«እናንተ ብትገቡበት አያቅታችሁም፤በቤተ ክህነት አጽናኝም አሸባሪም መኖሩን የተናገሩት» አባ ኤልሳዕ የደቡብ ጎንደር ሊቀ ጳጳስ
«ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስን በዙሪያው ኾኖ የሚጠብቅ፣ የቅዱስ
ሲኖዶሱን ውሳኔዎች በማስፈጸም ረገድም ቋሚ ተጠሪ ነው»
አባ ማትያስ የካናዳ ሊቀ ጳጳስ
«የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዳይናጋ “በወርድም በቁመትም
መሥራቱን” አጠናክሮ እንዲቀጥል» አባ ገብርኤል የሃዋሳ ሊቀ ጳጳስ
«ማኅበሩን መደገፍ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል እንደኾነ» ቄስ ኃ/ሥላሴ ዓለማየሁ
ከ40 ሚሊዮን ተከታዮች በላይ ያሏትን ቤተክርስቲያን ከመንበረ ፓትርያርክ
እስከ የገጠሪቱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ድረስ የመምራትና የማስተዳደር ሥልጣን የተረከቡ ሊቃነ ጳጳሳት ከቤተክርስቲያኒቱ የምእመናን
ማኅበር አንዱ አባል ለሆነው ለማኅበረ ቅዱሳን ይህን ያህል «ተቀመጥ በወንበሬ፤ ተናገር በከንፈሬ» ዲስኩር ለማሰማት መድረሳቸው
በእርግጥም የቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች እግዚአብሔርን ተስፋ ከማድረግ ወርደው፤ መንፈስ ቅዱስን አጋዥና መሪ ከማድረግ ወጥተው፤ ማኅበረ
ቅዱሳን የቤተክርስቲያኒቱ መንፈስ ቅዱስ ስለሆንክ አንተ ምራን ከሚሉበት ደረጃ መድረሳቸው አሳዛኝም ፤አሳፋሪም ነው።
አባ ኤልሳዕ የደቡብ ጎንደር ሊ ቀጳጳስ በሁለቱ ሲኖዶስ መካከል ያለውን ቅራኔ
ለመፍታት ማኅበረ ቅዱሳን ቢገባበት ምንም የሚያቅተው እንደሌለ መናገራቸው ሲሰማ በእርግጥ እኒህ አባት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይመራሉ?
ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። የ21 ዓመቱ ክፍፍል ሊያበቃ ያልቻለው ለካ፤ በሥጋዊ መንፈስ እየተመሩና የመንፈስ ቅዱስን ኃይል
ታምነው እንዳልነበረ ከማሳየቱም በላይ ዛሬም ከዚያው ስህተታቸው ሳይላቀቁ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማስቀደም መድፈራቸውን ስንመለከት ቤተክርስቲያኒቱ
የምትመራው በእነማን እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ይታየናል። «እናንተ ብትገቡበት
አያቅታችሁም» ማለታቸው የሚያሳየው እስከዛሬ የዘገውም ማኅበረ ቅዱሳን በእርቁ ውስጥ የማሸማገል ሚናውን ስላልተወጣ ነው ማለታቸው
ነው። ሲኖዶሱ ደካማና ለእርቁ መፈጸም አቅም የሌለው በመሆኑ እስካሁን የመዘግየቱ ምክንያት እንዲህ ከተገለጸላቸው ታዲያ ለምን ማኅበረ
ቅዱሳንን የሲኖዶሱ የእርቁ ቋሚ ተጠሪ አድርገው በመሾም ቶሎ እንዲፋጠን ያላደረጉ? በዚያውም ደግሞ በሲኖዶስ ጉባዔ ላይ እንደፓርላማ
ደንብ በአጋር ድርጅትነት ወንበር የማይሰጡት?
