አበው ዘይቤያዊ ምሳሌ ሲሰጡ፤ ፍሬ ነገሩን ሊገልጥ የሚችል
ጥሩ ኃይለ ቃል ይጠቀማሉ። በአንድ ዐረፍተ ነገር ብዙ ሐተታ ሊወጣው በሚችል መልኩ የጉዳዩን ብስለትና ጠጣርነት በደንብ ያሳዩበታል።
ለዚህም ነው «ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡት፤ ውሃ ቢያንቅ በምን ይውጡት?» በማለት መሆን የማይገባው ነገር ሆኖ ቢገኝ መፍትሄው
ግራ የሚያጋባ እንደሆነ ለማስረዳት ይፈለጉት። አዎ፤ በዘመነ አበው ምላጭ፤ እባጭ እንዲፈነዳ፤ የተቋጠረው መግል እንዲፈርጥ ይበጡበት ነበር። በገጠሪቱ
ኢትዮጵያ ዛሬም አልፎ፤ አልፎ ይሰራበታል። ነገር ግን ምላጭ ራሱ
ቢያብጥ በምን ይቆረጣል? ውሃስ ቢያንቅ በምን ማወራረድ ይቻላል? ግራ የሚያገባ ነገር ነው። መሆን የሌለበት ሆኖ ሲገኝ ያስገርማል፤
ያስደነግጣል፤ መፍትሄውም ሩቅ ይሆናል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታየ ያለው ድርጊት የዚሁ ምሳሌ ተመሳሳይ ነገር
ነው። በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ የቅዱስ ሲኖዶስ መንበር ከተመሠረተ ከ50 ዓመታት እጅግም ያልዘለለ ጊዜን ያስቆጠረ ቢሆንም በዚህ
አጭር እድሜው 50 ጉድ አሳልፏል። ፓትርያርኳን አሳልፋ በመስጠት ለደርግ ጭዳ ማቅረቧም በማስረጃ የተረጋገጠ እውነት ነው። ፓትርያርክ
አውርዳ ፓትርያርክ ሾማለች። ለሁለት የተከፈለ ሲኖዶስም የያዘችው በዚሁ አጭር እድሜዋ ነው። የሐዋርያትን መንበር ተረክቤአለሁ የምትለዋ
ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያት እንዳደረጉትና የራሱን ሥፍራ በለቀቀው በይሁዳ ምትክ እንደሾመችው ሐዋርያ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ እጣ ማጣጣል
ሲገባት እንደፖለቲካ የካድሬ ምርጫ በሰውኛ አሳብና እንደተሰጣቸው ተልእኮ በሚመለመሉ ሰዎች ምርጫ መሾሟም የዚሁ የአጭር ዘመን ታሪኳ
አንዱ ክፍል ነው።
ነውርና ነቀፋ የሌለበት፤ ራሱንና ቤተሰቡን በአግባቡ ስለመምራቱ በምእመናንና ምእመናት የተመሰከረለት አገልጋይ ሰው ኤጲስ
ቆጶስ እንዲሾም ቃለ ወንጌሉ ቢናገርም ከንባብና ከአንድምታው በዘለለ ተግባር ዳገቷ ቤተ ክርስቲያን ሆና ለሰሚ የሚቀፍ፤ ለሚያውቁት
የሚያሳፍር ሹመት እየፈጸመች በመገኘቷ እነሆ ጥቅምትና ግንቦት በመጣ ቁጥር የዘራችውን እያጨደች ትገኛለች።
«መልካም ዘር መልካም ፍሬ ያፈራል» እንዲል ወንጌል
የዚህ ተቃራኒ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ስለመዘራቱ ደግሞ ፍሬውን ሲኖዶስ በመጣ ቁጥር ጭቅጭቅ፤ ንትርክ፤ ሁከትና አድማ ሲያስተናግድ
ማየት የተለመደ ሆኗል። ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ለትውልድ የፈውስና የምሕረት መልእክተኛ መሆን የሚገባው አካል ለራሱ ከፈውስም
ሆነ ከምሕረት ስለራቀ መሆን በማይገባው ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።
«ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡታል፤ ውሃስ ቢያንቅ በምን ይውጡታል?» ማለት ይኼ ነው። ሰው በልቡ መታደስ ካልተለወጠና
የማይሞተውን የሞት አሸናፊ ካልለበሰ አዲስ ፍጥረት እንደማይሆን ሐዋርያው በመልእክቱ ነግሮናል። ካልተለወጠና የቀድሞ ግብሩን ካልተወ አሮጌነት ደግሞ አብሮት ያለው ማንነት
