Friday, November 1, 2013

አባ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ላይ እየፈጸሙ ያለው ሙስናና እየነፈጉ ያለው ፍትሕ ብዙዎችን እያማረረ ነው!


 
ከመግቢያችን ለጥቆ ያለው ርዕሱን ገላጭ የሆነው ጽሁፍ የተገኘው ከአባ ሰላማ ብሎግ ነው።

(እንደመግቢያ፤ ከደጀብርሃን)

ቅድሚያ ይድረስ ለፓትርያርክ ማትያስ!!

 ብዙ ጊዜ አስነዋሪ ገመና የተሸከሙ ሰዎች ገመናቸውን በንስሐ ማጠብ እርም ሆኖባቸው መቆየቱ ሳያንስ  ገመናቸውን ተሸክመው አርፈው እንደመቀመጥ ወደአደባባይ ይወጡና ጭራሹኑ የገመናቸውን መጠን ሲያሳድጉ ይታያሉ። አደባባይ ያወቀውን ገመና ተሸክመው ይኖሩ የነበሩትና ተሸፍኖላቸው እንደትልቅ ሰው የጅማ መሪ የሆኑት አባ እስጢፋኖስ የገመናውን ደረጃ ወዳሳደጉበት አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመልሰው ሲመጡ «ድመት መንኩሳ አመሏን ላትረሳ» ያሉ ብዙዎች ነበሩ። በእርግጥም እስከመቃብር አብሯቸው የሚዘልቀው ገመና ከሥጋ አልፎ አጥንታቸው ላይ የተጣበቀው አባ እስጢፋኖስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ከማኅበረ ቅዱሳን ነፍሰ በላዎች ጋር በመተጋገዝ እያጠቡት ይገኛሉ።   ማንም ሳይነካቸውና ገመናቸው ከሰፈር ወሬ ባለፈ የተናገረ ማንም ሳይኖር በራሳቸው ጊዜ  ገመናዬን አደባባይ አውጡልኝ፤ በሚዲያም ተናገሩልኝ ሲሉ በሥራቸው አላፊ አግዳሚውን ተጣሩ፤ እያፈናቀሉና ወሮ በላውን እያሳደጉ የማን ወዳጅ መሆናቸውን በተግባር አሳዩ።   አለመታደል ሆኖ እንጂ ሊቀ ጳጳሱ መልካም አስተዳደርና ሙስናን ተከላክለው ቢሆኑ ኖሮ ገመናቸውን በማውጣት ማንም ድካማቸውን ለመተረክ ጊዜውን ባላጠፋ ነበር። ይሁን እንጂ «ያዳቆነ ሰይጣን » እንዲሉ ክፉ ተግባራቸውን ለመተው መቼም ቢሆን ያልታደሉት የጥፋት ሰው አባ እስጢፋኖስ ደሃውን አስለቀሱ፤ ከስራ አፈናቀሉ፤ በአየር ላይ አንሳፈው ለረሃብና ለመከራ አጋልጠው ሰጡ፤ የሚሸጡትን ሰው ሸጡ፤ የሚገድሉትንም በደብዳቤ እንዳይነሳ አድርገው ጣሉ።  ከዚህ ሁሉ የከፋውና የሚያሳዝነው ደግሞ ፓትርያርክ ማትያስም ለዚህ ወንጀልና ለመጥፎ ድርጊት ተባባሪ ሆነው መገኘታቸው ነው።                                  
ዋናው ምክንያት ፓትርያርክ ማትያስን ላስመረጡበት ውለታ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተበረከተ ክፍያ ሲሆን በሌላ መልኩም «ግም ለግም አብረህ አዝግም»  የሚለው የብሂል ገመድ እየሳበ ፓትርያርኩን ስላስቸገረ ነው።  አባ ማትያስ ከፓትርያርክነታቸው በፊት የጵጵስና ዘመናቸውን የሚያጋልጥ ከወራት በፊት በእጃችን ላይ የደረሰው አስደማሚ መረጃ ቢኖርም አደባባይ ላይ ማውጣት ያልፈለግነው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ክብር ነበር። ቤተክርስቲያኒቱን አክብረው ማስከበር ሲገባቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለችግርና ለሰቆቃ አጋልጠው ለሚሰጡ አባ እስጢፋኖስን ለመሰሉ የዘመኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ እርግማን ለሆኑ ሰዎች ጥላና ከለላ መሆናቸው  ግምት ውስጥ የሚያስገባቸው ብቻ ሳይሆን የኔንም እንደውዴ አባ እስጢፋኖስ አደባባይ አውጡልኝ እያሉ በሰጡት የዐመጻ ድጋፍ አርፎ የተቀመጠውን ፋይል እየቀሰቀሱት መሆኑን ሊያውቁት ይገባል። ከዚያም በተረፈ የነማን ወዳጅ ምን ይመስላል? ለሚለው የሰዎች የጥያቄ እንቆቅልሽ መልስ እንዲያገኝ በር እየከፈቱ መሆንዎን ለፓትርያክነትዎ እንናገራለን። በዚህ ዘመን የተከደነ የማይገለጥ እንደሌለም ይወቁ። የአባ እስጢፋኖስ የገመና ሰማዕት መሆን ከፈለጉ ምርጫው የእርስዎ ብቻ ነው። እኛም ለእንደዚህ ዓይነት ሰዎች የሚኖረን ትዕግስት እስከመቼ ነው? አርፈው እንዲቀመጡ ሊነገራቸው ይገባል? ወይስ እነሱ የዐመጻቸውን ቆሻሻ ሲደፉብን ዝም ብለን እንሸከም? ብለን ራሳችንን እንጠይቃለን።
  በመጨረሻም ለፓትርያርክ ማትያስ የምናቀርበው ልመናና ተማጽኖ ሀገረ ስብከቱን እያወኩ የሚገኙት ሊቀ ጳጳስ ተብዬ ሰው ከቦታው ያንሱልን!!  ጳጳሱ ለዋሉት ውለታቸው ቤተ ክርስቲያንን በመሸጥ ሳይሆን  አሜሪካ ከሚከፈልዎ የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ደመወዝዎ ላይ ቀንሰው በዶላር ይስጡ። ያለምንም ማስፈራራት ቀጣዩ የአደባባይ ገመና የእርስዎ ይሆናል። ከዚያ በኋላ የትም ሄደው ቢደሰኩሩ እመራዋለሁ ከሚሉት ሕዝብ ፊት የሚታየው እርስዎ ያልተጸየፉትና ተከድኖ ሳይገለጥ የቆየው ገመናዎ ለአባ እስጢፋኖስ የቀረበ መስዋዕት ይሆንልዎታል።  ኃጢአትን የተለማመደ ሰው ይህ ምንም ስሜት ባይሰጠውም፤ ኃጢአታቸውን ለመሸፈን ሲሉ መልካም ለመሥራት ቃል ያልገቡ መሪዎች ሁሉ የሚከተላቸው የኃጢአታቸው ደብዳቤ መሆኑን ስለምንረዳ በመጨረሻው ዘመን የመንፈሳዊ ሰዎች መታጣት ስለሚታወቅ ብዙም አያስገርመንም።
                                                                  
«የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው ፍርድንም ያመለክታል፥ ሌሎችን ግን ይከተላቸዋል» 1ኛ ጢሞ 5፤24

የአባ ሰላማ ብሎግ የአባ እስጢፋኖስን ተግባር ያጋለጠበት ጽሁፍ ይህንን ይመስላል።
አባ ገብረ ሚካኤል ለጵጵስና ሲታጩ የዑራኤል አስተዳዳሪ የነበሩት አባ ላእከ የተባሉ አባት ለአቡነ ጳውሎስ “ምነው አባታችን የምናውቃቸውን አባ ገብረ ሚካኤልን ልንድራቸው ሲገባ እንዴት ያጰጵሳሉ? እነዚህ በሚመሯት ቤተክርስቲያን ውስጥ በኀላፊነት መሥራት አልፈልግም” ብለው “ኢታርእየኒ ሙስናሃ ለኢየሩሳሌም” ወይም “የኢየሩሳሌምን ጥፋቷን አታሳየን” እንዳለው ነቢይ የኦርቶዶክስን ጥፋት ላለማየት በመወሰን ወደ መርጡለማርያም ገዳም እንደገቡ ይነገራል፡፡ መልአከ ገነት አባ ኀይለ ማርያም የተባሉ አራዳ ጊዮርጊስ አለቃ የነበሩ አባትም በጊዜው በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የነበረውን ገንዘብ ለመዝረፍ ታስቦ እርሳቸው ለጵጵስና ሲታጩ (ከእነአባ ገብረሚካኤል ጋር)፣ “ወቅብዐ ኃጥኣንሰ ኢይትቀባዕ ርእስየ” እና “ወኢይደመር ውስተ ማኅበሮሙ ለእኩያን” የሚሉትን የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል በመጥቀስ የሚያስተዳድሩትን ደብር ለቀው ገዳም ሊገቡ ሲሉ በፓትርያርኩ ተለምነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው ነበር፡፡ ነገር ግን የአባ ገብረሚካኤል የድራፍት ቡድን አላላውስ አላንቀሳቅስ ስላላቸው የሚወዷትን አገራቸውንና ቤተክርስቲያናቸውን ጥለው በመሰደድ በብስጭትና በንዴት በስደት አገር ሳሉ ዐርፈዋል፡፡ እነዚህ አባቶች ያኔ የተናገሩት ቢሰማና አባ ገብረሚካኤል ወደ ጵጵስና ሳይሆን ወደ ትዳር እንዲገቡ ቢደረግ ኖሮ ዛሬ በእርሳቸው እየደረሰ ያለው ጥፋት በቤተክርስቲያን ላይ ባልደረሰ ነበር የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