ማኅበረ ቅዱሳን የራሱ የሆነ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ያለው ድርጅት ነው። በዚህ ስውርና ግልጽ የዓላማዎቹ
ጉዞ ላይ የሚቀበሉትን እስከነጉድፋቸው ተሸክሞ ለመጓዝ የማይጠየፍ፤ የማይቀበሉትን ደግሞ ምንም እንኳን ንጹሐን ቢሆኑ አራግፎ ለመጣል
ጥቂት የማያቅማማ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን እነ አቡነ ኤልሳዕን የመሳሰሉ ታማኞች «አንተ ስላልገባህ እኛ አቅቶናል» የሚል ድምጸት ያለውን ቃል ቢናገሩለት
ማን መሆናቸውን ከሚያሳዩ በስተቀር ስለማኅበረ ቅዱሳን ሁሉን አዋቂነትና የመፍትሄ ቁልፍነት መናገራቸው ማንንም አያሳምንም።
ሌላው አባትም ገና ከወደ ካናዳ ብቅ ከማለታቸው «እስመ አልቦ ነገር ዘይሰዓኖ
ለማኅበረ ቅዱሳን» የሚል ትርጉም ያለውን ቃል ሲናገሩ መስማት ለጆሮ ይቀፋል። እሳቸው የተናገሩት ነው ተብሎ በደጀ ሰላም የሠፈረውን
ይህን ቃል መዝኑት።
«ማኅበረ ቅዱሳን፤ ቅዱስ ሲኖዶስን በዙሪያው ኾኖ የሚጠብቅ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔዎች በማስፈጸም ረገድም ቋሚ ተጠሪ ነው»
ማኅበረ ቅዱሳን እውነት የሚታዘዝ ሆኖ ከሆነ ይታዘዛል፤ ይላካል፤ የሲኖዶሱን
ትእዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ ሲጠሩት አቤት፤ ሲልኩት ወዴት ይላል ብሎ ታዛዥነቱን መግለጽ አንድ ነገር ነው። ነገር ግን ማኅበረ ቅዱሳን፤
ቅዱስ ሲኖዶስን በዙሪያው ኾኖ ይጠብቀዋል ማለት ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኾኗል ማለት ነው። ቅዱስ ሲኖዶስ ዙሪያውን ሆኖ የሚጠብቀው መንፈስ ቅዱስ ነው ወይስ ማኅበረ
ቅዱሳን? የሲኖዶሱ አባል አባ ማትያስ ግን ሲኖዶሱ ዙሪያውን ሆኖ የሚጠብቀው ማኅበረ ቅዱሳን ነው ሲሉ በግልጽ መናገራቸው ማኅበረ
ቅዱሳን ሁሉን ማድረግ እንደሚችል የማወጃቸው ነገር አስገራሚ ነው። ሲኖዶሱ በምን ዓይነት ሰዎች እንደተሞላ ከማሳየት አልፎ ፓትርያርክነቱን
ለማግኘት ስለማኅበረ ቅዱሳን ታላቅነት መማል ፤ መገዘት የግድ ሆኗል ማለት ይቻላል።
አባ ማትያስ የሲኖዶሱ ጠባቂ ማኅበረ ቅዱሳንን ከማድረጋቸውም በላይ የሲኖዶሱን
ውሳኔዎች ለማስፈጸም የሲኖዶስ ቋሚ ተጠሪ መሆኑንም አያይዘው አውጀውልናል። አሁን እንግዲህ ማኅበረ ቅዱሳን ከማኅበር ጣሪያ በላይ
ወጥቷል። ከእንግዲህ ማኅበረ ቅዱሳን ድስት ያላጠለቀ ሲኖዶስ ነው ማለት ነው። በንግግር መሳት ካልቀረ እንደእነ አቡነ ማትያስ ጭልጥ
ብሎ መንጎድ እግዚአብሔር ሲኖዶስን ይጠብቃል፤ ሥራውን ሁሉ ያከናውናል እስኪባል ድረስ የሲኖዶስ ጣዖት ሆኖ ማኅበረ ቅዱሳን ይቀጥላል
ማለት ነው።
እነሱው በሰጡህ ፈቃድ መሠረት የሲኖዶስ ጠባቂ ማኅበረ ቅዱሳን ሆይ እነዚህን
ጳጳሳት ጠብቅ፤ ከፍ ከፍም አድርጋቸው!!! እንላለን።
ሌላው ሊቀ ጳጳስ ደግሞ አባ ገብርኤል ናቸው። በመሠረቱ አባ ገብርኤል ከሲኖዶሱ
ይልቅ በማኅበረ ቅዱሳን እንደሚታመኑና እንደሚመኩ ይታወቃል። አባ ገብርኤል ወደ ምድረ አሜሪካ ኰብልለው በመሄድ ኢህአዴግ ይውደም፤
አባ ጳውሎስ ይውረዱ በማለት የፖለቲካ ሰልፍ ሲመሩ እንደነበሩ መረጃዎቻችን ያሳያሉ። ከዚያም በድርድር ይሁን በእርቅ ለጊዜው በማይታወቀው
ምክንያት ግሪን ካርዳቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ በሁለት ዜግነት መግባታቸውን ደግሞ አየን። በእርግጥ ሰው ከስህተቱ ቢታረም አያስገርምም።
አባ ገብርኤልን ስንመለከት ከስህተት የሚማሩ አይመስሉም። ዛሬ ደግሞ የዳቦ ስሙን ላወጡለት ማኅበር እንዲህ ሲሉ ይደመጣሉ።
«የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዳይናጋ “በወርድም በቁመትም
መሥራቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል» ማኅበረ ቅዱሳን ያስፈልጋል ይሉናል።ኧረ ለመሆኑ የቤተክርስቲያኒቱ አንድነት እንዳይናጋ፤ በወርዷም፤ በቁመቷም ለመስራት አልነበረም
እንዴ አባ ገብርኤል ጵጵስና የተሾሙት? በተሰጣቸው ጵጵስና መስራት
ካቃታቸው ለሰጠቻቸው ቤተክርስቲያን መመለስ እንጂ ቤተክርስቲያንን እንዲመራ ውክልና ለሌለው ማኅበር ከወርድ እስከቁመቷ እንዲያዝባት
እነሱ ደግሞ በተራቸው አሳልፈው እንዴት ይሰጣሉ?
