Tuesday, October 9, 2012

መንግሥት ፓትርያርክ ማን ሊሆን እንደሚችል በውስጥ መሰየሙን ይነገራል።

ከታማኝ የውስጥ ምንጮች የደረሰን ዜና እንደሚያስረዳው ስድስተኛው ፓትርያርክ በመንግሥት ደረጃ ምልመላው ያለቀ ሲሆን ይህ መረጃም በማኅበረ ቅዱሳንና በቀንደኛ ጳጳሳት ዘንድም  የውስጥ ግንዛቤ እንዲያዝ ተደርጎበታል ተብሏል።
የእርቅ ሂደቱ ቢያልቅና የውጭዎቹ ጳጳሳት ከሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ጋር በሚደረገው ስምምነት ወደአንድነት ቢጠቃለሉ ሲኖዶሱ በሚሰጣቸው ቦታ የሚመደቡ ሲሆን፤ አቡነ መርቆሬዎስ ግን ለሥራ ብቁ በማያደርጋቸው የጤናና የእድሜ ክልል ውስጥ ስላሉ በፈለጉበት ቦታ ስመ ማእረጋቸው እንደተጠበቀ በጸሎት ተወስነው እንዲቀመጡ የተፈለገ መሆኑም ተዘግቧል።
የውጪው ሲኖዶስ በሚደረገው እርቅ መሠረት በስምምነት ወደአንድነቱ የማይመጣም ከሆነ ራሱ እንዳልፈለገ ተቆጥሮ በነበረበት ሁኔታ ልዩነቱ እንደሚቀጥልም ይነገራል። ይሁን እንጂ የስድሰተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ግን ከጥያቄ ውስጥ እንደማይገባና ወደፊት በሚመቻችለት ጊዜ ውስጥ ተመርጦ መንበረ ሥልጣኑን ተረክቦ ሥራውን እንደሚጀምር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በዚሁ የፓትርያርክነት የምልመላ መዝገብ ውስጥ በአንደኝነት የሰፈሩት ከዚህ በፊት በሰሜን አሜሪካ ሊቀጳጳስ የነበሩትና አሁን ወደ ኢየሩሳሌም ከተዛወሩ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠሩት አቡነ ማትያስ መሆናቸው ተነግሯል።

ውስጥ አዋቂ መረጃዎቻችን ያንን የሚጠቁሙ ሲሆን ለማንኛውም የሚሆነውን ጊዜው ሲደርስ እናያለን።

Thursday, October 4, 2012

«የዓላማ ሰው ከመሆን የሚከለክል ማንነትና መፍትሄው»