በአባ ገብረሚካኤል እጩነት ላይ አባ ላእከ እና መልአከ ገነት አባ ኃይለ ማርያም ያቀረቡት ቅሬታ ሰሚ ሳያገኝ እነርሱ ወደገዳምና ስደት በኋላም ወደሞት፣ አባ ገብረ ሚካኤልም “አባ እስጢፋኖስ” ተብለው ወደ ጵጵስና መጡ፡፡ አባ እስጢፋኖስን “አባ” ከማለት ይልቅ “አቶ” ማለት ይቀላል ይላሉ የሚያውቋቸው፡፡ በቆብ ውስጥ ትዳር ከመሰረቱና ባለትዳር መሆናቸው ከሚነገርላቸው ጳጳሳት መካከል አባ እስጢፋኖስ አንዱ ሲሆኑ የቆብ ውስጥ ትዳር በመመስረታቸው ብዙዎች የእሳቸው ይሻላል ቢሉም፣ ብዙ ውሽሞች ያሏቸው መሆናቸው እየተጋለጠ ሲመጣ ግን “እኛስ በአንድ በመወሰናቸው ደስ ብሎን ነበር ግን ምን ያደርጋል …” ወደማለት መጥተዋል፡፡
አባ እስጢፋኖስ ሊቀጳጳስነት እንደ ተሾሙ ከሌሎቹ ጳጳሳት ጋር አባ ጳውሎስ አክሱም ይዘዋቸው ሄደው የነበረ ሲሆን፣ ሌሎቹ ጳጳሳት ወደ ጽላት ቤት ይዘዋቸው ሲገቡ ለዚህ ጉዳይ እንጅግ የሚጠነቀቁት አክሱማውያን ካህናት ከጳጳሳቱ መካከል አባ አስጢፋኖስን የጽላት ቤቱን ያረክሱብናል በሚል “አሥመራ የወለድካቸውን ልጆች አሳድግ እንጂ አንተ እዚህ አትገባም” ብለው አግደዋቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ሊቄ ብርሃኑ “ሊቀጳጳስ  ናቸው እኮ” ብለው ሊከራከሩላቸው ቢሞክሩም ካህናቱ በአቋማቸው ጸንተው እንዳይገቡ አግደዋቸው ከደጅ ተመልሰዋል። ቀደም ብሎም ናዝሬት ላይ ሳሉም ሴት በመድፈር ተከሰው የነበረ መሆኑን በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መጋቢ እያሉም በአባ ሳሙኤል አምሳል ሴት ያስገቡ ያስወጡ እንደነበር በጊዜው ጥበቃ ከነበሩት አንዳንዶቹ ይመሰክራሉ፡፡

