Thursday, January 26, 2012

መግደልና ማቃጠል!!





በሀላባ ቁሊቶ አክራሪ ሙስሊሞች ለጥምቀት በዓል በወጡ ክርስቲያን ምዕመናን ላይ ጉዳት አደረሱ

የሀላባ እና አካባቢው ምዕመናን ከፍተኛ ክርስቲያናዊ ገድል በመጋደል ሃይማኖታቸውን መከላከላቸው ተሰማ

ጉባ በተባለች አነስተኛ መንደር ለገበያ በወጡ ክርስቲያኖች ላይ የማኅተም መበጠስና የገንዘብ ዝርፊያ ተካሂዷል

መንግሥት ተገቢውን እርምጃ ካልወሰደ መጪው ጊዜ እጅግ አስቸጋሪ እንደሚሆን ተገምቷል


በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከሻሸመኔ በስተምዕራብ በግምት 75 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ጥር 12 ቀን 2004 ዓ.ም ለጥምቀት በዓል በወጡ ክርስቲያኖች ላይ ጥቃት መድረሱን ከዚያው አካባቢ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

ሆን ተብሎ እና ታቅዶ በተሰነዘረው በዚህ ጥቃት በርካታ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች፣ ሕፃናትና ዐዋቂዎች ከፍተኛ የመፈንከትና የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ ጉዳቱ የደረሰው ምዕመናን የቅዱስ ሚካኤልና የመድኃኔዓለም ታቦታትን ወደ ቤተመቅደስ ለመመለስ አጅበው በሚጓዙበት ወቅት መሆኑን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡ በዕለቱ በክርስቲያኖች በኩል ከወትሮው የተለየ ግጭትን የሚያነሳሳ ምንም ነገር አለመፈጸሙንና ታቦታቱ ተጉዘው በከተማዋ አደባባይ ለዕረፍት በቆሙበት ወቅት፣ አድፍጠውና ተዘጋጅተው ምቹ ሰዓትና ቦታ ይጠብቁ በነበሩ ሙስሊሞች በኩል የድንጋይ እሩምታ መጀመሩን እማኞቻችን አስረድተዋል፡፡



በሙስሊሞች በኩል ለግጭቱ መነሻነት የቀረበው ምክንያት፣ ክርስቲያኖች ወትሮ ከሚጓዙበት መንገድ (አቅጣጫ) በመቀየር በመስጊድ አጠገብ አልፈዋል የሚል መሆኑ ከወደ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ሆኖም፣ ከአካባቢው ምዕመናን እንዳረጋገጥነው የከተማው ማዘጋጃ ቤት ክርስቲያኖች ያልፉበት የነበረው መንገድ በግንባታ ሰበብ በመዝጋቱ ካለፉት ሰባትና ከዚያ በላይ ዓመታት ወዲህ ይህንኑ መስመር ለመተላለፊያነት ሲጠቀሙበት እንደኖሩና ከመስጊድ ይዞታ ጋር የሚያያይዘው አንዳች ነገር እንደሌለ አስረግጠው ነግረውናል፡፡ ይሁን እንጂ ታቦታቱ ያልፉበት የነበረው ሰዓት ሙስሊሞች ለዓርብ ጁምዓ ጸሎታቸው ወደ መስጊድ ከሚጓዙበት ሰዓት ጋር መገጣጠሙ ግጭቱን ሳያባብሰው እንዳልቀረ የብዙዎች እምነት ነው፡፡

