Thursday, January 19, 2012
በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀበራችሁ!
(ከእንግሊዝኛ ማጣቀሻ ጋር)
ቆላስ ፪፥፲፪ (Colossians2:12) « በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ»
ኦሪቱ የአዲስ ኪዳኑን ጥምቀት በማንጻትሥርዓት ታከናውነዋለች። ከኃጢአት ማንጻት! ማንም ቅድስናንና ንጽሕናን ሲሻ ይህንን የማንጻት ልማድ መፈጸም ግዴታው ነው። እንደሕጉ የታዘዘውን መስዋዕት አቅርቦ የሥርዓቱ ማጠቃለያ በምንጭ ውሃ ሰውነቱ መታጠብ አለበት። የማንጻት ልማዱ የሚከናወነው ከሰፈር ውጭ ነው።
«ንጹሕም ሰው የጊደሪቱን አመድ ያከማቻል ከሰፈሩም ውጭ በንጹሕ ስፍራ ያኖረዋል ርኵሰትም ለሚያነጻ ውኃ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ይጠበቃል ከኃጢአት ለማንጻት የሚሆን ነው» ዘኁ ፲፱፣፱ (Numbers19:9)
ፈሳሽ ያለበት ይሁን ለምጽ የወጣበት ወይም ቆረቆር የታየበት ይሁን የመርገም ወራቷ የመጣባት ሴት ሁላቸውም እንደሕጉ የታዘዘውን የኃጢአት መስዋዕት አቅርበው ሲያበቁና ሥርዓቱ ከተከናወነ በኋላ ለመንጻት በምንጭ ውሃ መታጠብ የግድ ነው። ያኔ ነጽተው ወደሕዝቡ ይቀላቀላሉ። አለበለዚያ ከሕዝቡ ጋር ሕብረት አይኖቸውም።ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው ከፈሳሹ ነገር ሲነጻ ስለ መንጻቱ ሰባት ቀን ይቈጥራል ልብሱንም ያጥባል፥ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል» ዘሌ ፲፭፣፲፫ (Leviticus15:13)
«የሞተውን ወይም አውሬ የሰበረውን የሚበላ ሰው ሁሉ፥ የአገር ልጅ ወይም እንግዳ ቢሆን፥ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። ልብሱንና ገላውን ባያጥብ ግን ኃጢአቱን ይሸከማል» ዘሌ ፲፯፣፲፭-፲፮ (Leviticus17:15-16) ያ ማለት ኦሪት የምታነጻውና መስዋዕቱን ፍጹም የምታደርገው በውሃ በመታጠብ ነው።
የዚህ የማንጻት ልማድ የድንጋይ ጋኖች አብነት ሆነው በዘመነ ሐዲስ ከአንድ ሰርግ ቤት ተቀምጠው እናገኛቸዋለን። ቦታው ቃና ዘገሊላ ነው። እነዚህ የድንጋይ ጋኖች በኦሪቱ ለማንጻት ሥርዓት የምንጭ ውሃ የሚጠራቀምባቸው ነበሩ። ወንጌሉ አገልግሎታቸውን ለይቶ አስቀምጦልናል።
«አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር» ዮሐ ፪፣፮ (John2:6)
እነዚህ የማንጻት ሥርዓት የድንጋይ ጋኖች የመጀመሪያውን የአዲስ ኪዳን ተአምርም አስተናግደዋል። የእውነተኛው የወይን ግንድ ደም ለዓለሙ ሁሉ እንደሚፈስ ምሳሌ ሆነዋል። ቅድስት ማርያም ወይን እንዳለቀባቸው ባሳሰበች ጊዜ ጌታም እውነተኛው ወይን ለዓለሙ ሁሉ የሚፈስበት ጊዜ ገና መሆኑን ሲያስረዳ «ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት» ዮሐ ፪፣፬ (John2:4)እውነተኛ ወይን እስኪሰጥ የኦሪቱ የማንጻት ሥርዓት የድንጋይ ጋኖች ጊዜው እስኪደርስ ድረስ ተአምር አስተናግደዋል። እነሱ ሲፈጽሙ የቆዩበትን የማንጻት ሥርዓት አዲስ ኪዳን በማይደጋገምና አንዴ በሚፈጸም የኃጢአት ሥርየት ለውጣዋለች። እሱም «ጥምቀት» ነው። ኦሪት ከሰፈሩ ውጭ ሁልጊዜ በሚፈጸምና በሚፈሰው የደም መስዋዕት ማሳረጊያ የሚሆን የመንጻትን ሥርዓትን ታዛለች።
አዲስ ኪዳን ደግሞ ከሰፈሩ ውጭ በተሰቀለውና አንዴ በሞተው የበጉ መስዋዕት ምሳሌ የውሃ ጥምቀትን በመቀበሩ ጠልቀው፣ ከውሃው በመውጣት ትንሳዔውን መስክረው፣ አንዴ በፈጸሙት ሥርዓት የኃጢአት ስርየት ታስገኛለች።
ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ያለው።