«ከዓላማ መር መጽሐፍ» ለንባብ እንዲመች ተደርጎ የተወሰደ

ማንኛውም ሰው ሕይወት በአንድ ነገር ግፊት ይመራል። ብዙ መዝገበ ቃላት «አንቀሳቀሰ» ለሚለው ግሥ፦ መራ፤ ተቆጣጠረ ወይም አቅጣጫን ወሰነ» የሚል ፍቺ ይሰጡታል። መኪናም ነዳህ፤ ሚስማር በመዶሻ መታህ ወይም ኳስ አንከባለልህ፤ በዚያን ወቅት ያንን ነገር እየመራህ፤ እየተቆጣጠርክና አቅጣጫውን እየወሰንክ ነው። ታዲያ ልክ እንዲሁ ሕይወትህን የሚመራው ኃይል ምንድነው?
   በአሁኑ ጊዜ በአንድ በሆነ ችግር በሆነ ጫና፤ ወይም ማለቅ ያለበትን ሥራ ለመጨረስ በጥድፊያ በመራመድና በመንቀሳቀስ ላይ ትገኝ ይሆናል። በክፉ ትዝታ፤ በአስበርጋጊ ፍርሃት ወይም በቅጡ ባልገባህ አንድ ኅሊናዊ እምነት ትመራ ይሆናል። ሕይወትህን ሊያንቀሳቅሱና ሊመሩ የሚችሉ ብዙ ሁኔታዎች፤ የሕይወት ፋይዳዎችና ስሜቶች አሉ። ቀጥሎ የተዘረዘሩት አምስቱ /5/ በጣም የተለመዱና የታወቁ ናቸው።
1/ ብዙ ሰዎች በበደለኛነት ስሜት ይመራሉ።
እንዲህ ያሉ ሰዎች ዘመናቸውን ሁሉ ጸጸትና ቁጭት ከወለደው ሃፍረታቸው ለመሸሸግ ሲሸሹ ይኖራሉ። ቁጭትና ጸጸት የሚመራቸው ሰዎች የትዝታ ተጠቂዎች ናቸው። ያለፈው ሕይወታቸው መጪውን ህይወታቸውን እንዲቆጣጠረው ይፈቅዱለታል። ብዙውን ጊዜ ሳያውቁት የሕይወት ስኬታቸውን እያበላሹ እራሳቸውን ይቀጣሉ። ቃየል ኃጢአትን በሠራ ጊዜ በደሉ ከእግዚአብሔር ህልውና ለየው፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፦ «በምድር ላይ ኮብላይና ተንከራታች ትሆናለህ» ዘፍ 412። ይህ ቃል በዘመናችን ያለ ዓላማ በሕይወት ጎዳና የሚንከራተቱ ብዙ ሰዎችን ይገልጣል።
  ምንም እንኳን የዛሬ ኑሯችን የትናንት ውጤት ቢሆንም፤ የትናንት ኑሯችን ግን የዛሬ እስረኞች ሊያደርገን አይገባም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ዓላማ ባለፈው ሕይወትህ የሚወሰን አይደለም። እግዚአብሔር ሙሴ የተባለውን ሰው ገዳይ የነበረ ወደ ሕዝብ መሪነት፤ ጌዴዎን የተባለው ፈሪ ደግሞ ወደ ደፋር ጀግና ለውጧቸዋል። በአንተ ቀሪ ሕይወትም እንዲሁ አስደናቂ ነገሮችን ሊያደርግ ይችላል። እግዚአብሔር ለሰዎች አዲስ የሕይወት ጅማሬ በመስጠት የተካነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል። «መተላለፉ የተከደነለት፤ ኃጢአቱም የተሸነፈችለት እንዴት ብሩክ ነው» መዝ 321
2/ ብዙ ሰዎች በቂምና በቁጣ ይመራሉ።
እንዲህ ያሉ ሰዎች ደረሰብን የሚሉትን ጉዳት ከማስወገድ ይልቅ አቅፈውት ይኖራሉ። የጉዳታቸውን ስቃይ በይቅርታ ከማስወገድ ይልቅ በመደጋገም ያብሰለስሉታል። አንዳንዶቹ ደግሞ ዝም በማለት ንዴታቸውን ውስጣቸውን  «አምቀው» ይይዙታል። የቀሩት ደግሞ የታመቀ ቁጣቸውን «በማፈንዳት» በሌሎች ላይ ያምባርቃሉ። እነዚህ ሁሉ አጸፋዎች ጤናማ ያልሆኑ የማይጠቅሙ ናቸው።
