Wednesday, September 17, 2014

በምድራችን ላይ በክፉ መንፈስ ተነድተው ሕዝብን ያሳሳቱ ሀሰተኛ ክርስቶሶች!

ክፍል ሁለት )

ዘመኑ የቀሳጥያን፤ የሀሰተኛ ትምህርትና የክህደት መፍለቂያ መሆኑን የበለጠ ለማስረዳት ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩትን ማሳየት ጠቃሚ ይመስለናል። የሰው ልጅ በወንጌል ላይ የተገለጠውን ክርስቶስን ሳይሆን በሰው ብልሃት የተቋቋመችውን ምድራዊ ተቋም፤ የሰዎች ድርጅት፤ የአስተምህሮ መንገድና ስብከት እየተከተሉ ከእውነት ሲያፈነግጡ ማሳየት ተገቢ እንደሆነም ይሰማናል። ዛሬም ቢሆን ሰዎች የድርጅት፤ የተቋምና የሰዎች ተከታዮች ሆነው ይታያሉ። እውነታው ግን ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ የመሠረተው አንድም የእምነት ድርጅት ወይም ተቋም  አለመኖሩ ነው። ጲላጦስ ከመሰቀሉ በፊት ኢየሱስን «እውነት ምንድር ነው?» ብሎ ስለሆነው ነገር ጠይቆት ነበር። ( ዮሐ 18፤38) እውነቱ ግን ሰዎች «እስኪ ራሱን ያድን» እያሉ እየተዘባበቱበት የሰቀሉትን ኢየሱስን ማመን ነበር። አይሁዳውያን ሰዎች ራሷን ማዳን የማትችል ምድራዊት የእምነት ተቋም ስለነበራቸው ከእምነት እንጂ ከተቋም ስላልሆነችው የኢየሱስ ስብከት ጆሮአቸውን አልሰጡም። ስለዚህም እውነቱ አመለጣቸው። ዛሬም ሰዎች ክርስቶስን እናምናለን ቢሉም ከተቋምና ከድርጅት ስብከት አልወጡም። በዓለም ላይ በተለያየ ስም የተከፋፈለው የእምነት ተቋም መሠረቱ በሰዎች አስተምህሮ ላይ የተንጠላጠለ ነገር ግን ክርስቶስ ያጠለቀ በሚመስል ድርጅት የሚጠራ መሆኑ ነው። እውነቱ ግን «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም» ባለው ቃል ጸንቶ መገኘት ብቻ ነው። የምናምነውን ነገር በወንጌል መነጽር እንመርምረው። ወንጌል ካስተማረው ውጪ የሆነው ሁሉ ከሰይጣን የተገኘ ነው።

 
ሚዝራ ጉላም አህመድ (1835-1908)

 ይህ በሃይማኖቱ እስላም የሆነ ሕንዳዊ ዜግነት የነበረው ሰው በአንድ ወቅት ራሱን እንዲህ ሲል ገልጾ ነበር። እስላሞች በመጨረሻው ቀን ከሰማይ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት «ማህዲ» የተባለውን ነብይና ክርስቲያኖች ለፍርድ ዳግም ይመጣል ብለው የሚጠባበቁት «ኢየሱስ»ን የምወክል ስሆን እነሆ ሁለቱም በእኔ ውስጥ በሥጋ ተገልጸዋልና ተከተሉኝ በማለት ሲለፍፍ ቆይቷል። ማሳሳት ጥንተ ግብሩ የሆነው ሰይጣን በህንዳዊው አህመድ ውስጥ አድሮ እሱን ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች መሳሳት ምክንያት ሆኖ ከእስልምና ሴክት/ክፍል/ አንዱ የሆነውን «አህመዲያ» የተባለው ቅርንጫፍ ፈጥሮ በማለፍ ዛሬም ድረስ ከ20 ሚሊዮን ያላነሱ አባላትን በዓለም ዙሪያ ማፍራት ችሏል።

ሎ ደ ፓሊንግቦኸር (1898- 1968)

