Sunday, September 2, 2012

««ኦ አዳም መሬት አንተ ወትገብእ ውስተ መሬት»


አዳም ሆይ አንተ መሬት ነህና ወደ መሬት ትመለሳለህ»
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተወለዱ በ57 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው እነሆ ለሳምንት ከዘለቀው የሀዘን ቀናት በኋላ ዛሬ ነሐሴ 27/ 2004 ዓ/ም ስርዓተ ቀብራቸው በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።  በጸሎተ ፍትሃቱና ስርዓተ ቀብሩ ላይ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች፤ ሚኒስትሮች፤ ዲፕሎማቶች፤ የመንግሥታት ተወካዮች፤ አምባሳደሮች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማና ከየክልላቱ የመጡ የሀዘኑ ተካፋዮች በተገኙበት ሌሊት ከጀመረው ጸሎተ ፍትሃት አንስቶ እስከ ቀኑ 10 ሰዓት ግብዓተ መሬት እስከተፈጸመበት ጊዜ ድረስ ሳያቋርጥ ይጥል የነበረው ከፍተኛ ዝናብ በላያቸው እየወረደ ሙሉ ቀን ውለው እነሆ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አቶ መለስ ዜናዊን ዛሬ ሸኝተዋል።
ደጀ ብርሃን ብሎግ ላዘኑት መጽናናትን፤ ለቤተሰቦቻቸው መረጋጋትን፤ ለሀገሪቱ ደግሞ እግዚአብሔርን ሕዝቡንና ሀገሪቱን የሚወድ መሪ እንዲሰጥልን እንመኛለን።
የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመጨረሻው የሽኝት ድባብ ምን እንደሚመስል የፎቶ ምስሎችን እንድትመለከቱ እነሆ ግብዣችን ነው።

የቀብር ሽኝት ፎቶዎችን ለመመልከት እዚህ ይጫኑ 

Saturday, September 1, 2012

የደጀ ብርሃንን ኢሜል በመሰርሰር ከሰርቨር ለማውረድና ብሎክ ለማድረግ የተሞከረው ከየት ነው?

ከዚህ ቀደም ከብሎገር ጀማሪዎች ተርታ የምትመደብ ነገር ግን ብዙ መረጃዎችን ፈልፍላ በማውጣት የመልካም ነገር ሁሉ ጠላት በሆነ ቡድን ባለመወደዷ በኢትዮጵያ ውስጥ ብሎክ የተደረገችው «ዓውደ ምሕረት» ብሎግ አንድ ሰሞን ከኢትዮጵያ አድማስ ላይ ተሰውራ እንደነበር ይታወሳል። ከድርጊቶቹ ጀርባ ማን እንዳለ ለጊዜው የተገለጸ ነገር ባይኖርም ተመልሳ ለመንፈሳዊ አገልግሎቷ መብቃት ከመቻሏም በላይ የወርድ ፕሬስ አካውንትም እስከመክፈት መድረሷ ይታወቃል።
ምንም እንኳን እንደ ዓውደ ምሕረት ብሎግ ከጉግል ሰርቨር ማውረድ ባይችሉና ብሎክ አድርገው ከአገልግሎት ማስወጣት ቢያቅታቸውም ደጀ ብርሃን ብሎግንም ለማጥቃት ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጋቸው አልቀረም። ኢሜላችንን በመሰርሰር ብሎጋችንን ለመዝጋት፤ የሀሰት መልእክቶችን በመላክ ለማሰናከል ተደጋጋሚ ሙከራ ተደርጓል።
ይህንን ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረገብንን  የኢንተርኔት ፕሮቶኰል አድራሻ በመመዝገብ ማን? ከየት? መቼ? እንዴት? ሙከራውን እንደሚያደርግና የዚህ ፕሮቶኰል ቁጥር በዓለም ዓቀፉ የስፓም መልእክት ማጣሪያ ኔት ወርክ ውስጥ ያለው ሊስት፤ በዓለም አቀፍ የፕሮቶኰል ቁጥሮች ዝርዝር ውስጥ ያስተላለፋቸው መልእክቶች ዓይነትና ምንነት፤ አድራሻውን፤ የሚጠቀምበትን የሽፋን ሰርቨር የተመለከቱ መረጃዎችን በመሰብሰብ አደገኛነቱን ለማረጋገጥ ችለናል። ይህ ፕሮቶኰል ቁጥር  በአደገኛ ጥቁር መዝገብ /BLACK LIST/ የሰፈረ ሲሆን ይህንን በተመለከተ ኢትዮ ቴሌኮም ምን እንደሚል አናውቅም። ይሁን እንጂ የመንግሥትን ፖለቲካዊ ማንነት በመንቀፍ ይሁን በመደገፍ ያይደለ፤ በመንፈሳዊ ልኬታ ማለት የሚገባንን ብቻ የምንጽፍ ሆነን ሳለ ብሎጋችን በመንግሥት በኩል ጥቃት ይፈጸምበታል ብለን ቅንጣት አንጠራጠርም። ይልቁንም ጽሁፋችን ደስ የማያሰኛቸው የሁከት አባት፤ አባላት ያልገቡበት የመንግሥት ቢሮ ባለመኖሩ ይህንኑ ፍቅራቸውን ለማሳየት ይህንን አስጸያፊ ተግባራቸውን በመንግሥት አገልግሎት ሽፋን ሊጠቀሙ ይችላሉ ብለን እንጠረጥራለን።
የፕሮቶኰል ቁጥሩ ባለቤት ነኝ የሚል አካል ካለ ለምን በተለያዩ ዓለም የመረጃ መረብ ኔት ወርክ ውስጥ በአደገኛ ቁጥር ውስጥ ሊመዘገብ እንደቻለ፤ የሀሰት ኢሜሎችን በመላክና ኢሜል ለመሰርሰር/EXTRACT/ በማድረግ  ለምን እንደተጠመደ መልስ ይኖረው ይሆን?
በተለይም ኢትዮ ቴሌኰም ውስጥ በዚህ ፕሮቶኰል መስመር ላይ በኃላፊነት የተቀመጡ ግለሰብ ምን ዓይነት ምላሽ አላቸው? አድራሻቸውን ያገኘነውን ከዓለም አቀፉ የሲስኮ ካምፓኒ ኔትወርክ ነው።



