Friday, January 13, 2012

የተስፋው ቃል!





«እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና» ገላ ፭፣፭
በተስፋ የሚጠብቅ ክርስቲያን ትክክለኛ እምነትን የያዘ ነው። ፍጹም የሆነ እምነት በሌለበት የጽድቅን ተስፋ መጠባበቅ የለም። ስለሚጠባበቁት ተስፋ ፍጻሜ እምነት ሊኖር የግድ ነው።
ወንድና ሴት ሊጋቡ ሲወስኑ በጋብቻ ውስጥ ሳሉ ስለሚሆነው ነገር ሁሉ አስቀድመው በተስፋ አምነው ይፈጽማሉ። በጋብቻቸው ልጆችን ይወልዱ ዘንድ ተስፋ አድርገው ያምናሉ እንጂ እየወለዱ አይጋቡም። ሴትም በጽንሷ መጨረሻ ወራት ልጇን ትወልድ ዘንድ በተስፋ ትጠብቃለች እንጂ የጽንስ ውጤት ምን እንደሆነ ሳታውቅ ጽንስን አትለማመድም። ስለሚሆነው ነገር ባለው ጽኑ እምነት የተነሳ ውጤቱን በተስፋ መጠበቅ የግድ ይሆናል ማለት ነው።
አንድ ሰው ቃል ከገባለት ሌላ ሰው የተገባለትን ቃል ፍጻሜ በተስፋ ይጠብቃል። የገባለት ቃል ፍጻሜው ምንም ይሁን ምንም የተስፋውን ቃል ያይ ዘንድ በልቡ አስቀምጦ ይጠብቃል።
እንደዚሁ ሁሉ የተበደለ እንደሆነ የሚያምን ማንም ቢኖር ወደፍርድ አደባባይ ቢሄድ የበደሉን ዋጋ መልካም ፍርድን በተስፋ ይጠብቃል። በተስፋ ስለሚጠብቀው ነገር የጸና እምነት ባይኖረው ወደፍርድ አደባባይ በደሉን ይዞ ሊሄድ አይችልም።
ኦርቶዶክስ ይሁን እስላም፣ ይሁዲ ይሁን ጄሆቫ ዊትነስ፣ ፕሮቴስታንት ይሁን ካልቪኒስት የሁሉም ሃይማኖት ተከታይ በሚያምነው ሃይማኖት ውስጥ የመጨረሻ ግቡን በተስፋ ይጠባበቃል። ውጤቱ ምንም ይሁን ምንም የሚጠባበቀውን ተስፋ በእምነት ሳይቀበል ሃይማኖታዊ ልምምዱን በኑሮው ሁሉ ሊተገብር አይችልም።
ተስፋውን የሚጠባበቀው ከማመን ነው። ማመን ደግሞ ከመስማት ነው። በተስፋው ነገር ላይ እምነት ሳይኖረው ተስፋ አያደርግም። የሚያምነው ደግሞ ስለሚጠባበቀው ተስፋ በደንብ በመስማት ነው። ሳይሰማ እንዴት ያምናል? መጽሐፉም «እምነት ከመስማት ነው» ያለውም ለዚህ አይደል!!