በክፋትና በተንኮል ተግባር እየተገለጠ በዘመኑ ሁሉ ይቀጥላል። ዛሬም በሲኖዶስ ጉባዔ ላይ የሚታየው ችግር ሁሉ የውስጥ ማንነቱ ማሳያ
መስታወት ነው። ሰው የሌለውን ውበት ከየትም ሊበደር አይችልም።
ሰሞኑን እየተካሄደ ባለው ሲኖዶስ (ቅዱስ ለማለት ይከብደኛል) ምክንያቱም ካልተወሻሸንና ሞራል እንጠብቅ ካልተባለ በስተቀር
መንፈስ ቅዱስ የሁከትና የንትርክ አምላክ ስላይደለ ቅዱስ ለማለት ይከብዳል። በስብሰባው ላይ እየታየ ያለው ኢ-መንፈሳዊና ኢ-ሥነምግባራዊ
ድርጊት ከስምና ከማዕርግ እድገት በስተቀር ያልተለወጠ ማንነት የተንጸባረቀበት እጅግ አሳፋሪና አሳዛኝ ክስተት የታየበት ስለሆነ
ነው።
«ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን
ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ
ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን?» 1ኛ ቆሮ 6፤1-2
በቅዱስ ስም ተሰብስቦ፤ በዓለማውያን ምናልባትም እግዚአብሔርን በማያውቁ ዐመጸኞች ፊት የጉባዔ ዳኝነት ከመጠየቅ ወዲያ
ለሲኖዶስ ምን ሞት አለ? አሁን እውነት ሕይወት ያለው ሲኖዶስ የሚባል አካል አለ ማለት ነው? ይህ ሁሉ የሆነውና እየሆነ ያለው
በሞተ አካል ውስጥ ያለው የሙት መንፈስ ፍሬውን እያፈራ በመገኘቱ የተነሳ ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ፤
«በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን
ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው
የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ
እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ» በማለት የተናገረው። የሐዋ 20፤28-30
መንጋው ተበትኗል፤ ለሚጠፋው በግ የሚራራ እረኛ የለም፤ ቤተመቅደሱ በርግብ ሻጮችና በለዋጮች ተሞልቷል፤ እርስ በእርሳቸው
የሚነካከሱና የሚበላሉ ሆነዋል፤ ነገር ግን በሕይወት አለን ይላሉ። ለሥልጣን ሽሚያ፤ ለመፈንቅል፤ ለቡድን አሸናፊነት፤ ለማኅበር
የበላይነት ይጋደላሉ።
በየተመደቡበት ሀገረ ስብከት እንደነገሥታት የሚሰጣቸው
ስግደት ሳይጎድል፤ እንደሰማያዊ ሹም ሆነው መታየታቸው ሳይጠፋ ምንም የሰሩትና ያለሙት በሌለበት ሁኔታ ዓይናቸው ሁል ጊዜ የሚያየው
እዚያ ጣሪያ ላይ ነው። ጣሪያው ደካማ ይሁን ሰነፍ የሚያስቀምጠው አንድ ሰው ነው። ጣሪያው ላይ ሰው ሲቀመጥ ያልታገሉ ፈራህያን
ዛሬ የሚያደቡት ምን ለማግኘት ነው? ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስበው? ተጨንቀው? በጭራሽ አይደለም።
ጳጳሳቱ ሰው ከመቅጠርና ከማባረር ባለፈ ሚሊዮን ተከታዮቻቸውን
አሰልፈው ትምህርት ቤት፤ ጤና ጣቢያ፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ፤ የብሎኬት ማምረቻ፤ የእንጨት መሰንጠቂያ፤ የመስኖ ልማት፤ የልብስ ስፌት፤
የጧፍና ሻማ ማምረቻ፤ የአልባሳትና ቅርሳ ቅርስ ተቋም፤ የዶሮና የከብት እርባታ፤ የዳቦ መጋገሪያ፤ የካህናት ማሰልጠኛ፤ ኮሌጆች፤
ዩኒቨርሲቲዎች፤ የህጻናት ማሳደጊያ፤ የአረጋውያን መጦሪያ ለምን አያቋቁሙም? ለምን አይሰሩም? ማን ከለከላቸው?