ለማንኛውም ያገኘነውን ሙሉ መረጃ ከታች ያለውን ሊንክ ተጭነው በዝርዝር እንዲመለከቱ ጋብዘናል። ምናልባትም እርስዎም ከጥቃቱ ሰለባ አንዱ ሆነው ይችላልና። መልካም እይታ!!!

( ሙሉውን መረጃ ለመመልከት .click here )

Friday, August 31, 2012

በአሜሪካ ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ለአቡነ ጳውሎስ የሀዘን መግለጫ አወጣ!


ቤተክርስቲያን ለሁለት የመከፈሏ ምክንያት የሥርዓት ለውጥ መከሰቱ እንደሆነ ይታወቃል። ከጊዜው ንፋስ ወዲህና ወዲያ የሚነፍሱ ወገኖች አንደኛውን ወገን የዚያ ሥርዓት ጥገኛ ሲል አንደኛውን ደግሞ የዚህ ቡድን ደጋፊ እያለ የገመድ ጉተታ ዓይነት ሃሳብ በመዘፈቁ የቤተክርስቲያን እርቅና ሰላም በሰመመን ውስጥ ሰጥሟል። አንዳንዶች ደግሞ ፓትርያርክ መርቆሬዎስ ማናቸው? የት ናቸው? በማለት ከ21 ዓመት በኋላ ጥያቄ የሚያቀርብ ጽሁፎቻቸውን በየድረ ገጾቻቸው ላይ ለጥፈዋል። ድምጽዎትን እንስማ፤ እዚህ ቦታ አለሁ በሉን! የሚለው ጥያቄ የፍቅር ከሆነ ይህንን ጥያቄ ለማቅረብ ዛሬ ምን ተገኘ? እንድልንል ያደርገናል። እንዲያውም ወደመንበራቸው ይመለሱ! የሚባሉት እርስዎ ማነዎት? የሚለው ፌዝ መሰል ጥያቄ ግልጽነትና ምክንያታዊነት የጎደለው በመሆኑ የቤተክርስቲያንን እርቅ ገና ብዙ ፈተና እንደሚጠብቀው ያመላክታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው ሲኖዶስ በሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ፓትርያርክ ሞት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል። ለቤተክርስቲያን አንድነትና ሰላም በጋራ እንስራ! የሚል መልእክቱንም አስተላልፏል።
ከቤተ ጳውሎስ ድረ ገጽ ላይ ያገኘነውን መረጃ አካፍለናችኋልና ከታች ያለውን ሊንክ በመጫን እንዲያነቡ ተጋብዘዋል።


( መግለጫውን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)