ብዙ መጠላላትና መነቃቀፍ ብዙ ቦታ ተሰጥቶት መገኘቱን በየእለት ውሎአችን እናያለን። እውነት፤ እውነቱን መነጋገር ቢቻልም መነቃቀፍ በበዛበት ዓለም እውነቱን በእውነታ
ለመቀበል የሚቸገርም ሞልቷል። የሚቀበል ቢኖርም፤ ባይኖርም እውነት ነው ብለን ያመንበትን መናገር እንዳለብን ስለምናምን መናገራችንን አናቋርጥም። ዛሬም በዚህ
ጽሁፋችን የምናውቃቸውን እውነታዎች፤ አንዳንዱ እውነት ነው ብሎ እንደሚቀበልና የዚህ ተጻጻሪው ደግሞ ጥላሸት በመቀባት ልምዱ የቆመበትን
ስፍራ በቃሉ እንደሚያሳየን በማሰብ ጥቂት ለመግለጽ የምፈልጋቸው ነገሮች
አሉን። ጽሁፋችንም በቤተክርስቲያናችን ዙሪያ ያጠነጥናል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእምነት
ዓምድ /ዶግማ/ ማለትም ምሥጢረ ሥላሴን አብርታ፤ አምልታና አስፋፍታ በማስተማር፤ እንዲሁም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ሥጋ የለበሰበትን
ረቂቅ ምሥጢር ፤ ምሥጢረ ሥጋዌውን አብራርታ በመስበኳ የታነጸችበትን ሃይማኖታዊ አለት/ ኰክሕ/ ስንመለከት በእውነትም የእግዚአብሔር
ደጅ ናት ብንላት ቢያንሳት እንጂ አይበዛባትም። በክርስቶስ መሠረት ላይ የታነጸች፤ በሐዋርያት ትምህርት ያደገችና በሊቃውንቱ በእነአትናቴዎስ፤ ባስልዮስ፤
ጎርጎርዮስ ወዘተ የምሁራን አስተምህሮ የበለጸገች መሆኗን ማንም ሊክደው የማይችል የታሪክ እውነት ነው።
ዳሩ ግን ይህንን መሠረቷን የሚንዱ፤ ወንጌሏን ወደጎን የሚገፉ፤ አጋንንታዊ ልምምዶችን በስመ ሥሉስ ቅዱስ የሚያስፋፉ፣
ተከታዮቿ ዓይናቸውን ከክርስቶስ ላይ ነቅለው በየምናምኑ ላይ እንዲተክሉ
የሚያበረታቱ ብዙ አሳዛኝ መጻሕፍት በተረት፤ በእንቆቅልሽ፤ በወግና በአስማት ተሸፍነው የቤተክርስቲያኒቱን የወንጌል አስተምህሮ ማእድ
በመበከል መርዛቸውን ታቅፋ እንድትኖር መገደዷን አስተዋዩ በደንብ ሲረዳው፤ እልከኛውም በአፉ ለመመስከር ያቅተው እንደሆን እንጂ ችግር እንዳለ ልቡናው እንደሚመሰክርበት
እናስባለን።
ልበ ጠማሞች ደግሞ «በድሮ በሬ ያረሰ የለም» የሚለውን ብሂለ አበውን ከአፋቸው ሳያወርዱ ፤ በዚያው መራር አፋቸው ደግሞ
በድሮ ስር ለመደበቅ «የቀደመውን ድንበር አታፍርስ» ከማለታቸውም
በላይ ከእኔ ወዲያ ለአባቶቼ ርስት ቀናዒ የለም! በሚል የኩራት ካባ በመደረብ የቤተክርስቲያኒቱን የወንጌል ማእድ የመረዙትን ህጸጾች
መነካት የለባቸውም በማለት የግብር አባታቸውን ሥራ ተረክበው ሳያስተጓጉሉ ለማስጠበቅ ሲታገሉ ኖረዋል፤እየታገሉም ይገኛሉ ። ደግሞ እናንተ እነማን ናችሁ? በማለት ለጥያቄዎች
መልስ የመስጠት ብቃቱ ሳይኖራቸውና መልስ ይሰጡ ዘንድ ማንም ሳያስቀምጣቸው ራሳቸውን ሰይመው መገኘታቸውም የሚገርም ነው።