  የአንተ ቂም መያዝ፤ ቂም በያዝክበት ሰው ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ይበልጥ የሚጎዳው አንተን ነው። የጎዳህ ወይም ያስቀየመህ ሰው ድርጊቱን ረስቶ የራሱን ኑሮ እየመራ ይሆናል፤ አንተ ግን ያለፈውን ቂም አምቀህ በመያዝ በብስጭት ትብሰለሰላለህ።
 ልብ በል! ከዚህ በፊት የጎዱህ ሰዎች አልጥል ባልከው የገዛ ቂምህ ካልሆነ በቀር እየጎዱህ ሊኖሩ አይችሉም። ያለፈው ነገርህ አልፏል። ማንም ሊቀይረው አይችልም። በመራርነትህ ራስህን ብቻ ነው የምትጎዳው። በቃ ለራስህ ስትል ካለፈው ተማርና ተወው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ «ሞኙን ሰው ብስጭት ይገድለዋል፤ ቂሉንም ቅናት ያጠፋዋል» ኢዮብ 52
3/ ብዙ ሰዎች በፍርሃት ይመራሉ።
   እንዲህ ላሉ ሰዎች የሥጋታቸው ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉት ነገሮች በሕይወታቸው ያሳለፉት አስፈሪ ጉዳት በእውነላይ ያልተመሠረተ ምኞትና ጉጉት፤ ቁጥጥር ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ማደግ፤ ወይም በተፈጥሮ የመጣ ፍርሃት ያለባቸው ይሆኑ ይሆናል። ምክንያቱም ምንም ሆነ ምን በፍርሃት የሚኖሩ ሰዎች ድፍረት ከማጣታቸው የተነሳ ሁኔታዎችን ስለማይጋፈጡ ብዙ እድሎች ያመልጧቸዋል። ፍርሃትን በድፍረት ከማሸነፍ ይልቅ ችግር ካለበት ሁኔታ መሸሽንና ባሉበት ሁኔታ ውስጥ መቆየትን ይመርጣሉ።
ፍርሃት እግዚአብሔር ያቀደልህን እንዳትሆን የሚያደርግህና እራስህን ያስገባህበት እስር ቤት ነው። በፍቅርና በእምነት መሣሪያነት ልትጋፈጠው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ «በፍቅር ፍርሃት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሃት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።
4/ ብዙ ሰዎች ለመበልጸግ ባላቸው ምኞት ይመራሉ።
እንዲህ ያሉት ሰዎች የሕይወታቸው ዋና ግብ ሀብት ማግኘት ነው። እንዲህ ያለው ሁልጊዜ ሀብት የመፈለግ ግፊት የሚመነጨው ብዙ ሀብት ሲኖረኝ ይበልጥ ደስተኛ፤ ይበልጥ ታዋቂና ዋስትና ያለኝ እሆናለሁ ከሚል የተሳሳተ አመለካከት ነው። እነዚህ ሦስቱም አስተሳሰቦች ስህተት ናቸው። ሀብት ሊያስገኝ የሚችለው ጊዜያዊ ደስታን ነው። ምክንያቱም ቁሳዊ ነገሮች ስለማይለወጡ ያሰለቹናል። በመሆኑም አዳዲስ ትልልቅና የተሻሉ ነገሮችን እንደገና እንፈልጋለን።

