ነሐሴ
11/2004 ዓ/ም /Aug 17/2012
“ክቡር
ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር” (መዝ 115፥6)
የአምስተኛውን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ
ዶ/ር አቡነ ጳውሎስን ዕረፍት አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት
ጉባኤ ጽ/ቤት የተሰጠ የኃዘን መግለጫ።
ለኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ
አዲስ
አበባ፤ ኢትዮጵያ
እንዲሁም
በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያና በመላው ዓለም ለሚኖሩ የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን በሙሉ።
በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በአምስተኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የዓለም የሰላም አምባሳደር ድንገተኛ ዕረፍት ምክንያት የተሰማውን ከፍተኛና ትልቅ ኃዘን ይገልጻል። እንደሚታወቀው ቅዱስነታቸው ለቤተ ክርስቲያናችን
ዕድገትና መሻሻል፣ መጠናከርና መስፋፋት የሚጠቅሙ በርካታ መንፈሳዊ ተግባራትን ያከናወኑ ታላቅ የቤተ
ክርስቲያናችን አባትና የሥራ ሰው
ነበሩ። በመሆኑም ቅዱስነታቸው በአገልግሎት ዘመናቸው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከናወኗቸው ዘርፈ ብዙ ሐዋርያዊ ተግባራት ምን ጊዜም ሕያውነታቸውን ሲያስታውሱ ይኖራሉ። ቅዱስነታቸው ብሔራዊውን የአብነት ትምህርትና ዘመናዊውን ዕውቀት አገናዝበው የተማሩ ታላቅ ሊቅ ስለነበሩ ለቤተ ክርስቲያን እጅግ አስፈላጊ ቅዱስ አባት ነበሩ፤ ይልቁንም ባለንበት ዘመን ቤተ ክርስቲያናችንን በዓለም መድረክ ወክለው ያከናወኗቸው ብዙ ሥራዎች ዘወትር ሲታሰቡ ይኖራሉ። ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን እኒህን ታላቅ አባት በድንገት በማጣቷ ልባዊ ኃዘናችንን በድጋሚ እንገልጻለን። በእውነቱ የቅዱስነታቸው ድንገተኛ ዜና
ዕረፍት ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ኃዘን ነው።
ይልቁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በቅዱስነታቸው አባታዊ ቡራኬና በቅዱስነታቸው በሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መልካም ፈቃድ ሦስተኛውን ዙር የሰላምና አንድነት ጉባኤ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ሳለ ይህንን ቤተ ክርስቲያንን አንድ የሚያደርግ ታሪካዊ ሒደት ለፍጻሜ ሳይበቃ የቅዱስነታቸው ዜና ዕረፍት መስማቱ ጉባኤውን በእጅጉ አሳዝኖታል፤ ሊያስከትል የሚችለው ውጣ ውረድም ከወዲሁ አሳስቦታል። ቅዱስነታቸው የጀመሩትን የቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ጥረት የመጨረሻ ፍሬ ሳያዩ በድንገት በማለፋቸው ኃዘናችን ወሰን የለውም። የሰላምና አንድነት ጉባኤው በቅዱስነታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው የጉባኤውን የኃዘን መግለጫ የሚያደርሱ ልዑካንን ሰይሞ ለመላክ
በአንድነት ወስኗል።
የኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ቤተ ክርስቲያንን አሁን ካለችበት አሳሳቢ የልዩነት ፈተና ይበልጥ ወደ ባሰና ወደ ከፋ ችግር እንዳትሄድ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ተቀዳሚ ሥራው በማድረግ ለዘመናት በአንድነቷ ጽንታ የኖረችውን ቤተ ክርስቲያን የቀድሞ ታሪኳን ለመመለስና ለማደስ ተገቢውን ሥራ በአንድነት እንዲሠራና እስካሁን ድረስ የቆየው የልዩነት ምዕራፍ እንዲዘጋ፣ በቅዱስነታቸውና በቅዱስ ሲኖዶስ በጎ ፈቃድ የተጀመረውን የሰላምና አንድነት ሒደትም ለፍሬ ያበቃው ዘንድ ጉባኤው ከታላቅ አደራ ጋር ይማጸናል።
በመሆኑም
የሰላምና አንድነት ጉባኤው ለቅዱስ ሲኖዶስና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መላው ካህናትና ምእመናን ወምእመናት ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ያስተላልፋል።
1ኛ/
በቅዱስነታቸው ድንገተኛ ዕረፍት ምክንያት የተሰማንን ጽኑ ኃዘን እየገለጽን ከምንም በላይ በቅዱስ ሲኖዶስ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ዋነኛውና አንገብጋቢው ጉዳይ ቤተ ክርስቲያንን አንድ ማድረግ መሆኑን በአጽንኦት እንገልጻለን፤ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ባለፈው ሐምሌ ወር ሦስተኛውን ጉባኤ አበው ለማካሄድ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነበር። ይሁን እንጂ በግንቦቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የላክነው ደብዳቤና ባለ ሰባት ነጥብ የመፍትሔ ሐሳቦች በአገር ውስጥና በውጭው ዓለም የሚገኙት አባቶቻችን በዕርቀ ሰላም ውይይቱ ላይ ለመገኘት ሙሉ ፈቃዳቸው መሆኑን ገልጸውልን ነበር። በዚህ መካከል ግን በአዲስ አበባ በኩል በሰላምና አንድነት ጉባኤው የቀረቡትን ሰባቱን የመፍትሔ ሐሳቦች አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ በወርኃ ሐምሌ መግቢያ ላይ ተነገጋሮባቸው በአፋጣኝ መልስ እንደሚሰጠን በደብዳቤ ተገልጦልን ነበር።