እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? (ክፍል ፩)
የያዝነው
አርባ ጾም ዐቢይ (ታላቅ) ጾም እንደመሆኑ መጠን በመጽሐፍ ቅዱሳችን በምዕራፉ ሙሉ ስለጾም የሚናገረውን ትንቢተ
ኢሳይያስ ም. ፶፰ ከሕይወታችን ጋር በማያያዝ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን እናያለን።
ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፶፰፡-
ቁ .፩ በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር።
ኃጢአት
ሰዎችን ከእግዚአብሔርን የሚለይ ሲሆን ንስሐ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ የሚያደርግ ተግባር ነው። ሰዎች ወደ
እግዚአብሔር እንዲመለሱ ኃጢአታቸው ሊነገራቸው፡ እነርሱም ኃጢአታቸውን በመናገር ንስሐ ሊገቡ ይገባል። በዚህ ክፍል
እግዚአብሔር ነቢዩ ኢሳይያስን ለአይሁድ ኃጢአታቸውን እንዲነግራቸው ያዘዋል። አይሁድ እግዚአብሔርን የሚያውቁና
የሚያምኑ ሕዝቦች ቢሆኑም ጥፋታቸው ሊነገራቸው ይገባ ነበርና ነቢዩን ላከላቸው።
ዛሬ እግዚአብሔርን የሚያውቁና፡ በቤቱ ስለሚኖሩ ክርስቲያኖች ጥፋት ምን እያደረግን ነው? ጥፋታቸው ለራሳቸው ተነግሮአቸው ንስሐ እንዲገቡ ወይስ ለሌላው ተነግሮባቸው እንዲበረግጉ? ወንድሞቻችን ምንም ዓይነት ጥፋት ያጥፉ ቁም ነገሩ ለምን አጠፉ? ሳይሆን እንዴት ይመለሱ? መሆን አለበት። አንድ ወንድም «ከጥፋቴ በፊት መጥፋቴ ያሳስባችሁ» ብሎአል። ብዙ ጊዜ ስለ ጥፋታቸው እንጂ ስለመጥፋታቸው አናስብም። እግዚአብሔር ግን ሁሉም በጥፋታቸው ተጸጽተው በንስሐ ይመለሱ ዘንድ ጥሪ እንድናደርግ በኃይልህ ጩኽ፥ ዝም እንዳንልም አትቈጥብ ይለናል። በአንድምታውም ጩኽህ አስተምር፡ ማስተማሩን ቸል አትበል ይላል።