ችግሩ፣ የ"ጠብ ያለሽ በዳቦ" ጉዳይ ሆኖ እንጂ፣ አዲስ አበባ ላይ አንዋር መስጊድና ቅዱስ ራጉኤል አጠገብ ለአጠገብ ናቸው፡፡ በሀዋሳ የቅድስት ሥላሴ እና ሌሎች ታቦታት ታጅበው የሚሄዱት በመስጊዱ አጥር አጠገብ ነው፡፡ በአርሲ ሁሩታ፣ ሮቤና አሰላ ከተሞች፣ በባህርዳር፣ በሐረር፣ በቡታጀራ፣ በደሴ፣ በሚዛን ተፈሪ እና በናዝሬት ከተሞች በዓላቱ የሚከበሩት በመስጊዶቹ አጠገብ እየታለፉ ነው፡፡ ካለፉት የጨለማ ዘመናት ጀምሮ እምልኮ ያለምንም ችግር ተካሂዷል፡፡ ዘመን ሲሠለጥን እንደዚህ ዓይነቱ ጉድ ይመጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡

ግጭቱ ለክርስቲያኖች ዱብዕዳ ይሁን እንጂ በሙስሊሞች በኩል በቂ ዝግጅት መኖሩን የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ፡፡ ይኸውም፣ ጥር 11 ቀን 2004 ዓ.ም በጥምቀት በዓል ዕለት አንዲት ሙስሊም ሴትና አንድ ሙስሊም ወንድ ጠብ ለመጫር ሞክረው እንደነበረ እና ወገኖች በጥበብ እንደመለሷቸው፣ እንዲሁም የከተማው ከንቲባ አቶ ከድር ለቤተክርስቲያን አስተዳደር ሠራተኞች ኦፊሴላዊ (በጽሑፍ) ባልሆነ ትዕዛዝ በዓሉ እንዳይካሄድ አሳስበው እንደነበረ እና እርሳቸውም የጉዳዩን ጥልቀት ያውቁት እንደነበረ ተገልጿል፡፡ ከዚህም በላይ ምንም እንኳን ከጠበቀው በላይ ቢሆንም፣ መንግሥት በደረሰው የደኅንነት መረጃ ግጭት ሊከሰት እንደሚችል ያውቅ እንደነበረ ውስጥ ዐዋቂ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡ ከምዕመናን በደረሰን አስተያየትም መንግሥት ፌዴራልና ልዩ ኃይል የፖሊስ አካላትን ከሀዋሳ፣ ከሆሣዕና እና ከዱራሜ አካባቢ በመላክ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ሕዝቡን ታደጎታል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በሀላባ ልዩ ወረዳም ይሁን በከተማው አስተዳደር በኩል እንደዚህ ዓይነቱ ታላቅና ብሔራዊ በዓል በሠላም እንዲከበር በቂ የሥነ ሥርዓትና የፀጥታ ጥበቃ ዝግጅት አለመደረጉ የአካባቢው ባለሥልጣናት ብቃትና ፖለቲካዊ አመራር ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ በተለይም በበዓሉ ላይ የነበሩት ፖሊሶች ጥቂትና ትጥቅ ያልያዙ ባዶ እጃቸው የነበሩ መሆናቸው ሲስተዋል በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ጠባቦችና ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው ባለሥልጣናት እንዳሉ አያጠያይቅም፡፡

በሌላ በኩል በዓሉ እጅግ ደማቅ በሆነ ሁኔታ በመከበር ላይ የነበረ ሲሆን መምህር ተረፈ አበራ፣ ዘማሪት ምርትነሽ፣ ዘማሪት ቅድስት ምትኩ፣ መምህር መስፍን፣ ተፈሪ ኃይለ ሚካኤል፣ ወትሮ እንደሚያደርጉት ሁሉ በዝማሬ እና በወንጌል ያገለገሉ ሲሆን በተለይም የሀላባ ቅድስት ማርያም አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ዮናስ እና መምህር ተረፈ አበራ ግጭቱ እንዳይባባስ እና ምዕመናን እንዲረጋጉ በመምከር ኃላፊነታቸውን በመወጣት ታሪካዊ ተጋድሎ መፈጸማቸው ታውቋል፡፡ መምህር ተረፈ እና አባ ዮናስ በዚሁ መልዕክታቸው፣ ምዕመናን ለሚሰነዘርባቸው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ወደፊት እንዳይሄዱና ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ፣ ግጭቱ የተከሰተው ሙስሊሙን ኅብረተሰብ ሊወክሉ በማይችሉ ጥቂት አክራሪዎች ጠብ አጫሪነት መሆኑንና ጉዳዩን ወደ መንግሥት በማቅረብ በሕጋዊ እና በሠላማዊ መንገድ መፍትሔ እንደሚሰጠው በመግለጽ ሕዝቡን በሚያራራ እና በሚያጽናና ትምህርት አረጋግተዋል፡፡

