ቀሪውን 250 ሺህ ብር ሰፋ ባለ መርሐ ግብር ለማሟላት ዕቅድ ተይዟል
በከፍተኛ የልብ ሕመም በመሰቃየት ላይ ላለው ወጣት እንዳለ ገብሬ መታከሚያ በአንድ ቀን መንፈሳዊ አገልግሎት 200 ሺህ ብር ያህል ማሰባሰብ መቻሉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ (ታሪኩን በይበልጥ ለመረዳት፣ ከዚህ ቀደም ሲል ስለ ወጣቱ ችግር ካወጣናቸው ዘገባዎች ጋር ያስተያዩት) ይህንን ያህል ገቢ ሊሰባሰብ የቻለው በአሁኑ ወቅት "ማኅበረ ቅዱሳን" በሚያሳድዳቸው ውድ የሆኑት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የስብከተ ወንጌልና የመዝሙር አገልጋዮች ባዘጋጁት መንፈሳዊ ጉባዔ ነው፡፡
የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሻላ 17 17 መናፈሻ አዳራሽ በተካሄደው በዚህ መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ በግል በአድራሻ ጥሪ የተደረገላቸው ሦስት መቶ ያህል ሰዎች ተገኝተው ግማሽ ያህሉን ገንዘብ የለገሡ ሲሆን ቀሪውን ግማሽ መጠን በቃል መግቢያ ሠነድ እንደሚሰጡ ማረጋገጣቸው ታውቋል፡፡ የዕለቱን መርሐ ግብር የመራው መምህር ተረፈ አበራ ሲሆን፣ መምህር ታሪኩ አበራም በበኩሉ የወደቀውን ስላነሳው የደጉን ሣምራዊ ታሪክ ከወንጌል ጋር በማጣቀስ፣ ችግር ላይ የወደቁትን ወገኖች መርዳት ክርስቲያናዊ ግዴታችን መሆኑን ሰፋ ባለ ሁኔታ ትምህርት ሰጥቷል፡፡