Friday, June 29, 2012

«የታማኝ ወዳጆች መከዳዳት»


 ባንድ አገር የሚተማመኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። ከነዚህም አንደኛው በሀብቱ የገነነ በሽምግልናው የተከበረ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እየሠራ ከሚያፈራው ከዕለት ምግቡ ካመት ልብሱ የሚተርፈው ገንዘቡን እየወሰደ ባደራ ስም አኑርልኝ እያለ ለባለጸጋው የሚሰጥ ነበረ። ያም ታማኝ መሳዩ ሽማግሌ ያደራውን ገንዘብ እየተቀበለ ሲያስቀምጥለት ቆይቶ አንድ ቀን ባለ ገንዘቡ ለዕለት ችግሩ ካኖረው ሒሳብ ላይ ጥቂት እንዲሰጠው ቢጠይቀው ምን ሰጠኸኝና ትጠይቀኛለህ አላየሁም ብሎ ጨርሶ ካደው፤ እየተመላለሰ በማሳዘን ቢለምነውም አላዘነለትም፣ አልራራለትም። ቁርጡን ካወቀ በኋላ ላገሩ ዳኛ ክስ ለማቅረብ ሄዶ አመለከተ፤ ዳኛውም ስትሰጠው ያየህ ምስክር የሚሆን ሰው አለህን ብሎ ቢጠይቀው ከኔና ከሱ በቀር ማንም ሰው አልነበረም አለው። እንግዲያስ እኔ እጠይቅልሃለሁና ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሰህ እንድትመጣ ብሎ አስታወቀው።
ብልኁ ዳኛ አደራ አስቀማጩን ሰው ጠርቶ፣ አሁን ያስጠራሁህ እኔ በድንገት ከዚህ አገር ከሹመቴ ተሽሬ መሄዴ ነው፤ ብጠይቅ ባስጠይቅም ታማኝ ሽማግሌ ባገር ያለኸው አንተ መሆንህን ሰማሁ፡ ስለዚህ ዕቃዬንና ያለኝን ገንዘቤን በሙሉ አንድ ጊዜ አንሥቼ ለመሄድ ስለማይቻለኝ አንተ ዘንድ እንድታስቀምጥልኝና በየጊዜው ሰው ስልክ እንድትሰጥልኝ እለምንሃለሁ አለው።
ሽማግሌውም እንግዲህ ይህ ያገር ዳኛ ትልቅ ሰው ስለ ሆነ ባደራ የሚያስቀምጠው ገንዘብ በብዙ የሚቆጠር ዕቃውም ካይነቱ ብዛት ጋራ የበረከተ ይሆናልና ይኸን ተቀብዬ አላየሁም ብዬ ባለሀብት ባለገንዘብ እሆናለሁ ብሎ ደስ አለውና ለዳኛው እሺ ጌታዬ ሲል መልስ ሰጠው።
ከሦስት ቀንም በኋላ ባለገንዘብ ለዳኛው በቀጠሮዬ መጥቻለሁ ብሎ አመለከተው። እንግዲህ ሂድና አንዳችም ነገር ሳትጨምር ባገሩ ዳኛ ልከስህ ነውና ገንዘቤን ስጠኝ በለው፤ በዚያም ጊዜ ገንዘብህን በሙሉ አንድም ሳያስቀር ጨርሶ ይሰጥሃል አለው። እንደ ተባለውም ሁሉ ሄዶ ቢጠይቀው ይህን አልሰጥም ያልኩት እንደ ሆነ ለዳኛው ሲነግረው ከሓዲነቴን ያውቅብኝና የሱን ብዙውን ገንዘብና ዕቃ ያስቀርብኛል ሲል ገንዘቡን በሙሉ አውጥቶ ሰጠው ይባላል።
እንቅልፍ ለምኔ፣ 3 እትም። ከብ/ጌታ ማኅተመ ሥላሴ። 1960 አርቲስትክ ማተሚያ። /አ። ገጽ 184-185

Thursday, June 28, 2012

ሁሉም ነገር ወደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ ይመስላሉ አንዳንድ ብሎጎች!