በዜግነቱ ኔዘርላንዳዊ የሆነው ፓሊንግቦኸር በሙያው የተዋጣላት ዓሳ አጥማጅ ነበር። በዓሳ አጥማጅነት ሥራው ከሱ ዘንድ ዓሳ ለመግዛት ለሚመጡ ሸማቾች በትንሹ የጀመረውን ስብከት አሳድጎ በስህተት ሰው ወደ ማጥመድ ሥራ አሳደገው። ተከታዮችን ማፍራቱን እንዳረጋገጠ የዓሳ ጀልባውን በመሸጥ ስብከቱን የሙሉ ጊዜው ሥራው በማድረግ የቀጠለ ሲሆን ዓለም ከክፉ ነገር ሁሉ የምትድነው እኔን በማመን ነው እያለ በየጎዳናው ይለፈልፍ ነበር። ትምህርቱን እንደትክክለኛ አድርገው የተቀበሉ ተከታዮቹ ትልቅ የመኖሪያ ቤት ገዝተው የሰጡት ሲሆን በስተመጨረሻም እኔ «ኢየሱስ» ነኝ በማለት ስብከቱን ገፍቶበታል። አንዳንዶች ይህ ሰው ከሀዲ ነው ብለው ቢያወግዙትም ፓሊንግቦኸር «እግዚአብሔር» ወደመሆን ይለወጣል በማለት ይከራከሩለት የነበሩ ተከታዮችን ማፍራት ችሏል። ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ አግብቶ በመፍታት የሚታወቀው ይህ ቀሳጢ እንኳን ሌሎችን ሊያድን ይቅርና ራሱን ከሞት ማዳን ሳይችል ቀርቶ እስከወዲያኛው አሸልቧል።

ኃይለሥላሴ (1892-1975)

 የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ ራሳቸውን እንደመሲህ አድርገው ባይቆጥሩም መሢህ ናቸው የሚሏቸው ወገኖች አሉ። ንጉሡ በአንድ ወቅት በሳቸው ዙሪያ ስለሚባለው ነገር ተጠይቀው «እኛ ሰው ነን እንጂ መሲህ አይደለንም» ብለው የመለሱ ቢሆንም ተከታዮቻቸው በንጉሡ ምላሽ ዙሪያ የሰጡት ማስተባበያ «የኛ መሲህ ያለውን ትህትና ተመልከቱ» በማለት የንጉሡን ምላሽ ከአትህቶ ርእስ ጋር በማያያዝ ለማሳመን ቢሞክሩም እውነታው ግን አፄው መሲህ አለመሆናቸው ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለውለታ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ ለመታሰቢያቸው አርኬ እና መልክእ በመድረስ በነግህና በሰርክ ጸሎት ታስባቸው ነበር። አንዳንዶች የዋሃን አፄው አይሞቱም የሚል ግምት የነበራቸው ቢሆንም ደርግ የገደላቸው መሆኑ ይታወቃል። ከጃማይካ ህዝብ 5% የሚሆነው የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታይ ሲሆን በአሜሪካም ብዙ አባላት አሉት።

ኤርነስት ኖርማን (1904-1971)


  አሜሪካዊ የኤሌክትሪካል ኢንጂነር ባለሙያ የነበረና (ዩራንየስ አካዳሚ ኦፍ ሳይንስ) መስራች የሆነ ሰው በአንድ ወቅት ከሙያው ውጪ እብደት መሰል ስብከት ጀምሮ ነበር። ከዚህ በፊት በዚህ ምድር ላይ የተገለጸው «ኢየሱስ» እኔ ነበርኩ። ወደሰማይ ባርግም በዚህ ምድር ላይ በሊቀ መልአክ ሩፋኤል አምሳል ነበርኩኝ እያለ ቢቀላምድም ተከታዮችን ከማፍራት የከለከለው ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ ይህ የዘመኑ ቀሳጢ እንኳን ለሌሎች ሊተርፍ ይቅርና ለራሱም መሆን ሳይችል ቀርቶ በጉሮሮ ህመም ሲሰቃይ ቆይቶ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ክሪሽና ቬንታ (1911-1958)