ቆላስ ፪፣፲፪ (Colossians2:12) «በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ»
ጥምቀት ከንስሐ በኋላ የምትፈጸም ስለመሆኗ መገንዘብ ያስፈልጋል። ንስሐ ደግሞ ስላለፈው ተጸጽቶ፣ በጥምቀት ስለሚገኘው ጸጋ አምኖ መቀበልን ይጠይቃል። መጥምቁ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ዙሪያና በሄኖን ማጥመቂያው ሁሉ ሲናገር የነበረው የቅድሚያ አዋጅ «ንስሐ ግቡ» እያለ ይሰብክ እንደነበር እንያለን።
«ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ» ማር ፩፣፬ (Mark1:4)
«ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር» የሐዋ ፲፫፣፳፬ (Acts13:24)
«እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል»ማቴ ፫፣፲፩ (Matthew 3:11)
ሐዋርያው ጴጥሮስም በበዓለ ሃምሳ ተሰብስበው ለነበሩት ነፍሳት ሁሉ አዲሱን የምስራች ከሰበከ በኋላ «ምን እናድርግ?» ብለው በጠየቁት ጊዜ የሰጣቸው መልስ ቅድሚያው ንስሐ ግቡ ነው። ቀጥሎም ኃጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ ነው። ከዚያም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ትቀበላላችሁ ነበር ያላቸው ንግግሩን በማያያዝ።
«ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ» የሐዋ ፪፣፴፰ Acts2:38
«እምነት ከመስማት ነው፣ መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል ነው» ሮሜ፲፣፯ Rome10:7 የሚለው ትምህርት በመጀመሪያ ገቢር ላይ ሲውል የተነገራቸውን ቃል አመኑ፣ ያመኑበትን ተቀበሉ፣ በተቀበሉት ተጠመቁ፣ ከዚያም ወደ መዳን ሕይወት ተጨመሩ ይለናል መጽሐፉ።
« በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና። ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው። ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ» የሐዋ ፪፣፵-፵፩ Acts40:41
ታዲያ እኛስ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?
፩/ « እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ» እርሱን ስሙት ያለውን ብቻ ተቀብለን በማመን አንዲት ጥምቀት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ! ማቴ ፫፣፲፯,Matthew3:17 ኤፌ ፬፣፬, ማቴ ፳፰፣ ፲፱
፪/ ከተጠመቅን ደግሞ «ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና» ሮሜ ፮፣፮ እንዳለው ዳግም ወደኃጢአት አለመመለስ!
፫/ ያመነና የዳነ የክርስቶስ ፍሬ ይታይበት ዘንድ ግድ ነው። «በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል» ማቴ ፲፫፣፳፫ Matthew13:23
ከዚህ ከሦስቱ የወጣ ሁሉ ይህን ሆኗል ማለት ነው።
«አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ። የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል» ፪ኛ ጴጥ ፪፣፳፩-፳፪ 2 Peter2:21-22
ስለሆነም ጥምቀትን ከእውቀት ጋር ስለመዳናችን እንጂ ስለበዓል ጭፈራና የጭፈራ ስርዓት አከባበር እንዳይውል እንጠንቀቅ!
መልካም በዓለ ጥምቀት!!!!!!!!!
Friday, January 13, 2012
የተስፋው ቃል!
«እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና» ገላ ፭፣፭
በተስፋ የሚጠብቅ ክርስቲያን ትክክለኛ እምነትን የያዘ ነው። ፍጹም የሆነ እምነት በሌለበት የጽድቅን ተስፋ መጠባበቅ የለም። ስለሚጠባበቁት ተስፋ ፍጻሜ እምነት ሊኖር የግድ ነው።
ወንድና ሴት ሊጋቡ ሲወስኑ በጋብቻ ውስጥ ሳሉ ስለሚሆነው ነገር ሁሉ አስቀድመው በተስፋ አምነው ይፈጽማሉ። በጋብቻቸው ልጆችን ይወልዱ ዘንድ ተስፋ አድርገው ያምናሉ እንጂ እየወለዱ አይጋቡም። ሴትም በጽንሷ መጨረሻ ወራት ልጇን ትወልድ ዘንድ በተስፋ ትጠብቃለች እንጂ የጽንስ ውጤት ምን እንደሆነ ሳታውቅ ጽንስን አትለማመድም። ስለሚሆነው ነገር ባለው ጽኑ እምነት የተነሳ ውጤቱን በተስፋ መጠበቅ የግድ ይሆናል ማለት ነው።
አንድ ሰው ቃል ከገባለት ሌላ ሰው የተገባለትን ቃል ፍጻሜ በተስፋ ይጠብቃል። የገባለት ቃል ፍጻሜው ምንም ይሁን ምንም የተስፋውን ቃል ያይ ዘንድ በልቡ አስቀምጦ ይጠብቃል።
እንደዚሁ ሁሉ የተበደለ እንደሆነ የሚያምን ማንም ቢኖር ወደፍርድ አደባባይ ቢሄድ የበደሉን ዋጋ መልካም ፍርድን በተስፋ ይጠብቃል። በተስፋ ስለሚጠብቀው ነገር የጸና እምነት ባይኖረው ወደፍርድ አደባባይ በደሉን ይዞ ሊሄድ አይችልም።
ኦርቶዶክስ ይሁን እስላም፣ ይሁዲ ይሁን ጄሆቫ ዊትነስ፣ ፕሮቴስታንት ይሁን ካልቪኒስት የሁሉም ሃይማኖት ተከታይ በሚያምነው ሃይማኖት ውስጥ የመጨረሻ ግቡን በተስፋ ይጠባበቃል። ውጤቱ ምንም ይሁን ምንም የሚጠባበቀውን ተስፋ በእምነት ሳይቀበል ሃይማኖታዊ ልምምዱን በኑሮው ሁሉ ሊተገብር አይችልም።
ተስፋውን የሚጠባበቀው ከማመን ነው። ማመን ደግሞ ከመስማት ነው። በተስፋው ነገር ላይ እምነት ሳይኖረው ተስፋ አያደርግም። የሚያምነው ደግሞ ስለሚጠባበቀው ተስፋ በደንብ በመስማት ነው። ሳይሰማ እንዴት ያምናል? መጽሐፉም «እምነት ከመስማት ነው» ያለውም ለዚህ አይደል!!
Friday, January 6, 2012
እኔ ማነኝ?
(by dejebirhan)
«እኔ ማነኝ? አንተስ ወንድሜ ማነህ?»
እኔ አበባ ነኝ ፣ የማለዳ ጤዛ ያረፈብኝ፣
ፍካት፣ ድምቀት የከበበኝ፣
ያይን ስስት፣መዐዛ ሽታ፣ የሞላብኝ፣
የንብ ቀሰም፣ ጣፋጭ ማር ነኝ፣
የከበርኩኝ፣ ውበትን የታጠርኩኝ፣
አበባ ነኝ፣ አበባ ነኝ፣
«እኔ ማነኝ፣ እንዴት አልኩኝ?
«አንተስ ማነህ፣ ለምን አልኩኝ?።
ጠያቂ አዋቂ፣ ያ'በው ወግ፣
ጸገየ እጽ ፣ የፍጥረት ሕግ፣
ለካስ ነበር-ወደማታው፣ መጠውለግ፣
የመፍረስ ጫፍ ፣ ሌላ ጥግ፣
ታዲያስ እኔ ማነኝ?
ፍካት ድምቀት፣ የማይዘልቀኝ፣
ውበት ጤዛ፣ የሚያረግፈኝ፣
ከሰሎሞን የተሻልኩኝ፣ውበት የደረብኩኝ፣
ሆኜ ሳለሁ፣ ባዶ ገላ ያሸነፈኝ፣ እኔ ማነኝ?
መልስ አገኘሁ፣ የራሱ ካደረገኝ፣
ሳልፈልገው ከፈለገኝ።
እኔ የኔ አይደለሁም፣
ውበቴን ሽንፈት አይጥለውም፣
መርገፍ ልብሴ፣ ወልቆ አይቀርም፣
አበባዬ ክርስቶስ ነው፣
እርቃኔን የሸፈነው፣
የኔን ከለሜዳ የለበሰው፣
ክብሩን ለኔ ያወረሰው፣
ሞት ሸማዬን የገሰሰው፣
እኔ ማነኝ? ብዬ ስለው፣
አበባህ ረግፎ የማትቀረው፣
አንተ የኔ ነህ፣ ሲለኝ ሰማሁ፣
እኔም ያንተ፣ ቃሌን ሰጠሁ፣
ዛሬም አለሁ፣ ነገም አለሁ፣
አበባዬ አይረግፍም፣ ዛሬም አብባለሁ፣
ነገም በሰማይ አብቤ፣ አብሬው እኖራለሁ።
አንተስ ወንድሜ ማነህ? ያለኸው የትነው?፣
የወደቅኸው፣ ከወዴት ነው?፣
ስታበዛ ሩጫ፣ ልብስ ስትሻ፣
የትም የለ፣ ማካካሻ፣
የዚህ ዓለም ማረሳሻ፣
ይልቅ ና አበባ ሰው፣
መርገፍ ገላ፣ ከሚፈርሰው፣
አዲስ አርጎ፣ የሚያድሰው፣
ክርስቶስን ልበሰው!!!!
«ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ» ኤፌ 4፣24
Subscribe to:
Posts (Atom)