( ክፍል ሁለት )
3/የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት
በክፍል አንድ ጽሁፋችን ስለመላእክት ስያሜ ትርጉም፤ ስለአፈጣጠራቸው፤ ስለፈቃዳቸውና ተልእኰአቸው በጥቂቱ ለማየት ሞክረን ነበር። በክፍል ሁለት ጽሁፋችን ደግሞ ቀሪውን ነጥብ እግዚአብሔርን እንደፈቀደ መጠን ለማየት እንሞክራለን።
ቅዱሳን መላእክት የፈጣሪያቸውን ትእዛዝ ሳይጠብቁ የትም እንደማይንቀሳቀሱ እርግጥ ነው። በዚህም የተነሳ እግዚአብሔር በወደደውና በፈቃደው ቦታ ቅዱሳኑን መላእክት ለእርዳታና ለትድግና ይልካቸዋል።
«የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል» መዝ 34፤7
እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ሰዎች የእግዚአብሔር ጥበቃና እርዳታ ዘወትር ይደረግላቸዋል ማለት መላእክቱ በራሳቸው ፈቃድ ይንቀሳቀሳሉ ማለት አይደለም። አንዳንዶች ይህንን ጥቅስ በመጠቀም «መላእክት በተጠሩ ጊዜ በተናጠል መጥተው ያድኑናል» ወደሚል ድምዳሜ በመድረስ ከመላእክት አማላጅነት ጋር ለማያያዝ የሚፈልጉ ወገኖች አሉ። ነገር ግን ዳዊት በመዝሙሩ በግልጽ እንደተናገረው
«በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል» ካለ በኋላ ሰው ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ፈቃድ ስር ካደረገ
«እግዚአብሔርን፦ አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው» በማለት እግዚአብሔር ታዳጊ አምላክ እንደሆነ በማሳየት፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ደግሞ ለእንደዚህ ዓይነቱ አማኝ የተሰጠው የጥበቃ ተስፋ በቅዱሳን መላእክቱ በኩል መሆኑን ከታች ባለው ጥቅስ ይነግረናል።
«ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና»
ይላል በዝማሬው። መዝ 91፤ 1-16 (ሙሉውን ያንብቡ)
በተመሳሳይ መልኩ እግዚአብሔርን መታመኛቸው ላደረጉ ሰዎች የእግዚአብሔር ጥበቃ በመላእክቱ በኩል ሲፈጸም እንመለከታለን።
«ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ» የሐዋ 12፣11
ጴጥሮስን ሄዶ እንዲያድን የላከው ጌታ ነው። መልአኩ የተላከውም ጴጥሮስን እንዲያድን ነው። ቅዱሳን መላእክት እንደስማቸው ለሚገዙለት ጌታ ይላካሉ። አድኑ የተባሉትን ያድናሉ። ለመዓትም ይሁን ለምህረት መላእክቱ የሚላኩት በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንጂ ሰዎች ስለጠሯቸው ወይም ስለፈለጓቸው አይደለም።
በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ ወደቴስቢያዊው ኤልያስ መልአኩ በተላከ ጊዜም አካዝያስ ስለህመሙ ምክንያት እግዚአብሔርን በጸሎት ከመጠየቅ ፈንታ ወደአቃሮን ብዔል ዜቡል ፊቱን ባዞረ ጊዜ መልአኩ
«እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» በማለት የመጣበት ጉዳይ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም እንደሆነ አስረግጦ ሲናገር፤
«የእግዚአብሔርም መልአክ ቴስብያዊውን ኤልያስን፦ ተነሣ፥ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣና። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቁ ዘንድ የምትሄዱት በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን? ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም በላቸው አለው። ኤልያስም ሄደ» 1ኛ ነገ 1፤3-4
«እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» ማለቱ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተቀብሎ ለመፈጸም መምጣቱን ያስረዳል። ወደኤልያስ መልእክቱ ይመጣ ዘንድ ያስፈለገውም ኤልያስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይከተል ስለነበር መሆኑ እርግጥ ነው። በሌላ ቦታም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይፈጽሙ ከነበሩ ደጋግ ሰዎች መካከል አንዱ ወደሆነው ወደቆርኔሌዎስም ዘንድ ሲልክ እንመለከታለን።
«ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፦ በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና። ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ» የሐዋ 10፤ 30-31
የቆርኔሌዎስ ስለጸሎቱ መሰማትና ስለምጽዋቱም በእግዚአብሔርን ዘንድ መታሰብ የሚናገር መልእክተኛ መላኩን ስንመለከት ዳዊት በዝማሬው እንዳመለከተው በልዑል መጠጊያ ለሚኖሩ ሁሉ መላእክቱ እንደሚላኩላቸው በግልጽ ያረጋግጥልናል። በዚሁ ተመሳሳይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስረጂ በማቅረብ የመላእክቱን ተራዳዒነትና አጋዥነት መግለጽ ይቻላል። ነገር ግን አስረግጠን ማለፍ የሚገባን ቁም ነገር መላእክቱ የሚመጡት በእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ስር ላሉ ሲሆን ሰዎች የፈለጉትን መልአክ ስለጠሩ ወይም በልባቸው አምሮት የመረጧቸውን መላእክት ስም ስለተናገሩ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባናል። በሰዎች ጥሪ እገሌ የተባለ መልአክ መጣልኝ የሚል አንዳችም አስረጂ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ አይገኝም። በተራዳዒነትና አጋዥነት እንደተላኩ የሚነገርላቸው አብዛኛዎቹ መላእክትም በስም ተለይተው አይታወቁም። ቁም ነገሩ የትኛው መልአክ በታላቅ ኃይል ትእዛዙን ይፈጽማል በማለት በኛ ምርጫ የሚወሰን ሳይሆን በስም የተገለጹም ይሁን ያልተገለጹትን እግዚአብሔር መላእክቱን ልኮ የወደዳቸውን እንዴት ይታደጋል? የሚለውን ከመረዳቱ ላይ ልናተኩር ይገባል። ስለዚህም ተልከው ስላገዙን መላእክት የምንሰጠው ክብር እግዚአብሔር ለኛ ያደረገውን ታላቅ ሥራ ቀንሰን የምናካፍለው መሆን የለበትም። በርናባስና ጳውሎስ ከእናቱ ማህጸን ጀምሮ እግሩ የሰለለውን ሰው በፈወሱበት ወቅት የሊቃኦንያ ከተማ ሰዎች «አማልክት ከሰማይ ወደእኛ ወርደዋል» በማለት መስዋዕት ሊያቀርቡላቸው በወደዱ ጊዜ እነጳውሎስ ያደረጉትን ማየቱ ተገቢ ነው።
«ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፥ እንዲህም አሉ። እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን» የሐዋ 14፤14-15
ጳውሎስና በርናባስ ቅዱሳን በአገልግሎታቸው ሐዋርያት ሆነው ብናከብራቸውና ብንወዳቸውም ቅሉ በእነሱ እጅ በተሰራው አምላካዊ ድንቅ ሥራ ግን ምስጋናንና ክብርን በጋራ ሊቀበሉ አይችሉም። ክብርና ምስጋና ሁሉ ለእግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ራሳቸው እንደመሰከሩት የእግዚአብሔር የብቻው የሆነውን ወደፍጡራን መስጠት ተገቢ እንዳልሆነ ማወቅ ይገባናል።
4/ የእግዚአብሔር መላእክት ሳይላኩ በሰዎች ጥሪ ሥፍራቸው ለቀው ይሄዳሉን?
