Friday, April 22, 2016

የከፍያለው ቱፋ ጥፋቱ "ኢየሱስ፣ ኢየሱስ"ማለቱ!!



 ከፍያለው ቱፋ ወጣት መንፈሳዊ ተማሪና ሰባኪ ነበር። በዚህ ለጋ እድሜው ከስሞች ሁሉ በላይ ስም የሆነውን "ኢየሱስ ክርስቶስን" ከአፉ አይለይም።  በእርግጥም ያንን ማለት እንደጥፋት ከተቆጠረ ለጉባዔ ቀርቦ ቢቻል እውነቱን ነግሮ ወደሚፈለገው እውነት እንዲመለስ ማድረግ አለያም እኔ የያዝኩት እውነት ሌላ መልክ የለውም ካለም የራሱን ምርጫ አድርጎ ማሰናበት ሲቻል በበለው በለው ዘመቻ አስፈንጥሮ ማስወጣት አሳዛኝ ነው።  ከታች የቀረበው ጽሑፍ የሚያስረዳን ነገር በየቦታው የተደራጁ የዚያ ማኅበር ሰዎች ረጅም እጅና ቅብብሎሽ ምን ያህል የረዘመ ብቻ ሳይሆን የሰዎችን የኃጢአት ሸክም ለራሱ ፍላጎት መሳካት እንዴት መጠቀም እንደሚችል ያሳያል። ያንብቡ!

‹መንፈሳዊ ጉባኤ አዘጋጅተህ፥ ሰዎችን ሰብሰበሃል›› በሚል ተቃውሞ ክስ ተመስርቶበት፥ ከሰሞኑ 18 ከሚደርሱ ቅዱሳን ጋር መታሰሩን ሐራ ዘተዋህዶ መዘገቧ የሚታወቅ ነው፡፡ አሁን በደረሰን መረጃ መሰረት ደቀመዝሙር ከፍያለው ቱፋ የተከሰሰበት ክስ ፍሬ ከርስኪ መሆኑን ተረድቶ፥ ትላንት ማለትም 12/08/2008 ዓ/ም በአንድ ሺህ ብር ዋስ ፍርድ ቤቱ ሊለቀው ችሏል፡፡ ፍርድ ቤቱም አክሎም “የማንንም ሃይማኖት መስደብ፣ መንቀፍና መዝለፍ በሕግ ፈጽሞ የተከለከለ ነው፤ ደግሞም ማንም ሰው ያማነበትን እውነት መመስከርና መስበክ እንደሚችል” ገልጿል፡፡ በቦታው ላይ ፖሊስ ደርሶ ነገሩን ባይቆጣጠር ኖሮ ደም በማፍሰስ የሚያምነው ማህበሩ፥ የወንድሞችንና የእህቶችን ደም ከማፍሰስ እንደማይቦዝን የታወቀ ነው፡፡ ኽረ ለመሆኑ ለሃይማኖት የተደባደበ ሐዋርያ ማን ነው?

         አሁን አሁን በእናት ቤተክርስቲያናችን ውስጥ ባሉ አንዳንድ ጽንፈኛ ግለሰቦች ምክንያት ወንድሞች በጋራ ተሰባስበው መጽሐፍ ቅዱስን ከተማማሩ፣ በአንድነትም በመዝሙር በቅኔ ለአምላካቸው ከተቀኙ እንደ ምንፍቅና መታየት ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ይሁንም እንጂ ቅድስት ቤተክርስቲያን፥ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቀዳሚ ትምህርት መሰረት አድርጋ ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ በየትኛውም ሥፍራ መሰበክ እንዳለበት ታስተምራለች፡-

· “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡” ማቴ 28፡-19፡፡

         ደቀመዝሙሩና ከእርሱ ጋር የታሰሩ ወገኖች፥ ይሄንን የሐሰት ክስ ያቀነባበሩባቸውን ግለሰቦች መልሳችሁ መክሰስ ትችላላችሁ ቢባሉም እንኳ “በቀል የእግዚአብሔር ነው” በማለትና “ከአባታችን ከእግዚአብሔር የተማርነው ይቅርታና ምህረት ማድረግ ነው” በማለት አንዳችም አጸፋ ለማድረስ እንዳልፈለጉ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ ይሄ ደግሞ የአሰበ ተፈሪ ሐገረ ስብከት ሠራተኞችን ትዝብት ውስጥ የሚጥልና በቤተክርስቲያንም ወንጌል ለምን ተማማራችሁ በማለት የሚያሳስርና የሚከስ አባት የላትም፡፡ ይህንን ያደረጉት “የገባውን እውነት ቀብሮ ልጆቼን በምን አሳድጋለሁ ብሎ በግልጽ ወንጌልን የሚቃወመው ላዕከ ወንጌል ምንዳ ጉታ፥ ትዳሩን አያከብርም በሚባለው ሊቀ ብርሃናት ከሀሊ በቃሉ፥ እና በፀያፍ ቅጽል ስም የሚጠራው መልአከ ጸሐይ ዮሐንስ፣ ቀሲስ የማታ ወርቅ በተባሉ ግለሰቦች ሲሆኑ እነዚህ ሰዎች በዓመጻ ተነሳስተው ከማህበሩ በሚያገኙት. ድጋፍ ተነሳስተው  መሆኑ ታውቋል፡፡

“ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን” እንዲል መጽሐፍ ክብር ሁሉ ለእግዚአብሔር ብቻ ይሁን! አሜን!