Sunday, September 30, 2012

ክርስቲያን በፖለቲካ ውስጥ በንቃት መሳተፍ ይኖርበታልን?

                                             ከተስፋዬ ሮበሌ
                                                              ወርኀ ጥር 2004 .
                                                                                                         እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቈጣጠር
                                                                                                         ግራንድ ራፒድስ ፣ ሚሽገን

በአንድ መስቀለኛ መንገድ ላይ በየቀኑ አሠቃቂ አደጋ ይከሠታል፤ ከአደጋው የተነሣም በርካታ ሰዎች ይሞታሉ፤ ከፍተኛ ንብረትም ይወድማል፡፡ ሁኔታው ያሳሰባት፣ በዚህ አካባቢ የምትገኝ አንዲት ቤተ ክርስቲያን፣ የአደጋው ሰለባ የሆኑትን ሰዎች የሚረዱ ሐኪሞችንና ነርሶችን በማሠማራት የአካባቢውን ማኅበረሰብ በንቃት ማገልገሉን ሥራዬ ብላ ተያያዘችው፡፡ የሕዝብና የመኪና ቊጥር ዕለት በዕለት እየጨመረ በመሄዱ ምክንያት ግን፣ ችግሩ በዛው መጠን ተባብሶ ቀጠለ፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን እርዳታዋን በመጠንና በዐይነት ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ መለስተኛ ሆስፒታል አደጋው በሚከሠትበት አካባቢ አቋቋመች፡፡ ይህ ሠናይ ምግባር የሰለባዎቹን ጤንነትና ሕይወት ከመታደግ አንጻር ብዙ ጠቀሜታ ቢኖረውም፣ ችግሩን ግን ከምንጩ ማድረቅ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም የችግሩ ምንጭ የተሳሳተ የመንገድ ዲዛይን ነውና፡፡ በመስኩ የሠለጠኑ መሐንዲሶች መንገዱ በአዲስ መልክ ዲዛይን ቢደረግ ችግሩ ሊፈታ እንደሚችል የትራፊክ ፖሊስ ጽሕፈት ቤቱን በቃልም ሆነ በጽሑፍ ቢያሳስቡም፣ ባልታወቀ ምክንያት ጽሕፈት ቤቱ ጆሮ ዳባ ልበስ አለ፡፡ በየዘመናቱ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ሰጠኝ የምትለውን ዐደራ ከዳር ለማድረስ፣ በሚያስፈልገው ሁሉ በመውተርተር ላይ ትገኛለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ነዳያንን በማብላት፣ የታመሙትን በማስታመም፣ ለመበለቶች ዳኛ በመሆን ጥልቅ ስም አላት፡፡ በርግጥም ቤተ ክርስቲያን የምስካየ ኅዙናን መንበር ናት፡፡ ወደ ፊትም ይህንኑ ግብረ ሠናይ ምግባሯን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የምትችለው የተሳሳተ ፖሊሲ ያስከተለውን ፍሬ በመልቀም ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥት ትክክለኛ ፖሊሲ እንዲነድፍ ስታስተምር፣ መንግሥት ሲሳሳትም ስሕተቱን ስሕተት ነው ማለት ድፍረትና ክህሎት ሲኖራት ብቻ ነው፡፡
ፖለቲካ፣ የሕዝብ አስተዳደር መዘውር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የመዘውሩ ነገር ምን ተዳዬ የምትል ከሆነ ግን፣ በመዘውሩ እክል ምክንያት በሚከሠቱ ችግሮች ላይ ብቻ መጠመዷ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ውስጥ ሠርጾ በመዝለቁ ምክንያት፣ ወደ ፖለቲካው ዓለም የሚገቡ ወይም የፖለቲካ ሳይንስ የሚያጠኑ የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ ከመንፈሳዊነት እንደ ጐደሉ ምናልባትም ክርስቶስን ከመከተል እንዳፈገፈጉ ይታሰባል፡፡ ክርስቲያን የዓለም ብርሃንነው፣ የዓለም ጨውነው የሚለው የቃለ እግዚአብሔር ትምህርት፣ በፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ጨለማና አልጫ ነው ያለው ማነው? እንዲያውም ክርስቲያኖች በንቃት ሊሳተፉበት የሚገባ፣ ጨውነታቸውንና ብርሃንነታቸውን ሊገልጡበት