Saturday, January 5, 2013

ምንኩስናና ጋብቻ!

በንጽህናና በድንግልና እየኖሩ የክርስቶስን የማዳን ሥራ ዘወትር እያሰቡ መኖር የእውነተኛ ክርስቲያን አንዱ ገጽታ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም ይህንን ሲገልጸው  «ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባልና» በማለት ሳያገቡ የክርስቶስን  መከራ ሞት እያሰቡና የሕይወታቸው መመሪያ አድርገው ለሚኖሩ ትልቅ ሥፍራ ሰጥቷቸው ይገኛል። (1ኛ ቆሮ 7፤32)

ይህ ማለት ግን ያገቡ ሰዎች ክርስቶስን ማገልገል አይችሉም  ማለት አይደለም። እንዲያውም  የሌላቸውን ጸጋ ለማግኘት ሲሉ በትግልና በትልቅ ፈተና ስር ራሳቸውን ጥለው ሥጋቸውን በመጨቆን የሚያሰቃዩትን ሰዎች በድንግልና ያለመቀጠል ብቃታቸውን እንዲህ ሲል ከፈተናቸው እንዲላቀቁ በጌታ መንፈስ ይመክራቸዋል።
«ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ» 1ኛ ቆሮ 7፤ 9
ክርስቲያን መኖር የሚገባው በተሰጠው ጸጋ እንጂ የሌለውንና ያልተጠራበትን ጸጋ በጥረቱ ለማግኘት በመፈለግ ባለመሆኑ አንዳንዶች በድንግልና እንኖራለን ብለው ሲያበቁ አዳማዊ ማንነታቸው ከሔዋን ጋር የሚያጣምር ሲሆንባቸውና ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ምኞት ስር ሲጥላቸው የሥጋ ብልቶቻቸውን በቢላዋ ጎምደው እስከመጣል ይደርሳሉ። ይሁን እንጂ የሥጋ ብልታቸው መቆረጡ የልብ ምኞታቸውም ቆርጦ ሊያስቀረው የማይችል ስለሆነ ዘወትር እንደተቅበዘብዙ ይናራሉ።
«ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፥ አንዱ እንደዚህ ሁለተኛውም እንደዚያ»  1ኛ ቆሮ 7፤7

ሐዋርያው እንዳለው በድንግልና የጌታን ነገር ብቻ እያሰቡ መኖር የተሻለ መሆኑ አይካድም።  ይህ ጸጋ ለሁሉም የሚሰጥ ባለመሆኑ አንዳንዶች ጸጋቸውን ሳያውቁ ሰዎች በደነገጉት የድንግልና ሕግ ሥር ወድቀው የራሳቸውን የጽድቅ መንገድ ለማቆም እየታገሉና  እየተቃጠሉ መኖራቸው እርግጥ ነው። የሥጋ ብልቶቻቸውን ከመቁረጥ አንስቶ አስገድዶ እስከመድፈር ፤ እንስቶችን አባብሎ ከመዳራትና የስርቆሽ ዝሙት እስከመፈጸም መድረሳቸው  የሰውኛ ጥረት ውጤት ነው። አንዳንዶቹ የሥጋው ፈተና የመጨረሻው ጣሪያ ላይ ሲደርስባቸው ለክፉ መንፈስ ተጋልጠው ግብረ ሰዶም እስከመፈጸም ይደርሳሉ።
«የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም» ሮሜ 10፤3
 የተባለው  የእግዚአብሔርን ጽድቅ  ሳያውቁ ለመጽደቅና የራሳቸውን ጽድቅ ለማቆም  ሲታገሉ ከጽድቁ ሥራ ወጥተው የቀሩትን ይህ ቃለ እግዚአብሔር ተፈጽሞባቸዋል ማለት ይቻላል።