 
በፍቅር ለይኩን፡፡
የደጀ ብርሃን ጸሐፊዎች «አህያውን ፈርቶ ዳውላውን» እንዲሉ እባካችሁ የአባቶችን ገመና እና ኃጢአት እንዲህ ጨዋነት በጎደለው መልኩ በየአደባባዩ እያወጣንና እየዘረዘርን ከመንፈሳዊነት ሕይወት ውጭ አንሁን ይሄ ዓይነቱ መንገድ መንፈሳዊነቱ ቢቀር ኢትዮጵያዊው ጨዋነትና ባሕል አይፈቅደውም እና እንተወው ለሚል ጹሑፌ የዛሬ ሁለት ዓመት በጻፍኩት ጹሑፍ ተነስተው አንተ በመንግሥት ተቃዋሚ ድረ ገጾች አቡነ ጳውሎስንና ቤተ ክህነቱን እንዳሻህ ስታብጠለጥል ቆይተህና በአፍቃሪ ማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች ላይ እንዳሻህ ስትሆን ከርመህ ዛሬ እኛ ያሻነውን ብንል ምነው ቆጨህ በማለት፣ ያሻንን በማለት መብታችን ላይ አትምጣብን በማለት የክርክሩን ጭብጥ ለቀቀውና አይወርዱ አወራረድ ወርደው ከቆየ ጹሑፌ ጥቂት መስመሮችን ብቻ በመውሰድ የጹሑፌ አጠቃላይ ጭብጥና መንፈስ ምን መሆኑን ለአንባቢያን ሙሉ መረጃ በማይሰጥ መልኩ በዘረኝነትና በጎጠኝነት ሊፈርጁኝ ደፈሩ፡፡
ደጀ ብርሃኖች ለምን እንዲህ ዓይነቱን መሰሪ አካሄድ እንድመረጡትም ግራ ገብቶኛል፣ ምላሽ ልሰጣቸው አስቤ ነበር ግን ጽንፈኝነት የሞላበትና ሚዛናዊነት የጎደለው የሚመስለው አካሄዳቸው ስላልጣመኝ ተውኩት ደግሞም አንባቢያን ለሕይወታቸው የሚተርፍ የወንጌል ትምህርት ፍለጋ በሚቃርሙበት ጊዜያቸው የእኛን ሙግት እንዲያዳምጡ መጋበዝ ሌላ የባሰ ስህተት እንደሆነ አስበኩና አሳቤን ቀየርኩ፡፡ መቼም ቀውስጦስ የተባሉትን አባት «ቀውስና ጦስ» ናቸው በማለት ተራ የሆነ የቃላት ስንጠቃ ውስጥ በመግባት የሰውን ሞራልና ሰብእና መንካት እንዴት ሆኖ ለቤተ ክርስቲያን ህልውና ስንል ነው እንዲህ የጻፍነው የሚለው መከራከሪያ አሳብ በምን መልኩ ሚዛን እንደሚደፋ ኅሊና ያለው ሰው ይፍረደው፡፡
ከዚህ የሚብሰው ደግሞ አባ ሳሙኤልና ሚጡ ተብሎ የተጻፈው ጹሑፍ እንደዛ ልክ እንደ ዓለማዊ ትረካ ልብን በሚሰቅልና ከአሁን አሁን ምን ይከሰት ይሆን በሚል እስከ አንሶላ መጋፈፍ ያለውን የጓዳ ምስጢር ለመግለጽ ዳር ዳር ያሉበትና አባ ሳሙኤልና ሚጡ ተለዋውጠውታል የተባለው ለጆሮ የሚቀፍ ንግግርን በዝርዝር መዘገብ በምን መልኩ መንፈሳዊ ለዛ ያለው ለቤተ ክርስቲያን ህልውና የቆመ ጹሑፍ ሊሆን እንደሚችል አንባቢ ይፍረደው ከማለት ውጭ ሌላ ምን ማለት ይቻላል፡፡ 

