(by dejebirhan)
«እኔ ማነኝ? አንተስ ወንድሜ ማነህ?»
እኔ አበባ ነኝ ፣ የማለዳ ጤዛ ያረፈብኝ፣
ፍካት፣ ድምቀት የከበበኝ፣
ያይን ስስት፣መዐዛ ሽታ፣ የሞላብኝ፣
የንብ ቀሰም፣ ጣፋጭ ማር ነኝ፣
የከበርኩኝ፣ ውበትን የታጠርኩኝ፣
አበባ ነኝ፣ አበባ ነኝ፣
«እኔ ማነኝ፣ እንዴት አልኩኝ?
«አንተስ ማነህ፣ ለምን አልኩኝ?።
ጠያቂ አዋቂ፣ ያ'በው ወግ፣
ጸገየ እጽ ፣ የፍጥረት ሕግ፣
ለካስ ነበር-ወደማታው፣ መጠውለግ፣
የመፍረስ ጫፍ ፣ ሌላ ጥግ፣
ታዲያስ እኔ ማነኝ?
ፍካት ድምቀት፣ የማይዘልቀኝ፣
ውበት ጤዛ፣ የሚያረግፈኝ፣
ከሰሎሞን የተሻልኩኝ፣ውበት የደረብኩኝ፣
ሆኜ ሳለሁ፣ ባዶ ገላ ያሸነፈኝ፣ እኔ ማነኝ?
መልስ አገኘሁ፣ የራሱ ካደረገኝ፣
ሳልፈልገው ከፈለገኝ።
እኔ የኔ አይደለሁም፣
ውበቴን ሽንፈት አይጥለውም፣
መርገፍ ልብሴ፣ ወልቆ አይቀርም፣
አበባዬ ክርስቶስ ነው፣
እርቃኔን የሸፈነው፣
የኔን ከለሜዳ የለበሰው፣
ክብሩን ለኔ ያወረሰው፣
ሞት ሸማዬን የገሰሰው፣
እኔ ማነኝ? ብዬ ስለው፣
አበባህ ረግፎ የማትቀረው፣
አንተ የኔ ነህ፣ ሲለኝ ሰማሁ፣
እኔም ያንተ፣ ቃሌን ሰጠሁ፣
ዛሬም አለሁ፣ ነገም አለሁ፣
አበባዬ አይረግፍም፣ ዛሬም አብባለሁ፣
ነገም በሰማይ አብቤ፣ አብሬው እኖራለሁ።
አንተስ ወንድሜ ማነህ? ያለኸው የትነው?፣
የወደቅኸው፣ ከወዴት ነው?፣
ስታበዛ ሩጫ፣ ልብስ ስትሻ፣
የትም የለ፣ ማካካሻ፣
የዚህ ዓለም ማረሳሻ፣
ይልቅ ና አበባ ሰው፣
መርገፍ ገላ፣ ከሚፈርሰው፣
አዲስ አርጎ፣ የሚያድሰው፣
ክርስቶስን ልበሰው!!!!
«ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ» ኤፌ 4፣24