በሌላ በኩል የሀላባ ክርስቲያኖች የታቦቱን ክብር ለመጠበቅ ግንባራቸውን ለድንጋይ በመስጠት ካህናቱንና ታቦቱን ከጥቃት የተከላከሉ ሲሆን እስከዛሬው ዕለትና ሰዓት ውሎና አዳራቸውን በአብያተ ክርስቲያናቱ ቅጥር ግቢ በማድረግ ጥበቃ ላይ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ ሀላባና አካባቢው በከፍተኛ ውጥረት ላይ የሚገኝ ሲሆን እነዚሁ አክራሪ ሙስሊም ወጣቶች ጥረው ግረው በሚኖሩ ግለሰቦች ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በመሰንዘር የማሸማቀቅ ዘመቻ ላይ እንዳሉ ከአካባቢው የደረሰን ጥቆማ ያስረዳል፡፡ ከዚህም በላይ እነዚሁ የጽንፈኛ ቡድኖች ተላላኪዎች በፖሊስ ተሽከርካሪዎች ላይ ድንጋይ በመወርወር ጭምር ድፍረት ማሳየታቸው ታውቋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም አክራሪዎቹ የታዋቂውን የእግር ኳስ ተጫዋች የሰብስቤ ደፋርን ሆቴልና ሙዚቃ ቤት መስታወት ከመሰባበራቸውም በላይ ለማቃጠል የለኮሱት እሳት ብዙ ጉዳት ሳያደርስ ለማጥፋት ተችሏል፡፡ በነገራችን ላይ ስለ ሰብስቤ ደፋር ክርስቲያናዊ ሕይወት የዝግጅት ክፍላችን የደረሰው ነገር ባይኖርም በዜግነቱ ሠርቶ የሚኖር፣ ለባንኮች፣ ለሀዋሳ ከነማ እና ለአዳማ ከነማ የእግር ኳስ ክለቦች አስተዋፅዖ ያበረከተ ታላቅ ተጫዋች መሆኑን ሰዎች ይመሰክሩለታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ማክሰኞ ጥር 15 ቀን 2004 ዓ.ም ከሀላባ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ ጉባ በምትባል አነስተኛ ከተማ ለገበያ በሄዱ ክርስቲያን ወገኖች ላይ ማኅተም የመበጠስና የገንዘብ ዝርፊያ ወንጀል መፈጸሙን ከአካባቢው የደረሰን ጥቆማ ያመለክታል፡፡ በአሁኑ ወቅት አክራሪ ሙስሊሞቹ የዋሁን የገጠር ኅብረተሰብ "ክርስቲያኑ መስጊድህን አቃጠለብህ ተነስ" እያሉ በመቀስቀስ ልዩ ልዩ የስለት መሣሪያዎችን በማስያዝ በአይሱዙ ጭምር እያስጫኑ በከተማው ኅብረተሰብ ላይ "አላሁ አክበር" የሚል ሃይማኖታዊ መፈክር እያስፈከሩ እንደሆነ ስማቸውን ልንገልጽ የማንፈልገው ሙስሊም የልዩ ወረዳው ደኢህዴን የሥራ ኃላፊ መመስከራቸው ተገልጿል፡፡ የገጠሩ ኅብረተሰብም በእንደዚህ ዓይነቱ የሐሰት ወሬ እንዳይታለል ቅን አመለካከት ያላቸው ባለሥልጣናት አልፎ አልፎ መልዕክት እያስተላለፉ መሆኑን እማኞቻችን አረጋግጠውልናል፡፡