ሁሉ የሚያውቃቸው የትዳር አጋራቸው የዑራኤል ቤተክርስቲያን ጸሓፊ የሆኑት ወ/ሮ ትዕግሥት ሲባሉ አባው ከእርሳቸው ሦስት ወይም አራት ልጆችን አፍርተዋል ይላሉ ምንጮቻችን፡፡ የዚያው ቤተክርስቲያን ሒሳብ ሹም የኾኑትን ወ/ሮ መናንም ወሽመዋል እየተባለ በስፋት ይወራል፡፡ ወ/ሮ መና በሂሳብ ሹምነታቸው ብዙ ሙስና ቢፈጽሙም “ዋ እንዳላወጣው” እያሉ አባ እስጢፋኖስን በማስፈራራት በሀገረ ስብከቱ ያለመከሰስ መብታቸውን አስከብረዋል ነው የሚባለው፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ በሙስናው መዋቅር ውስጥ ገንዘብ በማቀባበልና የጉቦን መጠን ደረጃ በማውጣት ከሚደልሉላቸው ደላሎቻቸው መካከል የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ያደረጉት የዮናስ እናትና ሌሎችም ውሽሞቻቸው እንደሆኑ በካህናቱ መካከል የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የየካ ሚካኤል ቁጥጥር የሆነ ኢያሱና የአቡነ ጢሞቴዎስ ሾፌር የሆነው የልቤ ነጋም ልጆቻቸው መሆናቸውን ምንጮቻችን በእርግጥኝነትና በካህናቱ መካከል ሁሉም የሚያውቀው ሐቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ የልቤ የተባለው ልጅ “ነጋ” በሚባል የአባት ስም ይጠራ እንጂ ቁርጥ አባቱን አባ እስጢፋኖስ እንደሚመስል ይናገራሉ፡፡
አባ እስጢፋኖስ በፓትርያርክ ማትያስ ዘመን የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀጳጳስ ሆነው ሲሾሙ፣ በፓትርያርክ ምርጫው ላይ በነበራቸው የአስመራጭነት ሥልጣን አባ ማትያስ እንዲመረጡ ለማድረግ በተጫወቱት ሚና በጅማ ሀገረ ስብከት ላይ አዲስ አበባ እንደተጨመረላቸው የሚናገሩ አሉ፡፡ ከመጰጰሳቸው በፊት በተለይ በ1988 – 89 ዓ.ም ድረስ በነበሩት ዓመታት ውስጥ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ እያሉ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ሕገወጥ የድራፍትና የጉቦ ቡድኖችን በማደራጀት ቅጥርና ዝውውር በጉቦ እንዲፈጸም መሠረት በመጣል ተጠቃሽ ስለነበሩ፣ ሊቀጳጳስ ሆነው ሲመጡ ብዙዎች “የጀመሩትን የሙስና መንገድ እንዲያጠናክሩት ነው የተሾሙት ሲሉ” ስጋታቸውን ገልጸው ነበር፡፡
እርሳቸውም የቀድሞ ክፉ ስማቸው ዳግም እንዳይነሳ በመስጋት ስለሙስና አብዝቶ ማውራት ከሙስና ነጻ የሚያደርግ ስለመሰላቸው በየተገኙበት ሙስናን ሲኮንኑ ቢሰሙም እንደአሁኑ ጊዜ ሙስናና የፍትሕ እጦት የተስፋፋበት እንደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለ ስፍራ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ስለሙስና አብዝተው እያወሩ በኃይለኛ ሙስና ውስጥ ተዘፍቆ መገኘት የዘመኑ ፋሽን ሆኗል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ እንደ ነበረው እንደ ገብረዋሕድ ስለሙስና አብዝቶ ያወራ በሙስናም ተዘፍቆ የተገኘ ስለሌለ የገብርኤልን መገበሪያ የበላ ሳይነኩት ይለፈልፋል እንደሚባለው ሙስና ውስጥ የሚገኝ ስለ ሙስና አብዝቶ ማውራቱ እየተለመደ መጥቷል፡፡ እንዲህ ስንል ሁሉም ስለ ሙስና የሚያወራ ሙሰኛ ነው እያልን አይደለም፡፡ - በፍጹም! ሙስናን በቁርጠኝነት ለመታገል የተሰለፉ፣ ሙስናን የሚኮንኑ እውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጆችም እንዳሉ እናውቃለን፡፡
አባ እስጢፋኖስ በጅማ ሀገረ ስብከት ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከተጨመረላቸው ወዲህ ሙስናና ብልሹ አሰራር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየተስፋፋና በርካታ አገልጋዮች የሙሰኞች ሰለባ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ለዚህም በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ቁልፍ ቦታዎችን የያዙት ማለትም አስተዳደር ላይ የተቀመጠው ዮናስ፣ ደብዳቤ መሪ ተብሎ የተሰየመው ታዴዎስና ስብከተ ወንጌል ክፍሉን የሚመራው ዳዊት ቅጥርና ዝውውር ላይ ኃይለኛ ደላሎች በመሆን ጉቦ እየተቀበሉ አንዱን እየሾሙ ሌላውን በአየር ላይ እያንሳፍፉ ይገኛሉ፡፡ አለቃቸው አባ እስጢፋኖስም ምናልባት ተገኝተው አቤቱታ ሲሰሙ በተለይ ዮናስን በአቤቱታ አቅራቢው ፊት ሰድበውና ሞልጨው ይናገሩትና ከመጋረጃ በስተጀርባ የሚተገበረው ግን ዮናስ ያለው ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ጉቦው ወደ 30 እና 40 ሺህ ብር ከፍ ያለ መሆኑን እየተነገረ ነው፡፡ ጉቦ ለመብላት የተነደፈው ስልትም በየደብሩ በሐቅ የሚሰሩና ለዘራፊዎቹ ያልተመቹ አገልጋዮችንና በልዩ ልዩ ምክንያት የተጋጯቸውን አገልጋዮች አንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች ከደላሎቹ ጋር በመነጋገርና በመደራደር እገሌን ቀይርልኝና ይህን ያህል እሰጥሃለሁ ይላሉ፡፡ በዚህ መካከል ደላሎቹ ከአስተዳዳሪውም በዝውውር የተሻለ ቦታ ከተገኘላቸው ሟሳኝ አሟሳኝ ሰራተኞችም ዳጎስ ያለ ጉቦ ይቀበላሉ፡፡ ከፍለው ለሚዛወሩት ነገሩ አልጋ ባልጋ ሲሆንላቸው ያለበደላቸው ከሚያገለግሉበት ደብር እንዲዛወሩ ለሚደረጉት የደላላ ሰለባዎች ግን አባጣ ጎርባጣ ነው የሚሆንባቸው፡፡ ሀብታም ከሆነና መሀል ከተማ ከሚገኝ ደብር ከከተማ ወጣ ብሎ ወደሚገኝና ገቢው አነስተኛ ወደሆነ ደብር እንዲዛወሩ፣ የዝውውር ደብዳቤ ከተጻፈላቸውና የነበሩበትን ደብር ከለቀቁ በኋላ የተዛወሩበት ደብር እንዳይቀበላቸው የማድረግና አየር ላይ የማንሳፈፍ የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ የአባ ሳሙኤል ስልትም ተግባራዊ ይሆንባቸዋል፡፡
