በንጽህናና በድንግልና እየኖሩ የክርስቶስን የማዳን ሥራ ዘወትር እያሰቡ መኖር የእውነተኛ ክርስቲያን አንዱ ገጽታ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስም ይህንን ሲገልጸው «ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ
እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባልና» በማለት ሳያገቡ የክርስቶስን መከራ ሞት እያሰቡና የሕይወታቸው መመሪያ አድርገው ለሚኖሩ ትልቅ ሥፍራ ሰጥቷቸው
ይገኛል። (1ኛ ቆሮ 7፤32)
ይህ ማለት ግን ያገቡ ሰዎች ክርስቶስን ማገልገል አይችሉም ማለት አይደለም። እንዲያውም የሌላቸውን ጸጋ ለማግኘት ሲሉ በትግልና በትልቅ ፈተና ስር ራሳቸውን ጥለው
ሥጋቸውን በመጨቆን የሚያሰቃዩትን ሰዎች በድንግልና ያለመቀጠል ብቃታቸውን እንዲህ ሲል ከፈተናቸው እንዲላቀቁ በጌታ መንፈስ ይመክራቸዋል።
«ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ» 1ኛ ቆሮ 7፤ 9
ክርስቲያን መኖር የሚገባው በተሰጠው ጸጋ እንጂ የሌለውንና ያልተጠራበትን ጸጋ በጥረቱ ለማግኘት በመፈለግ ባለመሆኑ አንዳንዶች
በድንግልና እንኖራለን ብለው ሲያበቁ አዳማዊ ማንነታቸው ከሔዋን ጋር የሚያጣምር ሲሆንባቸውና ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ምኞት ስር ሲጥላቸው
የሥጋ ብልቶቻቸውን በቢላዋ ጎምደው እስከመጣል ይደርሳሉ። ይሁን እንጂ የሥጋ ብልታቸው መቆረጡ የልብ ምኞታቸውም ቆርጦ ሊያስቀረው
የማይችል ስለሆነ ዘወትር እንደተቅበዘብዙ ይናራሉ።
«ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፥ አንዱ እንደዚህ
ሁለተኛውም እንደዚያ» 1ኛ ቆሮ 7፤7
ሐዋርያው እንዳለው በድንግልና የጌታን ነገር ብቻ እያሰቡ መኖር የተሻለ መሆኑ አይካድም። ይህ ጸጋ ለሁሉም የሚሰጥ ባለመሆኑ አንዳንዶች ጸጋቸውን ሳያውቁ ሰዎች በደነገጉት
የድንግልና ሕግ ሥር ወድቀው የራሳቸውን የጽድቅ መንገድ ለማቆም እየታገሉና እየተቃጠሉ መኖራቸው እርግጥ ነው። የሥጋ ብልቶቻቸውን ከመቁረጥ አንስቶ አስገድዶ
እስከመድፈር ፤ እንስቶችን አባብሎ ከመዳራትና የስርቆሽ ዝሙት እስከመፈጸም መድረሳቸው የሰውኛ ጥረት ውጤት ነው። አንዳንዶቹ የሥጋው ፈተና የመጨረሻው ጣሪያ ላይ
ሲደርስባቸው ለክፉ መንፈስ ተጋልጠው ግብረ ሰዶም እስከመፈጸም ይደርሳሉ።
«የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም» ሮሜ 10፤3
የተባለው የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ ለመጽደቅና የራሳቸውን ጽድቅ ለማቆም ሲታገሉ ከጽድቁ ሥራ ወጥተው የቀሩትን ይህ ቃለ እግዚአብሔር ተፈጽሞባቸዋል
ማለት ይቻላል።
ከዓለማውያን ሰዎች ባልተሻለ መልኩ አባ እገሌ እገሊትን ደፍረው ተያዙ፤ አቡነ እገሌ ልጅ ወለዱ፤ እነአባ እገሌም ግብረ ሰዶም ፈጸሙ እየተባለ ለሰሚ የሚቀፍ ዜና የሚሰማው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ
የሌላቸውን ጸጋ ለማግኘት ሲታገሉ ቆይተው የጭናቸው እሳት እየፈጀ መቆሚያና መቀመጫ ስለሚያሳጣቸው ነው። በቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ
በሰው ሚስት ላይ የተያዙ፤ አስገድደው የደፈሩ፤ አልፎ ተርፎም ግብረ ሰዶም ፈጽመው የተገኙ የብዙ አባዎች ጉዳይ አሳሳቢነት ለሲኖዶስ
ጉባዔ መወያያ ሆኖ መቅረቡ አይዘነጋም።
ይህ እንግዲህ የምናውቃቸውንና የምንሰማቸውን አስጸያፊ ተግባራት ሳይጨምር መሆኑ ነው። ይህን ማንሳት በሥጋ ድካም መነኮሳት
የሰሩትን ኃጢአት ለማውራት ሳይሆን የጋብቻን ክቡርነት የሚናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል በመጋፋት የራሳቸውን ሕግ ለማቆም በመታገል
መካከል በሚፈጠረው ሽንፈት የተነሳ ኢ-ሞራላዊ፤ ኢ- ምግባራዊና ጸረ ሃይማኖታዊ አድራጎት እየተስፋፋ በመገኘቱ ምክንያት እንደሆነ
መታወቅ አለበት። የማይቻለውን ለመቻል ሲታገሉ ሽንፈታቸው መረን የለሽ ወደመሆን አድርሷቸው የመገኘታቸው ነገር ግልጽ ወጥቶ በመነጋገር አንድ እልባት
ላይ መድረስ ካልተቻለ ድርጊቱ ማቆሚያ የሌለው ሆኖ ይቀጥላል። ይህም በተጎጂው ላይ፤ በእምነቱ ተከታይ ውስጥ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ
አሉታዊ አስተሳሰብ እንዲኖር የማድረጉ ነገር ማብቂያ የለውም።