• በጣም የሚወዱትን መዝሙር ይንገሩኝ?
• አቶ ኃ/ማርያም፡- ‹‹እኔም እንደ ዳዊት ጨርቄን ልጣልልህ›› የሚለውን
• ጉባዔ ገብተው ሲያመልኩ ግን እንደ ባለሥልጣን የፕሮቶኮል ነገር አለ፡፡ የጥበቃ ጉዳይ አለ፡፡
ሌላም ሌላም፡፡ ይሄን ሁሉ ረስተው በነጻነት ለማምለክ አይቸገሩም?
አቶ ኃ/ማርያም፡ ምንም አልቸገርም፡፡ ጉባዔ ውስጥ
ካለሁ እኔ ስለ ራሴ ጨርሶ አላስብም፡፡ እነ ንጉሥ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ጨርቃቸውን ጥለው ያመልኩ ነበር፡፡ እኔስ የማመልከው
እግዚአብሔር ፊት እንደሆንኩ እንጂ የማስበው ሌላ ነገር አላስብም ማልቀስ ካለብኝ አለቅሳለሁ፣ መንበርከክ ካለብኝ እንበረከካለሁ፡፡
ጌታ ሁን ያለኝን ሁሉ ለመሆን ዝግጁ ሆኜ ነው የማመልከው፡፡
ልጆችዎ በቤተክርስቲያን ውስጥ የመክሊት (የአገልግሎት)
ሥራ ውስጥ ሲሳተፉ ይታያል፡፡ የእከሌ ልጅ ነኝ እኮ ብለው ሳይኩራሩ ወንድሞችና እህቶች የጠጡባቸውን የሻይ ብርጭቆዎች እየዞሩ ሲለቅሙ
እንዳየ ወንድሜ ፍጹም ነግሮኛል፡፡ በቤት ውስጥ ምን ብለው ቢያስተምሯቸው ነው?
አቶ ኃ/ማርያም፡- እኔም ባለቤቴም ቤት ውስጥ
ሁሉም የምንነግራቸው ነገር እኛ ጋር ምንም እንደሌለ እኛ ምንም እንዳልሆንን ሀብታችን ኢየሱስ እንደሆነ የማወርሳቸውም አምላኬን
እግዚአብሔርን ብቻ እንደሆነ ነው የምንነግራቸው፡፡ አንተ የራስህ መኪና እንኳን የለህም፡፡ ቤት የለህም፣ አሁን እናንተ አንድ ነገር
ብትሆኑ እኛ ምን አለን? ሲሉኝ እንኳን የምመልስላቸው መልስ የለንም ግን መኪና አጥተን እናውቃለን ወይ? ቤትስ አጥተን ማደሪያ
አጥተን እናውቃለን ወይ? መኪና ብገዛም ቤት ቢኖረንም የእኛ አይደለም፡፡ ሁሉንም ትተነው ነው የምናልፈው፡፡ ሀብታችን ጌታ ብቻ
ነው እላቸዋለሁ፡፡ በአገልግሎት እንዲበረቱም እንመክራቸዋለን፡፡
ለአገልግሎትና የክርስቶስን አካል ለማነጽ ልዩ
ልዩ ጸጋ ይሰጣል፡፡ ለእርሶ የተሰጦት የጸጋ ዓይነት ምንድነው?
አቶ ኃ/ማርያም፡ እንግዲህ ጥሪ የተለያየ ነው፡፡
ሁላችንም መሰዊያ ላይ ቆመን አንሰብክም፡፡ እኔን ደግሞ የሰጠኝ የሚመስለኝ ጸጋ ሕዝብን እና አገርን በመልካም አስተዳደር ማገልገል
ነው፡፡ ስለዚህ ለእኔ ሥራዬ ስራ ብቻ ሳይሆን አገልግሎትም ጭምር ነው ብዬ የተቀበልኩት፡፡
አቶ ኃ/ማርያም ጠዋት ከመኝታዎ ስንት ሰዓት ይነሳሉ?
አቶ ኃ/ማርያም፡/ሳቅ ብለው/ መመለስ አለብኝ
እኔ ሁልጊዜ ከእንቅልፌ ምነሳው ከለሊቱ 11 ሰዓት ነው፡፡ ጉዞ፣ እንደዚህ አይነቱ ነገር ካልረበሸኝ በስተቀር 11 ሰዓት እነሳለሁ፡፡
ከ11 ሰዓት እስከ 12 ድረስ የፀሎት ጊዜዬ ነው፡፡ ከ12 እስከ 12፡30 ትንሽ ‹‹ኤክሰርሳይስ›› (ስፖርት እሰራለሁ፡፡ በቀሪው
ጊዜ የዕለቱን የቢሮ ስራ አዘጋጅቼ 1፡30 አካባቢ ወደ ቢሮዬ እሄዳለሁ፡፡
አዘውትረው የሚጸልዩባቸው ጉዳዮች አሉ ካሉ ቢያስታውቁን?