ለመጥቀስ ያህል እንኳ የ1500 ብር ደሞዝተኛ የነበረ አገልጋይ ጉቦ ለዮናስ ሰጥቶ በ2400 ብር በቅርቡ ዝውውር ተፈጽሞለታል፡፡ ቦታውን እንዲለቅ የተደረገው ደግሞ ደሞዝ ቀንሶ ነው የተዛወረው፡፡ እንዲሁም የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን ሒሳብ ሹም የነበረውን አገልጋይም በቅርቡ አዲስ ተሹሞ የመጣው አለቃ (አባ ነአኩቶ ለአብ) አላስበላ ብሎኛል በሚል ከአባ እስጢፋኖስ ደላሎች ጋር በመመሳጠር ከሚያገኘው ደመወዝ 400 ብር ቀንሶ ወደ ጠሮ ሥላሴ እንዲዛወር ያደረገው ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ወደተዛወረበትም ተቀባይ ሳያገኝ አየር ላይ ተንሳፎ ይገኛል፡፡ ሌላው አገልጋይ ደግሞ የተሻለ ገቢ ከነበረው ከኩርፎ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከኮተቤ አለፍ ብሎ ወደሚገኘው ገጠር ቀመስ ቤተክርስቲያን ያዛወረው ሲሆን፣ ደብሩ ደሃና ወርሃዊ ደሞዝ እንኳን በቅጡ የማይከፈልበት፣ በየወሩ አንዳንድ ጊዜ የደሞዝ ግማሽ፣ አንዳንዴ ደግሞ ሩቡን ካልሆነም እስከ 20 ከመቶ ያህል የሚከፈልበት ደሃ ቤተክርስቲያን መሆኑ ይነገራል፡፡
ቄስ ለይኩን የተባለ አገልጋይ ደግሞ በደላላው ዳዊት አማካይነት ለአባ እስጢፋኖስ 40 ሺህ ብር ከፍለው ከኮተቤ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን የ1600 ብር ደሞዝ ወደ ሰዋስወብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን 2999 ብር ደሞዝ ከነአበሉ እንዲያገኙ ተደርጎ ተዛውረዋል፡፡ በቅርቡም በተመሳሳይ ተልእኮ ከአራዳ ጊዮርጊስ ወደ መካኒሳ ሚካኤል የተዛወረ አንድ ሰራተኛ የመንግስት ባለስልጣን የሆነ ዘመድ ስለነበረው በተጽእኖ ከመካኒሳ ሚካኤል ወደቅድስተ ስላሴ ካቴድራል እንዲዛወር ተደርጓል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ የሙሰኞች ሰለባ ሆነው ከደሞዛቸው ቀንሰው ተዛውራችኋል የተባሉና አየር ላይ ተንሳፈው የሚገኙ አገልጋዮች ጥቂት አይደሉም፡፡ አባ እስጢፋኖስ ደላሎቻቸውና በጉቦ ወደሚዘረፍበት ደብር ዓይናቸውን የጣሉ ሙሰኞች የከፈቱት “የዝውውር መስኮት” መቼ እንደሚዘጋ አንድዬ ነው የሚያውቀው፡፡
አባ እስጢፋኖስ በዚህ ብቻ ሳይገቱ አንድ እግራቸውን ጅማ አንድ እግራቸውን አዲስ አበባ ላይ የተከሉ እንደመሆናቸው በአብዛኛው አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደላሎቹ በኩል ካልሆነ በቀር የማይገኙ ከመሆናቸውም በላይ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት ለጅማ ሀገረ ስብከት በሚል ከአንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች ጋር በመመሳጠር ገንዘብ እየጠየቁና እየተሰጣቸው መሆኑን ምንጮችን ይናገራሉ፡፡ በቅርቡ እንኳ ከአስኮ ገብርኤል 34 ሺህ ብር መውሰዳቸው ታውቋል፡፡ በጅማ ሀገረ ስብከት ስም ለአባ እስጢፋኖስ ፈሰስ የማያደርጉ አለቆች ግን ጥርስ ውስጥ ገብተው የዝውውር ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን እየተካሄደ ባለው የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ የአባ እስጢፋኖስ ጉዳይ ተነስቶ በሲኖዶስ አባላት ከሀገረ ስብከቱ ይነሱ የሚል ውሳኔ በጳጳሳቱ ሁሉ የተላለፈ ቢሆንም ፓትርያርክ ማትያስ ግን “ሀገረ ስብከቱ የእኔ ነው አይነሱም ይቀጥላሉ” ብለው መቃወማቸው ተሰምቷል፡፡ ጳጳሳቱ ግን በግልም ለአባ እስጢፋኖስ “ሳይዋረዱ ቀድመው ቢወርዱ ይሻላል” ብለው ምክር የሰጧቸው መሆናቸውን እየተናገሩ ነው፡፡ በተያያዘም ከድለላው ክበብ ውጪ ያሉ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች በሌሎች የአድባራትና ገዳማት ሠራተኞች ላይ የሚፈጸምውን ግፍና በደል፣ አቤቱታ ሰሚም በመታጣቱና ፍትሕ እየተዛባ በመሆኑ ምክንያት ከአባ እስጢፋኖስ ጋር አንሰራም በሚል ውስጥ ውስጡን ከፍተኛ ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን አብሯቸው እየሠራ ያለውና በሀገረ ስብከቱ እያዘዘ የሚገኘው ማቅ ለምን ዝም አለ? ዝርዝሩን በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን፡፡