የሚገባው የሕይወት ክፍል ፖለቲካ ነው፡፡ እንደ ንጉሥ ዳዊት፣ እንደ ንጉሥ ሰሎሞን ያሉ የእምነት አበው ፖለቲከኞች ነበሩ፡፡ እንደ ነቢዩ ናታን፣ ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ነቢዩ ዳንኤል፣ ነቢዩ አሞጽ ወዘተ ያሉ ነቢያት ደግሞ መንግሥትን በማማከር አገልግለው እንዳለፉ ገድላቸው የናገራል፡፡ መንግሥት ሲስት ይገሥጹና ከስሕተቱ እንዲመለስ መንገድ የመላክቱ እንደ ነበር ቅዱስ ቃሉ ያስተምረናል፡፡ እንዲያውም ባልንጀራህን/ጐረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ የሚለው የክርስቶስ ቃል ከየትኛውም የትምህርት ዘርፍ ይልቅ ፖለቲካን የሚያመላክት ነው (ማቴዎስ 22÷39)፡፡ ለተጠቃው ከመጮኽ፣ የታረዘውን ከማልበስ፣ ፍትሕ ያጣውን ለፍትሑ ከመሟገት በላይ ምን ጐረቤትን መውደድ አለ? እግዚአብሔር አምላክ ለንጉሥ ሰሎሞን የሰጠው ስጦታ የፖለቲካ ስጦታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፖለቲካ የጸጋ ስጦታ መሆኑን የሚያጸና ነው፡፡
ወገኖቼ ክርስትና የማይዳስሰው የሕይወት ክፍል የለም፡፡ ክርስቲያኖች በፖለቲካው ውስጥ በመግባት ብርሃንና ጨው መሆን ካልቻሉ፣ ክርስቲያን ያልሆኑና እኵይ ሥነ ምግባር ያለቸው ሰዎች የፖለቲካውን መድረክ መቈጣጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ እየሆነም ያለ ይመስላል፡፡ ወገኖቼ፣ ኀጥኣን ከፍ ከፍ ሲሉ ሕዝብ ይጨነቃልየሚለው የጠቢቡ ሰሎሞን አነጋገር ፖለቲካን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ወዲህም ወዲያም ብታገላብጡት ሐቁ ይኸው ነው፡፡ ክርስትናና ፖለቲካ ዐይንና ናጫ ናቸው ወዘተረፈ የሚለው ወልጋዳ አስተሳሰብ የብዙዎችን ጐዳና አሰናክሏል፡፡ ከዚህም የተነሣ ብዙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ ስለ ፖለቲካ ያለን ዕውቀት በየጋዜጣው ላይ ከሚጻፉ መጣጥፎች አንዲሁም በየዜና አውታሮች ከሚተላለፉ ፕሮግራሞች የዘለለ አይደለም፡፡ ይህ ዐይነቱ ዕውቀት ደግሞ፣ ለፕሮፖጋንዳ ውዥንብር በቀላሉ ይዳረጋል፡፡ ቃላትን ቀምሮና እውነትን አስታኮ የመጣ ብልጣብልጥ ፖለቲካኛ ሁሉ ወዳሻው ቦታ ይዞት ይሄዳል፡፡ ወደድንም ጠላንም የአገሬ ጕዳይ ግድ ይለኛልየምንል ሰዎች ሁሉ፣ ቢያንስ መሠረታውያን የሚባሉትን የፖለቲካ መርሖች በቅጡ ልናውቃቸው ግድ ነው፡፡ ለምሳሌ ፖለቲካ በአገር ግንባታ ውስጥ ያለው ቦታ እስከምን ድረስ ነው? ሰብአዊ መብት ማለት ምን ማለት ነው? ኢሕአዴግ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲብሎ የሚጠራው የፖለቲካ አካሄድ፣ ከምዕራባውያኑ ለዘብተኛ (ሊብራል) ዴሞክራሲ በምን ይለያል?
ይህ የፖለቲካ ፍልስፍና በአገሪቱ ፖለቲካና ምጣኔ ሀብት የሚያስከትለው አሉታዊ መዘዝም ሆነ አዎንታዊ እንድምታ እንዴት ይተነተናል? ክርስቲያኖች በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው ወይስ የዳር ታዛቢ መሆናቸው ብቻ ጥሩ ዜጋ ያሰኛቸዋል? ሕዝባዊና ማኅበራዊ ተቋማት ማለትም የመገናኛ ብዙኃን፣ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤቶችና የምርጫ ቦርድ ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ፍጹም ነጻ መሆን አለባቸውየሚባለው ለምንድን ነው? ነጻናቸው የሚባል ከሆነስ ደግሞ ነጻነታቸው በምን መስፈርት ይለካል? ፖለቲካ ለምጣኔ ሀብት ሕግጋት ይገዛል ወይስ ምጣኔ ሀብት ለፖለቲካ ሎሌ ያድራል? ወይስ ሁለቱም ለየቅል ናቸው? አንድ አገር ፖለቲካ ሰብአዊ መብትን እንዳሻው እየጨፈለቀ የምጣኔ ሀብት በረከት ሊያመጣ ይችላል? የማይቻል ከሆነ የቻይና ጕዳይ እንዴት ይታያል? የመናገር መብት፣ የመጻፍ መብት፣ የመደራጀት መብት ወዘተ የሚባሉት ጕዳዮች፣ በሰብአውያን ሕይወትና ዕድገት ውስጥ ያለቸው ስፍራ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፖለቲካ የሚያስተምረው ትምህርት ምንድን ነው