Monday, July 16, 2012

በመልካም መበደል



                       የጽሁፍ ምንጭ፤ ቤተፍቅር/www.betefikir.blogspot.com/
 

         ከምድራችን ጩኸት አንዱ የመልካም ያለህ የሚለው ነው፡፡ በጎውን ማድረግ ሰው የተፈጠረበት ዓላማ ሆኖ ሳለ ዛሬ አንድ መልካም ማግኘት የአንድ በዓልን ያህል የሚያስቦርቅ ሆኖአል፡፡ በእርግጥም በክፉ በተያዘው ዓለም ክፉዎች አይደንቁንም፡፡ ጥሩ ነገር ከሰዎች ልቦና በተንጠፋጠፈበት፣ ለዓመጽ የተዘረጉ፤ ለመታደግ የታጠፉ እጆች በበረከቱበት፣ ለመርዶ የሚፋጠኑ፤ ለምስራች ሽባ የሆኑ እግሮች በሚስተዋሉበት፣ አደበት ሁሉ ስንፍናን አብዝቶ በሚያወራበት ዓለም መልካምነት ጌጡ የሆነ ሰው ሲገኝ ከዚህም በላይ ያስደስታል፡፡ ልብ ብለነው ከሆነ ግን መልካም መሆን፤ በጎ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በዚያ መልካም ላለመበደል፣ በዚያ በጎ ላለመሳት መጠንቀቅም እንደ እግዚአብሔር አሳብ ሊኖሩ ለሚፈልጉና ከሕሊና ውቅሻ ማምለጥ ለሚሹ ሁሉ የተገባ ነው፡፡
        አብዛኛውን ጊዜ በውጪው ዓለም ላይ በሥራ የሚሰማሩ ወገኖቻችን የኑሮአቸውን ያህል የሚኖሩት ለቤተሰብና ለዘመዶቻቸው ጭምር ነው፡፡ አንዳንዴም የራሳቸውን እስኪረሱ ለቤተሰብ የሚኖሩ፣ የሚለፉ ሰዎችን አስተውለናል፡፡ አገር ቤት ያለውን ነገር ስንመለከተው ደግሞ በእህትና ዘመድ ልፋት ሳይማሩ፣ ሳይሠሩ፣ ሳይጥሩ የሰው ወዝ ባመጣው የሚኖሩ ወጣቶችንና ወላጆችን ታዝበናል፡፡ ነገር ግን ረጂዎቹ አስተውለውት ከሆነ በመልካምነት እየበደሉ ነው፡፡ መስጠት ስላለብን እንጂ ብር ስላለን ብቻ አንሰጥም፡፡ መርዳት ስላለብን እንጂ መርዳት ስለቻልን ብቻ አንረዳም፡፡ ምናልባት ይህንን ከመንፈሳዊው ጎን ተመልክታችሁ ልክ ያልሆነ አባባል እንደሆነ ሊሰማችሁ ይችል ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን መንፈስ ሁሉን ይመረምራል፡፡ የእግዚአብሔር አሳብም ሞኝነትን አያበረታታም፡፡ ሁሉን ለማነጽ እንድናደርገው ታዘናል፡፡

Saturday, July 14, 2012

ማኅበራት የክፍፍል መድረኮችና የሁከት ምንጮች ሆነው እያስቸገሩ ነው!



ከወደ ጠቅላይ ቤተክህነት አካባቢ ሰሞኑን «ጉባዔ አርድእት» የሚባል ጊዜያዊ ማኅበር ይቋቋማልን እንደማንኛውም ሰው ሰምተናል። እኛን ግራ የገባን ይህ «ጉባዔ አርድእት« የተባለው መቋቋሙ ሳይሆን ከተቋቋመ 20 ዓመቴን ሞልቻለሁ የሚለው ጎረምሳው ማኅበር ማቅ ግን ሽብር የገባበት ምክንያት አስገራሚ መሆኑ ነው። 

ሁለት ነገር እንድናነሳ ተገደድን። አንደኛ ማኅበሩ ከእኔ ወዲያ ሌላ ማኅበር አያስፈግም  የሚል የጽንፈኝነት ጥግን የታጠቀና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በእኔ በኩል ያላለፈ መንፈስ ቅዱስ እንዴት እዚያ ይደርሳል? ስለዚህ እፍ! ያላልኩበት  ማኅበር ሊኖር አይችልም የሚል ስግብግብነት የሞላው ጠባብ አስተሳሰቡ ነው።

በአንድ በኩል የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እና የቅድስት ሥላሴ ኰሌጅ ደቀመዛሙርት ማኅበራት መኖራቸውን እደግፋለሁ ሲል እየተደመጠ በሌላ በኩል ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንትና አመራር ላይ ያሉ ሰዎች ስብስብ እንደሆነ የሚነገርለት «ጉባዔ አርድእት» መቋቋምን  ስመለከት ዓይኔ ደም ይለብሳል  ዓይነት ቅናት ከሰይጣን እንጂ ከመንፈስ ቅዱስ ሊሆን አይችልም።
ይህ ይቋቋማል የሚባለው የጉባዔ አርድእት ማኅበር አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ  በሥራ ላይ ያሉ የቤተክርስቲያኒቱ ሰዎች እስከሆኑ ድረስ ማኅበረ ቅዱሳንን ይህን ያህል ያስጨነቀው ለምንድነው?   ቤተክርስቲያኒቱን  ይጥቀምም፤ አይጥቀምም ራሱ ማቅ እንደ ማኅበር የተቋቋመበትን መንገድ ሌሎች የዚሁ መብት ተጠቃሚ የመሆን  መብት እንዳይኖራቸው መጮሁስ ምን ይባላል?

ማንም የሾመው ባይኖርም« ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው እንዲሉ» ራሱን በራሱ ሾሞ  ከጉባዔ አርድእት አባላት መካከል  አንዳንዶቹን በተሐድሶነት ይወነጅላል።  በተለመደ የድራማው ትወና  አፈኞቹን ጉዳይ ፈጻሚዎቹን በደንብ ጭኖና አስፈራርቶ እነዚያ የሚወነጅላቸውን ሰዎች በቀጣይ ጉባዔ እስኪያስወግዝ ድረስ የቤተክርስቲያኒቱ አባላት መሆናቸውን አምኖ መቀበል የግድ ይሆናል። ስለዚህ ጉዳይ ፈጻሚ  አባቶቹ የማኅበሩን ተልእኰ ተቀብለው ውግዘት  እስኪያወርዱ ድረስ በሥራ ላይ ያሉ ሰዎች የቤተክርስቲያኒቱ አባላት ናቸውና ማቅ ማኅበር ሆኖ እንደሚንቀሳቀሰው ሰዎቹንም ማኅበር እንዳያቋቁሙ የሚከለክላቸው ምንም አሳማኝ ነገር የለም።
ይልቁንም  ማኅበርሩን እንደዚህ ሽብር ውስጥ የከተተውን ነገር ከማኅበሩ ግልጽና  ስውር ዓላማ አንጻር ከታች የተመለከቱትን ነጥቦች ማንሳት እንችላለን።

1/ ጉባዔ አርድእት በቤተክርስቲያን ሙያ የበለጸጉ ምሁራንና በዘመናዊውም የበሰሉ ሰዎች ስብስብ እንጂ እንደ ማቅ አባላት የክብር ቅስና ያልተሸከሙና  የንግድ ግዛት /ኢምፓየር/ ያላቋቋሙ በመሆናቸው፤

2/ የጉባዔ አርድእት አባላት ናቸው ተብለው የሚነገርላቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ በቤተክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የአመራር እርከን ላይ የሚገኙና  በሰንበት /ቤት ሽፋን አንድ እግራቸውን እንደማቅ ውጪ ያላደረጉ ስለሆነ፤

3/ በዚሁ በአዲሱ ማኅበር ውስጥ ይካተታሉ የሚባሉት ሰዎች አብዛኛዎቹን ማቅ ሲወጋቸውና ሲያደማቸው የቆዩ በመሆናቸው ውሎ አድሮ የእጄ ይከፈለኛል የሚል ፍርሃት ማቅን ስለሚያስጨንቀው፤

4/ በማኅበረ ካህናቱ ዘንድ «ማቅ፤ ጢም የሌለው አልቃኢዳ» እየተባለ መጠራቱ የሚታወቅ ሲሆን ጉባዔ አርድእት ህልው ሆኖ ከተቋቋመ በአባልነት ይሁን በተሳታፊነት ማኅበረ ካህናቱን ሁሉ ስለሚጠቀልል  መንቀሳቀሻ ስፍራ ያሳጡኛል የሚል ስጋት፤

5/ በሕዝብና በመንግሥት ዘንድ አስቸጋሪነቴ ግልጽ ይወጣል ከሚል ፍርሃት፣

 6/ ተሐድሶ ወይም ጴንጤ እያልኩ የዓይኑ ቀለም ያላማረውንና ለእኔ ያልተንበረከከውን ሁሉ ለማድቀቅ ይቸግረኛል ከሚል እሳቤ የተነሳ፤
7/ የታዛዦቼን ሊቃነ ጳጳሳት ቅስም በመስበርና በማስፈራራት ለአቡነ ጳውሎስ እንዲገዙ በማድረግ የሲኖዶስ ላይ ስውር ድምጼ ይታፈናል፤ አባ ጳውሎስም  ጉባዔ አርድእትን እንደአንድ ኃይል ሊጠቀሙት ይችላሉ ብሎ በመስጋት፤

8/ አሁን ያለኝ እንቅስቃሴ ከጫፍ እጫፍ መድረሱ እክል ሊገጥመው ይችላል ብሎ ለእጀ ረጅምነቱ ከመጨነቅ አንጻር ሲሆን

ከብዙ በአጭሩ ሊነሳ የሚችል ውጥረቶቹ እንደሆኑ እነዚህን ልንገምት እንችላለን። እንዲያውም ከግምት በዘለለ የማኅበሩ አፈቀላጤ የሆነው «ደጀ ሰላም» ማቅ ይደርስብኛል ብሎ ከሚያስበው አንዱን ስጋት እንዲህ ሲል ተናግሯል።

«የአባ ጳውሎስን ዐምባገነንት ለማጠናከር፣ መንፈሳውያን ማኅበራትን ለማፈራረስ፣ የግል እና የቡድን ጥቅሞቹን ለማስጠበቅ….» በማለት በግልጽ አስቀምጧል።

Friday, July 13, 2012

«ክስን፤ ጥቆማንና ዳኝነትን ለይቶ ያልወሰነ ስብሰባ!»


የታመመ ሰው ሕክምና የሚሄደው ለሕመሙ ተገቢውን ህክምና ለማግኘት ነው። ሐኪሙ፤ ከታማሚው የሚያገኘውን የቃል መረጃና በምርመራ ያገኘውን ውጤት አንድ ላይ አዋሕዶ ካልሰራ በስተቀር ፈዋሽ መድኃኒት ማዘዝ አይችልም። ቢያዝ እንኳን ለማያውቀውና መርምሮ ላልደረሰበት በሽታ የሚሰጠው መድኃኒት ከፈዋሽነቱ ይልቅ ጎጂ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ይሆናል።
እንደዚሁ ሁሉ በጥቅምት ወር 2004 ዓ/ም ላይ የቤተክርስቲያን መሪዎች ሊቃነ ጳጳሳት ስብሰባ ተቀምጠው ነበር። ታማሚውን፤ የሕመሙን ዓይነትና ለሕመሙ የተስማማ መድኃኒት ለይቶ ለመስጠት በተሰየመ አጀንዳ ላይ ውይይት አድርጎ ማዘዙን የተመለከተ መረጃ «አባ ሰላማ» በድረ ገጹ አስነብቦናል። ይህንኑ ተመልከተን አንዳንድ ጥያቄዎችን አጫረብንና በዚያ ላይ የተድበሰበሰውን አካሄድ ለመግለጥና  «ሲያውቅ የተኛ ቢጠሩት አይሰማም» እንዲሉ  መደረግ የነበረበትን አካሄድ ሁሉ ለማኅበረ ቅዱሳን ደስታ ሲባል የተተወ መሆኑን ብናውቅም ለታሪክና ለትውልድ ትልልቁን ግድፈት ለማሳየት ወደድን።

1/ የቀረበው ክስ ነው ወይስ ጥቆማ?

ሀ/ ክስ ፤/accusation/
ክስ /accusation/ በእንግሊዝኛው ፍቺ፤ አንድ ሰው ወይም ቡድን በሌላ ሰው ወይም ቡድን ላይ ሕገ ወጥ ነገር ፈጽሟል ብሎ የሚያቀርበው የሕግ መብትን የማስከበር አቤቱታ ነው።
ይህንኑ ቃል አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ እንዲህ ሲሉ በመዝገበ ቃላቸው ላይ ፈትተውታል።
«ከሰሰ- በዳኛ ተማጠነ፤ እገሌን አቅርብልኝ፤ ዳኘን አለ። በደሉን፤ ግፉን ተናገረ፤ አመለከተ፤ ጠላቱን አሳጣ» በማለት ተርጉመውታል።
ክስ በሚለው ቃል ላይ እንደ አስረጂ በቀረቡት ትርጉሞች ላይ ከተግባባን  በማኅበረ ቅዱሳን ከሳሽነት እና በተከሳሽ 7 ድርጅቶችና 16 ግለሰቦች  መካከል  ለተቀደሰው ጉባዔ ቀርቦ የታየ ነገር ነበርን? ብለን ብንጠይቅ አዎ ለማለት የሚያስችል ጭብጥ የለንም። ምክንያቱም «ክስ» የሚለውን ዐውደ ቃል ሊያሟላ የሚችል ሂደት አልነበርምና ነው። ይሁን እንጂ የሊቃነ ጳጳሳቱ ስብሰባ የሰጠው ውሳኔ እንዲህ ሲል ይናገራል።

«………….7 ድርጅቶችና 16 ግለሰቦች የቀረበባቸው ክስ በተጨባጭ በመረጋገጡ» ይላል። ማን ከሳሽ? ማን ተከሳሽ? ማን መርማሪ? ምን ዓይነት መልስና ማስረጃ ቀረቦ ታየ? የሚታወቅ ነገር የለም። በክስ አግባብና  አካሄድ ያልሄደ ሆኖ ሳለ እንዴት ነው በተጨባጭ የሚረጋገጠው? እዚያው ፍጪው! እዚያው አቡኪው! ከመሆን የዘለለ አልነበረም። ስለዚህ በየትኛውም መመዘኛ «ክስ» የሚለውን ስያሜ ለመያዝ የሚያበቃው ስላልሆነ ይህንን ስም ሲያነሱት ሊያፍሩ ይገባቸዋል። በዚህ ዘመን በተደበላለቀ ጫወታ/game/፤ ትላልቆች የተቀመጡበትን ሥፍራ ለሌሎች ዓላማ መሳካት ማዋል ያስተዛዝባል። ያሳዝናልም።