Thursday, October 31, 2013

«የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በምድር ያደረገውንም ተኣምራት እንድታዩ ኑ» መዝ ፵፮፤፰


መዝሙረ ዳዊት
40፥5
አቤቱ አምላኬ፥ ያደረግኸው ተአምራት ብዙ ነው፥ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም ባወራም ብናገርም ከቍጥር ሁሉ በዛ።
46፥8
የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በምድር ያደረገውንም ተኣምራት እንድታዩ ኑ።
86፥10
አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና።


ቃል ኪዳንህ ከምድረ በዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና። ኢዮብ 5፥23




Wednesday, October 30, 2013

የማይቀረው ለውጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መጎብኘቱ አይቀርም!


ባልተዘጋጀችበትና በሚመጣው ለውጥ የሚደርስባት ጉዳት ከባድ ነው።
(ክፍል አምስት)
በክፍል አራት ጽሁፋችን በፍላጎት መጠን ማደግ፤ ለስኬት በሚደረገው ሩጫ፤ በኢንዱስትሪው ትንግርታዊ ግስጋሴና ለአእምሮ ልሽቀት የመጋለጥ አደጋ መካከል በሚኖረው ዕለታዊ የኑሮ መስተጋብር የተነሳ የአውሮፓውያን ሃይማኖቶች የማሽቆልቆል፤ የትርፍ ጊዜ ጉዳይ የማድረግ፤ ከዚያም አልፎ ተርፎ በሥራ ብቻ እንጂ በስብከት ልምምድ ምንም ጠብ የሚል ነገር እንደሌለ በመቁጠር ወደ ክሂዶተ እግዚአብሔር የመሄድ ነገር መጠኑ እንደጨመረ እንደሄደና ይህም ክስተት በኢትዮጵያችንም እየታየ መገኘቱን ለማመልከት ሞክረን ነበር። ከዚህም የተነሳ አብያተ ክርስቲያናት በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባት ነገር ግን ተግዳሮቶችን ለመከላከል የተወሰደ የጅማሮ ፍንጭ አለመኖሩን በማመልከት ለጉዳት የመጋለጣችንን አይቀሬነት በመጠቆም ጥቂት ለማሳየት ሞክረን ነበር። በዚህ ክፍል ደግሞ ቀጣዩን ነጥብ እንመለከታለን።

3/ የኑሮ ምቾት፤ ድሎት የተነሳ በሚከተለው ስግብግብነትና  የምኞት ከፍታ በሚያስከትለው የአእምሮ ድንዛዜ የተነሳ የሚመጣው የእምነት ጉድለት፤

በመስከረም ወር ኒውዮርክ ላይ ተደርጎ በነበረው  የተመድ ጉባዔ ላይ ከዓለም የመጨረሻው ደሃ ፕሬዚዳንት እንደሆኑ የሚታወቁት የኡሩጓይ/Uruguay/ ፕሬዚዳንት ጆሴ ሙጂካ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግር እንዲህ ብለው ነበር።
«ድሃ ማነው? የሚለውን ጥያቄ በኔ አፈታት ሲተረጎም ለመኖር ሲል ብዙ የሚፈልግ አስተሳሰብ ያለው ነው» ሲሉ መናገራቸው የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ነበር። ለምን? እንዲህ እንዳሉም በሰጡት ማብራሪያ «ብዙ የሚፈልጉ ሰዎች ያንን ለማሟላት የኅሊና እረፍት የላቸውም፤ ከዚህም የተነሳ በሕይወታቸው ሙሉ እንደሮጡና እንደደከሙ ይኖራሉ፤ በቃኝን አያውቁም። ከእነዚህ የበለጠ የመኖር እርካታ የሌላቸው ደሃ የትም የለም» በማለት ጉባዔውን አስደምመውት ነበር። የፕሬዚዳንት ጆሴ ሙጂካ ንግግር በኢትዮጵያውያን ምሳሌ በአጭር ቃል ሲቀመጥ «ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ» እን,ደማለት መሆኑ ነው። የ78 ዓመቱ ጆሴ ሙጂካ የኡሩጓይ ፕሬዚዳንት ይሁኑ እንጂ የሚተዳደሩት የገጠር መሬታቸውን በትራክተራቸው እያረሱ የሚተክሉትን ስኳር ድንችና ለውዝ ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸው በዓለማችን ላይ ካሉ የሀገር መሪዎች ልዩ ያደርጋቸዋል። በቅርቡ ለአንድ ቴሌቪዥን በሰጡት የቃለ መጠይቅ ምላሽ ላይ «የኑሮ ምቾትህ በጣም የተደላደለ ከሆነና ከሌላው ሕዝብ የተለህ እንደሆነ ማሰብ ከጀመርህ፤ በጣም ስግብግብና ስለምትኖርበት ዓለም ማሰብ የማይችል የደነዘዘ አእምሮ ተሸካሚ ትሆናለህ» በማለት መናገራቸው ብዙዎችን አስገርሟል። ሲወጡና ሲገቡ ቀይ ምንጣፍ የሚረግጡ መሪዎች፤ ተራ ሰው የነበሩና አጋጣሚዎች ከፍታ ላይ ያስቀመጣቸው ሰዎች በአብዛኛው ስግብግቦች ስለሆኑ ስለወጡበት ማኅበረሰብ ደንታ የላቸውም። ምክንያቱም ሰዎቹ ማሰብ ስለማይፈልጉ ሳይሆን የሚያስቡበትን አእምሮ የኑሮው ምቾትና የአእምሮ ድንዛዜ እንዳያስቡ ዘግቶ ስለሚይዛቸው ነው» ሲሉ ፕሬዚዳንቱ አክለው ተናግረው ነበር።