ቅዱሳን መላእክትን ቅዱሳን ያሰኛቸው ዋናው ቁም ነገር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ማክበር መቻላቸው ነው። ከእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ውጪ የሆኑትማ ከማዕርጋቸው ተሰናብተዋል። ስለዚህ ቅዱሳን መላእክቱ ሰዎች ስለጠሯቸው ወይም ስማቸው ነጋ ጠባ ስለተነሳ ተጠርተናል በሚል ሰበብ ወደየትም አይሄዱም። ከላይ በማስረጃ ለማስረዳት እንደተሞከረው ቅዱሳኑ መላእክት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለፈጸሙ ወይም እግዚአብሔር ፈቃዱ ይፈጸም ዘንድ በወደደበት ቦታ መላእክቱን ከሚልክ በስተቀር የትኛውም መልአክ ስሙ ስለተጠራ ወይም ስለተወሳ ተከብሬአለሁና ልሂድ፤ ልውረድ በማለት ከተማውን ለቆ የትም አይሄድም። አንዳንድ ሰዎች የመላእክቱን ስም ለይተው በመጥራት ናልኝ የሚሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካልሆነ ትምህርት የተገኘ ልምምድ ውጤት ነው።
ስሙ ተጠርቶ ይቅርና ገና ሳይጠራ ስፍራውን ለቆ የትም የሚዞረው ሰይጣን ብቻ ነው። ሰይጣን ቦታውን ለቆ የትም የሚዞረው ከእግዚአሔር ፈቃድ ውጪ ያፈነገጠ ሽፍታ ስለሆነ ነው። ቅዱሳን መላእክቱ ያለእግዚአብሔር ትእዛዝ ስማቸው ስለተጠራ ብቻ ሥፍራቸውን ለቀው እንደማይንቀሳቀሱ የሚያውቀው ሰይጣን ራሱን የብርሃን መልአክ አስመስሎ ሊያታልል እንደሚችል ወንጌል ያስረዳናል።
«ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና» 2ኛ ቆሮ 11፤14
ሰይጣን በራሱ ፈቃድ የሚተዳደር ዐመጸኛ ስለሆነ በዓለሙ ሁሉ እየዞረ ሰዎችን ሲያሳስት ይውላል። በተለይም የእግዚአብሔርን ፊት በሚሹ ሰዎች ዙሪያ የጥፋት ወጥመዱን ሊዘረጋ አጥብቆ ይተጋል። ጻድቅ የሆነው ኢዮብንም ያገኘው በዚህ የጥፋት አደናው ወቅት ዓለምን ሲያስስ እንደነበር ከንግግሩ ታይቷል።
«እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ»ኢዮብ 1፣7
ስለዚህ ክርስቲያኖች እንደእግዚአብሔር ፈቃድ እየኖሩ ለትእዛዙ በተገዙ ጊዜ በመልካም ትሩፋታቸው ይሁን በችግራቸው ወይም በመከራቸው ወቅት እንዲራዷቸው ቅዱሳኑ መላእክት ከሚላኩ በስተቀር ሰዎች በቀጥታ መላእክቱን ስለጠሯቸው ወይም በስማቸው ስለተማጸኑ የሚመጡ ባለመሆናቸው ከመሰል ስህተት ልንጠነቀቅ ይገባል። ይልቁንም ከእግዚአብሔር ተልእኮ ውጪ ቅዱሳኑ እንደማይንቀሳቀሱ የሚያውቁት የሰይጣን ሠራዊት የብርሃን መልአክ በመምሰል ራሳቸውን ቀይረው ከሚፈጽሙብን ሽንገላ ልንጠነቀቅ ይገባል።
እንደማጠቃለያ፤
ቅዱሳን መላእክት ሰዎችን ይራዳሉ፤ ያግዛሉ ማለት በሥልጣናቸው የራሳቸውን ክብር ስም ለማስጠበቅ ይሠራሉ ማለት አይደለም። በተፈጥሮአቸውም ውሱን ስለሆኑ በዓለም ላይ በአንድ ጊዜ በስፍሐትና በምልዓት የመገኘት ብቃት የላቸውም። በሁሉም ሥፍራ ተገኝተው ሰዎች ሰለጠሯቸው መልስ አይሰጡም። ይሁን እንጂ በዓለም ላይ በስማቸው ተሠራ በሚባለው ቤተ ጸሎት በአንድ ጊዜ በስፍሐትና በምልዓት ተገኝተው ጸሎት እንደሚቀበሉ ተቆጥሮ ስማቸው ሲጠራ ይታያል። በቅዱሳን መላእክት ተራዳዒነት እናምናለን ማለት ቅዱሳን መላእክት