Saturday, January 19, 2013

እንኳን ለ1975ኛው ዓመት በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ!




ውሃ ለሥጋችን ሕይወት ነው። ከዚያም በላይ የፍሳችንን መዳኛ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት የምናዘክርበት ትልቅ ተስፋችን ነው። ውሃ በዘመነ ኖኅ የኃጢአት በትር ሆኖ የሰው ልጆችን የቀጣ ቢሆንም ነገሮችን አዲስ ማድረግ የባህሪው የሆነው እግዚአብሔር ውሃን በልጁ  ሞት ሞተን ፤ በኃይል ስለመነሳታችን  የምስክርነት ተስፋ አድርጎ ሰጥቶናል።
ውሃ የሞት መሣሪያ በሆነበት ዘመን «ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ» 2ኛ ጴጥ 2፤5  ካጠፋቸው በኋላ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የትንሣዔው ኅብረት ምልክት ሆኖ፤«በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ» ቆላ 2፤12 በማለት  በትንሣዔው  ያለንን አንድነት ነግሮናል።
እንደዚሁ ሁሉ በክርስቶስ ያመኑቱ ሁሉ ሊያደርጉት የሚገባና የሕያውነት ምስክርነታቸውን የሚሰጡበት የጥምቀት ዝክረ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከከተራው ጀምሮ የጌታ ጥምቀት ተፈጽሞበታል ተብሎ እስከሚታሰበው እለት ድረስ ብዙ ሺህ ሕዝብ በተገኘበት፤ የውጪ ቱሪስቶች ለጉብኝት በሚገኙበት ሥርዓት ጥር 11/2005 ዓ/ም በጃንሜዳና በየአድባራቱ ተከብሮ እንደሚውል ይታወቃል።  በአዲስ አበባ ጃንሜዳ የተከናውነውን ሥነ ሥርዓት  ከፊል ምሥል አቅርበናል።

Friday, January 18, 2013

የአሜሪካው ሲኖዶስ መግለጫ አወጣ!


በ4ኛው ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመራው የአሜሪካው ሲኖዶስ ጠንከር ያለና መሠረታዊ የልዩነት ነጥቦችን የሚያመላክት መግለጫ አውጥቷል። የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ሕጋዊ እንዳልሆነና ሕጋዊ ሊባል የሚቻለው በአቡነ መርቆሬዎስ የሚመራው ሲኖዶስ እንደሆነ ሕገ ቤተክርስቲያንን አጣቅሶ ያቀረበ ሲሆን ከመንበር ላይ በመሰደድ ቅዱስነታቸው በቤተክርስቲያን ታሪክ የመጀመሪያ እንዳልሆኑ በማመልከት ሁሉም ስደቶች የአባቶች ጥንካሬና የምእመናን ብርታት አሰዳጆችን እምቢ በማለት አንድነትና ኅብረትን ያሳየ ሆኖ ከማለፉ በስተቀር ለመኳንንቱ ፍላጎት ይሁንታን በመስጠት ኅብረታቸውን በታትነው እንደዚህ እንደዛሬው አለመታየታቸውን በመግለጽ  መግለጫው ሰፊ ሀተታ አቅርቧል።
ወደ 6ኛ ፓትርያርክ ምርጫ ለመግባት ጥቂት የሥልጣን ጥመኞች ጳጳሳት መንግሥትን ተገን አድርገው ያቀናበሩት እንደሆኑ በማመልከት በቤተክርስቲያናችን ታሪክ  ሌላኛውን ስህተት ለመፈጸም በመቋመጥ  ወደምርጫ የመሄድ አድራጎቱን በውግዘት ኮንኖታል።
 ከአባ ሰላማ ብሎግ ላይ ያገኘነውን ሙሉውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ላይ( Click here )

Wednesday, January 16, 2013

ሰበር ዜና፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ስድስተኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ ውሳኔ አሳለፈ

ጥር 8/2005 ዓ/ም  ምሽት ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባስተላለፈው ዜና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከጥር 6 ጀምሮ ባደረገው ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ በሰጠው መግለጫ 6ኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ ውሳኔ ማስተላለፉን ገልጿል።


ዜና ዘገባው አያይዞ እንደገለጸው በአሜሪካ ካሉ አባቶች ጋር ሲደረግ የቆየው ድርድር ሁሉ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ሲኖዶሱ በቀጥታ ወደምርጫ ለመግባት የተገደደ መሆኑን በመጠቆም፤ ነገር ግን የአሜሪካው ሲኖዶስ ወደእርቁ ተመልሶ አብሮ ለመሥራት ፈቃደኛ ከሆነ ለመቀበል ፈቃደኝነቱ እንዳለም አያይዞ አስረድቷል።
  ይህም ቀደም ሲል ሲነገር እንደቆየው አቡነ መርቆሬዎስ በፈለጉት ቦታ በጡረታ ከሚቀመጡ በቀር 5ኛ ፓትርያርክ ስንል ቆይተን፤ ቁልቁል ተመልሰን 4ኛ ፓትርያርክ በማለት የራሳችንን ሥራ የምናፈርስበት ምክንያት የለም የሚለውን ሃሳብ በደንብ ያንጸባረቀና ግልጽ ያደረገ መግለጫ ነበር። በሞት የተለዩትን ፓትርያርክ ሕገ ወጥ ናቸው በማለት የውጪው ሲኖዶስ ሲሞግት የቆየበትን ጥያቄ ተቀብሎ 4ኛውን ፓትርያርክ ወደመንበር መመለስ ማለት በ5ኛው ፓትርያርክ የተሰሩትና የተሾሙትን ጳጳሳትም በሕገ ወጥ ስልጣን የተገኘ ሹመት በማሰኘት ጥያቄ ውስጥ የሚከትና ወይም እንደገና ሊታደስ ይገባዋል የሚልን መንፈስ የሚያስነሳ ስለሆነ ከወዲሁ ስለአራተኛ ፓትርያርክ መመለስ ጉዳይ የሚነሳውን ፋይል ዘግተን ወደ 6ኛው ተሸጋግረናል በማለት እቅጩን የተናገረ ዘገባ ይመስላል። ይህም በፓትርያርኩ በራሳቸው አንደበት በቀጥታ  ባይሰማም በእነ አቡነ መልከ ጼዴቅ ይነሳ የነበረው የ4ኛው ፓትርያርክ ወደሥልጣን የመመለስ የእርቅ ክርክር እዚሁ ላይ ያቆማል ማለት ነው። 
የሀገር ቤቱን ሲኖዶስ እንደብቸኛ ሲኖዶስ በመቀበል፤ የውጪው ሲኖዶስ ከሀገር ቤቱ ጋር ለመቀላቀል ዝግጁ ይሆን? ያ ካልሆነ የእርቁ ፋይል እዚህ ላይ ይዘጋል!  ሁሉም ወገን ሥልጣን አይቅርብኝ የሚል ፈላጊ ስለነበር አንድ መሆን አልተቻለም። ሥልጣን የማያስጎመጅ አማራጭ ይኖር ይሆን?