽሙ እናያለን።
v መዝ 148፤2 «መላእክቱ ሁሉ፥ አመስግኑት ሠራዊቱ ሁሉ፥ አመስግኑት»
v መዝ 91፥11 «በመንገድህ
ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋል»
v ማቴ 13፥41 «የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን
ይለቅማሉ»
ሐ/ የመላእክት
ሥልጣንና ተልእኰ
መላእክት ተፈጥሮአቸው አንድ ዓይነት ቢሆንም
በክብርና በሥልጣን ልዩነት እንዳላቸው ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል።
ስለዚህ በክብር፤ በሥልጣንና በአገልግሎት የተለያዩ እንደመሆናቸው መጠን የመላእክቱ ተልዕኰና ሥልጣንም የተለያየ ነው። ለምሳሌ ቅዱስ
ሚካኤል የመላእክት አለቃ እንደሆነ በይሁዳ መልእክት (ምዕ 1፤ቁጥር9) ላይ ሚካኤል ከዲያብሎስ ጋር ስለመከራከሩ በተጠቀሰበት
አንቀጽ ላይ «የመላእክት አለቃ» ተብሎ ሥልጣኑ ተጠቅሷል።
በሌላ መልኩም ምንም እንኳን ስሙ በትክክል ባይገለጽም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙ፤ በበደልና
በኃጢአት ሙት በሆኑ በዚህ ዓለም ልጆች ላይ ለሚሠራው መንፈስ አለቃ የሆነ በአየር ላይ ሥልጣን የተሰጠው አለቃ እንዳለም ቅዱስ
ወንጌል ይነግረናል። ( ኤፌ 2፤1-2 ) በሌላ ቦታ
«ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፤ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና» 1ኛ ዮሐ 3፤8 ስለሚል በስም የተጠራውና በኃጢአት ላይ የሰለጠነው ይህ አለቃ ዲያብሎስ ነው
ማለት ነው።
ከዚህ ቃል ተነስተን መላእክትን ሥልጣንና
ተግባራቸውን በመመልከት የሚያመሰግኑ፤ የሚላኩትንና የሚታዘዙትን «ቅዱሳን» መላእክት ስንል፤ ለእግዚአብሔር በማይታዘዙ ላይ የሰለጠኑትና በኃጢአት ላይ ሥልጣን ያላቸውን
ደግሞ «ርኩሳን» ብለን ልንከፍላቸው እንችላለን። ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበትን አገልግሎት የሚፈጽሙ ሲሆኑ ርኩሳኑ
መላእክት ደግሞ በጥፋት ላይ የተሰማሩ ናቸው ማለት ነው።
ንስሐ በሚገባ አንድ ኃጢአተኛ የተነሳ በሰማይ ባሉ መላእክት ዘንድ ደስታ እንደሚሆነው
ሁሉ ( «እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት
ደስታ ይሆናል» ሉቃ 15፤10 )
እንደዚሁ ሁሉ ኃጢአተኛ ሲቀጣ ለተልዕኰው የሚወጡ ክፉዎች መላእክት ስለመኖራቸውም
(«የመዓቱን መቅሠፍት በላያቸው ሰደደ መቅሠፍትን መዓትንም መከራንም በክፉዎች መላእክት
ሰደደ » መዝ 78፤49 ) ሲል ክፉዎች መላእክት መኖራቸውን
እንረዳለን።
ስለዚህ በሰው ልጆች ወደእግዚአብሔር መመለስ
የሚደሰቱ ቅዱሳን መላእክት እንዳሉ ሁሉ መቅሰፍትን፤ መዓትንና መከራን
የሚያመጡ ክፉዎች መላእክትም አሉ ማለት ነው። ከዚህ ተነስተን መላእክትን በሁለት ልንከፍል እንችላለን።
መ/ ቅዱሳን መላእክትና
ክፉዎች መላእክት
« ንቁም በበኅላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ»
በማለት ያረጋጋው ገብርኤል ነው፤ የካደውና እኔ ፈጣሪ ነኝ ብሎ የታበየው ሣጥናኤል ነው የሚል አስተምህሮ አለ። በሌላ ጊዜም ይህ ገብርኤል መልአክ የወረወረው ሰይፍ እስከምጽአት ድረስ ወደመሬት ውስጥ
እየተምዘገዘገ እየወረደ ነው የሚልም ትምህርት ይሰማል። ገብርኤል «ንቍም በበኅላዌነ» ማለቱን በወቅቱ የሰማና ጽፎ ያቆየልን የለም።
መጽሐፍ ቅዱሳችንም ይህን ስለማለቱ አልገለጸውም። ስለዚህ እግዚአብሔር በፈቃዱ ሳይነግረን ወደተወው ጉዳይ ገብተን አንዳክርም። ነገር
ግን በክፋትና በኃጢአት ላይ የሰለጠነው ዲያብሎስ በትዕቢት ከማዕርጉ መውረዱን መጽሐፍ ስለሚነግረን ያንን በመቀበል «አለቃ» እንደመባሉ
መጠን በአለቅነቱ አብረውት የተሰለፉ ሠራዊት መኖራቸውንም እንገነዘባለን ።
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ቅዱሳን መላእክት የእግዚአብሔርን ፈቃድና
ደስ የሚያሰኘውን አገልግሎት ፈጻሚዎች ሲሆኑ ክፉዎቹ መላእክት ደግሞ የጥፋትና የዐመጻ ኃይሎች ናቸው። ቅዱሳኑ መላእክት ቅዱሳን
ያሰኛቸው ዋናው ምክንያት እግዚአብሔርን በመፍራት የሚያገለግሉ፤ ፈቃዱንም ለመፈጸም ፈቃደኞች የሆኑ፤ በተቀመጡበትን ሥፍራ በአምልኰ
ጸንተው የተገኙ ናቸው። ክፉዎቹ መላእክት ደግሞ በእግዚአብሔር ሥልጣን ሥር ቢሆኑም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ያፈነገጡ፤ የተቀመጡበትን
ሥፍራ ትተው የወጡ የጥፋት ኃይሎች ናቸው።
ይሁዳ 1፤6 «መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ
የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል»
በቅዱሳኑ መላእክት ላይ የአለቅነት ሥልጣን
ያለው ቅዱስ ሚካኤል ነው።
ራእይ12፥7 «በሰማይም
ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም»
ዳን 12፥1 «በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ
ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን
ይሆናል በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል»
በክፉ መናፍስት ላይ ሥልጣን ያለው ደግሞ
ሰይጣን (ተቃዋሚ)፤ እባብ (ጠላት)፤ ዲያብሎስ (ከሳሽ) የተባለው
ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዘንዶ ነው። ( ራእይ 12፤9 ) ከቅዱሳኑ
መላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልና ከመላእክቶቹ ጋር ይኼው ዲያብሎስ
ተዋግቶ ተሸንፏል።
ስለዚህም ይህ የተሸነፈው ዲያብሎስ በዚህ
ዓለም ላይ ከነሠራዊቱ አሳች ሆኖ ይገኛል። በዚህ ምድር ላይ ለሚፈጸመው ጥፋት፤ ኃጢአትና ዐመጻ ሁሉ ዋናው አስፈጻሚ ይህ ሰይጣን
የተባለውና ሠራዊቱ ናቸው።
3/ የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት
ይቀጥላል%