ይህ ሁሉ ሊሆን እንደሚገባ እውነታ አድርገን ብንቀበል ተስፋ ማድረግና እሱን መጠበቅ ግን እንዲህ ቀላል ነገር አይደለም። ተስፋ ማድረግ ትልቅ የእምነት ጥንካሬን፣ ያለመጠራጠርን፣ ወደኋላ ያለማፈግፈግን፣ የሚጠበቀውን ተስፋ የሚመስል ወይም የሚተካ ሌላ ተስፋ ሲመጣ አቅጣጫን ያለመቀየርን አቋም እንደሚጠይቅ ለአፍታ ሊዘነጋ አይገባም።
አበ ብዙኃን የሆነው አብርሃም ከካራን ወጥቶ ወደምድረ ከነዓናዊቷ ሴኬም የገባው እድሜው ሰባ አምስት ያህል ሲሆነው ነበር። አብርሃም ምንም ልጅ ያልነበረው ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር ተገልጾለት ምድሪቱን ለዘርህ እሰጣለሁ ሲለው ያለምንም መጠራጠር ስለእግዚአብሔር ቃል እውነት፣ በእምነት መሰዊያን ሰራ። ዘፍ፲፪፣፬-፯ - ዘፍ ፲፫፣፲፮
በሰባ አምስት አመት እድሜው የተነገረው ለዘርህ እሰጣለሁ ያለው የእግዚአብሔር ቃል ዳግመኛ ተገልጾ የፍጻሜውን ማረጋገጫ እስኪሰማ የዘጠና ዘጠኝ እድሜው ጊዜ ድረስ ግን አብርሃም ምንም ልጅ አልነበረውም። አብርሃም የሚሰጠውን ዘር ለመጠበቅ ሃያ አምስት ዓመት በተስፋ መጠበቅ ግድ ሆኖበታል። የሚገርመው ነገር ልጅ ለመውለድ ተስፋ የሚደረግበት የሰው ልጅ የሥጋ ብርታት የሆነው ሙቀት ሁሉ ከአብርሃምም ሆነ ከሳራ ለምልክት ያልቀረ ሆኖ ሳለ ወራሽ ዘር ለማግኘት በተስፋ መጠበቅ እጅግ ከባድ ነገር ነው።
አብርሃም ይህንኑ የተስፋ ቃል ጠይቋል። ዘር ስለሌለኝ በቤቴ የተወለደ ይወርሰኛል ሲል እግዚአብሔር ግን ከጉልበትህ የሚወጣ ይወርስሃል ባለው ጊዜ ተስፋውን በእምነትና፣ እምነቱም የጽድቅ ዋጋው ሆኖ ተቆጠረለት። ዘፍ ፲፭፣፩-፭
እንግዲህ «ተስፋ» ከእምነት ነው። እምነትም ከሰማው ነገር ነው። የሰማውን ይሆንልኛል ይደረግልኛል ብሎ ማመን ደግሞ ጽድቅ ነው። በዚህ ላይ ያልተመሠረተ እምነት፣ ሃይማኖት ሊባል አይችልም። አብርሃም ከካራን ሳይወጣ የከነዓንን የተስፋ ቃል መስማት እንዳልቻለ ሁሉ ሃይማኖቶች ተስፋቸውን ከእምነት፣ እምነታቸውን ከመስማት፣ ጽድቃቸውን ከእምነታቸው ያገኙ ዘንድ ወደፍጻሜይቱ ተስፋ ሀገር መግባት የግድ ነው። ብዙ ሃይማኖቶች ከዚህ ሳይገቡ ቀርተዋል። ተስፋቸውን በብዙ ነገር ላይ እያስደገፉ ያምናሉ። የሰሙትን ከማመን ይልቅ የሚያደርጉትን በተስፋ ይጠብቃሉ። ስለዚህም እምነታቸው ስለጽድቅ የሚቆጠር እንደሆነ ከማመን የተለዩ ሆኑ።
ለዚህም ነው ብዙዎች ተስፋቸውን በእምነት እንደአብርሃም ከመጠበቅ ይልቅ ወደተስፋ የሚያደርሳቸውን ልዩ ልዩ መንገድ በመፈለግ ሌሊትና ቀን የሚደክሙት።
ሣራ ግድ ባለችው ጊዜ ከአጋር ልጅ መውለዱ ተስፋው እንደተፈጸመ ወይም ወደተስፋው የደረሰ አልነበረም። ዛሬም አንዳንድ ሃይማኖቶች ተስፋቸው እንዲፈጸም ወይም ወደተስፋው ለመድረስ ይህንን ዓይነቱን የተስፋ መንገድ ዕለት እለት ያከናውናሉ። ይሁን እንጂ በዚያ መንገድ የተነገረውን የተስፋ ቃል በምንም መልኩ ሊያገኙ አይችሉም። የአጋር ልጅ ከአብርሃም ጉልበት ስለወጣ ፣ ከጉልበትህ የወጣ ይወርስሃል ያለው የእግዚአብሔር ቃል መፈጸሙን ለአብርሃም አላረጋገጠም። እንደዚሁ ሁሉ ብዙ ሰዎች ወደተስፋቸው ለመድረስ የሚወጡበትና የሚወርዱበት መንገድ፣ የሚያከናውኑት ክርስቲያናዊ የተስፋ መንገዶቻቸው ስላላረጋገጡላቸው ራሳቸውን እንደጻድቅ ቆጥረው አያውቁም። ተስፋቸውን ለመሙላት ከመድከም አያቋርጡም። ይሁን እንጂ መቼም ሳይሞሉ ይኖራሉ።
አብርሃም ግን እስከ ተስፋው ፍጻሜ እግዚአብሔር ያለውን ለመጠበቅ አመነ፣ እንደሚሆንለትም ስላመነ፣ ማመኑ ብቻውን ጻድቅ አደረገው። ቃሉም ያለው ያንን ነው።
«አብራምም በእግዚአብሔር አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት» ዘፍ ፲፭፣፮
«እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው» ዕብ ፲፩፣፩
እስራኤል ዘሥጋ ለእግዚአብሔር የተለዩ ሕዝቦች ነበሩ። ከባርነትም ወጥተው ወደተስፋይቱ ምድር ይሄዱ ዘንድ እግዚአብሔር በወሰነ ጊዜ ተስፋውን ያገኙት ተስፋውን የጠበቁ ብቻ ናቸው። ወተትና ማር ወደምታፈስ ሀገር አገባችኋለሁ ሲል ቃሉ እንደሚሆን አምነው በተስፋው መኖር ሲገባቸው የግብጽ ሽንኩርትና ድንች ያማራቸው ከተስፋው በፊት ወድቀው ቀርተዋል። ወተት የሚሰጡ እንስሳት፣ ማር የሚያመነጩ እጽዋት ይሰጣችኋል የተባለውን ቃል በእምነታቸው ተስፋ አድርገው ከመጠበቅ ይልቅ የግብጽ የምንቸት ቅቅልና ሥጋ አማረን ብለው ከበረሀ እንዲቀሩ ሆነዋል። ተስፋውን ቃል በቃል ሰምተው መጠበቅ ያልቻሉት ቀርተው ተስፋውን ከመጽሐፍ ሰምተው ያመኑና የጠበቁ ትውልዶች ከአርባ ዘመን በኋላ አግኝተውታል። ዕብ ፫፣፲፯-፲፱ «አርባ አመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፥ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን? ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? ባለማመናቸውም ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን»
ተስፋን የሚያገኙ ብዙ እድሜ ያስቆጠሩ ወይም የሰሙት ሁሉ ሳይሆን የሰሙትን አምነው በተስፋ የጠበቁ ናቸው። የተስፋው መንገድ ደግሞ ወደግራም ወደቀኝም ወይም ወደኋላ አይደለም። የማናየውን ነገር እንዳየን አድርገው በእምነት የምንጠብቃት ሀገር እግዚአብሔር የነገረን ናት። «በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል?» ሮሜ ፰፣፳፬
ይስሐቅ የተስፋው ቃል ልጅ፣ የአባቱን የአብርሃምን ቤት ወርሷል። በእጸ ሳቤቅ የታሰረው የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ፣ እንደተሰጠን ተስፋ በሞቱ ሰማያዊውን ቤት ለእኛ ለዘሮቹ አውርሷል። ምክንያቱም ይላል ጳውሎስ «የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ» ገላ ፫፣፲፬
ዳሩ ግን ዛሬ የእምነታቸውን ተስፋ በልዩ ልዩ ልምምዶችና ማጠናከሪያዎች ላይ በማስደገፍ የሚጠብቁ ወደእረፍቱ ሳይገቡ እንዳይቀሩ ያስፈራል። ጳውሎስም ይህንኑ ይነግረናል።
« ዕብ ፬፣፩-፪ እንግዲህ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት ተስፋ ገና ቀርቶልን ከሆነ፥ ምናልባት ከእናንተ ማንም የማይበቃ መስሎ እንዳይታይ እንፍራ። ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም»
ስለዚህ ዋናው ጥያቄ ተስፋችንን እንዴት እንጠብቅ ነው መሆን ያለበት! ብዙ ተስፋ ያላቸውን የሚመስሉ መንገዶችን መተው፣ በሊቀካህናቱ የወራሽነት የተስፋው መንገድ ላይ ወደእረፍቱ እንድንገባ በእምነት እንከተል! ወንጌሉም የሚናገረው እኛ ወደዚያ ተስፋ እንድንደርስ ነው።
« የእነዚህም ስርየት ባለበት ዘንድ፥ ከዚህ ወዲህ ስለ ኃጢአት ማቅረብ የለም። እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን፥በእግዚአብሔርም ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን ስላለን፥ ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ፤ የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ፣ ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ» ዕብ ፲፣፲8-፳፬