 ቬንታ በሳንፍራንሲስኮ የተወለደው ሲሆን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የአሜሪካ ወታደር በመሆን አገልግሏል። ከተመለሰም በኋላ ቀደም ሲል አቋቁሞት የነበረውን ተቋም በማንቀሳቀስ 1948 ዓ/ም «የጥበብ፤ የእውቀት፤ የእምነትና የፍቅር ፏፏቴ» የተሰኘ የክህደት ድርጅት ሥራውን ጀምሯል። ቬንታ የክህደት ደረጃውን በማሳደግ «እኔ ኢየሱስ ነኝ» ከማለቱም ባሻገር የማኅበሩ አባል ለሚሆኑ ሰዎች «ያላችሁን ሀብትና ንብረት ለማኅበሩ ገቢ አድርጉና ሰማያዊ መዝገብ አከማቹ» በማለት ሀብታቸውን በመሰብሰብ ለበጎ አድራጎት ሥራ ለማዋል የሞከረ ቢሆንም ሀብታቸውን ተሞልጨው፤ ሚስቶቻቸውን በቬንታ የማማገጥ ተግባር የተፈጸመባቸው ሁለት ተከታዮቹ በቂም በቀል ተነሳስተው ቦንብ በማፈንዳት አብረው ሊሞቱ ችለዋል። የክሪንሽና ቬንታ የክህደት ተግባርም እስከወዲያኛው በዚያው አክትሟል።

አህን ሳንግ ሆንግ (1918- 1985)

 በደቡብ ኮሪያ የተወለደ ይህ ሰው  በ1964 ዓ/ም «የአዲስ ኪዳን ፋሲካ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን» የሚል የሃይማኖት ተቋም መስርቶ ነበር። በኋላ ላይ ደግሞ «ዓለም አቀፍ የተልእኮ ማኅበር የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን»  የሚል ሁለተኛውን ድርጅት አቋቁሟል። ሳንግ ሆንግ እሱ የኢየሱስ ዳግም ምጽአት ምልክት መሆኑን ይሰብክ ነበር። በአዲስ ኪዳን ፋሲካ ቤተ ክርስቲያኑ እንደመምህር ሲቆጠር በዓለም አቀፍ የተልእኮ ቤተክርስቲያኑ ደግሞ እንደእግዚአብሔር ይቆጠራል።  የቤተክርስቲያኒቱ ዋና አመራር የሆነችው ዛንግ ጊልጃህ የተባለችው ሴት በገላትያ 4፤26 ላይ የተመለከተውን ትንቢት የምታሟላ እሷ ናት ስለሆነች «የኢየሩሳሌም እናት» ወይም «የእግዚአብሔር እናት» ተብላ ትጠራለች።
የቤተ ክርስቲያኑ መሥራች ሳንግ ሆንግ ደግሞ «እግዚአብሔር አብ» ተብሎ ይጠራል።


ሱን ሚዩንግ ሙን (1920- 2012)


 በሰሜን ኮሪያ ተወልዶ በደቡብ ኮሪያ ያደገው ሙን «የውህደት ቤተ ክርስቲያን» መሥራች ሲሆን ራሱን ሁለተኛው ኢየሱስ እንደሆነና  ከዚህ ቀደም ኢየሱስ በሥጋ ተገልጦ ሳለ ሳይጨርሳቸው የሄደውን ጉዳይ የሱ መገለጽ ማስፈለጉን በአደባባይ የሚናገር ሰው ነበር። ሚስተር ሙን ባለቤቱን « ሃክ ጃን ሃን»ን የሚጠራት አዳምና ሔዋን ያበላሹትን ዓለም በማጽዳት መልካም ቤተሰብን በዓለም ላይ ለመመሥረት የተፈጠረች ናት በማለት ያሞካሻት ነበር። ሙን «የተባረከ የኅብረት ጋብቻ» በሚል ዘመቻ በአንድ ቀን እስከ 30 ሺህ የሚቆጠሩ ጥንዶችን  አሜሪካ ባለችው በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ጋብቻ በማስፈጸም ዝናው ይታወቃል። ሙን በአሜሪካን ሀገር ሳለ በፈጸመው የታክስ ማጭበርበር ወንጀል ተከሶ 18 ወራት ተወስኖበት፤ ከዚህ ውስጥ የ13 ወራት እስራቱን ቅሞ በአመክሮ ሊለቀቅ ችሏል። ሱን ሙን  ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ሃብት ያለው ሲሆን የተለያዩ ኮርፖሬሽኖችንና የአክሲዮን ማኅበራት አሉት። ሃሳዊው ሙን በተወለደ በ92 ዓመቱ በኒሞንያ በሽታ ሞቶ እስከወዲያኛው ተቀብሯል። እሱ ቢሞትም በሱ የሀሰት ትምህርት የተታለሉ 4 ሚሊዮን አባላት በተለያዩ የዓለም ሀገራትን ለማፍራት ችሏል።

ይቀጥላል%