አባባላቸው ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያለው ነው። ይህ ሁኔታ በአውሮፓውያኑና በአጠቃላይ በምዕራባውያኑ ዘንድ ስር በመስደዱ የተነሳ የቅንጦት/Luxury/ ኑሯቸው መጠን የለሽ ወደመሆን በመሸጋገሩ የነበረውን አዲስ ነገር አውጥቶ በመጣል ለበለጠ አዲስ ነገር ራስን በማስገዛት አዲስ ቤት፤ አዲስ መኪና፤ አዲስ የቤት እቃ፤ አዲስ አዲስ ሁሉን አዲስ በማድረግ አባዜ አእምሮአቸው ደንዝዟል። ስግብግብነትና በቃኝ የማለትን ገደብ የማለፉ አስተሳሰብ የሚጎትተው እንከን ለተራበ ያለማዘንን፤ ለሰዎች ችግር አለመድረስ ብቻ ሳይሆን ደንታ ቢስ መሆንን፤ ተካፍሎ መብላት የሚለው ብሂል የሰነፎች መፈክር እንደሆነ ማሰብን የመሳሰሉ ችግሮችን ያስከትላል። ምንም እንኳን የተስተካከለ ኑሮን መኖር ጥፋት ባይሆንም በቃኝን አለማወቅ ግን ትልቅ በደል ነው። በተለይም ደግሞ ክርስቲያኖች ኑሮዬ ይበቃኛል ማለትን ካልተማሩ እግዚአብሔር እነሱን ለቅንጦት እንደፈጠራቸው ማሰብን መለማመዳቸው አይቀርም።
  ይህንን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ በመልእክቱ እንዲህ ይለናል። «ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ» ፊልጵ 4፤10-14

የጠገቡና በዚህ ጥጋብ  የተነሳ አእምሮአቸው የደነዘዘ፤ የሌሎችን ጥጋብ በማየት ለማግኘት የሚራወጡ፤ ትግላቸው ሁሉ የሥጋን ፍላጎት መሠረት  ያደረጉ ሰዎች በሌሎች ችግር የመካፈል ፍላጎት የላቸውም።  እምነት እንዳላቸው ቢያስቡም የእምነታቸው ከፊል ምኞታቸውን በማሳካት ላይ የታጠረ ነው። በአውሮፓ ይህንን መሰሉ ቅንጦትና መጠን የሌለው ምቾት በአእምሮ ላይ በመሰልጠኑ የተነሳ አብያተ ክርስቲያናቱ አማኞችን ከማስተናገድ ተላቀው ወደመዝናኛና ሆቴልነት፤ የገበያ አዳራሽነትና ጋራዥነት ለመቀየር ተገደዋል። በክርስትና ስም ከሚጠራው ተከታይ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በዕለተ እሁድ የጸሎት ፕሮግራም ላይ የሚገኘው ተሳታፊ ቁጥር በጣም አሽቆልቁሏል። በእንግሊዝ 1,4% ፤ በፈረንሳይ 0,9%፤ በጀርመን 1,2% ብቻ እንደሚገኙ ክርስቲያን ፖስት በ2011 ዓ/ም ባደረገው ጥናት የችግሩን ጥልቀት ለማሳየት ሞክሯል። የሥነ ምግባር ልሽቀት፤ ስግብግብነት፤ የግብረ ገብነት ድቀት መነሻው የሰው ልጅ የተፈጠረበትን ምክንያት ካለማወቅና ባወቀው ላይ ለመኖር ካለመፈለግ የሚመነጭ ውስጣዊና ውጫዊ ግፊት የተነሳ የሚመጣ ነው። ምዕራባዊው ኑሮ አሁን አሁን መሥፈሪያውን የሞላ/ Saturate/ ያደረገ ይመስላል። እድገቱን የጨረሰ የወይን ግንድ  እንደገና ተገርዞ ካልታደሰ በስተቀር ፍሬ ከማፍራት መለየቱና መድረቁ የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የማብቃቱ ጉዳይ ሳይታለም የተፈታ ነው።
ኢትዮጵያችንን ስንቃኝ የእድገት መሥፈሪያዋ ሞልቷን ማለት አንችልም። ይሁን እንጂ እንደሀገር ለመቀጠል መስራትና ማደግ የግድ የማለቱን ያህል ዕለታዊ የኑሮ መስተጋብራችንን የሚሻማ የሥራና የሩጫ ሕይወት ወደመለማመዱ መግባታችን አይቀሬ ነው። ከዚህም የተነሳ ዘመኑን የዋጀ የሃይማኖት አስተምህሮና የተግባር ተሞክሮ በአማኞቻችን ውስጥ ማሳደግ ካልቻልን ጥያቄን በሚያጭሩ፤ እምነትን በሚሸረሽሩና ምላሽ በሚጠይቁ ዙሪያ ገባ ጥያቄዎች መወጠራችን አይቀርም። ትውልዱን አስፈራርተው፤ በማያረካ ምክንያት ውስጥ አእምሮን በመደበቅ ማሳመን አይቻልም። ወደዚህ ምድር የመጣበትን ምክንያትና የመኖር ልኬታን የማይዘነጋ ልቡናን እንዲጨብጥ የሚያስችል መንፈሳዊ የቃል ወተትን መጋት፤ እንደአዋቂ ማሰብ የሚችልበትን የእምነት ተስፋ እንዲጠባበቅ ካላደረግነው ቤተ ክርስቲያን የታሪክ ትምህርት ቤት ወደመሆን መቀየሯ አይቀርም። ኑሮዬ ይበቃኛልን ማሰብ የተወ ትውልድ ሌብነትን፤ ዝርፊያን፤ ሙስናን፤ ዝሙትን፤አስገድዶ መድፈርን፤ ግድያንና ልዩ ልዩ ወንጀልን መላመዱ አይቀርም። እውነተኛ እምነት ከዚህ ሁሉ አስከፊ ማንነት ይከላከላል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አሁን ያለንበት መንፈስ በቆየ መልካም ባህልና ከቤተሰብእ በተወረሰ ልምድ ብዙ የሚያሳስብ የላሸቀ የትውልድ ውድቀት ባይታይም ፍንጮች መኖራቸውን መካድ አይቻልም። ከሁሉም ሃይማኖቶች ዘንድ ጉድለቶቹ የትውልዱን ድክመት እያመላከቱ ናቸው። ገንዘብንና ጥቅምን መሠረት ያደረጉ አብያተ ክርስቲያናት መስፋፋታቸው፤ በአስነዋሪ ስነ ምግባራቸው የተነሳ በሰማይም በምድርም  ከፍ ያለው የእግዚአብሔር ስም እንዲሰደብ ምክንያት መሆናቸውን እያየን ነው። ዝሙት፤ ስርቆት፤ ስግብግብነት፤ ዘረኝነት፤ አድልዎ፤ ፍትህ ማጣመም፤ በደልና ብቀላ እየነገሠ ነው። ጥላቻና ቂም እየተዘራና እያደገ ይገኛል። ዘረፋና ጉቦ የብዙዎችን ዓይን አሳውሯል። «ማሰነ» ከሚለው ግእዛዊ ግስ የተጨለፈችው «ሙስና» የተሰኘችው ዘመናዊ ቃል የሚዲያ የእርግማን ጸሎት መሆን ከጀመረችም ሰነባብታለች። በዚህ ላይ የአብያተ ክርስቲያናቱ ስፍራ የት ነው? ብለን እንጠይቃለን።
አብያተ ክርስቲያናቱ እንኳን ለሌላው ብርሃን ሊሆኑ ቀርተው ራሳቸው በችግሩ ማስነዋል። ስግብግብነት፤ ለድሎትና ምቾት የመራወጥ አባዜ ተበራክቷል። ገንዘብን ብቻ ማዕከል ያደረገ በእግዚአብሔር ስም የመሸቀጥ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። ዝሙትና ገንዘብ መለያቸው ሆኗል። ከወንጌላውያኑ ጀምሮ እስከ ኦርቶዶክሳውያኑ ድረስ የዚህ በሽታ ምልክት  ስር ሰዷል። የዚህ ዓይነቱ ፈሪሃ እግዚአብሔር የመጥፋቱ ነገር ለኑሮ ስኬት የሚራወጠውን ህዝብ አእምሮ አይበርዘውም ማለት አይቻልም።

