የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ሆነውና ያሉበትን ሥፍራ ተተግነው እንደልዩ የመረጃ
ምንጭ መስለው ቅጥፈት የሚዘሩ ብሎጎች ብቅ ብቅ ማለታቸውን ስናይ ቆይተናል። ከእነዚህም አንዱ «እኔ የቤተክርስቲያን ወታደር ነኝ»
በማለት ራሱን ያስተዋወቀው አንድ ብሎግ ወታደርነቱን እጠብቃታለሁ ለሚለው ቤተክርስቲያን ዓላማ ብቻ ማዋል ሲገባው ሲፈልግ ለግለሰቦች
ጋሻና መከታነቱን የሚያሳይ፤ ዛሩ ሲነሳበት ደግሞ ጋሻ የሆነላቸውን ሰዎች ቆሌ በመግፈፍ ካርታው እንደጠፋበት ወታደር እዚህም፤ እዚያም
የሚዳክር ሆኖ ይስተዋላል።
በእጃችን ያሉ መረጃዎችን መሠረት አድርገን፤ ነገር ግን መረጃዎቹን ትተን
ጥቅል ችግሮቹን ብቻ ከዚህ በፊት ስለዝዋይ ገዳም አስነዋሪ ተግባራት በዘገብን ጊዜ ይህ ወታደር ነኝ ባዩ ብሎግ ሽንጡን ገትሮ ለሊቀጳጳሱ
በመከራከር እንባ ቀረሽ ልቅሶውን በጽሁፍ ባስነበበን ጊዜ ወታደር ነኝ የሚለው ዲስኩሩን ትተን «የዓይጥ ምስክር ድንቢጥ» በማለት
አልፈነው ነበር።
ይኸው የቤተክርስቲያን ወታደር ነኝ ባዩ ብሎግ ስለዝዋዩ ሊቀጳጳስ ጠበቃ መሆኑን
በጽሁፉ ባሰፈረ ጊዜ በልማት፤ በማኅበራዊና በመንፈሳዊ እድገት ትልቅ
እመርታ ማሳየታቸውን ጠቅሶ ሊቀጳጳሱ ላይ የስም ማጥፋት እርምጃ ለመውሰድ የፈለጉ ወገኖች መነሻ ምክንያታቸው «የኦሮሞ ፓትርያርክ
ለማሾም የሚራወጡ ቡድኖች ጠባብ አስተሳሰብ ያመጣው ችግር ነው» በማለት
ነጭ ውሸቱን በድጋፍ ዘመቻው በማከል ጠበቃነቱን ማሳየቱ አይዘነጋም። ጽሁፉን ያነበብን አንዳንድ ወገኖች የኦሮሞ ፓትርያርክ ዝዋይ ላይ መሾም እንዴት እንደሚቻል አዲሱን ግኝት አያይዞ
ባለማብራራቱ ግር ብንሰኝም እንደአስፈጋጊ ቀልድ እውነታውን ስለምናውቅ በወቅቱ አልፈነው ነበር። ይኼው ብሎግ ለሊቀጳጳሱ በወቅቱ
ከሰጠው ምስክርነት ጥቂቱን ጠቅሰው ወደሌላው «በአንድ ራስ ሁለት ምላስ» ጽሁፉ እናመራለን።
«ሁለቱም አካላት በተለያዩ መንሥኤዎች የገዳሙንና የብፁዕነታቸውን ስም ለማጥፋት ይሞክሩ እንጂ በአንድ
ጎራ ያሰለፋቸው ስጋት ተመሳሳይ እንደኾነ ምንጮቹ ጨምረው ያስረዳሉ፡፡ ይህም ስጋት ብፁዕነታቸው በቀድሞው ፓትርያሪክ እንደ እንደራሴም
እንደ ተተኪም መታጨታቸውና ለዚህም ዓላማ ፓትርያሪኩ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋራ እንዳስተዋወቋቸው የሚነገርላቸው ብፁዕ
አቡነ ጎርጎሬዎስ ስድስተኛው ፓትርያሪክ ለመኾን በመንግሥት ታጭተዋል
በሚል የመነገሩ ወሬ ነው»
ይህ ከላይ በቀይ የተቀመጠው ጽሁፍ የቤተክርስቲያን ወታደር ነኝ ባዩ ብሎግ
የሊቀጳጳሱ ወታደር ሆኖ በወቅቱ የጽሁፍ ምስክርነቱን በመስጠት በብሎጉ ላይ ያሰፈረው ነበር። ይኼው ብሎግ ከወራት በኋላ ማለትም ጥር 6/2005 ጀምሮ የተደረገውን የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ
ተከትሎ በሚወጡ ዘገባዎች ላይ የሊቀጳጳሱ ጫና እያየለና ተሰሚነታቸው እየተጠናከረ መምጣቱን ተከትሎ ወደ ፓትርያርክነት የሚያደርጉትን
የእጩነት ጉዞ በማጥላላት ዘመቻ ውስጥ ገብቶ፤በመዘገብ ላይ መጠመዱ ነገሩን ሁሉ አስገራሚ ያደርገዋል።