ባልተዘጋጀችበትና በማትፈልገው ለውጥ የሚደርስባት ጉዳት ከባድ ነው!
ክፍል ሁለት / ነሐሴ 21/ 2005/
በክፍል አንድ ጽሁፋችን ስለለውጥና የለውጥ አስተሳሰብ ጥቂት ለማለት ሞክረን ነበር። ጊዜውን ጠብቆ በመጣው ለውጥ ሳቢያ
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስላቋቋመችው የለውጥ ማስታገሻ መንገድና ስለኢየሱሳውያን/ JESUIT/ አመሰራረት መንስዔም በመጠኑ አስቃኝተናል።
ስለጀስዊትስ ዓላማና ግብ በዝርዝር እዚህ ላይ እንዳንሄድ የተነሳንበት ርእስ መሠረተ ሃሳብ ይገድበናልና ትተነዋል። አንባቢዎቻችን
ተጨማሪ መረጃ ያገኙ ዘንድ በዚህ ሊንክ እንዲገቡ እንጠቁማለን።/http://www.biblebelievers.org.au/jesuits.htm
የጀስዊትስ መመሥረት የአዲስ አስተሳሰብና የለውጥ እንቅስቃሴን ባያቆምም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ከመፈራረስ በተወሰነ መልኩ አግዟታል።
ወደማትፈልገውና ወዳላሳበችው የለውጥ መንገድ እንድትንሸራተት ያስገደዳት ሲሆን የነበራትን የሮማን ህግና ደንብ በየሀገራቱ ውስጥ
ከመትከል ይልቅ የየሀገራቱን ባህልና ወግ ከካቶሊክ አመለካከት ጋር እያስማማች ለመጓዝ ረድቷታል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው
ሕዝብ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ እንደመሆኑ መጠን የኢትዮጵያ ካቶሊክም ኢትዮጵያዊ ካቶሊክ እንዲመስል እንጂ ቫቲካናዊ
ካቶሊክ እንዲመስል ስለማይጠበቅበት ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግልባጭ ነው።
ታንዛንያ ስንሄድ ደግሞ ታንዛንያዊ ቋንቋ፤ ባህልና ወግን ይከተላል። ሌላ ቋንቋ፤ ባህልና ሥርዓት አምጥቶ ከመጫን ይልቅ ሕዝቡ በሚኖርበት
ቋንቋ፤ ባህልና ሥርዓት ሲያስተምሩት ውጤታማ መሆኑ አይጠረጠርም። ሐዋርያው ጳውሎስም ያደረገው እንዲሁ ነበር። ያልተገረዘ ወደ መገረዝ
አይሂድ ማለቱ ወንጌል ማለት አይሁዳዊውን ሥርዓት በሌላ ሕዝብ ላይ በመጫን የሚፈጸም እንዳልሆነ መግለጡ ነበር። እንኳን ግእዝን
አማርኛን በውል ለማይሰማ ለሸኮ መዠንገር ሕዝብ ሄደህ የያሬድ የቅዳሴ ዜማ ነው ብለህ ብትጮህለት ለምሥጋናህ እንዴት አሜን ሊል
ይችላል? ክርስትና የሰዎችን ቁጥር የማብዛት ጉዳይ ባይሆንም ወንጌል ያልደረሳቸውን ለማዳረስ ትክክለኛው መንገድ እኛ የምንኖርበትን
ሥርዓትና ሕግ በማያውቀው ሌላ ሕዝብ ላይ የመጫን ጉዳይ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወታችን መድኃኒት መሆኑን ከማስተማር ባለፈ
አሳማ በመብላትና ባለመብላት የማትገኘውን የጽድቅ መንገድ በላተኛውን በመከልከል ሊሆን አይችልም።
በዚህ አንጻር የካቶሊክ ተገዳዳሪ ሆኖ ለመጣው አዲስ የፕሮቴስታንት ዓለም ያልተፈለገውን የለውጥ መንገድ ለመጀመር ምክንያት
ሆኗል። በ 12ኛው ክ/ዘመን መገባደጃ ላይ ካቶሊክ የፈጠረችውን የመካነ ንሥሐ/ purgatory/ ጽንሰ ሃሳብ የግድ ህግ እንደሆነ
ማስተማርን ለመተው ተገዳለች። ኃጥእ ሰው ንስሐ ሳይገባ ከሞተ፤ የንስሐ ቦታ በሰማይ አለው የሚለው ጸረ ወንጌል አስተሳሰብ በአዲስ
ለውጥ እንቅስቃሴ ተቀባይነቱን አጥቷል። በእርግጥ ይህ አስተምህሮ ዛሬም ሳይጠፋ ተጠብቆ በሀገራችን ይገኛል። መጽሐፈ ግንዘት «እምድኅረ ሞቱ ለሰብእ አልቦቱ ንስሐ» ሰው ከሞተ በኋላ
የንስሐ ጊዜ የለውም» ቢልም ፍታትና ተስካር ንስሐ ሳይገባ የሞተውን ሰው ሥርየት ለማሰጠት የሚደረገው ሥርዓት አሁን ድረስ አለ።
በካቶሊክ አስተምህሮ ላይ ከተነሳው የለውጥ ጥያቄ አንዱ ይህ ነበር።