በሌላ በኩል፣ ግጭቱን ለመፍታት በወረዳው የሃይማኖቶች ሕብረት ለሠላም ምክር ቤት፣ በልዩ ወረዳው እና በክልሉ መንግሥታዊ አካላት ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ ሲሆን ችግሩን በሽምግልና ለማየት ለቀጣዩ ቅዳሜ ጥር 19 ቀን 2004 ዓ.ም ቀጠሮ መያዙን የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በሀላባ ከተማ የሚገኙ ቤተክርስቲያናት ረቡዕ፣ ዓርብና ሐሙስ እግዚአብሔር ሠላምና ጥበቃውን ያደርግላቸው፣ ምሕረትና ቸርነቱን ይሰጣቸው ዘንድ በጾምና በጸሎት ተወስነው ወደ ፈጣሪ ለመማለድ የሦስት ቀናት ሱባዔ አውጀዋል፡፡ እኛም በያለንበት እናስባቸው ዘንድ ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት አክራሪዎች በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ውስጥ ተሰግስገው ከክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ለማጋጨት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆኑ፣ ሰዎች ሞተዋል፣ ቤተክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ሀብት ንብረት ወድሟል፡፡ ቁርኝቱ ዓለም አቀፍ እና ተያያዥነት ያለው ነው፡፡ ከሳውዲ ዐረቢያና ሌሎች መካከለኛ ምሥራቅ ሀገራት፣ ከፓኪስታንና ከኢንዶኔዥያ በሚደረግ የገንዘብ ዝውውር ኢትዮጵያን የሽብር ማዕከል የማድረግ ጠንካራ እንቅስቃሴ እንዳለ ይስተዋላል፡፡ በተለይም በሀላባ፣ በጉራጌ፣ በሥልጤ፣ በአጋሮ፣ በመቱ እና በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ግጭቶች እያቆጠቆጡ ናቸው፡፡

የአክራሪ እስልምና (ጽንፈኝነት) በሌሎች ሃይማኖቶችና ሃይማኖት የለሾች ላይ ብቻ ሳይሆን በሙስሊሙም ዘንድ እየተጠላ የከፋ ችግር እያመጣ መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቱ በ9ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው ማሳወቁን ሪፖርተር ጋዜጣ ጥር 13 ቀን 2004 ዓ.ም ባወጣው ዘገባ ተንትኖታል፡፡ ምክር ቤቱ በዚሁ ጉባዔው ጽንፈኛና አክራሪ አስተሳሰብ በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ላይ ለመጫን ጥረት የሚያደርጉ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጉባዔው ማሳሰቡን ጋዜጣው አያይዞ ገልጿል፡፡ በአወሊያ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በቅርቡ የተፈጠረው አለመግባባት የተከሰተው ጽንፈኝነትን በሚያራምዱ አንዳንድ አካላት መሆኑን እና ሙስሊሙ ኅብረተሰብና ምክር ቤቱ እንደሚያወግዙት ጋዜጣው ጨምሮ ያብራራል፡፡

መንግሥት እየተባባሰ የመጣውን ሃይማኖት ለበስ ችግር በአግባቡ ካልተቆጣጠረውና የሕዝቡ በሠላም የመኖርና የማምለክ ሕገመንግሥታዊ መብት ካልተከበረ የመንግሥትና የመኖራችን ሕልውና አደጋ ላይ ነው የሚሉ ወገኖች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!!!
የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃዋ፣
የጻድቃን ሰማዕታት ረድኤታቸው፣ ከእኛ አይለየን!!!
አሜን!!!
Posted by Dejeselaam at 4:30 AM