አቶ ኃ/ማርያም፡እኔ ዘወትር በአራት ርዕሰ ጉዳዮች
ላይ እጸልያለሁ፡፡ አንደኛ ሰላምና በረከት ለዚህች አገር እንዲበዛ እጸልያሁ፡፡ ለመሪዎቿ፣ ለመንግሥት፣ ባለሥልጣናት ጥበብና ማስተዋልን
እንዲሰጥ እጸልያሁ፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች ያለ አድልዎ እና ልዩነት በእኩልነት እና በመቻቻል እንዲኖሩ እመኛለሁ፡፡ ሁለተኛ የእግዚአብሔር
ቃል ‹‹ሰው ሁሉ ወደ መዳን እንዲመጣ›› ይላል፡፡ ስለዚህ ሰው ሁሉ እንዲድን እጸልያለሁ፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና፡፡
ሶስተኛ እናቴ አልዳነችምና ለወላጅ እናቴ በተለይ እጸልያለሁ፡፡ አራተኛ ለልጆቼና ለቤተሰቤ ዘወትር እጸልያለሁ፡፡
እንደው በግልጽ ለመጠየቅ ያህል ወደ ሥልጣን ሲመጡ
አብረው የሚመጡና ለመሥራትም የሚመቹ የኃጢአት ፈተናዎች ይኖራሉ፡፡ እርስዎ እስካሁን ድረስ የገጠምዎትን ፈተና በምን መንገድ አልፈውታል?
አቶ ኃ/ማርያም፡ የእውነት ለመናገር እስካሁን
እግዚአብሔር ረድቶኛል፡፡ በፈተናዎቹ አልፌአለሁ እላለሁ፡፡ ይሄን ከልቤ ነው የምልህ፡፡ ንጉሥ ዳዊት የተከበረ በእግዚአብሔር ዘንድም
የተወደደ በብዙ ነገር በጣም የተመሰገነ ንጉሥ ነበር፡፡ እስራኤልን የሚመስል ትልቅ ሕዝብ መግዛት የቻለ ዳዊት ግን ራሱን መግዛት
አልቻለም ነበር፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ከተማን ከመግዛት ይልቅ ራስን መግዛት ይበልጣል ያለው፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ የሚመክረው
ራስን ቤተሰብን መግዛት እንድንችል ነው፡፡ አለ አይደል ከተማን በመግዛትህ ሁሉን እገዛለሁ አትበል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ውስጣዊ ሰብዓዊ
ውድቀት ሊኖርብህ እንደሚችል አስበህ ጥንቃቄ አድርግ፡፡ ጥንቃቄ ይጠብቅሃል አይደል የሚለው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዝሙት ሊያታልህ ይችላል፡፡
ዝሙት እንዳይጥልህ ጥንቃቄ አድርግ፡፡ የሥጋ ምኞት፣ ገንዘብ ፍቅርና የዓይን አምሮት የሚባሉት አይደሉም ሰውን የሚጥሉት፡፡ ስለዚህ
ከተማን የገዛ ሰው፣ በተለይ እነዚህ ሶስት ነገሮች ላይ መጠንቀቅ አለበት፡፡ እኛ ኢህአዴጎች ስኳር ነው የምንለው፡፡ ስኳሩ እንዳያታልልህ
ጥንቃቄ መደረግ አለበት ነው ሀሳቡ፡፡ ፓርቲዬን በጣም የምወድበት ትልቁ ምክንያት ሙስናን፣ ያለ አግባብ፣ ጥቅም ለማግኘት የሚደረግን
ጥረት ፓርቲዬ የኪራይ ሰብሳቢ አመለካከት የሚላቸው በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወገዙ ናቸው፡፡ እነዚህ መሰረታዊ መርሆች ከመጽሐፍ
ቅዱስ አስተምህሮት ጋር ይጣጣሙልኛል፡፡ አይቃረኑም፡፡ ስለዚህ ሙስና፣ አላስፈላጊ ጥቅማጥቅሞች፣ ውሸት ውስጥ ሳትገባ ሕዝብን ማገልገል
አለብህ ስለሚል የኔ ፓርቲ እነዚህን መርሆዎች ስለሚያራምድ ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስለሆነ በጣም ደስ ብሎኝ ነው የምሰራው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንተ ራስህ ከእግዚአብሔር ጋር ንስሐ በመግባት የምትፈታው ነገር ከተገኘ ተገምግመህ እንድትስተካከል ይሆናል
ወይም ደግሞ ልትባረርም ትችላለህ፡፡ ስለዚህ ፓርቲዬ በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም በጣም ጠንካራ አቋም አለው፡፡ እና በዚህ ዓይነት ነው፡፡
የሚጸጸቱበትን ውሳኔ አስተላልፈው ያውቃሉ?