ከ15 ሚሊዮን ያልበለጠ ተከታዮች ያሏት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት በረሃውን ገነት ያደረጉት፤ ምርትና
ሃብታቸው የተትረፈረፈው እንደእኛ ጳጳሳት በፎጣ በመሸፋፈን ሳይሆን በአጭር ታጥቀው ከእስላም ሰይፈኞች ጋር በመታገልና ተግተው በመስራታቸውና
በማሰራታቸው ነው። ከላይ ከተዘረዘሩት ውስጥ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ያልሰራችው የልማት ስራ የለም። በጀት ተመድቦላቸው፤ ባለሙያ ተቀጥሮላቸው ሳይሆን መነኮሳቱን፤ ካህናቱን፤ ምእመናኑን
በማስተማርና በማሰልጠን በራስ አገዝ የልማት ተሳትፎ የተመሰረተ ነው።
የኛዎቹ ለግንቦቱ ጉባዔ ከጥቅምት ጀምሮ ከመዶለትና ለጥቅምቱ
ጉባዔ ደግሞ ከግንቦት ጀምሮ ሴራ ከመጎንጎን በስተቀር በሀገረ ስብከታቸው የልማት ርእይ፤ እቅድና ግብ በጭራሽ የላቸውም። ከሐውልት
ምርቃት፤ ከቀብር ክፍያ፤ ከክርስትና፤ ከጋብቻ፤ ከፍትሃት፤ ከጸበል፤ ከሰበካ ጉባዔ አባልነት ወዘተ የሚሰበስቡትን ሚሊዮኖች ብር
ለደመወዝና ለስራ ማስኬጂያ ከማዋል ባለፈ ተመልሶ ለሕዝቡ ልማት የዋለው ምን ያህሉ ነው? በደቡብ ክልል አካባቢ ያሉ የኦርቶዶክስ
ምእመናን «እናንተ አምጡ እንጂ እንደሌሎቹ እንኩ አታውቁም» ማለታቸውን ስንሰማ የኛዎቹ መስጠትን ሳይማሩ አምጡን ከየት ለመዱት
ያሰኛል።
በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውድቀትና ማሽቆልቆል ተጠያቂዎቹ ጳጳሳቱ ናቸው። ለመንጋው መበተን፤
ለስርቆትና ሥነ ምግባር ጉድለት ኃላፊነቱን መውሰድ አለባቸው። የታጣው መሪ እንጂ ለመመራት ፈቃደኛ፤ ለመስጠት እጁን የማይዘረጋ ምእመን የለም። ደግሞስ እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመን እጁን
የሚዘረጋ አለ እንዴ?
በሀገረ ስብከታቸው ልማት ሳያሳዩ ወደላይ መንጠራራት ስንፍናቸውን
እንጂ አዋቂነታቸውን አያመለክትም። ጳጳሳቱ ለድክመታቸው ምክንያት ፓትርያርኩ ላይ አመልካች ጣታቸውን ከመቀሰራቸው በፊት እኔ በሀገረ
ስብከቴ ምን ሰራሁ? ብለው ራሳቸውን ይጠይቁ። ብዙዎቹን ጳጳሳት ከምንኩስና ጀምሮ ስለምናውቃቸው ስለማንነታቸው ነጋሪ አያሻንም።
ከታች ጀምሮ ያልተገነባ ስብእናና ችሎታ ደረጃቸው ስላደገ ባንዴ አብሮ አይመነደግም። ቁም ነገሩ እንደእኛው ችሎታ የሚያጥራቸው ሰዎች
መሆናቸው ሲሆን አሁን አለቃቸውን ማስቸገር ቀደም ሲል በአለቅነታቸው ካዳበሩት ችግር የተማሩት ብቸኛ እውቀት ይመስለኛል። ከዚያ ባሻገር በልማታቸው ለሕዝቡ የመኖር ተስፋ ወይም በጸሎታቸው ለሀገር የሚተርፉ
ሆነው 15 ሚሊዮን ሕዝባችንን ከድርቅ ሲታደጉ አላየንም። ከመንጋ ጳጳስ እንዴት አንድ ኤልያስ ይጥፋ? ተግባር እንጂ ስም አላልኩም።
በግንቦቱ ሲኖዶስ ተሰብስበው በፓትርያርክ ማትያስ የችሎታ ማነስ ላይ ከመሳለቅ አስቀድመው በራሳቸው የአቅም ማነስ ላይ
ቢወያዩ የተሻለ ነበር። ምሳሌ እንስጥ፤ ከ1985 ዓ/ም ጀምሮ
23 ዓመት በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው የቆዩት የአሁኑ አባ ጎርጎርዮስ፤ ሟቹ አቡነ ጎርጎርዮስ ከመሰረቱት የዝዋይ
ካህናት ማሰልጠኛና የአትክልት ልማት ወዲህ ስንት ማሰልጠኛ አቋቋሙ? ስንት የልማት አውታር ተከሉ? እውነታው ምንም ነው። አባ ቄርሎስስ
በሰሜን ወሎ ሀ/ስብከት ስንት የካህናት ማሰልጠኛ፤ ስንትስ የእደ ጥበብ ተቋም ተከሉ? ስንት የከብት ማድለቢና የዶሮ እርባታ አቋቋሙ?