ከዓለማውያን ሰዎች ባልተሻለ መልኩ አባ እገሌ እገሊትን ደፍረው ተያዙ፤ አቡነ እገሌ ልጅ ወለዱ፤ እነአባ እገሌም  ግብረ ሰዶም ፈጸሙ እየተባለ ለሰሚ የሚቀፍ ዜና የሚሰማው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ የሌላቸውን ጸጋ ለማግኘት ሲታገሉ ቆይተው የጭናቸው እሳት እየፈጀ መቆሚያና መቀመጫ ስለሚያሳጣቸው ነው። በቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ በሰው ሚስት ላይ የተያዙ፤ አስገድደው የደፈሩ፤ አልፎ ተርፎም ግብረ ሰዶም ፈጽመው የተገኙ የብዙ አባዎች ጉዳይ አሳሳቢነት ለሲኖዶስ ጉባዔ መወያያ  ሆኖ  መቅረቡ አይዘነጋም።
ይህ እንግዲህ የምናውቃቸውንና የምንሰማቸውን አስጸያፊ ተግባራት ሳይጨምር መሆኑ ነው። ይህን ማንሳት በሥጋ ድካም መነኮሳት የሰሩትን ኃጢአት ለማውራት ሳይሆን የጋብቻን ክቡርነት የሚናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል በመጋፋት የራሳቸውን ሕግ ለማቆም በመታገል መካከል በሚፈጠረው ሽንፈት የተነሳ ኢ-ሞራላዊ፤ ኢ- ምግባራዊና ጸረ ሃይማኖታዊ አድራጎት እየተስፋፋ በመገኘቱ ምክንያት እንደሆነ መታወቅ አለበት። የማይቻለውን ለመቻል ሲታገሉ ሽንፈታቸው መረን የለሽ ወደመሆን አድርሷቸው  የመገኘታቸው ነገር ግልጽ ወጥቶ በመነጋገር  አንድ  እልባት ላይ መድረስ ካልተቻለ ድርጊቱ ማቆሚያ የሌለው ሆኖ ይቀጥላል። ይህም በተጎጂው ላይ፤ በእምነቱ ተከታይ ውስጥ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ አሉታዊ አስተሳሰብ እንዲኖር የማድረጉ ነገር ማብቂያ የለውም።

Friday, January 4, 2013

«የሦስት ልጆች አባት የሆነው አምላክ፤ የኢሬቻ በዓል»



12, 000 ሺህ ዓመት በፊት የኩሾች ፈርዖን፤ የሰማይና ጸሐይ   «አስራ» የተባለው አምላክ ሦስት ልጆችን ወለደ።  የመጀመሪያ ወንድ ልጁ «ሴቴ»፤ ሁለተኛው ልጁ ደግሞ «ኦራ» ሲባል የመጨረሻ ሴት ልጁ ደግሞ «አቴቴ» ወይም አድባር የምትባል ነበረች። ከጸሐይና ከሰማይ አምላክ «አስራ»  ልጆች መካከል ሴቴ የተባለው የመጀመሪያ ልጁ ታናሽ ወንድሙን ኦራን በድንጋይ ገደለው። በወንድሟ ሞት እጅግ ያዘነችው «አቴቴ»  ዐባይ ወንዝ ዳርቻ ባረፈው በሟች በወንድሟ መቃብር ላይ «ኦዳ» የተባለውን ዛፍ ለመታሰቢያነት ተከለች።
አቴቴ (አድባር) በመቀጠልም ያደረገችው ነገር በገዳይና በሟች ወንድሞቿ ቤተሰቦች መካከል በቀልና ጥላቻ እንዳይኖር ወደሰማይና ጸሐይ አምላክ አባቷ  ወደ አስራ በማመልከቷ የሰላም ምልክት እንዲሆን ከሰማያት ዝናብ ዘንቦ የተከለችውን «ኦዳ» የተባለውን በማለምለም ሰላም እንዲሰፍን አድርጎላታል።

ሟች ኦራም በኦዳ ዛፍ ልምላሜ የተነሳ በጸሐይና በሰማይ አምላክ አባቱ ሥልጣን ምክንያት ከሞት የተነሳና ያረገ ሲሆን ይኸው በኦዳ ዛፍ ስር ሟች ኦራን በማስታወስ የሚደረገው የሰላምና የምህረት አከባበር ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ቀጥሏል። በቀደምት ኑቢያውያን የሚደረገው አከባበር  በጥንታውያን የአክሱም ስርወ መንግሥትም ዘመን የኦራ መታሰቢያን የሚያመለክት ቋሚ ድንጋዮችን በመትከል ሲታሰብ ኖሯል።

Wednesday, January 2, 2013

አቡነ አብርሃም ቃለ ዐዋዲን ጥሰው ሕገ ወጥ ሥራ እንዲሠራ ትዕዛዝ አስተላለፉ!

