ባልተዘጋጀችበትና በማትፈልገው ለውጥ ሳቢያ የሚደርስባት ጉዳት ከባድ ነው።
(ክፍል አራት)
በክፍል ሦስት ጽሁፋችን በአውሮፓ ሀገራት የእምነት መላሸቅ ስላስከተለውና በለውጡ ገፊ ምክንያትነት በቁጥር አንድ ስለተመዘገበው
ነጥብ ጥቂት ለማለት ሞክረናል። በሥራ ውጥረትና በጊዜ ማጣት የተነሳ
የሰው አእምሮ በመባከኑ ሳቢያ በማኅበራዊ ኑሮው ያለውን ግንኙነት አላልቷል። ቤተሰባዊ ፍቅሩን የሚያሳልፍበትን ሰዓት አጣቧል። ከፍላጎት
ማደግና ከወጪ ዓይነት ንረት ጋር ለመታገል በሚያደርገው ሩጫ የተነሳ ማንነቱን ለዚህ ዓለም ኑሮ አሳልፎ በመስጠቱ ለሰማያዊ እሱነቱ
የሚገባውን እሳቤ ሸርሽሮታል። በዚህም የተዳከመ የእምነት ሰው አለያም እምነት ማለት ሰርቶ ኑሮን ማሸነፍ ብቻ ነው ወደሚል እሳቤ
ወስዶታል። ከመላው አውሮፓ የክርስቲያን ቁጥር ውስጥ 45% ክርስትናውን ትቶታል ወይም ክዶታል። በፈረንሳይ ብቻ 40% እምነት የለሽ
ወደመሆን የወረደው በክፍል ሦስት ያየነው ለለውጡ ገፊ ምክንያት በሆነው አንዱ ነጥብ የተነሳ ነው። ያንንም ምክንያት ከሀገራችን
ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተን የት ነበርን? የት ደረስን? አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ እንገኛለን? አሉታዊ ጎኑን ለማስወገድ የወስድናቸው
ርምጃዎች ካሉም ያንን በማንሳት ጥቂት ለመዳሰስ ሞክረን ነበር። በዚህ ጽሁፋችን ደግሞ ሁለተኛውን ምክንያት በማንሳት ጥቂት እንላለን።
2/ ኢንዱስትሪው በየጊዜው በሚፈጥረው ትንግርታዊ እድገትና ጥበብ የሰው ልብ መማረኩ፤ ያልነበሩና የማይታወቁ ልምዶችን፤
ባህሎችንና ሥነ ምግባርን የሚያላሽቁ ክስተቶች መምጣታቸው፤
ኢንዱስትሪው ረጅም የሥራ ጊዜና ኃይል እንደመውሰዱ አእምሮን ሁሉ ለእውቀትና ለእድገት ሽግግር ጋብዞታል። በዚህም የተነሳ ቴክኖሎጂው መጥቆ ትንግርት እስኪሆን
ድረስ ፈጠራና ክሂሎት ተመንድጓል። የመረጃ መረብ መዘርጋት፤ በመረጃ መረብ ላይ የሚተላለፉ የድምጽ፤ የምስል፤ የጽሁፍና የፈጠራ
ውጤቶች ሉላዊውን ዓለም እንደማቀራረቡ መጠን የሰውን ሁሉ ልብ ሰርቆታል። ይህ ሰፊና ቁጥጥር የለሽ መረጃ መረብ የሚያስተናግደው
ቁም ነገር ብቻ ሳይሆን ጸያፍና ጋጠ ወጥ የሆነው ሁሉ የሚለቀቅበት በመሆኑ የሰው ልብ በሚታይ ነገር እንዲማረክ፤ የማያውቀውን ልምምድ
እንዲለማመድ፤ የነበረውን ባህል እንዲያራግፍ፤ ሥነ ምግባሩ እንዲላሽቅና የሥራ ውጥረቱን በሚያባብስ የክዋኔ ሂደት ውስጥ በማስገባቱ
የተነሳ መንፈሳዊውን ዓለም በገሃዳዊው ዓለም የደስታም ይሆን የኅሊና ስካር እንዲለውጥ አስገድዶታል። ለልቅ ወሲብ/Pornography/፤
ለግብረ ሰዶም፤ ለአደንቋሪ ዘፈንና ጫጫታ፤ በስፖርት ሽፋን መንፈሳዊ ልብን ለሚሰርቅ የዓይን ጫወታ ስሱዕ መሆን፤ ለዕጽ ተጠቃሚነት፤
ለአስገድዶ መድፈር፤ ለሰው ጉልበት ሽያጭ ወዘተ ድርጊቶች በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ተገዢ እንዲሆን አድርጎታል።