ማን እንዳያደርጉ ከለከላቸው? ሟቹ አባ ጳውሎስ ወይስ ሕያው አባ ማትያስ?
በምሥራቅ ጎጃምና በምዕራብ ጎጃምስ ምን ተሰራ፤ በሰሜንና
ደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከትስ ምን ልማት ተቋቋመ? በአጭር ጊዜና በረጅም ጊዜ እቅዳችሁ ምን አሳካችሁ? በደን ልማት ላይ ሕዝቡን በማስተባበር በዚህ ዓመት ስንት ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል
ተዘጋጅታችኋል?
እርግጥ ነው ጳጳሳቱ በሌላ የሥራ መስክ ላይ አልቦዘኑም። የግል ቤታቸውን ገንብተዋል፤ ዘመናዊ መኪና አስገዝተዋል። በባንክ
ገንዘባቸውን አጭቀዋል። ዘመድ አዝማዳቸውን በየቤተ ክርስቲያናቱ ቀጥረዋል።
በአንድ ወቅት መንግሥቱ ኃ/ማርያም ሚኒስትሮቹን ሰብስቦ « የምትነዱትን የመኪና ዓይነትና ብዛት፤ ያላችሁን ቤት፤ የምትውሉበትን፤
የምታድሩበትን ቦታና ጭምር ይኽ ሕዝብ ብታምኑም ፤ ባታምኑም አሳምሮ ያውቃል» ብሏቸው ነበር። ሕዝብ ምን የማያውቀው አለ? ተከድኖ ይብሰል ብለነው እንጂ የኛዎቹን ስንቱን
ጉድ እናውቃለን።
አሁን እነሱ ምን ስለሆኑ ነው፤ እንደራሴ ይሾም የሚሉት?
እንደራሴ ምን ያድርግላቸው? መፈንቅለ ፓትርያርክ መሆኑ ነው ወይስ
እንደራሴው በየሀገረ ስብከታቸው እየሄደ ት/ቤት ሊሰራላቸው ነው? ጉዳዩ ፓትርያርኩን ወደጎን አስቀምጦ ለጳጳሳቱና ለማኅበረ ቅዱሳን
ያደረ ሰው ለማስቀመጥ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው። እቅዱም የኃጢአታቸው ዐቃቤ ኃጢአት ከሆነው ከማኅበረ ቅዱሳን ሴራነት የዘለለ
አይደለም። የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ነገር የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር
እንደራሴ ለመሾም ይችሉ ዘንድ እንዲያግዛቸው መለመናቸው ነው።
የፖለቲካ ሰው ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ቅዱስ በሚባለው
ጉባዔያችሁ ተቀምጦ ሲነገራችሁ ከመስማት ሞት ይሻላችሁ ነበር። ዳሩ ግን የሞታችሁት ቀድሞ ነውና ይኼ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ውርደት
ለእናንተ ግን ክብር ነው። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በጠሩት ጉባዔ ላይ አንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ የተናገረውን ጠቅሼ
ልቋጭ። «ፖለቲከኛው እጣን፤ እጣን ሲሸት፤ የሃይማኖት አባት ፖለቲካ፤ ፖለቲካ ሲሸት አስቸጋሪ ነው» ማለቱን አስታውሳለሁ።
አዎ፤«ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡት፤ ውሃ ቢያንቅ በምን ይውጡት?» እንዲሉ።