 በአዲስ አበቤው ካህን ዘንድ «የጉድ ሙዳይ» የሚል ስመ ተጸውዖ አላቸው። በየሄዱበት የራሳቸውንና የማቅን ስርወ መንግሥት ማደራጀት ተቀዳሚ ተግባራቸው ነው። ከአሜሪካ ተነስተው ሐረር ከወረዱ አንስቶ እንደ በቆሎ የሚጠብሱት የሐረር ምእመናንና ካህናት ፍዳውን እያየ ነው። ከብዙ ወሰን አልባና ጠያቂ የለሽ እርምጃዎቻቸው መካከል በ /www.deselaam-dejeselaam.blogspot.com/ ያገኘነውን  መረጃ፤ አካፍለናችሗል።። መልካም ንባብ!

በሐረር መድኃኔዓለም ደብር አስተዳዳሪ ላይ ሥልጣነ ክህነት እስከመያዝ የሚያደርስ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ
የዘረኝነት መንፈስ የተጠናወታቸው አቡነ አብርሃም ከጉርሱም ያመጡትን ጎጃሜ የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ነፃነትን የሐረር መድኃኔዓለም ስብከተ ወንጌል ኃላፊ ሆኖ እንዲመደብ አስገዳጅ ትዕዛዘ አስተላለፉ፡፡ ሊቀጳጳሱ ይህንን ትዕዛዝ ከማስተላለፋቸው በፊት በዓመታዊው የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ቁልቢ የሄዱ ሲሆን ወደ ሐረር እስከሚመለሱ አላደርስ ብሏቸው ካሉበት ሆነው የመድኃኔ ዓለም አስተዳዳሪውንና የሰበካ ጉባዔው ምክትል ሰብሳቢውን ጠርተው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡
ለማስጠንቀቂያው የተጠቀሰው ዋና ምክንያት የደብሩ ሰበካ ጉባዔ በውስጥ ካሉት ካህናት መካከል በማስታወቂያ አወዳድሮ መመደቡ ሲሆን፣ ደብሩ ይህንን ሽሮ የሥራ መደቡን ለጉርሱሙ የራጉኤል ደብር አለቃ ክፍት አድርጎ ለምን አልተቀበላቸውም የሚል ነው፡፡ የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤቱ የደብሩን ስብከተ ወንጌል ኃላፊ ቀሲስ ፋሲል አጥናፉን በዕድገት ወደ ራሱ ጽ/ቤት ስብከተ ወንጌል ክፍል ሲወስድ በተፈጠረው ክፍት መደብ ላይ የደብሩ ሰበካ ጉባዔ አወዳድሮ መቅጠሩ በአቡነ አብርሃም ዘንድ እንደ ጥፋትና ድፍረት ተቆጥሯል፡፡
ቃለ ዐዋዲው የደብሩ ሰበካ ጉባዔ ከካህናት መካከል አወዳድሮ በደብሩ ስብከተ ወንጌል ኃላፊነት የሥራ መደብ ላይ የመመደብ ሙሉ ሥልጣን ያለው ሲሆን የተመደቡት ካህንም ሙሉ መስፈርቱን አሟልተው ዕድገቱን እስካገኙ ድረስ አቡነ አብርሃም በሥራ አስኪያጃቸው በኩል ይህንኑ ተቀብለው ማፅደቅ ነበረባቸው፡፡ ይሁን እንጂ፣ እርሳቸው ይህንን በጉልበት ሽረው "የጉርሱሙን አስተዳዳሪ ተቀበሉ"! ብለው ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ በየትኛው ማስታወቂያ አወዳድረው እንደቀጠሩ ሲጠየቁ "ዕወቅ እንጂ፣ አትመራመር" በሚል አምባገነናዊ አስተሳሰብ ያሻኝን አደርጋለሁ በሚል ስሜት ቀጭን ትዕዛዝ በማስተላለፍ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የጉርሱሙ የደብር አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ነፃነት ወደ ሐረር መድኃኔዓለም ደብር ስብከተ ወንጌል ኃላፊነት መደብ ተዛውረው ሲመጡ የሽረት(የዝቅታ) ያህል ነው፡፡ "አቡነ አብርሃም ለሰውዬው ካዘኑላቸው ለምን እዚያው ሀገረ ስብከት ጽ/ቤቱ ውስጥ ቦታ አልፈለጉላቸውም"? ብለው ብዙዎች ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን አቡነ አብርሃምም ሆኑ አስተደሳዳሪው ያንን መደብ ለመያዝ የቋመጡበት ምክንያት በይፋ ባይታወቅም፣ ቤተክርስቲያንን በጎጃሜዎች ለመሙላት እና እግረ መንገድም አድባራትንና ገዳማትን በ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባላት ለማስያዝ  ነው ሲሉ ብዙዎች አስተያየት ይሰጣሉ፡፡