ከዚህም የተነሳ ሃይማኖት ለእግዚአብሔር አምልኮ የምንሰራበት የማንነታችን ቤት እንደሆነ የማሰቡ ነገር ይቀርና ክህዶተ እግዚአብሔር የሚስፋፋበት፤ አእምሮአችንን ከተስፋ ማጣት የተነሳ ደንዝዞ ሥጋንና ሥጋን ብቻ ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ተሸካሚዎች እንዳንሆን ያስፈራል። ይህ የእምነት ጉድለት ደግሞ ከእግዚአብሔር ጥበቃና ከለላ ውጭ ሊያደርገን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ «ኑሮዬ ይበቃኛል አለማለት ወደጥፋት ያደርሳል» ማለቱን ማስተዋል ተገቢ ነው።
  «ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል»1ኛ ጢሞ 6፤6-11
አውሮፓውያኑንም ሲጀምራቸው እንደዚሁ በትንሽ በትንሹ ነበር። ምቾትና ምኞት የወለደው ስግብግብነት ሩጫቸውን  በእጦት ቀውስ እየመታው ይገኛል። በእነሱ የደረሰ በእኛም ይህ እንዳይሆንብን ከፈለግን መሥራት የሚገባን ዛሬ ነው። የቀነሰብንን የሰው ቁጥር ለማወቅ ስንፈልግ ያለንን እንዳናጣ እኛው ራሳችን ለመቆጠር የሚያበቃ ማንነትን እንዳለን ቆም ብለን እናስተውል። ምድራዊው ቁጥር የሰማያዊውን መዝገብ ቁጥር አይተካምና።
 ከፕሬዚዳንት ጆሴ ሙጂካ አብነታዊ ቃል ጠቅሰን ጽሁፋችንን እናጠቃልል።  «እኔ የተወለድኩት ከሕዝቡ ነው። የኖርኩትና ያደኩት ሕዝቡ መሃከል ነው። ያሳደገኝ ሕዝብ ሲሾመኝ ስራልኝ እንጂ የተሻለ ኑሮ ኑርልኝ የሚል ውክልና አልሰጠኝም። የቻልኩትን ሁሉ ሕዝቡና ለምርጫው የፈቀደኝ እግዚአብሔር የሰጠኝን ችሎታ ሁሉ ሰርቼ ይበቃሃል ሲሉኝ ሕዝቡ መሐከል ተመልሼ እኖራለሁ። በሕይወቴ ሙሉ ኑሮዬ ይበቃኛልን ስለተማርኩ ወደሥልጣን ስመጣ ባዶዬን ነበርኩ፤ ስሄድም ባዶዬን ነው፤ ሳልመጣም፤ ከመጣሁም በኋላ ይሁን ስሄድ ድንች ተክዬ በላቤ ወዝ ብቻ ሰርቼ እኖራለሁ»