በራሳቸው ፈቃድ ስለጠራናቸው ይደርሱልናል ማለት አይደለም። ቅዱሳን መላእክት ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ሳይደርሳቸው አይንቀሳቀሱም። የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማም ቅዱሳኑን መላእክት ስናከብራቸው አስተሳሰባችንን በመለጠጥ የምንጓዝበት የእምነት ጽንፍ ወደስህተት እንዳይጥለን ለማስገንዘብ ነው። ቅዱሳኑን ያለትእዛዝ ስለጠራናቸው ብቻ በማይመጡበት ሥፍራ ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ ከሚፈጽመው ማታለል ለመጠበቅ ነው።
በአንዳንድ የእምነት ተቋማት ዘንድ ስለመላእክት ያለው አስተምህሮ የተዛባ ምስልን እንደያዘ መገንዘብ ይቻላል።
በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አንዳንዶች የመላእክቱን ተፈጥሮ ዘንግተው ሁሉን የመስማት፤ የማወቅና በሁሉ ሥፍራ የመገኘት ችሎታ እንዳላቸው ሲቆጥሩ መታየቱ ተለምዷል። መላእክት በተጠሩ ጊዜ መልስ እንደሚሰጡና እንደሚራዱ የሚሰጠውም ግምት ያለትእዛዝ በራሳቸው ፈቃድ እንደሚንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል። ይህም ወደ እግዚአብሔር ሳይሆን በተራዳዒነት ሰበብ ወደ መላእክቱ ጸሎት የሚያደርሱ ሰዎችን አስገኝቷል። «እንደአናንያ፤ እንደአዛርያ፤ እንደሚሳኤል አድነን ገብርኤል» እያሉ መዘመር እንደተገቢ ከተቆጠረ ውሎ አድሯል። ሠለስቱ ደቂቅን ያዳነው ገብርኤል ነው ከሚለው የትርጉም ፍልሰት ጀምሮ «ገብርኤል አዳኝ ነው» ወደሚለው መልአኩን ለይቶ የማመስገን የፍቺ ጽንፍ ድረስ ስለመላእክት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ምስል መስጠት ጉዳዩን አደገኛ ያደርገዋል። እኛ የሚያድኑን እግዚአብሔር ፈቃዱን የፈጸመባቸው መላእክቱ ወይስ የእግዚአብሔር ኃይል? በሚለው ሃሳብ ላይም መቀላቀል የታየበት ሁኔታ ሕዝቡ መላእክቱን በተናጠል ወደመጣራት ሲገፋው ይስተዋላል። ከሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ሚካኤል አንተ ታውቃለህ? ብሎ የመጸልይ ልምምድ ስለመላእክቱና ስለእግዚአብሔር ፈቃድ የተቀላቀለ ትምህርት ውጤት ነው።
አንድ ክርስቲያን በአንድ ጊዜ ወደእግዚአብሔርም፤ ወደመላእክቱም ጸሎት ማድረስ አይችልም። ይህ መተላለፍ ነው። እግዚአብሔር ደግሞ ከክብሩም፤ ከምስጋናውም ለማንም አያጋራም። ቀናተኛ አምላክ የሚባለውም ለዚህ ነው። ኢያሱ ወልደነዌ ለህዝቡ እንዲህ አለ።
«ኢያሱም ሕዝቡን፦ እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም» ኢያ 24፤19ስለዚህ ስለመላእክት ተፈጥሮ፤ ተልዕኰና አገልግሎት በደንብ ማወቅ የሚገባን የእግዚአብሔርን ለመላእክት፤ የመላእክትንም ለእግዚአብሔር በመስጠት የእምነት ሥፍራውን እንዳናቀላቅል ሲባል ነው። ተፈጥሮአቸውን፤ ተልእኰአቸውንና ተግባራቸውን ለይተን እንወቅ። ከስህተትም ላይ እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ። ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን!