ብዙዎቻችን ኢትዮጵያዊ መሆን ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ
መወለድ ብቻ አድርገን እንቆጥራለን። ያ ግን ከእውነታው ብዙ የራቀ አስተሳሰብ ነው። በምንም መመዘኛ ኢትዮጵያ ውስጥ መወለድና ኢትዮጵያ
ዜጋ መያዝ ማለት ኢትዮጵያዊ ማለት አይደለም የሚል አቋም አለኝ። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ማለት በኑሮው፤ በባህሉ፤ በወጉ፤ በቋንቋው፤
በእምነቱ፤ በታሪኩ፤ በድርጊቱ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መገኘት ነውና። ባህሉን፤ አኗኗሩን፤ ወጉን፤ ቋንቋውን ታሪኩንና እምነቱን፤ትውፊቱን
ሁሉ ከኢትዮጵያዊነት አተያይ ውጪ ያደረገ ትውልድ እንደ ሸቀጥ /Made in………/ ተብሎ ኑረቱ የሚገለጽበትን የባእድ ሀገር የማንነት
ስያሜ ይሰጠዋል እንጂ ኢትዮጵያዊ ሰው ሊባል የተገባው አይደለም። ኢትዮጵያዊ ሆኖ ከመኖር ውጪ ኢትዮጵያዊነት ሊኖር አይችልምና።
ያ ማለት ግን ከሌላው ዓለም ሚዛን ጋር ራሱን እየጠበቀ፤ የጎደለውን እየሞላ፤ የጎዳውን እያረመ አይሄድም ማለት ሳይሆን ማንነቱን
በሌሎች ማንነት ውስጥ በመለወጥ፤ በመተካት ወይም በመደረት ኢትዮጵያዊ
መባል እንዳይቻል ለማሳየት ተፈልጎ ነው።
ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የተጻፉ ሰፋፊ ጥናቶች
እንደተጠበቁ ሆነው በዚህ ጽሁፍ ለመዳሰስ የተፈለገው በርእሱ ላይ የተጠቀሰውን «ትውልድ ያላወቀው ኢትዮጵያዊውን ሰው» በተመለከተ
በአጭር ምልከታ ለማብራራት ነው።
«ትውልድ ያላወቀው ኢትዮጵያዊ ሰው» በብዙዎች
ዘንድ መምሩ/መምሬ/ ወይም ቄስ ተብሎ በማእረገ ክህነቱ የሚጠራው የኢትዮጵያው የገጠር ቤተክርስቲያን አገልጋይ /ካህን/ ነው። በእርግጥ
ዘመኑ መምሩ/ መምሬ/ ወይም ቄስ የሚለውን ስመ ተጸውኦ ሲያዘምነው በከተሜው ዘንድ «ቀሲስ» መባሉ ቢታወቅም ያ የገጠሩ ቄስ/ መምሩ/፤
ከዚህ እንግዳ የዝመና ጥሪ ጋር ብዙም ትውውቅ ስለሌለው ያችን ከምንም በላይ የሚያከብራትን፤ የሚወዳትንና የሚጠብቃትን የ«መምሬ»
እገሌን ጥሪ እስከዛሬ ሳይለቅ እንደያዘ ይገኛል። ቄስ እገሌ ወይም መምሬ እገሌ ተብሎ መጠራታቸው ለእነርሱ ኩራታቸውና ክብራቸው
ስለመሆኑ በቅርብ የምናውቃቸው ዘመዶቻችን እንደሚናገሩ ለዚህ ዋቢዎች ነን።
እነ መምሩ/መምህሩ/ የሚከበሩትና የሚወደዱት ገጠር ስለኖሩ ሳይሆን ለነግህ ኪዳን፣ ለሰርክ ጸሎት የሚተጉ ከመሆናቸው
ባሻገር እንደ ተራው ህዝብ ኑረትን ኖረው፤አርሰው ቆፍረውና ጎልጉለው የሚተዳደሩ፤ የተጣሉትን አስታርቀው፤ የታመሙትን ጠይቀው፤ በቤታቸው፤
በጎረቤታቸውና በአካባቢያቸው ፈሪሃ እግዚአብሔርን ኖረውትና አስተምረው፤ ሕዝቡ በግብረ ገብነትና በመከባበር ማኅበራዊ ኑሮውን በኅሊና
ዳኝነት እንዲገፋ በማድረግ ከማንም በላይ ኢትዮጵያዊነት የሚታይባቸው የሕብረተሰብእ አንጓዎች በመሆናቸው ነው።
እነመምሩ በቀደሙት ዘመናት ከቤተክርስቲያን የምትሰጣቸውን
10 ብርና 20 ብር ወይም በቁና የምትሰፈርላቸውን የእህል የድርጎ
መዋጮ እንደክፍያ ቆጥረው ሳይሆን ኃላፊነትና ግዴታቸውን አውቀው በማኅሌቱ፤ በሰዓታቱ ቆመው ሲያድሩ ብርታታቸውና ጥንካሬአቸው በእውነቱ
ያስገርማል። የሀገር ዳኛ ሳለ እነመምሩ የምእመናን ዳኛ ናቸው። ቃላቸው ይፈራል፤ ይከበራል። ምክራቸውና ተግሳጻቸው በሁሉም ዘንድ
ቅቡል ነው።