ሲኖዶሱ ከመንበረ ፓትርያርክ አንስቶ እስከ ገጠሪቱ የሳር ክዳን አጥቢያ ድረስ
መዋቅሩን የዘረጋው በወርዷም፤ በቁመቷም ለመሥራት አይደለም እንዴ?
አባ ገብርኤል ግን ያቃተቸው ይመስላል። ይልቁንም እኛ ስራውን ሁሉ ለማኅበረ ቅዱሳን እናስረክብና በወርዷም፤ በቁመቷም
እሱው ይዘዝባት እያሉ አዋጅ ማስነገር ይዘዋል። አባ ገብርኤልስ የሌላ ሀገር ዜግነት ስላላቸው ነገር ዓለሙ መበላሸቱን ሲያዩ እብስ
ብለው ወደ ጥንት የሰልፍ ሀገራቸው አሜሪካ ሊሄዱ ይችላሉ! ማኅበረ ቅዱሳን እንኳን በወርድ በቁመቷ፤ አንዲት ጋት በቤተክርስቲያን
ላይ የማዘዝ መብት የለውም የሚሉ የቤተክርስቲያን ልጆችንስ ጅቡ ማኅበር ይዋጣቸው ማለት ነው?
እስከሚገባን ድረስ የቤተክርስቲያኒቱ ራስ እግዚአብሔር ነው። አንዳንድ ጳጳሳት
ጠባቂያችን ማኅበረ ቅዱሳን ቢሉም እስከሚገባን ድረስ የሲኖዶሱ ጠባቂ መንፈስ ቅዱስ ነው። እግዚአብሔርን ራስ አድርጎ ሲኖዶሱ በመንፈስ
ቅዱስ ኃይልና መገለጥ ቤተክርስቲያንን በወርድና በቁመቷ ይመራታል እንላለን። ከእነ አባ ገብርኤል የተገኘው አዲስ ግኝት ግን በወርድና
በቁመቷ ለመሥራት ሥልጣኑ የማኅበረ ቅዱሳን ሆኗል። አባ ገብርኤል ፓትርያርክነቷ ተወርውራ እኔ ጋር ትደርሳለች ብለው አስበው ይሆን?
አንድ ጊዜ ሥልጣናቸው ተገፎ አቶ ኢያሱ የተባሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግመው ኮብልለው
የፖለቲካ ሰልፍ ሲመሩ የነበረ፤ በኋላም ተመልሰው የወደዷቸውን ጸረ ኢህአዴጎችን ከአሜሪካ ከድተው ፤ የጠሉትን ኢህአዴግን ወደው፤
የጽዋውን ማኅበር ማኅበረ ቅዱሳንን አነግሳለሁ እያሉ በአደባባይ በማወጅ የተጠመዱና በአንድ ቦታ በአንድ ቃል የማይረጉ አባ፤ እንኳን ፓትርያርክ ሊመረጡ ለእጩነትም ሊቀርቡ ተገቢ አይደለም። መጽሐፍ «በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም
ምስክር ሊኖረው ይገባዋል» ይላልና። አባ ገብርኤል ለምንም ሹመት የሚበቁ አይደሉም እንላለን። « ሆያ ሆዬ ጉዴ ፤ብሯን ብሯን ይላል
ሆዴ» እንደሚሉት የሆያ ሆዬ ጫወታ የእሳቸውም ሆድ ቁንጮዋን መጨበጥ ስለሆነ ሆዳቸውን እየቆረጠ እንዳይቸገሩ ቁርጣቸውን ማሳወቅ
ተገቢ ነው።