Wednesday, June 27, 2012

"...መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ" ማቴ. 5፥16

በመምህር ሙሴ ኃይሉ

ምንጭ፤ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መ/ ድረ ገጽ

 መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ማር እንደ ወተት የሚጣፍጠውን ትምህርቱ ለመስተማርና በተለያዩ ምክንያቶች (ተአምራትን ለማየት፣ ምግበ ሥጋን ለመመገብ፣ ሐሰት አግኝተው ለመፈተን...) ከአምስት ገበያ በላይ ሕዝብ ተሰብስበው በተመለከተ ጊዜ ከፍ ወዳለ ተራራ ወጥቶ በወርቃማ አምላካዊ አንደበቱ በተራራማ ስብከቱ ካስተማራቸው የመንፈሳዊነት፣ የሐዋርያዊነት፣ የአገልግሎት፣ የምግባርና የትሩፋት ትምህርት አንዱ ነው፡፡ ይኸው ትምህርት ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያትና በሐዋርያት እግር ሥር የሚተኩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ምዕመናንና ምዕመናትን የሕይወት መርህ በማድረግ እስከ መጨረሻ ህቅታ ድረስ አጽንተው እንዲጠብቁ የተሰጠ የምግባርና የትሩፋት (የሥነ ምግባር) አስተምህሮ ነው፡፡ ብርሃን በተለያዩ ዓይነት የትምህርት ዘርፎች የተለያዩ ትርጉም ቢኖረውም መጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ዕውቀታችን አድርገን ለምናምን ለኛ ግን ብርሃን የእግዚአብሔር የባሕርይ መገለጫው ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት ብርሃን ፈጣሬ ዓለማት፣ ሠራዔ ዓለማት፣ መጋቤ ዓለማት እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለሆነም ብርሃን ሀሉን ያስገኘ፣ ሁሉን የፈጠረ እንጂ በዚህ ዘመን ተገኘ፣ ከዚህ ዘመን በኋላ ያልፋል ተብሎ የማይነገርለት ምሥጢረ መለኮት ነው፡፡ እውነተኛ ዘለአለማዊ ብርሃን እግዚአብሔር መሆኑ ዘመነ መርገም አብቅቶ የዘመነ ምሕረት የምሥራች በተነገረበት ጊዜ ድኅነት ሰጪው፣ አዳኙም ሆነ ድኅነት ተቀባዩ ራሱ የሆነ የባሕርይ ዘለአለማዊ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ (ነባቤ መለኮት) ስለ እውነተኛ ብርሃን ምሥጢር በመጀመሪያ ምዕራፉ ሲጽፍ፡-"...ብርሃን በጨለማ ይበራል ጨለማም አላሸነፈውም፡፡ ...ለሰው ሁሉ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር፡፡ በዓለም ነበረ ዓለሙም በእርሱ ሆነ ዓለሙም አላወቀውም'' (ዮሐ. 1፡1-10) በማለት ጀምሮ የረቀቁ የሥነ መለኮት ትምህርቶችን በምጥቀት ያትታል፡፡


ይህ ማለት አማናዊ ብርሃን እግዘአብሔር መሆኑንና በዚሁ አማናዊ ብርሃንም ሁሉን እንደተገኘ እንረዳለን፡፡ መምህረ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ እውነተኛ አስተምህሮ በግልጽ ሲያስረዳ ማለት እውነተኛ (አማናዊ) ዘለአለማዊ ብርሃን ራሱ "ወልደ አብ ወልደ ድንግል" ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ለደቀ መዛሙርቱና በወቅቱ ለተሰበሰቡት ሕዝብ በግልጽ በአደባባይ አስተምሮአል፡፡ "ደግሞም ኢየሱስ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው" ዮሐ. 8፥12 "በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ" ዮሐ. 12፥36 "የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳላችሁ በብርሃን እመኑ" ዮሐ. 12፥46 እንዲል፡፡ የዓለም ሕዝብ በተለይ ደግሞ ሕግ ተሠርቶላቸው፣ ጽላት ተቀርጾላቸው፣ ነቢያት ተልኮላቸው የነበሩ እስራኤላውያን ሕግን እንጠብቃለን ሲሉ ሕግን እየሻሩና ወደ ራሳቸው (ወደ ሥጋዊ ፍላጎታቸው) ብቻ እየተረጐሙ በኃጢአት ጨለማ ውስጥ ሲኖሩ የጨለማ ጠላት የሆነው እውነተኛ ብርሃን መምጣቱንና ሰዎቹም አለመቀበላቸውን ቅዱስ ዮሐንስ ሲገልጽ፣ "ብርሃን ወደ ዓለም ስለመጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነው" (ዮሐ. 3፥19) በማለት ይገልጽልናል፡፡ የመድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃንነት ከነቢያት ጀምሮ "በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ በሞት አገርና በጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው" (ማቴ. 4፥14-16) በማለት ሲገልጽ የመጣ ሲሆን ይህንኑ አማናዊ ብርሃን አንቀበልም ብለው ኃጢአት ሳይኖርበት እንደ በደለኛ በብርሃኑ ላይ ማመጻቸውም ነቢያት በመንፈሰ እግዚአብሔር ተመርተው አስቀድመው ተነብየውታል፡፡ "እነዚህ በብርሃን ላይ የሚያምጹ ናቸዉ፡፡ መንገዱን አያውቅም በጐዳውም አይጸኑም" (ኢዮብ.24፥13) እንዲል እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነታዎች መረዳት የሚችለው አማናዊ (እውነተኛ) ብርሃን እግዚአብሔር መሆኑን ነው፡፡ የፀሐይና ጨረቃ እንዲሁም የክዋክብት ተፈጥሮስ? አንዳንድ ሊቃውንት ብርሃንን ሲተረጉሙ የተፈጠረ ብርሃንና ያልተፈጠረ ብርሃን በማለት ይተረጉማሉ፡፡