Tuesday, October 9, 2012

መንግሥት ፓትርያርክ ማን ሊሆን እንደሚችል በውስጥ መሰየሙን ይነገራል።

ከታማኝ የውስጥ ምንጮች የደረሰን ዜና እንደሚያስረዳው ስድስተኛው ፓትርያርክ በመንግሥት ደረጃ ምልመላው ያለቀ ሲሆን ይህ መረጃም በማኅበረ ቅዱሳንና በቀንደኛ ጳጳሳት ዘንድም  የውስጥ ግንዛቤ እንዲያዝ ተደርጎበታል ተብሏል።
የእርቅ ሂደቱ ቢያልቅና የውጭዎቹ ጳጳሳት ከሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ጋር በሚደረገው ስምምነት ወደአንድነት ቢጠቃለሉ ሲኖዶሱ በሚሰጣቸው ቦታ የሚመደቡ ሲሆን፤ አቡነ መርቆሬዎስ ግን ለሥራ ብቁ በማያደርጋቸው የጤናና የእድሜ ክልል ውስጥ ስላሉ በፈለጉበት ቦታ ስመ ማእረጋቸው እንደተጠበቀ በጸሎት ተወስነው እንዲቀመጡ የተፈለገ መሆኑም ተዘግቧል።
የውጪው ሲኖዶስ በሚደረገው እርቅ መሠረት በስምምነት ወደአንድነቱ የማይመጣም ከሆነ ራሱ እንዳልፈለገ ተቆጥሮ በነበረበት ሁኔታ ልዩነቱ እንደሚቀጥልም ይነገራል። ይሁን እንጂ የስድሰተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ግን ከጥያቄ ውስጥ እንደማይገባና ወደፊት በሚመቻችለት ጊዜ ውስጥ ተመርጦ መንበረ ሥልጣኑን ተረክቦ ሥራውን እንደሚጀምር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በዚሁ የፓትርያርክነት የምልመላ መዝገብ ውስጥ በአንደኝነት የሰፈሩት ከዚህ በፊት በሰሜን አሜሪካ ሊቀጳጳስ የነበሩትና አሁን ወደ ኢየሩሳሌም ከተዛወሩ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠሩት አቡነ ማትያስ መሆናቸው ተነግሯል።

ውስጥ አዋቂ መረጃዎቻችን ያንን የሚጠቁሙ ሲሆን ለማንኛውም የሚሆነውን ጊዜው ሲደርስ እናያለን።